ኮንትራቶችን የሚመለከቱ ማሳሰቢያዎች
የአስተዳደር አካሉ መጽሔቶች በኮንትራት መላካቸው እንዲቆም ያደረገውን ውሳኔ ልናስታውሳችሁ እንወዳለን። በአሁኑ ወቅት ያሉት የመጠበቂያ ግንብ እና የንቁ! መጽሔት ኮንትራቶች መላካቸውን የሚቀጥሉት ጊዜያቸው እስኪያበቃ ድረስ ብቻ ይሆናል።
ስለዚህ በአሁኑ ወቅት መጽሔቶችን በኮንትራት እያገኙ ያሉ አስፋፊዎች ኮንትራቱ ሲያበቃ እንደገና ማደስ የሌለባቸው ሲሆን የግል የመጽሔት ቅጂያቸውን ለጉባኤው በቋሚነት ከሚላኩት መጽሔቶች መውሰድ ይችላሉ። የአንድ አስፋፊ ኮንትራት ማለቁን የሚያሳውቅ ቅጽ ለጉባኤው እንደደረሰ አስፋፊው በኮንትራት ያገኝ የነበረውን መጽሔት ከግምት ውስጥ በማስገባት ወዲያውኑ ከጉባኤ የሚወስደውን የመጽሔት ብዛት መጨመሩ ተገቢ ይሆናል። የመጽሔት አገልጋዩ መጽሔቶቹ ለጉባኤው እንደደረሱ ወዲያውኑ አስፋፊዎች እንዲያገኟቸው ማድረግ አለበት። የግል ቅጂያችሁን በስሕተት መስክ ላይ እንዳታበረክቱት መጽሔቱን እንደወሰዳችሁ ወዲያውኑ ስማችሁን ልትጽፉበት ትችላላችሁ።
በክልሉ ውስጥ ያሉ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች የመጽሔት ኮንትራታቸው ማለቁን የሚያሳውቅ ቅጽ ለጉባኤው ሲደርስ ቅጾቹ ኮንትራቱን ላስገባው አስፋፊ መሰጠት አለባቸው። አስፋፊው ግለሰቡ ዘንድ ሄዶ ኮንትራቱ አንዴ ካለቀ መጽሔቶቹን ራሱ በግንባር እንደሚያመጣለት ሊነግረው ይገባል።
ኮንትራቶች እንዳሉ የሚቀጥሉት ልባዊ ፍላጎት ላላቸው ሆኖም በቋሚነት መጽሔቶቹን በግንባር ማድረስ በማይቻልባቸው ሩቅ በሆኑ ቦታዎች ለሚገኙ ሰዎች ብቻ ነው። በጉባኤው የአገልግሎት ክልል ውስጥ ያሉ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ግን የመጽሔት ደንበኞች ማድረግ ይቻላል። መጽሔቶቹን ለማድረስ የሚደረጉት ተመላልሶ መጠየቆች አስፋፊው የግለሰቡን ፍላጎት እንዲኮተኩትና አዳዲስ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን እንዲያስጀምር አጋጣሚ ይከፍቱለታል። ለእነዚህ ፍላጎት ያሳዩ የመጽሔት ደንበኞች በቋሚነት መጽሔቶቹን ለማድረስ አስፋፊዎች ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል። አስፋፊዎች እነዚህን ፍላጎት ያሳዩ ሰዎች የመጽሔት ደንበኛ ለማድረግ በሚያደርጉት ጥረት የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ሊረዳቸው ይችላል።
በስጦታ የሚገኙ ኮንትራቶች ከአሁን በኋላ አይኖሩም። ይሁን እንጂ የብሬይል ኮንትራቶች ከዚህ ቀደም እንደነበረው ይቀጥላሉ። አንድ አስፋፊ ወይም ፍላጎት ያሳየ ሰው ከእንግሊዝኛ፣ ከአማርኛና ከትግርኛ ውጭ በሌላ ቋንቋ ኮንትራት ከነበረው ለጉባኤው ከሚላኩት መጽሔቶች ጋር አብሮ እንዲላክለት በጉባኤው በኩል ትእዛዝ መላክ ይቻላል። ለየት ያሉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ግን በአየር የሚላኩ ኮንትራቶችን ማመቻቸት ይቻላል።
በዚህ አዲስ አሠራር የተነሳ ሳምንታዊ ኮንትራት (M-203)፣ የኮንትራት አድራሻ ለውጥ (M-205) እና How to Handle Subscriptions Properly (S-11) የተባሉት ቅጾች ከአሁን በኋላ አያስፈልጉም። ጉባኤው እስካሁን እነዚህ ቅጾች ካሉት እባካችሁ አስወግዷቸው።