የክልል ስብሰባ ማሳሰቢያዎች
የስብሰባው ሰዓት፦ በመሰብሰቢያ ቦታው ወንበር መያዝ የሚቻለው ከጠዋቱ 2:00 ጀምሮ ነው። በሦስቱም ቀናት የመክፈቻው ሙዚቃ የሚጀምረው ከጠዋቱ 3:20 ላይ ነው። በዚህ ጊዜ ሁላችንም ቦታ ቦታችንን መያዝ ይኖርብናል፤ ይህም ፕሮግራሙን ክብር ባለው መንገድ ለማስጀመር ያስችላል። ስብሰባው የሚደመደመው ዓርብና ቅዳሜ 11 ሰዓት ገደማ እንዲሁም እሁድ 10 ሰዓት ገደማ ይሆናል።
‘ይሖዋን በመዝሙር ማወደስ’፦ ጥንት የነበሩ የአምላክ አገልጋዮች ይሖዋን በመዝሙር ያወድሱት ነበር፤ እስከ ዛሬ ድረስም መዝሙር የእውነተኛው አምልኮ አቢይ ገጽታ ሆኖ ቀጥሏል። (መዝ. 28:7) በክልል ስብሰባው ወቅት እያንዳንዱ ክፍለ ጊዜ ሲጀምር ሙዚቃ ይሰማል። ሙዚቃው የተዘጋጀው ፕሮግራሙ እስኪጀምር ድረስ ማቆያ እንዲሆን ተብሎ ሳይሆን ስለ ይሖዋ እንድንማርና እሱን እንድናመልክ ለመርዳት ታስቦ ነው። በመሆኑም ሊቀ መንበሩ ሙዚቃው ሊጀምር እንደሆነ ሲያስተዋውቅ ወንበራችን ላይ ተቀምጠን ሙዚቃውን በአድናቆት ማዳመጥ እንጂ ከሌሎች ጋር ማውራት አይኖርብንም። እንዲህ ማድረጋችን የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የመዘምራን ቡድን ሙዚቃውን ለማዘጋጀት ያደረገውን ጥረት እንደምናደንቅ ያሳያል። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች በዓመት ሁለት ጊዜ በራሳቸው ወጪ ወደ ፓተርሰን ኒው ዮርክ በመጓዝ ግሩም ጣዕም ያላቸውን ሙዚቃዎች ያዘጋጁልናል። ሙዚቃውን በጥሞና ካዳመጥን በኋላ ሁላችንም የመንግሥቱን መዝሙሮች አብረን በመዘመር ይሖዋን ማወደስ ይኖርብናል።
መኪና ማቆሚያ፦ የክልል ስብሰባ በሚደረግባቸው በሁሉም ቦታዎች ላይ የመኪና ማቆሚያው ስፍራ በእኛ ቁጥጥር ሥር ከሆነ ተሰብሳቢዎቹ በሙሉ እንደ አመጣጣቸው ያለምንም ክፍያ ይስተናገዳሉ። ያለው የመኪና ማቆሚያ አብዛኛውን ጊዜ ውስን ስለሚሆን በተቻለ መጠን መኪናችሁን በመተው ከሌላው ጋር ተዳብላችሁ የምትሄዱ ከሆነ የመኪናዎችን ቁጥር መቀነስ ይቻላል።
ወንበር መያዝ፦ እባካችሁ፣ ጠዋት ላይ የስብሰባው ቦታ በሮች ሲከፈቱ የምትፈልጉትን ቦታ ለመያዝ ስትሉ አትሽቀዳደሙ። ለወንድሞቻችሁ ስትሉ የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቅባችሁ ቢሆንም እንኳ እባካችሁ ለሌሎች አሳቢነት አሳዩ። የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ማሳየታችን እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናችንን ለይቶ የሚያሳውቅ ከመሆኑም ሌላ የሚመለከቱን ሰዎች አምላክን እንዲያከብሩ ያነሳሳቸዋል። (ዮሐ. 13:34, 35፤ 1 ቆሮ. 13:5፤ 1 ጴጥ. 2:12) ወንበር መያዝ የሚቻለው ከእናንተ ጋር በመኪና ለሚመጡ፣ በአንድ ቤት አብረዋችሁ ለሚኖሩ እንዲሁም ከእናንተ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናት ላይ ለሚገኙ ሰዎች ብቻ መሆኑን አስታውሱ። እባካችሁ ባልያዛችሁት ወንበር ላይ ዕቃዎቻችሁን አታስቀምጡ። በዚህ ረገድ የምታደርጉት ትብብር ሌሎች ሰዎች ወንበሩ ክፍት መሆን አለመሆኑን ለመለየት ያስችላቸዋል። ስብሰባው በሚደርግባቸው አንዳንድ አካባቢዎች፣ ለአረጋውያንና የአቅም ገደብ ላለባቸው የሚመደቡ ወንበሮች ይኖራሉ። እነዚህ ወንበሮች ውስን በመሆናቸው ከአረጋውያኑ ወይም የአቅም ገደብ ካላቸው ጋር እንዲቀመጡ የሚፈቀድላቸው እነሱን የሚንከባከቡ አንድ ወይም ሁለት ሰዎች ብቻ ናቸው።
ልከኛ አለባበስ፦ በስብሰባው ላይ የሚኖረን አለባበስ ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቅና ልከኛ መሆን ይኖርበታል፤ እንዲሁም በዓለም ላይ የተለመደውን ቅጥ ያጣ የአለባበስ ዘይቤ የሚያንጸባርቅ መሆን የለበትም። (1 ጢሞ. 2:9) ከስብሰባው በፊትና በኋላ ባሉት ጊዜያት ዘና ስንል አለባበሳችን ቅጥ ያጣ ወይም የተዝረከረከ እንዳይሆን መጠንቀቅ አለብን። ይህም የስብሰባውን ባጅ አድርገን ስንታይ ከመሸማቀቅ ይልቅ ኩራት እንዲሰማንና ለመስበክ የሚያስችል አጋጣሚ ስናገኝ በአለባበሳችን አፍረን ወደኋላ እንዳንል ያስችለናል። በቅርቡ በምናደርገው ትልቅ ስብሰባ ላይ ስንገኝ የሚኖረን አለባበስና መልካም ምግባር፣ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ሕይወት አድን የሆነ መልእክት እንዲሰሙ ከማነሳሳት ባለፈ ይሖዋንም ያስደስተዋል።—ሶፎ. 3:17
ከኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ጥሩ ምግባር ማሳየት፦ ስብሰባው በሚካሄድበት ወቅት ሞባይል ስልካችን ወይም ሌሎች የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቻችን ሌሎችን እንዳይረብሹ ማስተካከያ በማድረግ ጥሩ ምግባር እንዳለን እናሳያለን። ካሜራ፣ ቪዲዮ መቅረጫ፣ ታብሌት ወይም እንዲህ ያሉ ሌሎች መሣሪያዎችን የምንጠቀም ከሆነ የሌሎችን ትኩረት ባለመከፋፈል ወይም እይታ ባለመጋረድ አሳቢነት እናሳያለን። በተጨማሪም በስብሰባው ወቅት ሳያስፈልግ የጽሑፍ መልእክት ወይም ኢ-ሜይል ከመላላክ በመቆጠብ ጥሩ ምግባር እናሳያለን።
ምሳ፦ በእረፍት ሰዓት ምግብ ፍለጋ ከስብሰባው ቦታ ወጥታችሁ ከመሄድ ይልቅ እባካችሁ ምሳ ይዛችሁ ኑ። ወንበር ሥር ሊቀመጥ የሚችል የምግብ መያዣ ዕቃ መጠቀም ይቻላል። ትላልቅ የምግብ መያዣ ዕቃዎችንና ጠርሙስ ነክ ዕቃዎችን ወደ ስብሰባው ቦታ ማምጣት አይፈቀድም።
መዋጮ፦ በክልል ስብሰባ ላይ ለዓለም አቀፉ ሥራ በፈቃደኝነት መዋጮ በማድረግ ለዝግጅቱ ያለንን አድናቆት መግለጽ እንችላለን። መዋጮው የሚደረገው በቼክ ከሆነ ለ“የይሖዋ ምሥክሮች” የሚከፈል መሆኑ መገለጽ አለበት።
መድኃኒቶች፦ በሐኪም ትእዛዝ የምትወስዱት መድኃኒት ካለ እንዲህ ዓይነት መድኃኒቶች በስብሰባው ቦታ ስለማይኖሩ እባካችሁ የምትወስዷቸውን መድኃኒቶች በበቂ መጠን መያዛችሁን አረጋግጡ። የስኳር ሕመምተኞች የሚጠቀሙባቸው ሲሪንጆችና መርፌዎች፣ አደጋ የሚያስከትሉ ቆሻሻዎች በመሆናቸው በተገቢው ሁኔታ መወገድ ይኖርባቸዋል እንጂ በስብሰባው ቦታና በሆቴሎች ውስጥ በሚገኝ የቆሻሻ መጣያ ቅርጫት ውስጥ መጣል አይኖርባቸውም።
የደህንነት ጥንቃቄ፦ እባካችሁ በተለይ የመንሸራተትና የመደናቀፍ አደጋ እንዳይደርስባችሁ አስፈላጊውን ጥንቃቄ አድርጉ። በየዓመቱ በተለይ በታኮ ጫማ ምክንያት ጉዳት ይደርሳል። በመሆኑም ሊያንሸራትቱ በሚችሉ ስፍራዎች፣ በደረጃዎች፣ የሚያሾልኩ ቀዳዳዎች ባሉት ወለል ላይና እነዚህን በመሳሰሉ ቦታዎች ስትራመዱ ጉዳት እንዳይደርስባችሁ ልከኛና ምቹ የሆነ ጫማ እንድታደርጉ እናበረታታችኋለን።
የመስማት ችግር ያለባቸው፦ በአንዳንድ ቦታዎች ላይ ስብሰባው በኤፍኤም የሬዲዮ ሞገድ ይተላለፋል። በዚህ ዝግጅት መጠቀም የምትፈልጉ ከሆነ በባትሪ የሚሠራ የኤፍኤም መቀበያና የጆሮ ማዳመጫ ይዛችሁ መምጣት ያስፈልጋችኋል።
የሕፃናት ጋሪዎችና የመናፈሻ ወንበሮች፦ የሕፃናት ጋሪዎችንና የመናፈሻ ወንበሮችን ወደ ስብሰባው ቦታ ይዞ መምጣት አይፈቀድም። ይሁን እንጂ ከወላጆች አጠገብ ባለ ወንበር ላይ ሊታሰሩ የሚችሉ ለልጆች ደህንነት ተብለው የሚዘጋጁ ወንበሮችን (ቻይልድ ሴፍቲ ሲትስ) ይዞ መምጣት ይቻላል።
የአትክልት ቦታዎች፦ በስብሰባ ቦታው ላይ ያሉ አበቦችንና ሌሎች ተክሎችን ማሳደግ እንዲሁም መንከባከብ ጉልበትና ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑ እባካችሁ ልጆቻችሁ አበቦችንም ሆነ ተክሎችን እንዳይቀጥፉ ወይም እንዳይነቅሉ አስተምሯቸው።
እባካችሁ ተከታትላችሁ እርዱት (S-43) የተባለው ቅጽ፦ እባካችሁ ተከታትላችሁ እርዱት የሚለው ቅጽ በስብሰባው ላይ መደበኛ ባልሆነ መንገድ መሥክረንለት ፍላጎት ያሳየን ሰው በሚመለከት መረጃ ለመስጠት ያገለግላል። ቅጹን ከሞላችሁ በኋላ ለክልል ስብሰባው የጽሑፍ ክፍል አሊያም ወደ ጉባኤያችሁ ስትመለሱ ለጉባኤው ጸሐፊ ልትሰጡት ትችላላችሁ።
ምግብ ቤቶች፦ ምግብ ቤት በምትመገቡበት ጊዜ መልካም ምግባር በማሳየት የይሖዋን ስም አስከብሩ። ከአንድ ክርስቲያን የሚጠበቅ አለባበስ ይኑራችሁ። በአካባቢው የተለመደ ከሆነ ለአስተናጋጆች ጉርሻ ወይም ቲፕ ስጡ።
የመንግሥት አዳራሾችን መጠቀም፦ የመንግሥት አዳራሾችን የማደሪያ ቦታ አድርገን ባንጠቀምባቸው እንመርጣለን። ይሁን እንጂ በሁኔታዎች አስገዳጅነት አንድን የመንግሥት አዳራሽ ለዚህ ዓላማ መጠቀም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ በዚያ የሚያርፉት በሙሉ አዳራሹ በማንኛውም ሰዓት ንጹሕና ያልተዝረከረከ እንዲሆን የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። አንሶላና ብርድ ልብሳቸውን አጣጥፈው ማስቀመጥ፣ የተደፋ ነገር ካለ ወዲያውኑ ማጽዳት እንዲሁም ወረቀቶችንና ሌሎች ቆሻሻዎችን ለዚህ ዓላማ በተዘጋጁ ቅርጫቶች ወይም ዕቃዎች ውስጥ መጣል ይኖርባቸዋል።
ሆቴሎች፦
እባካችሁ ከሚያስፈልጋችሁ ቁጥር በላይ ክፍል እንዲያዝላችሁ አትጠይቁ፤ እንዲሁም ሆቴሉ ከሚፈቅደው በላይ ሰዎችን በክፍላችሁ አታሳድሩ።
ከአቅም በላይ የሆነ ነገር ካላጋጠማችሁ በስተቀር የያዛችሁትን ሆቴል አትሰርዙ፤ ይሁንና መሰረዝ ካስፈለጋችሁ በአፋጣኝ ለሆቴሉ አሳውቁ፤ እንዲህ ማድረጋችሁ ሌሎች ክፍል ማግኘት እንዲችሉ ይረዳል። (ማቴ. 5:37)
በአካባቢው የተለመደ ከሆነ የሆቴሉ ሠራተኞች ሻንጣ ሲሸከሙላችሁ ጉርሻ ስጧቸው፤ የሆቴል ክፍላችሁን ለሚያጸዳው ግለሰብም እንዲህ ማድረጋችሁን አትርሱ።
ምግብ ማብሰል የሚኖርባችሁ ማብሰል በሚፈቀድባቸው ክፍሎች ውስጥ ብቻ ነው።
ከሆቴሉ ሠራተኞች ጋር ባላችሁ ግንኙነት ምንጊዜም የመንፈስ ፍሬን አንጸባርቁ። ሠራተኞቹ ብዙ ሰዎችን ስለሚያስተናግዱ ደግነትና ትዕግሥት ብናሳያቸው እንዲሁም ምክንያታዊ ብንሆን ደስ ይላቸዋል።
ወላጆች ልጆቻቸው በሆቴሉ ውስጥ የሚያደርጉትን ነገር ምንጊዜም መቆጣጠር ይገባቸዋል፤ ይህ ደግሞ ልጆቻቸው በአሳንሰር አጠቃቀም እንዲሁም በመዋኛ ቦታ፣ በእንግዳ መቀበያው አካባቢ፣ በጂምናዝየምና በሌሎች አካባቢዎች የሚያሳዩትን ባሕርይ መከታተልን ይጨምራል።
ንጽሕና፦ የንጽሕና ክፍሉ የስብሰባ ቦታው በፕሮግራም እንዲጸዳ ዝግጅት የሚያደርግ ቢሆንም ሁላችንም ይሖዋ ከሕዝቡ የሚጠብቀውን ላቅ ያለ የንጽሕና ደረጃ ለማሟላት የበኩላችንን አስተዋጽኦ ማድረግ እንችላለን። በመሆኑም በአዳራሹ ወለል ላይም ሆነ በግቢው ውስጥ የተጣሉ ወረቀቶች ወይም ሌሎች ቆሻሻዎች ሊታዩ አይገባም። እነዚህን ቆሻሻዎች ወዲያውኑ ለእነሱ በተመደበው የቆሻሻ መጣያ ውስጥ መጣል ተገቢ ነው፤ ይህም የስብሰባው ቦታ ፕሮግራሙ በሚካሄድበት ወቅትም ሆነ በምሳ እረፍት ሰዓት ውበቱን የጠበቀ ሆኖ እንዲቀጥል ያደርጋል። በተጨማሪም ወንበራችንን ለቀን ከመሄዳችን በፊት በአካባቢያችን የተጣሉ ነገሮች መኖራቸውን ብናጣራ እንዲሁም የተጣሉ ነገሮች ካሉ ብናነሳቸው ጥሩ ነው።
የፈቃደኛ አገልግሎት፦ ፈቃደኛ ሠራተኛ ሆነው ማገልገል የሚፈልጉ ሁሉ በስብሰባው ቦታ ለሚገኘው የፈቃደኛ አገልግሎት ክፍል ማሳወቅ ይኖርባቸዋል። ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ልጆች በወላጃቸው ወይም በአሳዳጊያቸው አሊያም ወላጃቸው ወይም አሳዳጊያቸው ኃላፊነት በሰጠው ሌላ ትልቅ ሰው ሥር በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ።