ለሰብዓዊ ባለ ሥልጣናት ሊኖረን የሚገባው አመለካከትa
“ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል!” (ሥራ 5:29) ለአምላክ ያለብንን ይህን ግዴታ ማክበር “ቄሳር” ከሚፈልግብን ነገር ጋር የሚጋጭ ሊሆን ቢችልም በግላችን የማንስማማባቸውን ሕጎች ሆን ብለን መጣስ ግን ከዚህ ፈጽሞ ይለያል። እርግጥ ነው ከግል አመለካከታችን አንጻር አንዳንድ ሕጎች አላስፈላጊ ወይም ምንም መፈናፈኛ የሌላቸው መስለው ሊታዩን ይችላሉ። ይሁን እንጂ ይህ ከአምላክ ሕግጋት ጋር የማይጋጩ ሰብዓዊ ሕግጋትን ለመጣስ ምክንያት ሊሆነን አይችልም። ሰዎች ሁሉ ለራሳቸው የሚጠቅሙ ሆነው ያገኟቸውን ሕግጋት ብቻ መታዘዝ ቢጀምሩ ውጤቱ ምን ይሆን ነበር? ሕገ ወጥነት ይስፋፋ ነበር።
አንድ ሰው ሊያዝና ሊቀጣ የሚችልበት አጋጣሚ ጠባብ ስለሆነ ሕግን ጥሶ ያሻውን ማድረግ እንደሚችል ሊሰማው ይችላል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ አስተሳሰብ በጣም አደገኛ ነው። ግለሰቡ መጀመሪያ ላይ ሕግ የሚጥሰው በጥቃቅን ጉዳዮች ብቻ ቢሆንም ከቅጣት ለማምለጥ መቻሉ ከበድ ያሉ ሕጎችንም እንዲጥስ ሊያደፋፍረው ይችላል። መክብብ 8:11 እንደሚለው “በወንጀል ላይ ባፋጣኝ ፍርድ ካልተሰጠ፣ የሰዎች ልብ ክፉን በማድረግ ዕቅድ ይሞላል።” ይሁን እንጂ ለሕግ የምንገዛበት ዋነኛ ምክንያት ያለመታዘዛችን የሚያስከትለውን ቅጣት በመፍራት ነው? አንድ ክርስቲያን ለሕግ እንዲታዘዝ የሚገፋፋው ከዚህ የበለጠ ጠንካራ ምክንያት አለው። ሐዋርያው ጳውሎስ ዋነኛው ምክንያት ንጹሕ ሕሊና እንዲኖረን ያለን ፍላጎት እንደሆነ ተናግሯል። (ሮሜ 13:5) ቅዱስ ጽሑፋዊ በሆኑ መሠረታዊ ሥርዓቶች የሰለጠነ ሕሊና ያለው ሰው ሕግን መጣስ “በእግዚአብሔር ሥርዐት ላይ” ማመጽ እንደሆነ ያውቃል። (ሮሜ 13:1, 2) የምናደርገውን ነገር ሰዎች ባያውቁም እንኳን አምላክ ማወቁ አይቀርም፤ የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋችን የተመካው ደግሞ በእርሱ ላይ ነው።—1 ጴጥ. 2:12-17
ይህ ሥርዓት አንድ ወጣት ለመምህሩ እንዲሁም አንድ አዋቂ ሰው ለአሠሪው ሊኖረው በሚገባው አመለካከት ላይም ይሠራል። ብዙ ሰዎች መጥፎ ነገር የሚያደርጉ መሆናቸው እኛም እንደዚያ ለማድረግ ምክንያት ሊሆነን አይገባም። የምናደርገውን ነገር መምህራችን ወይም አሠሪያችን ማወቅ አለማወቁ ልዩነት አያመጣም። ወሳኙ ነገር ትክክለኛ የሆነው ድርጊት የቱ ነው? አምላክን የሚያስደስተው ምንድን ነው? የሚለው ነው። እንድናደርግ የተጠየቅነው ነገር ከአምላክ ሕጎች ወይም ከጽድቅ መሠረታዊ ሥርዓቶቹ ጋር የማይጋጭ ከሆነ መተባበር ይኖርብናል። መምህራን በአጠቃላይ ሲታይ ለሰብዓዊ መንግሥታት ማለትም “በሥልጣን ላሉት ሹማምንት” ወኪሎች ስለሆኑ አክብሮት ሊሰጣቸው ይገባል። አሠሪዎችን በሚመለከት ደግሞ በቲቶ 2:9, 10 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ተግባራዊ ሊሆን ይችላል። እርግጥ ነው፣ ጳውሎስ የጻፈው በባሪያዎችና በጌቶች መካከል ስላለው ግንኙነት ቢሆንም እንዲህ ብሎ ነበር:- “[ጌቶቻቸውን] ደስ እንዲያሰኟቸው፣ . . . ይኸውም በሁሉም መንገድ የአዳኛችን የእግዚአብሔር ትምህርት ይወደድ ዘንድ ፍጹም ታማኝ መሆናቸውን እንዲያስመሰክሩ ነው።” በመሆኑም ‘በማይታዘዙ ሰዎች ላይ ከሚሠራው’ ከሰይጣን መንፈስ ተጽዕኖ በመራቅ ከሰዎች ሁሉ ጋር ሰላማዊ ግንኙነት እንዲኖረን ጥረት እናደርጋለን።—ኤፌ. 2:2, 3
a [የግርጌ ማስታወሻ]
* ይህ ጽሑፍ የተወሰደው እውነተኛ ሰላምና ደኅንነት (እንግሊዝኛ) ከተባለው መጽሐፍ ገጽ 134-136 ላይ ነው።