በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩ—ኤርትራ
የኤርትራ መንግሥት ለበርካታ ዓመታት የይሖዋ ምሥክሮችን በቁጥጥር ሥር ሲያውልና ሲያስር ቆይቷል። ሴቶችንና አረጋውያንን ጨምሮ የይሖዋ ምሥክሮች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ወይም ክስ ሳይመሠረትባቸው ይታሰራሉ። ፕሬዚዳንት ኢሳይያስ ኣፈወርቂ ጥቅምት 25, 1994 ባወጡት ፕሬዚዳንታዊ አዋጅ አማካኝነት የይሖዋ ምሥክሮችን ዜግነት ነጥቀዋል፤ ለዚህም እንደ ምክንያት የቀረበው የይሖዋ ምሥክሮች በ1993 ኤርትራ ነፃነቷን ባወጀችበት ሕዝበ ውሳኔ ለመሳተፍ ፈቃደኛ አለመሆናቸው እንዲሁም በሕሊናቸው ምክንያት በወታደራዊ አገልግሎት የማይካፈሉ መሆኑ ነው። ኤርትራ ውስጥ የውትድርና ምልመላ ከመጀመሩ በፊት ባለሥልጣናቱ የሲቪል አገልግሎት የመስጠት አማራጭ አዘጋጅተው ነበር። በርካታ የይሖዋ ምሥክሮች በተለያዩ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ ይህን አገልግሎት ሰጥተዋል። ባለሥልጣናቱም ይህን ብሔራዊ አገልግሎት ላጠናቀቁ ሰዎች የምሥክር ወረቀት የሰጡ ሲሆን ላከናወኑት ጥሩ ሥራም አመስግነዋቸው ነበር። ይሁን እንጂ ፕሬዚዳንታዊው አዋጅ ከወጣ በኋላ የደህንነት ኃይሎች የይሖዋ ምሥክሮችን ሃይማኖታቸውን እንዲክዱ ለማስገደድ ሲሉ አስረዋቸዋል፣ አሠቃይተዋቸዋል እንዲሁም አንገላተዋቸዋል።
በአሁኑ ወቅት 65 የይሖዋ ምሥክሮች (38 ወንዶችና 27 ሴቶች) እስር ቤት ይገኛሉ። ይህ ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ የጨመረው መስከረም 2024 የደህንነት ባለሥልጣናት ወደ አንድ መኖሪያ ቤት ሰብረው መግባታቸውን ተከትሎ ነው፤ ቤቱ ውስጥ ሰላማዊ የሆነ ሃይማኖታዊ ስብሰባ እያካሄዱ የነበሩ 24 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አዋሉ። ከተያዙት መካከል ሁለቱ ልጆች በኋላ ላይ ተለቀቁ። ከተወሰኑ ቀናት በኋላ ደግሞ የ85 ዓመት አረጋዊት የሆኑ አንዲት የይሖዋ ምሥክር ተያዙ። ከዚያም 23ቱም የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ማይ ስርዋ እስር ቤት ተዛወሩ። ታኅሣሥ 7, 2024 ከእነዚህ መካከል አንዷ የሆነችው ሳሮን ገብሩ ከእስር ተለቀቀች፤ በወቅቱ ሳሮን የመጀመሪያ ልጇን የዘጠኝ ወር ነፍሰ ጡር ነበረች። ጥር 15, 2025 ደግሞ የ82 ዓመት አረጋዊት የሆኑት ሚዛን ገብረየሱስ ከእስር ተፈቱ።
ኅዳር 1, 2024 የደህንነት ባለሥልጣናት በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ያነጣጠረ ሌላ እርምጃ ወሰዱ፤ ዕድሜያቸው ከ16 እስከ 18 ዓመት የሆኑ አራት የይሖዋ ምሥክር ተማሪዎችን በቁጥጥር ሥር አዋሉ። ወጣቶቹ ምርመራ ከተካሄደባቸው በኋላ ወዲያውኑ ወደ ማይ ስርዋ እስር ቤት ተወሰዱ። ኅዳር 22 ደግሞ ባለሥልጣናቱ የኣልማዝ ገብረህይወትን ትንሽ ልጅ ከትምህርት ቤት ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዷት። ኣልማዝ ልጇን ለመውሰድ ወደ ፖሊስ ጣቢያው ስትሄድ ባለሥልጣናቱ ልጇን ለቅቀው ኣልማዝን በቁጥጥር ሥር አዋሏት። በአሁኑ ወቅት ኣልማዝ ኣስመራ ውስጥ 5ተኛ ፖሊስ ጣቢያ ታስራለች።
በቅርቡ ሁለት እህቶች ከእስር መፈታታቸው አስደስቶናል። ሚካል ታደሰ የካቲት 25, 2025 ከማይ ስርዋ ወህኒ ቤት፣ ብርኽቲ ገብረታትዮስ ደግሞ መጋቢት 12, 2025 ከዓዲ ኣበይቶ እስር ቤት ተለቅቀዋል።
እስር ቤት ያለው አስከፊ ሁኔታ
በማይ ስርዋም ሆነ በሌሎች ወህኒ ቤቶች የታሰሩ የይሖዋ ምሥክሮች የሚገኙበት ሁኔታ እጅግ አስከፊ ነው። እስረኞች ጠባብ በሆኑ ክፍሎች ውስጥ እጭቅ ተደርገው ይታጎራሉ፤ በመሆኑም በጀርባቸው ለመተኛት የሚበቃ ቦታ ስለማይኖር ጥግትግት ብለው በጎናቸው ለመተኛት ይገደዳሉ። ንጽሕናን ለመጠበቅ የሚያስችል ዝግጅት የለም። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ወደ መጸዳጃ ቤት መሄድ የሚፈቀድላቸው በቀን ሁለት ጊዜ በተወሰነ ሰዓት ብቻ ሲሆን ወታደሮቹ በዚህ ጊዜም ቢሆን ከአጠገባቸው አይለዩም። እስረኞች በቂ የሕክምና አገልግሎት አያገኙም፤ የምግብና የውኃ አቅርቦትም እንዲሁ በቂ አይደለም።
በዚህ እጅግ አስከፊ ሁኔታ የተነሳ ኤርትራ ውስጥ አራት የይሖዋ ምሥክሮች እስር ቤት እያሉ ሕይወታቸው አልፏል፤ ሦስት አረጋውያን የይሖዋ ምሥክሮች ደግሞ ከእስር ከተለቀቁ በኋላ አርፈዋል፤ ለዚህ ምክንያት የሆነው እስር ቤት ውስጥ የነበረው አስከፊ ሁኔታ ነው።
በ2011 እና በ2012 ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች በምዕጢር እስር ቤት በደረሰባቸው ኢሰብዓዊ እንግልት ምክንያት ሕይወታቸው አልፏል። ምስግና ገብረትንሳኤ፣ ምድር ቤት በሚገኝ ከፍተኛ ሙቀት ያለው የቅጣት ቦታ ውስጥ በመቆየቱ የተነሳ ሐምሌ 2011 በ62 ዓመቱ አርፏል። ዮሃንስ ሃይለ ደግሞ በዚያው ቦታ ለአራት ዓመታት ገደማ ከታሰረ በኋላ ነሐሴ 16, 2012 በ68 ዓመቱ ሕይወቱ አልፏል።
ካሕሳይ መኰነን፣ ጐይትኦም ገብረክርስቶስ እና ጸሃየ ተስፋማርያም የተባሉ ሦስት አረጋውያን የይሖዋ ምሥክሮች ከእስር ከተፈቱ በኋላ አርፈዋል፤ ለሞታቸው ምክንያት የሆነው በምዕጢር እስር ቤት የነበረው አስከፊ ሁኔታ ነው።
በ2018 ደግሞ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ማይ ስርዋ እስር ቤት ከተዛወሩ በኋላ ሕይወታቸው አልፏል። ጥር 3 ሃብተሚካኤል ተስፋማርያም በ76 ዓመቱ አርፏል፤ ሃብተሚካኤል መኰነን ደግሞ መጋቢት 6 በ77 ዓመቱ ሕይወቱ አልፏል። የኤርትራ ባለሥልጣናት ሁለቱንም ሰዎች ከ2008 ጀምሮ ያለፍርድ አስረዋቸው ነበር።
ማብቂያ የሌለው እስራት
ኤርትራ ውስጥ የታሰሩት አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች እስራታቸው ማብቂያ የለውም፤ እስኪሞቱ ወይም ሞት አፋፍ ላይ እስኪደርሱ ድረስ የመፈታት ተስፋ የላቸውም። ይህን ሁኔታ የሚያስተካክል ሕጋዊ አሠራር ወይም መፍትሔ በአገሪቱ ስለሌለ፣ እነዚህ የይሖዋ ምሥክሮች የዕድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደባቸው ሊቆጠር ይችላል።
የጊዜ ሰሌዳ
ሰኔ 17, 2025
በአጠቃላይ 65 የይሖዋ ምሥክሮች ታስረዋል።
ኅዳር 22, 2024
ኣልማዝ ገብረህይወት የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲ አባል ለመሆን ፈቃደኛ ባለመሆኗ ታሰረች።
ኅዳር 1, 2024
ተማሪ የሆኑ አራት የይሖዋ ምሥክሮች በቁጥጥር ሥር ውለው ወደ ማይ ስርዋ ወህኒ ቤት ተወሰዱ።
መስከረም 27, 2024
ሃያ ሦስት የይሖዋ ምሥክሮች በቁጥጥር ሥር ውለው ወደ ማይ ስርዋ ወህኒ ቤት ተወሰዱ፤ ሁለቱ በኋላ ላይ ተፈትተዋል።
የካቲት 1, 2021
ሦስት የይሖዋ ምሥክሮች ከእስር ቤት ተፈቱ።
ጥር 29, 2021
አንድ የይሖዋ ምሥክር ከእስር ቤት ተፈታ።
ታኅሣሥ 4, 2020
ሃያ ስምንት የይሖዋ ምሥክሮች ከእስር ቤት ተፈቱ።
መጋቢት 6, 2018
ሃብተሚካኤል መኰነን ወደ ማይ ስርዋ እስር ቤት ከተዛወረ በኋላ በ77 ዓመቱ አረፈ።
ጥር 3, 2018
ሃብተሚካኤል ተስፋማርያም ወደ ማይ ስርዋ እስር ቤት ከተዛወረ በኋላ በ76 ዓመቱ አረፈ።
ሐምሌ 2017
በምዕጢር እስር ቤት የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች በሙሉ በኣስመራ አቅራቢያ ወደሚገኘው ወደ ማይ ስርዋ እስር ቤት ተዛወሩ።
ሐምሌ 25, 2014
ሚያዝያ 14 በቁጥጥር ሥር ከዋሉት የይሖዋ ምሥክሮች አብዛኞቹ ተለቀቁ፤ ሚያዝያ 27 ከተያዙት መካከል 20ዎቹ ግን አልተፈቱም።
ሚያዝያ 27, 2014
ሠላሳ አንድ የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ተሰብስበው እያለ ተያዙ።
ሚያዝያ 14, 2014
በዓመታዊው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ የተገኙ ከ90 በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ተያዙ።
ነሐሴ 16, 2012
አስከፊ በሆነ እስር ቤት ውስጥ የነበረው ዮሃንስ ሃይለ በ68 ዓመቱ ሕይወቱ አለፈ።
ሐምሌ 2011
አስከፊ በሆነ እስር ቤት ውስጥ የነበረው ምስግና ገብረትንሳኤ በ62 ዓመቱ ሕይወቱ አለፈ።
ሰኔ 28, 2009
በአንድ የይሖዋ ምሥክር ቤት ሃይማኖታዊ ስብሰባ እየተካሄደ ሳለ ፖሊሶች በድንገት በመግባት በስብሰባው ላይ የተገኙትን 23ቱንም የይሖዋ ምሥክሮች በቁጥጥር ሥር አዋሏቸው፤ የተያዙት ሰዎች ከ2 እስከ 80 ዓመት ባለው የዕድሜ ክልል የሚገኙ ናቸው።
ሚያዝያ 28, 2009
ባለሥልጣናቱ፣ ፖሊስ ጣቢያ ከታሰሩት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል አንዱ ሲቀር ሌሎቹን በሙሉ ወደ ምዕጢር እስር ቤት ወሰዷቸው።
ሐምሌ 8, 2008
ፖሊሶች 24 የይሖዋ ምሥክሮችን ከመኖሪያ ቤታቸውና ከሥራ ቦታቸው ለቅመው አሰሯቸው፤ ከተያዙት አብዛኞቹ የቤተሰብ አስተዳዳሪዎች ናቸው።
ግንቦት 2002
መንግሥት ከፈቀደላቸው አራት ሃይማኖቶች ውጭ ያሉ ሌሎች ሃይማኖቶች በሙሉ ታገዱ።
ጥቅምት 25, 1994
ፕሬዚዳንቱ የይሖዋ ምሥክሮች ዜግነታቸውንና መሠረታዊ መብቶቻቸውን እንዲነጠቁ የሚያደርግ አዋጅ አወጡ።
መስከረም 17, 1994
ጳውሎስ እያሱ፣ ይስሃቅ ሞገስ እና ነገደ ተኽለማርያም ያለክስ እና ያለፍርድ ታሰሩ።
1950ዎቹ
ኤርትራ ውስጥ የመጀመሪያዎቹ የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ጀመሩ።