ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን እውነት አስታውቁ
1 ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሌሎች በጎች ክፍል በሆኑት አጋሮቻቸው እየታገዙ ‘ስለ ኢየሱስ ይመሠክራሉ’። (ራእይ 12:17) መዳን የሚገኘው በእርሱ በኩል ብቻ ስለሆነ ይህ ተልዕኮ ትልቁን ቦታ የሚይዝ ነው።—ዮሐ. 17:3፤ ሥራ 4:12
2 ‘መንገድ፣ እውነትና ሕይወት’:- ኢየሱስ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ” በማለት ተናግሯል። “በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።” (ዮሐ. 14:6) ወደ አምላክ በጸሎት መቅረብና ከእርሱ ጋር ጥሩ ዝምድና መመሥረት የምንችለው “መንገድ” በሆነው በኢየሱስ በኩል ብቻ ነው። (ዮሐ. 15:16) በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሰፈሩት ትንቢቶችና ጥላዎች ፍጻሜያቸውን ያገኙት በእርሱ ላይ በመሆኑ ኢየሱስ “እውነት” ነው። (ዮሐ. 1:17፤ ቆላ. 2:16, 17) እንዲያውም ትንቢት የሚነገርበት ዋነኛ ዓላማ ኢየሱስ የአምላክን ዓላማ በማስፈጸም ረገድ በሚጫወተው ወሳኝ ሚና ላይ የእውቀት ብርሃን ለመፈንጠቅ ነው። (ራእይ 19:10) በተጨማሪም ኢየሱስ “ሕይወት” ነው። የዘላለምን ሕይወት ስጦታ ለማግኘት ሁሉም ሰው በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ማመን አለበት።—ዮሐ. 3:16, 36፤ ዕብ. 2:9
3 የጉባኤ ራስና በመግዛት ላይ የሚገኝ ንጉሥ:- በተጨማሪም ይሖዋ ለልጁ ከፍተኛ የአስተዳደር ሥልጣን እንደሰጠው ሰዎች አምነው መቀበል አለባቸው። ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ ተሹሟል። “የአሕዛብ መታዘዝም ለእርሱ ይሆናል።” (ዘፍ. 49:10) ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ የጉባኤው ራስ አድርጎ ሾሞታል። (ኤፌ. 1:22, 23) የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ኢየሱስ ጉባኤውን እንዴት እንደሚመራና መንፈሳዊ ‘ምግብ በጊዜው’ ለማቅረብ ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ እንዴት እንደሚጠቀም እንዲገነዘቡ መርዳት ይኖርብናል።—ማቴ. 24:45-47
4 ሩኅሩኅ ሊቀ ካህናት:- ኢየሱስ ሰው ሆኖ መከራና ሥቃይን ስለቀመሰ ‘ፈተና የሚደርስባቸውን ሊረዳቸው ይችላል።’ (ዕብ. 2:17, 18) ፍጽምና የጎደላቸው የሰው ዘሮች ኢየሱስ ድክመታቸውን ተመልክቶ እንደሚራራላቸውና በደግነት እንደሚማልድላቸው ማወቃቸው ምንኛ ያስደስታቸዋል! (ሮሜ 8:34) በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕትና ሊቀ ካህናት ሆኖ በሚሰጠው አገልግሎት በመጠቀም ‘በሚያስፈልገን ጊዜ እርዳታ ለማግኘት’ ወደ ይሖዋ ‘በእምነት መቅረብ’ እንችላለን።—ዕብ. 4:15, 16
5 ሰዎች ስለ ኢየሱስ የሚናገረውን እውነት ማወቃቸው ከእኛ ጋር ሆነው እርሱን እንዲታዘዙና እንዲያገለግሉት የሚያነሳሳቸው እንዲሆን እንመኛለን።—ዮሐ. 14:15, 21