በዘመናችን መቶ ዓመት ባስቆጠረው ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት እየተካፈላችሁ ነውን?
1 የይሖዋ ሕዝቦች በዘመናችን በተደራጀ መልኩ ከቤት ወደ ቤት ማገልገል ከጀመሩ በዚህ ወር መቶ ዓመት እንደሚሞላቸው ታውቃለህ? ምንም እንኳን ወንድሞች ከዚያ ቀደም ብለውም በግለሰብ ደረጃ ከቤት ወደ ቤት ያገለግሉ የነበረ ቢሆንም እያንዳንዱን ሰው ማግኘት እንዲቻል ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ትራክት እንዲያሰራጩ ማበረታቻ የተሰጠው በግንቦት 15, 1903 መጠበቂያ ግንብ ላይ ነበር። ኢየሱስና ሐዋርያቱ የተጠቀሙበት ይህ የስብከት ዘዴ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ይበልጥ ስፋትና ጥራት ባለው መንገድ እየተሠራበት ነው። በተለይም በደንብ የታሰበበት ጥቅስ በመጠቀም ሰዎችን ለማነጋገር ጥረት ይደረጋል። (ማቴ. 10:12፤ ሥራ 5:42) ላለፉት በርካታ ዓመታት ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው አገልገሎት የይሖዋ ምሥክሮች “መለያ ምልክት” ሆኖ ቆይቷል።
2 በአብዛኞቹ አገሮች ቀናተኛ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች የአገልግሎት ክልላቸውን በሙሉ በዓመት ውስጥ በተደጋጋሚ ጊዜያት፣ አንዳንድ ጊዜም በየወሩ ይሸፍናሉ። ሆኖም በአንዳንድ አካባቢዎች ብዙ ሰዎች እምብዛም ቤታቸው አይገኙም። ስለሆነም ወንድሞች በመንገድ ላይ፣ በመናፈሻ ቦታዎች፣ በንግድ አካባቢዎች እንዲሁም ሰዎችን ማግኘት በሚቻልበት በማንኛውም ቦታና ጊዜ ሁሉ እንዲሰብኩ ማበረታቻ ተሰጥቷቸዋል። በእኛ አገር ሰዎች በሚገኙበት ቦታ ሁሉ መደበኛ በሆነና መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመስበክ ረዘም ላሉ ዓመታት ጥረት ሲደረግ የቆየ ሲሆን ይህም ጥሩ ውጤት አስገኝቷል። ይሁን እንጂ ለማንም ሳናዳላ ሁሉንም ሰው ማነጋገር እንድንችል ከቤት ወደ ቤት ሄደን ክልላችንን በመሸፈን ረገድ ብዙ መሥራት ያስፈልገናል። በእኛ አገር ከቤት ወደ ቤት ስንሄድ በአብዛኛው አንድ ሰው ቤት ውስጥ አናጣም። ብዙውን ጊዜ ሰዎች ለመወያየት ፈቃደኞች ከመሆናቸውም በላይ በቀላሉ ተመላልሶ መጠየቅ ማድረግ እንችላለን። ተመላልሶ መጠየቅ በማድረግም ረገድ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል።
3 ከቤት ወደ ቤት ማገልገል በይሖዋ ላይ መመካትን ስለሚጠይቅብንና የአምላክ ቃል የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ለመጠቀም አጋጣሚ ስለሚከፍትልን መንፈሳዊነታችንን ለማሳደግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደርጋል። በእርግጥም በዚህ መንገድ ክልሎችን መሸፈናችን መጽሔቶችን ከማበርከት በተጨማሪ በአገልግሎታችን መጽሐፍ ቅዱስን እንድንጠቀም ያስችለናል። ይህ የአገልግሎቱ ዘርፍ የወንድማማች ማኅበራችን መለያ በሆነውና ኢየሱስ ክርስቶስ ባስጀመረው የአገልግሎት ዘዴ መካፈል ስለሚያስችለን ልዩ ደስታ ይሰጠናል።
4 ከቤት ወደ ቤት ማገልገል የራሱ የሆኑ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚኖሩት እሙን ነው። ቤታቸው ስለሄድን በጣም የሚያመናጭቁን ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች እንዲህ ያለ ምላሽ የሚሰጡት በቀጥታ ለእኛ ሳይሆን ለይሖዋና ለመንግሥቱ እውነቶች መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ይህንን ካስታወስን የሚደርስብንን መከራ እንደ ደስታ ልንቆጥረው እንችላለን። ማቴዎስ 5:11, 12 እና ፊልጵስዩስ 1:27-29 ይህንን ያጎሉልናል።
5 አልፎ አልፎ አንዳንድ ሃይማኖታዊ አክራሪዎች ረብሻ እንደፈጠሩ መስማታችን በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ ከመካፈል ወደ ኋላ እንድንል ሊያደርገን ይገባልን? ሐዋርያቱ ተመሳሳይ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ምን ማድረግ እንዳለባቸው ኢየሱስ በማቴዎስ 10:26-31 ላይ የሰጣቸውን ምክር ማስታወሳችን ትክክለኛ አመለካከት እንድንይዝ ሊረዳን ይችላል። በእርግጥም ይሖዋ እንደሚመራንና እንደሚጠብቀን ልንተማመን እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ ከወረዳ የበላይ ተመልካቾቻችን አንዱ ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥ በግምት ከ1, 500 ሰዓታት በላይ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት በማሳለፉ በርካታ አስደሳች ተሞክሮዎችን ያገኘ ሲሆን ረብሻ የሚያስነሱ ሰዎች ያጋጠሙት ሁለት ጊዜ ብቻ ነበር። በእነዚህም ጊዜያት ቢሆን ምንም ዓይነት ጉዳት አልደረሰበትም። እንደዚህ ዓይነት ተቃውሞ አክራሪ ከሆኑ ዘመዶቻችን ወይም ወደ ክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ስንሄድ መንገድ ላይ ከሚያጋጥሙን ሰዎች ሊሰነዘርብን እንደሚችል ማስታወሳችን ከቤት ወደ ቤት ለሚደረገው አገልግሎት ትክክለኛ አመለካከት እንድንይዝ ይረዳናል። ሆኖም በእነዚህ ጊዜያት በይሖዋ እንደምንታመን የታወቀ ነው።—ምሳሌ 29:25
6 የአገልግሎት ክልላችንን ለመሸፈን ልዩ ዘመቻ በምናደርግበት በዚህ ወቅት ከቤት ወደ ቤት ለሚደረገው አገልግሎት ቅድሚያ መስጠታችን ተገቢ ነው። ይህም አብዛኛውን ጊዜያቸውን በቤታቸው አካባቢ የሚያሳልፉ ሰዎች ውድ የሆነውን መልእክታችንን እንዲሰሙ አጋጣሚ ይከፍትላቸዋል። ይሁን እንጂ ከዚያ በኋላ ባለው ጊዜም ቢሆን ሁላችንም በዚህ የአገልግሎታችን ዘርፍ በድፍረትና በቅንዓት ለመካፈል ጥረት እናድርግ። ይሖዋ እንደሚባርከን ምንም ጥርጥር የለውም። እኛም ሐዋርያው ጳውሎስ በሥራ 20:21, 26 (NW ) ላይ እንደተናገረው ‘የተሟላ ምስክርነት ሰጥቻለሁ’ ስለዚህም ‘ከሰው ሁሉ ደም ንጹሕ ነኝ’ ብለን መናገር በመቻላችን እርካታ እናገኛለን።