ማመራመር የተባለውን መጽሐፍ እየተጠቀማችሁበት ነው?
1. ሐዋርያው ጳውሎስና ኢየሱስ ሌሎችን ያስተምሩ የነበረው እንዴት ነው?
1 ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ሰዎችን ለማወያየት’ ይጥር ነበር። (ሥራ 17:2, 3፤ 18:19) በዚህ መንገድ የኢየሱስን ምሳሌ ኮርጇል። ኢየሱስ፣ አድማጮቹ የአምላክን ፈቃድ እንዲያስተውሉ ለመርዳት ዘወትር ከቅዱሳን መጻሕፍት ይጠቅስና ምሳሌዎችን ይጠቀም ነበር። (ማቴ. 12:1-12) ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር የተባለው መጽሐፍ እኛም ይህን ማድረግ እንድንችል ለመርዳት ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
2. ውጤታማ መግቢያዎችን ለመዘጋጀት ማመራመር የተባለውን መጽሐፍ መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
2 ውጤታማ መግቢያዎችን መዘጋጀት፦ ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሱ ማመራመር የተባለው መጽሐፍ ከገጽ 9 እስከ 15 ላይ የሰዎችን ፍላጎት የሚቀሰቅሱ መግቢያዎችን ይዟል። በተለይ ክልላችሁን በተደጋጋሚ የምትሸፍኑ ከሆነ የተለያዩ መግቢያዎችን መዘጋጀታችሁና መጠቀማችሁ እንደየሁኔታው መግቢያችሁን መለዋወጥ እንዲሁም ሰዎችን ውጤታማ በሆነ መንገድ ማነጋገር እንድትችሉ ይረዳችኋል። በስልክ ተጠቅማችሁ ስትመሠክሩ ልትጠቀሙበት ያሰባችሁትን መግቢያ በቀጥታ ከመጽሐፉ ማንበብ ትችሉ ይሆናል።
3. ማመራመር በተባለው መጽሐፍ ከገጽ 16 እስከ 24 ላይ በአገልግሎት ሊረዱን የሚችሉ ምን ሐሳቦች ይገኛሉ?
3 ውይይት የሚያስቆሙ ሐሳቦች በሚሰነዘሩበት ጊዜ፦ በክልላችሁ ውስጥ በምታገለግሉበት ጊዜ ውይይቱን ለማስቆም የሚሞክሩ ሰዎች ሊያጋጥሟችሁ እንደሚችሉ በማሰብ አገልግሎት ከመጀመራችሁ በፊት ጥቂት ደቂቃዎች ወስዳችሁ ከገጽ 16 እስከ 21 ላይ ያሉትን ሐሳቦች ለምን አትከልሱም? ከቤት ወደ ቤት ስታገለግሉ ቡዲስቶች፣ ሂንዱዎች፣ አይሁዶችና ሙስሊሞች ያጋጥሟችሁ ይሆን? ከሆነ ከገጽ 21 እስከ 24 ላይ የሚገኙት ሐሳቦች ይረዷችኋል።
4. አንድ ጥያቄ ወይም አከራካሪ ርዕሰ ጉዳይ በሚነሳበት ጊዜ ማመራመር የተባለውን መጽሐፍ እንዴት ልንጠቀምበት እንችላለን?
4 ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ መስጠት፦ ማመራመር የተባለው መጽሐፍ፣ ጥያቄ ወይም አከራካሪ ርዕሰ ጉዳይ በሚነሳበት ጊዜም ሊረዳን ይችላል። እያነጋገራችሁት ያለውን ሰው ከተነሳው ርዕሰ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ከማመራመር መጽሐፍ ላይ አንድ ጠቃሚ ሐሳብ ልታሳዩት እንደምትፈልጉ ልትገልጹለት ትችላላችሁ። ከዚያም የርዕስ ማውጫውን ተጠቅማችሁ የምትፈልጉትን ርዕስ አውጡ። ደመቅ ብለው የተጻፉትን ጥያቄዎች አለፍ አለፍ እያላችሁ ተመልከቱ። የምትፈልጉትን ሐሳብ ቶሎ ማግኘት ካልቻላችሁ በመጽሐፉ የመጨረሻ ገጾች ላይ በሚገኘው ማውጫ መጠቀም ትችላላችሁ። የምትፈልጉትን ሐሳብ ስታገኙ በቀጥታ ከመጽሐፉ ላይ አንብቡለት። በአንድ ጥቅስ ላይ እየተወያያችሁ ከሆነ ደግሞ በገጽ 445 ላይ የሚገኘውን “አለቦታቸው የሚጠቀሱ ጥቅሶች” የሚለውን ርዕስ መመልከት ትችላላችሁ።
5. ማመራመር የተባለው መጽሐፍ ምን ተጨማሪ ጥቅሞች አሉት?
5 ተጨማሪ ጥቅሞች፦ አንዳንዶች፣ ‘ዓመት በዓላትን የማታከብረው ለምንድን ነው?’ እንደሚሉት ላሉ ጥያቄዎች መልስ ለመስጠት እንዲረዳቸው ማመራመር የተባለውን መጽሐፍ ወደ ሥራ ቦታቸው ወይም ወደ ትምህርት ቤት ይዘውት ይሄዳሉ። አንዳንድ ጊዜ ወጣቶች በትምህርት ቤት የሚቀርብ ጽሑፍ ሲያዘጋጁ “ፍጥረት” እና “ዝግመተ ለውጥ” በሚሉት ርዕሶች ሥር ያሉትን መረጃዎች ይጠቀማሉ። ለታመመ አሊያም ሐዘን ላይ ላለ ሰው ቅዱስ ጽሑፋዊ ማጽናኛ ለመስጠት “ማበረታቻ” በሚለው ርዕስ ሥር የሚገኘውን ሐሳብ ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ። በተጨማሪም ማመራመር የተባለው መጽሐፍ ንግግር ለሚዘጋጁ እንዲሁም የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ለሚመሩ ወንድሞች ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦችን ይዟል።
6. በምንሰብክበት ጊዜ ዓላማችን ምንድን ነው?
6 በምንሰብክበት ጊዜ ዓላማችን ተከራክሮ መርታት ወይም መረጃ መስጠት ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀስን በደንብ ማስረዳት እንፈልጋለን። ማመራመር በተባለው መጽሐፍ በሚገባ መጠቀማችን ለምናስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት እንደምንሰጥ ያሳያል።—1 ጢሞ. 4:16