አምላክ ላሳየን ምሕረት አመስጋኝ መሆን
1 ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት የክርስትናን መስፋፋት አጥብቆ ይቃወም ነበር። ይሁን እንጂ እንዲህ ያደረገው ባለማወቅ በመሆኑ ምሕረት አግኝቷል። ይሖዋ ለጳውሎስ የማይገባ ደግነት በማሳየት የስብከት ሥራ ሰጥቶታል። ጳውሎስ የተሰጠውን ሥራ በከፍተኛ አድናቆት ተመልክቶታል። (ሥራ 26:9-18፤ 1 ጢሞ. 1:12-14) ጳውሎስ፣ ይሖዋ ላሳየው ምሕረት ያደረበት የአመስጋኝነት ስሜት አገልግሎቱን ለመፈጸም ሲል የራሱን ጥቅም እንዲሠዋ አነሳስቶታል።—2 ቆሮ. 12:15
2 በአምላክ ምሕረት የተነሳ እኛም የአገልግሎት መብት ተሰጥቶናል። (2 ቆሮ. 4:1) እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም ሌሎች በመንፈሳዊ ዕድገት እንዲያደርጉ ራሳችንን ሳንቆጥብ በመርዳት ለተደረገልን ምሕረት አመስጋኝነታችንን መግለጽ እንችላለን። ይህንን ማድረግ የምንችልበት አንደኛው መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በማስጀመርና በማስጠናት ነው።
3 የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ማስጀመር:- የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ማስጀመር የምንችልበት አንደኛው መንገድ የመጽሔት ደንበኞች በማፍራት ነው። ደንበኞቻችንን ደጋግመን በጠየቅናቸው መጠን የሚያሳስቧቸውን ነገሮች ይበልጥ ማወቅ እንችላለን። ውሎ አድሮ በመጽሔቶቻችን ላይ የወጣ አንድ ርዕስ አምላክ ከእኛ የሚፈልገው በተባለው ብሮሹር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማስጀመር መንገድ ሊከፍትልን ይችላል። ከዚህ በኋላ መጽሔት ለማበርከት በምንሄድባቸው ጊዜያት በብሮሹሩ ውይይታችንን መቀጠል እንችል ይሆናል።
4 ጸሎት የታከለበት ጥረት ማድረግ አስፈላጊ ነው:- ጥናት ለማግኘት ከመጸለያችን በተጨማሪ ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረጋችን የስብከት ሥራችንን ውጤታማ ያደርግልናል። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የነበራት አንዲት አቅኚ ይሖዋን ተጨማሪ ጥናቶች ለማግኘት እንዲረዳት ለመነችው። ከዚህ በተጨማሪ በጸሎቷ ላይ የራሷን ጥረት አከለችበት። የአገልግሎት እንቅስቃሴዋን ቆም ብላ ስትገመግም ተመላልሶ መጠየቅ ለምታደርግላቸው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ ሐሳብ እንደማታቀርብላቸው አስተዋለች። በዚህ ረገድ ማሻሻያ በማድረጓ በጥቂት ጊዜ ውስጥ ሁለት ተጨማሪ ጥናቶች አገኘች።
5 “የእግዚአብሔርን ጸጋ ወንጌልን” የማሳወቅ መብት በማግኘታችን ምንኛ ታድለናል! (ሥራ 20:24) አምላክ ላሳየን ምሕረት ያለን አመስጋኝነት ሌሎች ከይሖዋ የማይገባ ደግነት እንዲጠቀሙ በመርዳት ረገድ በትጋት ለመሥራት እንዲያነሳሳን እንመኛለን።