በምድር ላይ ከሚገኙ ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ደስተኛ የሆኑት ሕዝቦች
1 “እግዚአብሔር አምላኩ የሆነ ሕዝብ ምስጉን [“ደስተኛ፣” NW ] ነው።” (መዝ. 144:15) እነዚህ ቃላት የይሖዋ ምሥክሮች በምድር ላይ ከሚገኙ ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ደስተኞች እንደሆኑ ያሳያሉ። ብቻውን እውነተኛና ሕያው አምላክ የሆነውን ይሖዋን በማገልገል ከሚገኝ ደስታ የበለጠ ምንም ነገር የለም። እሱ ‘ደስተኛ አምላክ’ በመሆኑ አምላኪዎቹም የሱን ደስታ ያንጸባርቃሉ። (1 ጢሞ. 1:11 NW) ይህን ያህል ደስተኞች እንድንሆን አስተዋጽኦ የሚያደርጉት አንዳንዶቹ የአምልኮታችን ዘርፎች የትኞቹ ናቸው?
2 ደስተኛ እንድንሆን የሚያደርጉን ምክንያቶች:- ኢየሱስ “ለመንፈሳዊ ፍላጎታ[ችን] ንቁ” መሆን ደስታ እንደሚያመጣልን አረጋግጦልናል። (ማቴ. 5:3 NW) ሳያሰልሱ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በሁሉም ክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ መገኘት ይህንን ፍላጎት ያሟላል። የአምላክን ቃል እውነት መማራችን ከሃይማኖታዊ ውሸትና ስህተት ነፃ አውጥቶናል። (ዮሐ. 8:32) በተጨማሪም ቅዱሳን ጽሑፎች ከሁሉ የተሻለውን የሕይወት መንገድ አስተምረውናል። (ኢሳ. 48:17) በመሆኑም ደስተኛ በሆነው የወንድማማች ማህበር ውስጥ ባገኘነው ጤናማ ክርስቲያናዊ ወዳጅነት እንደሰታለን።—1 ተሰ. 2:19, 20፤ 1 ጴጥ. 2:17
3 የአምላክን ከፍተኛ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መታዘዛችን ለራሳችን ጥበቃ እንደሚሆንልንና ይሖዋንም እንደሚያስደስተው ስለምናውቅ ጥልቅ እርካታ እናገኛለን። (ምሳሌ 27:11) አንድ የጋዜጣ ዘጋቢ እንዲህ ብሏል:- “የይሖዋ ምሥክሮች ጥብቅ መሥፈርቶች ቢኖሯቸውም ደስታ የራቃቸው አይደሉም። ከዚህ በተቃራኒ [በመካከላቸው ያሉ] ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን እጅግ ደስተኞችና ሚዛናዊ ናቸው።” ሌሎች እኛ ያገኘነውን አስደሳች ሕይወት እንዲያገኙ ልንረዳቸው የምንችለው እንዴት ነው?
4 ሌሎችም ደስተኞች እንዲሆኑ እርዷቸው፦ ዓለም ደስታ ርቆታል። በአጠቃላይ ሲታይ ሰዎች ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያላቸው አመለካከት የጨለመ ነው። እኛ ግን ሐዘን የሚወገድበት ጊዜ እንደሚመጣ ስለምናውቅ ብሩህ አመለካከት አለን። (ራእይ 21:3, 4) ስለዚህ ተስፋችንንና ይሖዋን በተመለከተ ያለንን እምነት የምናካፍላቸው ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በመፈለግ በአገልግሎታችን በቅንዓት እንሳተፋለን።—ሕዝ. 9:4
5 አንዲት አቅኚ እህት “ሰዎች ይሖዋንና እውነቱን እንዲያውቁ ከመርዳት የበለጠ እርካታ የሚያስገኝ ሥራ የለም” ብላለች። ብዙ ተጨማሪ ሰዎች የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲጀምሩ ለማበረታታት የምንችለውን ሁሉ እናድርግ። ይሖዋን ማገልገልና ሌሎች እሱን እንዲያገለግሉ ለመርዳት ራሳችንን ማቅረብ ከሁሉ የበለጠውን ደስታ ያስገኛል።—ሥራ 20:35