ፍቅር—ፍሬያማ የሆነ አገልግሎት ለማከናወን የሚያስችል ቁልፍ
1 “ወደ እኔ ኑ፤ እኔም ዕረፍት እሰጣችኋለሁ።” (ማቴ. 11:28) እነዚህ ማራኪ ቃላት ኢየሱስ ለሰዎች ያለውን ጥልቅ ፍቅር ያንጸባርቃሉ። ክርስቲያን አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ፍቅር የጠፋበት ይህ ዓለም በሚያሳድረው ተጽዕኖ ለዛሉ ሰዎች ፍቅራችንን በማሳየት ኢየሱስን መምሰል እንፈልጋለን። በስብከቱ ሥራችን ለሰዎች ፍቅር ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው?
2 በንግግራችን:- ኢየሱስ፣ ለሰዎች ፍቅር ስለነበረው ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ ምሥራቹን ይሰብክ ነበር። (ዮሐ. 4:7-14) መደበኛ ባልሆነ መንገድ ለመመሥከር የምንፈራ ከሆነ ፍቅር ይህን ስሜት ለማሸነፍ ይረዳናል። አንዲት የስድስት ዓመት ልጅ በሆስፒታል ተራ መጠበቂያ ክፍል ውስጥ አጠገቧ ለተቀመጠች ሴት ግሩም አድርጋ መሠከረችላት። እንዲህ እንድታደርግ ያነሳሳት ምንድን ነው? “ሴትየዋ ስለ ይሖዋ ማወቅ የሚያስፈልጋት ትመስል ነበር” ብላለች።
3 ከልብ በመነጨ ሞቅ ያለ ፈገግታና ወዳጃዊ በሆነ የድምፅ ቃና ለሰዎች እንደምናስብ ማሳየት እንችላለን። ከዚህም በተጨማሪ የሚሰጡትን ሐሳብ በጥሞና በማዳመጥ፣ የሚያሳስባቸውን ነገር በመረዳት እንዲሁም ከልብ የመነጨ አሳቢነት በማሳየት ለሌሎች ያለንን ፍቅር እንገልጻለን። (ምሳሌ 15:23) እኛም ልክ እንደ ኢየሱስ ለሰዎች አጽናኝ የሆነውን የመንግሥቱን መልእክትና የይሖዋን ፍቅራዊ ርኅራኄ ጎላ አድርገን መግለጽ ይኖርብናል።—ማቴ. 24:14፤ ሉቃስ 4:18
4 በተግባራችን:- ኢየሱስ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ሊጠቅማቸው በሚችል መንገድ ለመርዳት ንቁ ነበር። (ማቴ. 15:32) እኛም በአገልግሎት ላይ ስንሆን ፍቅራዊ ደግነት ለማሳየት አጋጣሚ ልናገኝ እንችላለን። አንዲት ሴት አስፈላጊ ለሆነ ጉዳይ የደወለላት ሰው የሚነግራትን ለመረዳት እንደተቸገረች አንዲት እህት ተመለከተች። እህታችንም ለሴትየዋ የደወለላት ሰው የሚናገረውን በመተርጎም ረዳቻት። ይህ ፍቅራዊ እርዳታ ቅዱስ ጽሑፋዊ ውይይት እንዲያደርጉ መንገድ የከፈተ ሲሆን ሴትየዋም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለመጀመር ተስማማች። በሌላ አጋጣሚ ደግሞ አንድ ወንድም ተመላልሶ መጠየቅ በሚያደርግበት ጊዜ፣ የቤቱ ባለቤት ከባድ የሆነ ሶፋ በበሩ በኩል ለማሳለፍ ሲሞክር ተቀርቅሮበት ሲበሳጭ አገኘው። ወንድም ሶፋውን ለማስገባት ሰውየውን ካገዘው በኋላ ለተደረገለት እርዳታ አመስጋኝ የሆነውን ይህን ሰው በዚያው ሶፋ ላይ ተቀምጦ መጽሐፍ ቅዱስ ማስጠናት ጀመረ።
5 በአገልግሎት ስንካፈል ለአምላክና ለሰዎች ያለንን ፍቅር እናሳያለን። (ማቴ. 22:36-40) በንግግራችንም ሆነ በተግባራችን የምናሳየው እንዲህ ያለው ፍቅር ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች እውነትን መያዛችንን እንዲገነዘቡ ያደርጋል።