የጥያቄ ሣጥን
◼ በጉባኤ ውስጥ ለሚሰጡን የሥራ ምድቦች ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል?
በይሖዋ ሕዝቦች ጉባኤ ውስጥ እያንዳንዱ ነገር በሥርዓት የሚከናወነው ሁሉም ሰው ተባብሮ ስለሚሠራ ነው። (1 ቆሮ. 14:33, 40) እስቲ አንድ የጉባኤ ስብሰባ ብቻ እንኳ ምን ምን ነገሮች እንደሚያስፈልጉት አስብ። ስብሰባውን ሳይጨምር ከስብሰባው በፊትና በኋላ ወንድሞችና እህቶች ተመድበው የሚሠሯቸው ብዙ ሥራዎች አሉ። አንዳንዶቹ እኛ የማናያቸው ቢሆኑም እንኳን አስፈላጊና ጠቃሚ እንደሆኑ አይካድም። ታዲያ ሁላችንም በዚህ ዝግጅት ውስጥ የበኩላችንን ድርሻ ማበርከት የምንችለው እንዴት ነው?
ራስህን አቅርብ። በፈቃደኝነት ራሳቸውን የሚያቀርቡ ሁሉ የሚሠሩት ብዙ ሥራ አለ። (መዝ. 110:3) ለታመሙና ለአረጋውያን አሳቢነት በማሳየት፣ የመንግሥት አዳራሽ በማፅዳት እንዲሁም ሌሎች ጠቃሚ የሆኑ ሥራዎችን የግድ ትእዛዝ እስኪሰጠን ድረስ ሳንጠብቅ በመሥራት የፈቃደኝነት መንፈስ እንዳለን ማሳየት እንችላለን።
በትሕትና አገልግል። ትሑት የሆኑ ሰዎች ሌሎችን ማገልገል ያስደስታቸዋል። (ሉቃስ 9:48) ትሑት መሆናችን ከአቅማችን በላይ የሆኑ ኃላፊነቶችን እንዳንቀበል እንዲሁም አለቦታችን እንዳንገባ ይረዳናል።—ምሳሌ 11:2
እምነት የሚጣልብህ ሁን። ሙሴ በጥንቷ እስራኤል የኃላፊነት ቦታዎችን እንዲይዙ “እምነት የሚጣልባቸውን ሰዎች” እንዲመርጥ ተነግሮት ነበር። (ዘፀ. 18:21 NW) ዛሬም ይህ ባሕርይ አስፈላጊ ነው። የተሰጠህን ማንኛውንም ዓይነት ሥራ በጥንቃቄ መሥራት ይኖርብሃል። (ሉቃስ 16:10) የተሰጠህን ሥራ መሥራት የማትችልበት አጋጣሚ ቢፈጠር አንተን የሚተካ ሌላ ሰው እንዲመደብ ማድረግ ይኖርብሃል።
ምርጥህን ስጥ። ክርስቲያኖች ሰብዓዊ ሥራቸውንም እንኳ በሙሉ ልብ እንዲሠሩ ተመክረዋል። (ቆላ. 3:22-24) እውነተኛውን አምልኮ ለመደገፍማ በሙሉ ልብ መሥራት እንደሚኖርባቸው ምንም ጥርጥር የለውም። የተሰጠን የሥራ ምድብ አነስተኛ ወይም ብዙም የማያስፈልግ ሊመስል ቢችልም ከልባችን ከሠራነው ለጉባኤው ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
እያንዳንዱ የሚሰጠን ሥራ ለይሖዋም ሆነ ለወንድሞቻችን ያለንን ፍቅር የምናሳይበትን አጋጣሚ ይከፍትልናል። (ማቴ. 22:37-39) እንግዲያውስ የተሰጠንን ማንኛውንም ዓይነት ሥራ በታማኝነት እናከናውን።