ክርስቲያናዊ ሕይወት
‘ጳውሎስ አምላክን አመሰገነ፤ እንዲሁም ተበረታታ’
በሮም የሚገኘው ጉባኤ አባላት ጳውሎስ እየመጣ መሆኑን ሲሰሙ፣ የተወሰኑ ወንድሞችን በመላክ 64 ኪሎ ሜትር ያህል ተጉዘው መንገድ ላይ እንዲቀበሉት አደረጉ። ወንድሞች የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት አድርገው እንዲህ ያለ ፍቅር በማሳየታቸው ጳውሎስ ምን ተሰማው? “ጳውሎስም ባያቸው ጊዜ አምላክን አመሰገነ፤ እንዲሁም ተበረታታ።” (ሥራ 28:15) ጳውሎስ የሚጎበኛቸውን ጉባኤዎች በማበረታታት የሚታወቅ ቢሆንም እስረኛ በነበረበት በዚህ ወቅት ግን ወንድሞች እሱን አበረታተውታል።—2ቆሮ 13:10
በዛሬው ጊዜም የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ከአንዱ ጉባኤ ወደ ሌላው ጉባኤ በመሄድ ወንድሞችንና እህቶችን ያበረታታሉ። ይሁንና እንደ ማንኛውም ክርስቲያን ሁሉ እነሱም አንዳንድ ጊዜ ሊዝሉ፣ ሊጨነቁ እንዲሁም ተስፋ ሊቆርጡ ይችላሉ። የወረዳ የበላይ ተመልካቹና ባለቤቱ ጉባኤያችሁን በሚጎበኙበት ጊዜ ከእነሱ ጋር ‘እርስ በርስ ለመበረታታት’ አጋጣሚ ታገኛላችሁ፤ ታዲያ እነሱን ለማበረታታት ምን ማድረግ ትችላላችሁ?—ሮም 1:11, 12
በመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ ላይ ተገኙ። አስፋፊዎች በጉብኝት ሳምንት ከሚኖረው ፕሮግራም ሙሉ ጥቅም ለማግኘት ሲሉ መሥዋዕት መክፈላቸው የወረዳ የበላይ ተመልካቹን ያበረታታዋል። (1ተሰ 1:2, 3፤ 2:20) የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ጉባኤያችሁን በሚጎበኝበት ወር ረዳት አቅኚ ሆናችሁ ለማገልገል ሞክሩ። ከእሱ ወይም ከባለቤቱ ጋር በስብከቱ ሥራ መካፈል አሊያም ከሁለት አንዳቸውን ጥናት መጋበዝ ትችሉ ይሆን? የወረዳ የበላይ ተመልካቹና ባለቤቱ፣ አዳዲስ አስፋፊዎችንና ጥሩ ችሎታ እንደሌላቸው የሚሰማቸውን ክርስቲያኖች ጨምሮ ከተለያዩ ወንድሞችና እህቶች ጋር ማገልገል ያስደስታቸዋል።
በእንግድነት ተቀበሏቸው። ማረፊያ ልታዘጋጁላቸው ወይም ምግብ ልትጋብዟቸው ትችላላችሁ? እንዲህ ማድረጋችሁ እንደምትወዷቸው ያሳያል። የወረዳ የበላይ ተመልካቹና ባለቤቱ ብዙ ነገር አይፈልጉም።—ሉቃስ 10:38-42
የወረዳ የበላይ ተመልካቹ የሚሰጠውን መመሪያና ምክር ተቀብላችሁ ተግባራዊ አድርጉ። የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ለይሖዋ በምናቀርበው አገልግሎት ማሻሻያ ማድረግ እንድንችል ፍቅር የተንጸባረቀበት ምክር ይሰጠናል። አንዳንድ ጊዜም ጠንከር ያለ ምክር መስጠት ሊያስፈልገው ይችላል። (1ቆሮ 5:1-5) የምንታዘዝና የምንገዛ ከሆነ የወረዳ የበላይ ተመልካቹ ይደሰታል።—ዕብ 13:17
አድናቆታችሁን ግለጹ። የወረዳ የበላይ ተመልካቹና ባለቤቱ የሚያከናውኑት አገልግሎት እንዴት እንደጠቀመህ ንገራቸው። አድናቆትህን በቃልህ ልትነግራቸው አሊያም ካርድ ጽፈህ ልትሰጣቸው ትችላለህ።—ቆላ 3:15