መጽሔቶችን ለማበርከት ምን ማለት ይቻላል?
መጠበቂያ ግንብ ሐምሌ 1
“በችግር በተሞላው በዚህ ዓለም ውስጥ ብዙ ሰዎች ‘ሕይወት ይህን ያህል በመከራ የተሞላው ለምንድን ነው? አምላክ በእርግጥ ካለ፣ መከራን ለማስወገድ አንድ እርምጃ የማይወስደው ለምንድን ነው?’ በማለት ይጠይቃሉ። እርስዎስ እንዲህ ብለው ጠይቀው ያውቃሉ? [መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው።] ይህ መጽሔት መጽሐፍ ቅዱስ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠውን መልስ ይዟል።” ሁለተኛ ጢሞቴዎስ 3:16ን አንብብ።
ንቁ! ሐምሌ 2006
“በዛሬው ጊዜ ውጥረት ውስጥ የገቡ ትዳሮች ቁጥር እየጨመረ ነው። ባለትዳሮች በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን ይህን ምክር ቢከተሉ ጥቅም የሚያገኙ ይመስልዎታል? [ኤፌሶን 4:32ን አንብብ። ከዚያም መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው።] ይህ ንቁ! መጽሔት ደስታ የሰፈነበት ትዳር ለመመሥረት የሚረዱንን ዘመን የማይሽራቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎች ያብራራል።”
መጠበቂያ ግንብ ሐምሌ 15
“ለሰው ልጆች ችግሮች መፍትሔ የሚያስገኝ መንግሥት የምናይበት ጊዜ ይመጣል ብለው ያስባሉ? [መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው።] በማቴዎስ 6:9, 10 ላይ ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ዓይነት መንግሥት እንዲመጣላቸው ጸሎት እንዲያቀርቡ አስተምሯቸዋል። [ጥቅሱን አንብብ።] ይህ መጽሔት የአምላክ መንግሥት ከሰብዓዊ መንግሥታት በምን እንደሚበልጥና ለሰው ልጆች ምን በረከቶችን እንደሚያመጣላቸው ያብራራል።”
ንቁ! ሐምሌ 2006
ወጣት በምታገኙበት ጊዜ እንዲህ ማለት ትችላላችሁ:- “በአንተ ዕድሜ ያሉ ብዙ ወጣቶች ስለ ትዳር ያስባሉ። ይህን ጉዳይ በተመለከተ አስተማማኝ መረጃ ማግኘት የምትችለው ከየት ይመስልሃል? [መልስ እስኪሰጥ ጠብቀው።] ጋብቻን ያቋቋመው ማን እንደሆነ እስቲ ተመልከት። [ማቴዎስ 19:6ን አንብብ።] ይህ መጽሔት ደስተኛ ትዳር ለመመሥረት የሚረዱ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መመሪያዎችን ያብራራል።”