አዲስ የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም
1 ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ መከራ እንደሚደርስባቸው አስቀድሞ ተናግሮ ነበር። (ማቴ. 24:9) ለመከራ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? የሚደርስብንን መከራ በጽናት እንድናሳልፍ የሚያስችለን ምንድን ነው? ለ2004 የአገልግሎት ዓመት የተዘጋጀው የወረዳ ስብሰባ ፕሮግራም ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይዟል። ጭብጡ ‘በተስፋ ደስ ይበላችሁ፤ በመከራ ጽኑ’ የሚል ነው።—ሮሜ 12:12
2 ሁለት ተከታታይ ንግግሮች:- “በመጽናት ፍሬ ማፍራት” የሚል ርዕስ ባለው በመጀመሪያው ተከታታይ ንግግር ላይ ፍሬ ማፍራት የምንችልባቸው መንገዶች ይብራራሉ። በመስበኩና በማስተማሩ ሥራ በጥድፊያ ስሜት የሚካፈሉበትን መንገድ በተመለከተ ከበርካታ አስፋፊዎች ጋር ቃለ ምልልስ ይደረጋል። ወላጆች “ይሖዋ በሚገሥጸን ጊዜ” ለሚለው ንግግር ልዩ ትኩረት እንደሚሰጡ የታወቀ ነው። በዚህ ንግግር ላይ ወላጆች ማስረጃ እያቀረቡ እንዴት ልጆቻቸውን ማግባባት እንደሚችሉ ይብራራል። የዚህን ተከታታይ ንግግር የመጨረሻ ክፍል የሚያቀርበው ወንድም ዓለም ቀስ በቀስ አቋማችንን በማዳከም ፍሬ ቢሶች እንዳያደርገን ለመከላከል ምን ማድረግ እንዳለብን ይገልጻል።—ማር. 4:19
3 የሁለተኛው ተከታታይ ንግግር ጭብጥ “ሩጫውን በጽናት ሩጡ” ይላል። ክርስቲያናዊ አኗኗራችን በሩጫ ሊመሰል የሚችልበት መንገድ ይብራራል። በሕጉ መሠረት መሮጥ ያለብን ለምንድን ነው? በሕይወት ሩጫ ላይ ሸክምን ሁሉ ማስወገድና ሳንዝል መሮጥ የምንችለው እንዴት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተው ወቅታዊ ምክር ሁላችንም በጽናት መሮጣችንን እንድንቀጥል ያበረታታናል።
4 ጽናት በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያስገኝልናል:- ተጓዥ የበላይ ተመልካቾቹ የሚያቀርቧቸውን ንግግሮች አዳምጠው በተግባር የሚያውሉ ሰዎች እምነታቸው ይጠናከራል። የአውራጃ የበላይ ተመልካቹ ከሚያቀርባቸው ንግግሮች መካከል አንደኛው “ጽናት መለኮታዊ ተቀባይነት ያስገኛል” የሚል ርዕስ አለው። የሕዝብ ንግግሩ፣ ብሔራት ተስፋ ማድረግ ያለባቸው በማን ስም ነው? ይህስ ምን ነገሮችን ያካትታል? ለሚሉት ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል። “በመጽናታችሁ ነፍሳችሁን ታድናላችሁ” በሚለው የመደምደሚያ ንግግር ላይ ኢየሱስ ያሳደዱትን ሰዎች በጥላቻ ዓይን ሳይመለከት የደረሰበትን የፍትሕ መጓደል እንዴት በጽናት መወጣት እንደቻለ ይብራራል።
5 የአገልግሎት ትምህርት ቤት መጽሐፋችሁንና በዚያ ሳምንት የሚጠናውን መጠበቂያ ግንብ ይዛችሁ መምጣት አትርሱ። ትምህርቱን በትኩረት ለመከታተል እንዲረዳችሁና ወደፊት ለክለሳ እንዲጠቅማችሁ ማስታወሻ ያዙ። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ፕሮግራሙ በጉባኤ ስብሰባ ላይ በክለሳ ይቀርባል።
6 ይህን የመንፈሳዊ ምግብ ድግስ ያዘጋጀው ይሖዋ ራሱ ነው። መጥታችሁ እንድትመገቡ ተጋብዛችኋል! ከመላው ፕሮግራም ለመጠቀም በስብሰባው ላይ የምንገኝ ከሆነ ልባችን በደስታ ይሞላል።—ኢሳ. 65:14