ለጥናት የሚረዱ ሐሳቦች
ልብህን አዘጋጅ
መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና የአምላክ አስተሳሰብ በልባችን ወይም በውስጣዊ ማንነታችን ላይ ለውጥ እንዲያመጣ እንፈልጋለን። ዕዝራ በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቷል፤ “የይሖዋን ሕግ ለመመርመር . . . ልቡን አዘጋጅቶ ነበር።” (ዕዝራ 7:10) እኛስ ልባችንን ማዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው?
ጸልይ። እያንዳንዱን የጥናት ፕሮግራም በጸሎት ጀምር። ይሖዋ የተማርከውን ነገር ለመረዳትና በሥራ ላይ ለማዋል እንዲረዳህ ጠይቀው።—መዝ. 119:18, 34
ትሕትና አዳብር። አምላክ በራሳቸው ማስተዋል ከሚታመኑ ኩሩ ሰዎች እውነትን ይሰውራል። (ሉቃስ 10:21) ሌሎችን ለማስደመም ብለህ ምርምር ከማድረግ ተቆጠብ። አስተሳሰብህ ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር እንደማይስማማ ከተገነዘብክ በትሕትና ማስተካከያ አድርግ።
የመንግሥቱን መዝሙር አዳምጥ። ሙዚቃ ልባችንን የመንካትና ለአምልኮ እንድንዘጋጅ የመርዳት ኃይል አለው። የጥናት ፕሮግራምህን ስትጀምር የመንግሥቱን መዝሙር ማዳመጥህ ልብህን ለማዘጋጀት ሊረዳህ ይችላል።