የመስክ አገልግሎት ጎላ ያሉ ገጽታዎች
እውነቱን ማወቅ ትፈልጋለህ? የተባለው ትራክት በአገራችን በሰባት ቋንቋዎች ከ400,000 ቅጂዎች በላይ በሰፊው ተሰራጭቷል። በአንድ ከተማ ውስጥ የሚኖር አንድ ሰው የትራክቱን ስርጭት አስመልክቶ ሲናገር “እንደ ሱናሚ” ነበር ብሏል። በመላው አገሪቱ ከ93,000 በላይ ተመላልሶ መጠየቆች ተደርገዋል፤ ይህም ትልቅ መሻሻል ነው። ይህ ትራክት ወደፊት ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ለማስጀመር ትልቅ እገዛ ያደርጋል የሚል እምነት አለን።
በኅዳር ወር 8,363 የደረሰ አዲስ ከፍተኛ የአስፋፊዎች ቁጥር ሪፖርት የተደረገ ሲሆን ይህም በዚህ የአገልግሎት ዓመት ባሉት የመጀመሪያ ሦስት ወራት 2 በመቶ ጭማሪ እንዳገኘን ያሳያል። ባለፈው ዓመት አንዳንድ ጉባኤዎች 12, 13 እና 14 ሌላው ቀርቶ 17 የሚያህሉ አዳዲስ አስፋፊዎች አግኝተዋል። ይህ ደግሞ አሁንም እንኳ በርካታ አዳዲስ ሰዎች እርምጃ እየወሰዱ መሆኑን የሚጠቁም ነው!
አሁን ደግሞ ትኩረት የምናደርገው አዳዲስ ክልሎችን ለመሸፈን በሚካሄደው ልዩ ዘመቻ ላይ ነው። እስከ ታኅሣሥ አጋማሽ ድረስ ከአምስት የውጭ አገራት ማመልከቻዎች ደርሰውናል፤ በእነዚህ አገሮች የሚኖሩ ወንድሞችና እህቶች በስብከቱ ሥራ እኛን ለመርዳት ከፍተኛ ወጪ አውጥተው ይመጣሉ። በተጨማሪም በአገራችን ከሚገኙ ጉባኤዎች ወደ 400 የሚጠጉ ወንድሞችና እህቶች ራቅ ወዳሉ ቦታዎች ሄደው ለማገልገል አመልክተዋል። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ጥሩ ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን በማስታወሻቸው መዝግበው እንደሚይዙና ተመላልሶ መጠየቅ ለማድረግ ንቁ እንደሚሆኑ እንተማመናለን።