የቀድሞው ፍቅራችሁ እንዳይጠፋ ተጠንቀቁ
1 ክብር የተጎናጸፈው ኢየሱስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኤፌሶን ይገኝ የነበረውን ጉባኤ እንዲህ በማለት መክሮት ነበር:- “የምነቅፍብህ ነገር አለኝ፤ ይኸውም የቀድሞውን ፍቅርህን ትተሃል።” (ራእይ 2:4) ከዚህ ለመረዳት እንደሚቻለው ብዙዎቹ ለይሖዋ የነበራቸው የቀድሞ ፍቅር ጠፍቶ ነበር። እውነትን ስንማር ለአምላክም ሆነ ለሰዎች ጠንካራ ፍቅር አዳብረን የነበረ ሲሆን ይህ ደግሞ አዲስ ያገኘነውን ተስፋ በቅንዓት ለሌሎች እንድናካፍል ገፋፍቶን ነበር። ታዲያ የቀድሞው ፍቅራችን እንዳይጠፋና ለአገልግሎት ያለን ቅንዓት እንዳይቀዘቅዝ ምን ሊረዳን ይችላል?
2 የግል ጥናትና በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ መገኘት:- በመጀመሪያ ላይ እውነትን ስንማር ለአምላክና ለሰዎች ፍቅር እንድናዳብር የረዳን ነገር ምንድን ነው? ይህን ፍቅር ለማዳበር የቻልነው ቅዱሳን መጻሕፍትን አጥንተን ስለ ይሖዋ በማወቃችን አይደለም? (1 ዮሐ. 4:16, 19) በመሆኑም ፍቅራችን “በዝቶ እንዲትረፈረፍ” ከፈለግን “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር” በመቆፈር ትክክለኛውን እውቀት መቅሰማችንን እንቀጥል።—ፊልጵ. 1:9-11፤ 1 ቆሮ. 2:10
3 በእነዚህ የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ የተለያዩ ጭንቀቶችና ትኩረታችንን የሚከፋፍሉ ነገሮች በመኖራቸው ጥሩ የግል ጥናት ልማድ ማዳበር አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። (2 ጢሞ. 3:1) ሆኖም መንፈሳዊ ምግብ ለመመገብ ጊዜ መመደብ አለብን። በተለይ “ቀኑ እየተቃረበ መምጣቱን” ስናይ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን መገኘታችን አስፈላጊ ነው።—ዕብ. 10:24, 25
4 አገልግሎት:- በአገልግሎት ላይ በቅንዓት መሳተፋችን ለአምላክ የነበረንን የቀድሞ ፍቅር አጽንተን እንድንይዝ ይረዳናል። ምሥራቹን መስበካችን የይሖዋን ተስፋዎች እንድናስታውስ የሚያደርገን ሲሆን ይህ ደግሞ ተስፋችን ብሩህ እንዲሆንና ፍቅራችን ሕያው ሆኖ እንዲቀጥል ይረዳናል። የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች ማስተማር እኛ ራሳችን ትምህርቱን በግልጽ ለመረዳት ስንል ምርምር ማድረግ ይጠይቅብናል፤ ይህ ደግሞ እምነታችንን ያጠናክርልናል።—1 ጢሞ. 4:15, 16
5 ይሖዋ፣ ፍቅራችንን ጨምሮ ሁሉን ነገር ልንሰጠው የሚገባው አምላክ ነው። (ራእይ 4:11) በመሆኑም ፍቅራችሁ እየቀነሰ እንዲሄድ አትፍቀዱ። ትጋት የተሞላበት የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማድረግ፣ በጉባኤ ስብሰባዎች አዘውትሮ በመገኘትና በጣም የምትወዱትን የምሥራች ለሌሎች በቅንዓት በማወጅ የቀድሞውን ፍቅራችሁን አጽንታችሁ ያዙ።—ሮሜ 10:10