ንድፍ አውጪ አለው?
ሆርሞኖች የሰውነታችንን ሂደቶች የሚቆጣጠሩበት መንገድ
ሰውነታችን ሥራውን በአግባቡ እንዲያከናውን ከተፈለገ በደማችን ውስጥ ያለው እንደ ካልሲየም ያሉ ማዕድናት መጠን ከሚፈለገው በትንሹም ቢሆን መብለጥ ወይም ማነስ የለበትም። ሆኖም ወደ ሰውነታችን የምናስገባው የማዕድናት መጠን ከዕለት ወደ ዕለት የተለያየ ነው። ታዲያ ሰውነታችን በደማችን ውስጥ ያለውን የማዕድናት መጠን የሚያስተካክለው እንዴት ነው?
ሰውነታችን ጤናማ እስከሆነ ድረስ ሆርሞኖችን በማምረት፣ በማከማቸትና ወደ ደማችን በማስገባት የማዕድናትን መጠን ያስተካክላል። ሆርሞኖች የተለያዩ የሰውነት ሂደቶችን የሚቆጣጠሩ ኬሚካሎች ናቸው። በጣም ትንሽ ሆርሞን እንኳ በሰውነታችን ላይ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል። ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ እንደገለጸው ሆርሞኖች የሚመነጩት “በዘፈቀደ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ተመጣጥነው እና በጥንቃቄ ተለክተው ነው።”
ለምሳሌ ፓራታይሮይድ ተብለው የሚጠሩት በአንገታችን ውስጥ ያሉት ዕጢዎች በደማችን ውስጥ ያለው የካልሲየም መጠን በትንሹም እንኳ ሲቀየር የማወቅ ችሎታ አላቸው። አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ዕጢዎች አራት ናቸው፤ የእያንዳንዳቸው መጠን የሩዝ ቅንጣት ያክላል።
እነዚህ ዕጢዎች በደማችን ውስጥ ያለው የካልሲየም መጠን ከሚፈለገው እንዳነሰ ሲገነዘቡ በፍጥነት፣ ምናልባትም በሴኮንዶች ውስጥ አንድ ሆርሞን ያመነጫሉ። ይህ ሆርሞን አጥንቶቻችን በውስጣቸው ያከማቹትን ካልሲየም ወደ ደም እንዲያስገቡ ይነግራቸዋል። በተጨማሪም ይህ ሆርሞን፣ ኩላሊታችን በደማችን ውስጥ ያለውን ካልሲየም አጣርቶ ማስወገዱን እንዲያቆም እንዲሁም ትንሹ አንጀታችን ከምግብ የሚወስደውን የካልሲየም መጠን እንዲጨምር ያደርጋል።
ይሁንና በደማችን ውስጥ ያለው ካልሲየም ከሚፈለገው መጠን ከበዛ ታይሮይድ በመባል የሚጠራ ሌላ ዕጢ አንድ ሆርሞን ያመነጫል። ይህ ሆርሞን ደግሞ አጥንቶቻችን ተጨማሪ ካልሲየም ወደ ውስጣቸው እንዲያስገቡና እንዲያከማቹ ይነግራቸዋል፤ ኩላሊታችን ደግሞ ከወትሮው የበለጠ ካልሲየም አጣርቶ እንዲያስወግድ ያደርጋል።
ሰውነታችን የተለያዩ ሂደቶችን ለመቆጣጠር የሚጠቀምባቸው ከመቶ የሚበልጡ ሆርሞኖች አሉ፤ አሁን የተመለከትነው ሁለቱን ብቻ ነው።
ታዲያ ምን ይመስልሃል? ሆርሞኖች የሰውነታችንን ሂደቶች የሚቆጣጠሩበት መንገድ በዝግመተ ለውጥ የተገኘ ነው? ወይስ ንድፍ አውጪ አለው?