ከዓለም አካባቢ
በክህደት ላይ ክህደት
የዩናይትድ ስቴትሱ የሉተራን ቤተ ክርስቲያንና የብሪታንያው የሜቶዲስት ቤተ ክርስቲያን አከራካሪውን የግብረ ሰዶም ጉዳይ በሚመለከት ባለፈው ሰሞን መግለጫ ሰጥተው ነበር። በብሪታንያ ውስጥ የተደረገው የሜቶዲስቶች ኮንፍረንስ አንድ ውሳኔ ላይ ደርሷል። ግብረ ሰዶም የሚፈጽሙ ወንዶችንም ሆነ ሴቶችን ከእንግዲህ የቤተ ክርስቲያኑ አገልጋይ አድርጎ ላለመሾም ወስኗል። ሆኖም ቤተ ክርስቲያኑ “ሌዝቢያኖችና ግብረ ሰዶም ፈጻሚዎች በቤተ ክርስቲያኑ ውስጥ የሚያደርጉትን ተሳትፎና አገልግሎት እንደሚቀበል፣ እንደሚያጸድቅና እንደሚያደንቅ” ገልጿል። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ያለ አንድ የሉተራን ቤተ ክርስቲያን ግብረ ኃይል 19,000 ለሚሆኑት የቤተ ክርስቲያኑ ቀሳውስት የሚላክ ባለ 21 ገጽ ሪፖርት ያወጣ ሲሆን ቄሶቹ የሚሰጡትን መልስ እየተጠባበቀ ነው። ዘ አሶሺየትድ ፕሬስ እንደገለጸው ሪፖርቱ መጽሐፍ ቅዱስ የተመሳሳይ ጾታን ጥምረት ይደግፋል ሲል ይከራከራል። በተጨማሪም ሪፖርቱ ብልትን በማሻሸት የጾታ እርካታ የማግኘት ልማድ “በጥቅሉ ተገቢና ጤናማ ድርጊት ነው” ባይ ነው። ሪፖርቱ ባቀረበው በዚህ ክርክሩና አባባሉ መጽሐፍ ቅዱስ በነዚህ ጉዳዮች ላይ ካለው አቋም ጋር ይቃረናል።—ሮሜ 1:26, 27፤ 1 ቆሮንቶስ 6:9, 10፤ ቆላስይስ 3:6, 7
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰችው ከተማ ተገኘች
አንድ የጃፓን የአርኪኦሎጂስቶች ቡድን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት አምስት ጥንታውያን ከተሞች ውስጥ አንዷ የሆነችውን አፌቅ ተብላ የምትጠራ ከተማ ማግኘቱን ለ ፊጋሮ የተባለው የፈረንሳይ ጋዜጣ ሪፖርት አድርጓል። ምሁራን ይህች ጥንታዊት ከተማ የምትገኘው ከገሊላ ባሕር በስተ ምሥራቅ በሦስት ማይሎች ርቀት ላይ ያለችው ዘመናዊቷ አፍሪክ ወይም ፊክ የተባለች መንደር የምትገኝበት ቦታ ላይ መሆኑን ለማመልከት ለብዙ ዘመናት ሙከራ ቢያደርጉም ሳይሳካላቸው ቀርቶ ነበር። ይሁን እንጂ አርኪኦሎጂስት ሂሮሺ ካናሴኪ፣ ኢን ጌቭ በሚባለው የገሊላ ባሕር ዳርቻ አካባቢ የተገኘው የአንድ ጥንታዊ ግንብ ፍርስራሽ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሰችው የአፌቅ ከተማ ከዘመናት በፊት ትገኝ የነበረችበት ይህ ቦታ መሆኑን እንደሚያረጋግጥ ያምናሉ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዚህ ቦታ ላይ የሶርያው ንጉሥ ዳግማዊ ቤንሃዳድ (በ1954 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ እትም አጠራር ወልደ አዴር) በንጉሥ አክዓብ ይመራ በነበረው የእስራኤል ሠራዊት እንደተሸነፈ በ1 ነገሥት 20:26 ላይ (በ1954 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ እትም በ1 ነገሥት 21:26 ላይ) ተጠቅሷል።
ሙዚቃና ነፍስ ግድያ
በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በቴክሳስ ክፍለ አገር በቅርቡ በተፈጸሙ ሁለት የነፍስ ግድያ ወንጀሎች ላይ ሙዚቃ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሳያደርግ አልቀረም። አንደኛውን ወንጀል የፈጸመው መኪና እየነዳ የነበረ አንድ የ19 ዓመት ልጅ ሲሆን የመቀጫ ወረቀት ሊሰጠው ጥግ ይዞ እንዲያቆም የጠየቀውን ፖሊስ ተኩሶ ገድሎታል። የወጣቱ ጠበቃ ልጁ በፖሊሱ ላይ የተኮሰበት በዚያን ሰዓት ስለ ዓመፅ የሚዘፍን ራፕ ሙዚቃ ሲሰማ ስለነበረ ነው ከማለቱም ሌላ ልጁ የነፍስ ግድያ ወንጀል ለመፈጸም ‘የተገፋፋው’ እንዲህ ዓይነት ሙዚቃዎችን ለረጅም ጊዜ ሲሰማ ስለከረመ ነው ሲል ተከራክሮለት ነበር። የፍርድ ቤት ታዛቢዎች በዚህ አባባል መሠረት ወጣቱ በወሰደው እርምጃ ላይ ሙዚቃ ከፍተኛ ሚና እንደነበረው አምነውበታል። ክሱን የመሠረተው አቃቤ ሕግ ግን “የሙዚቃው ጉዳይ ልጁን በወንጀሉ ተጠያቂ ከመሆን የሚያድነው ሆኖ እንደማይሰማቸው” ገልጸዋል። ወጣቱ ሞት ተፈረደበት። በተመሳሳይ አንድ የ15 ዓመት ልጅ እናቱን ተኩሶ መግደሉን የተናዘዘ ሲሆን ይህንንም ያደረገው ሜጋዴዝ የተባለ የሙዚቃ ጓድ በዘፈነው የሄቪ ሜታል ዘፈን ውስጥ አጋንንት ግድያውን እንዲፈጽም ስላዘዙት መሆኑን ተናግሯል።
በሥልጣን መባለግና ኑዛዜ
ሁለት ጣሊያናውያን ጸሐፊዎች የፖለቲካ ሰዎች ወይም ነጋዴዎች በመምሰል በርካታ የካቶሊክ ቄሶች ዘንድ ሄደው ‘በሥልጣናችን በመባለግ ለሠራነው ኃጢአት ይቅር በሉን’ በማለት ኃጢአታቸውን ሲናዘዙ ሰነበቱ። በኋላም ኑዛዜያቸውን የሰሙ ቄሶች ምን ማለት እንደነበረባቸው የሚገልጽ ጽሑፍ አሳተሙ። ላ ሪፑብሊካ የተባለው ጋዜጣ ሪፖርት ሲያደርግ “ቤተ ክርስቲያኒቱ [ጸሐፊዎቹ] እርኩስ ተግባር እንደፈጸሙ በዚህም ጥፋታቸው ነቀፋና ውግዘት እንደደረሰባቸው አድርጋ ታምናለች” ብሏል። ሆኖም ጋዜጣው ጨምሮ እንደገለጸው በማስመሰል የፈጸሟቸው እነዚህ ኑዛዜዎች “36,000 ከሚሆኑት የጣሊያን ቀሳውስት ውስጥ ብዙዎቹ ከፍተኛ የማደናገር ድርጊቶች የሚፈጽሙ፣ ብቃት የሌላቸውና ልል መሆናቸውን በግልጽ አሳይተዋል። ብዙውን ጊዜ እነዚህን ቄሶች የሚማርኳቸው በማኅበረሰቡ ላይ የተፈጸሙ ኃጢአቶች ሳይሆኑ ከጾታ ጋር ግንኙነት ያላቸው ኃጢአቶች ይመስላሉ።” ከጸሐፊዎቹ አንዱ የሆነው ፒኖ ኒኮትሪ ኃጢአቱን “ከተናዘዘላቸው” 49 ቀሳውስት ውስጥ ከአንዱ በስተቀር ኃጢአቱን ይቅር እንደማይልለትና የፈጸመውን ወንጀል ለሚመለከታቸው ባለ ሥልጣኖች እንዲናገር የነገረው አልነበረም። ላ ሪፑብሊካ በጉዳዩ ላይ ሐሳብ ሲሰጥ “ሌሎቹ ግን ወይ ጉቦ ኃጢአት አይደለም አለዚያም የሚያስፈልገው የአምላክ ይቅርታ ብቻ ስለሆነ ወደ ዳኛ መሄድ እርባና የለውም ባዮች ናቸው።”
የዝናብ አማልክት አምላኪዎቻቸውን አሳፈሩ
በቅርቡ በደቡብ ምሥራቅ ህንድ የምትገኘው የአንድህራ ፐራዴሽ መንግሥት ከባድ ድርቅ እያንዣበበበት ሳለ ዝናብ ለማዝነብ አንድ እንግዳ የሆነ መንገድ ተጠቅሞ ነበር። ኢንድያ ቱዴይ የተባለው መጽሔት እንደገለጸው የአገሪቱ መንግሥት “በጥንታዊው የቬዲክ ሥርዓት አማካኝነት የዝናብን አምላክ ለመለማመን” የገንዘብ ድጋፍ አድርጓል። የአገሪቱ የእርዳታ አሰባሳቢ ድርጅት ሚኒስትር “አምላክ ይደርስልናል” ብለው ነበር። ከ50 ቤተ መቅደሶች የተውጣጡ ቀሳውስት ለ11 ቀናት ሥርዓተ ጸሎት ሲያከናውኑ ሰነበቱ። ምን ውጤት ተገኘ? “አማልክቱ በተደረገላቸው ሥርዓተ ጸሎት እንዳልተማረኩ ገሃድ ሆኗል። . . . በሃይማኖት አኳያ የተደረገው ሙከራ ስለከሸፈ አሁን መንግሥት በሳይንሳዊው መንገድ ደግሞ ለመሞከር ስለወሰነ” ደመና መፍጠር በሚቻልበት ዘዴ በመጠቀም “ሰው ሠራሽ በሆነ መንገድ ዝናብ ለማዝነብ አንዳንድ እርምጃዎች እየወሰደ ነው” ሲል ኢንድያ ቱዴይ አትቷል።
የሳምባ ነቀርሳ እየጨመረ ነው
የሳምባ ነቀርሳ (ቲዩበርክሎሲስ) በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ እጅግ በጣም ብዙ ሕዝብ በመጨረስ ላይ ያለ በሽታ ሆኗል ሲል ዳገንስ ኒየሄተር የተባለው የስዊድን ዕለታዊ ጋዜጣ ሪፖርት አደረገ። በ1992 ከ3, 000,000 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ማለትም በኤድስ፣ በኮሌራና በወባ በሽታ ከሞቱት እጅግ የሚበልጡ ሰዎች በዚሁ በሽታ ሳቢያ አልቀዋል። የዓለም የጤና ድርጅት የሳምባ ነቀርሳ እንዳይዛመት ለመግታት ሲል በቅርቡ በለንደን ኮንፍረንስ አድርጎ ነበር። በሽታው ያላደጉ አገሮችን ይበልጥ እያጠቃ ያለ አሳሳቢ ዓለም አቀፍ ወረርሽኝ መሆኑ በኮንፍረንሱ ላይ ተገልጿል። ሆኖም ከቦታ ወደ ቦታ የሚጓጓዘውና ከየቦታው የሚጎርፈው ሕዝብ እየጨመረ ስለሄደ በሽታው በኢንዱስትሪ በበለጸጉት አገሮችም ላይ በመዛመት ላይ ነው። በጣም ተስፋፍቶ በሚገኘውና በሰፊው በሚታወቀው የሳምባ ነቀርሳ ዓይነት ከሚለከፉት ሰዎች ውስጥ 95 በመቶው ሊፈወሱ የሚችሉ ሲሆኑ በአዲሱና መድኃኒቶችን የመቋቋም ኃይል ባለው የሳምባ ነቀርሳ ዓይነት ከተያዙት ውስጥ ግን ሊድኑ የሚችሉት ከ40 በመቶ ያነሱት ናቸው።
በሚልዮን የሚቆጠሩት የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናት
“በዓለም ዙሪያ ከ100 ሚልዮን የሚበልጡ ሕፃናት የሚኖሩት ጎዳና ላይ ነው፤ ከነዚህም ውስጥ ቢያንስ ቢያንስ እኩሌቶቹ አደንዛዥ ዕፅ ይወስዳሉ” በማለት የዓለም የጤና ድርጅት ሪፖርት አድርጓል። እንደ ሪዮ ዲ ጃኔሮ፣ ማኒላ፣ ሉሳካ፣ ሞንትሪያልና ቶሮንቶ በመሳሰሉ ትልልቅ ከተሞች ውስጥ የተደረገ ጥናት እንደሚያሳየው በነዚህ ከተሞች ውስጥ ያሉ አደንዛዥ ዕፅ የሚወስዱ የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናት ቁጥር ብዙም አይበላለጥም። የጥናቱ አስተባባሪ የነበሩት የኢኮኖሚ ጠበብቱ ሃንስ ኢምብሌድ እንዳሉት ከሆነ “አደንዛዥ ዕፅ የሚወስዱትን ልጆች ብዛት የሚወስነው የአደንዛዥ ዕፁ በቀላሉ መገኘት ወይም አለመገኘት ይመስላል።” ሆኖም “የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናትን ጉዳይ እንደሚከታተሉት ሌሎች ማኅበራዊ ተቋሞች ሁሉ ባለ ሥልጣኖችም የሕፃናቱን አደንዛዥ ዕፅ የመውሰድ ጉዳይ ችላ ወደማለቱ አመዝነዋል” ሲሉ አክለው ተናግረዋል። ምንም እንኳን እንደ ኢምብሌድ አባባል ሌሎቹ ሰዎች “ልጆቹን ከአካባቢው ሊያባርሯቸው ቢሞክሩም ችግሩ ልጆቹ የሚሄዱበት የሌላቸው መሆኑ ነው።” ኦ ኤሰታዶ ዴ ኤስ ፓውሎ በተባለው ጋዜጣ ላይ የወጣው ዘገባ እንደገለጸው ደግሞ እነዚህ የጎዳና ተዳዳሪ ሕፃናት “መኖር ይፈልጋሉ።”
በቀቀኑ የሰጠው ምሥክርነት
ኬራላ በምትባለው በደቡባዊ ህንድ ክፍለ አገር ውስጥ በዋለው ችሎት ላይ አንድ በቀቀን (ፓሮት) ዋና ምሥክር ሆኖ ቀረበ። ኢንድያን ኤክስፕረስ የተባለው ጋዜጣ እንደዘገበው በሁለት ጎረቤታሞች መሐል በበቀቀኑ ባለቤት ማንነት ላይ ጭቅጭቅ ይነሣና ጉዳዩ ለፍርድ ቤት ይቀርባል። ጭቅጭቁን ለመፍታት ዳኛው በቀቀኑ ራሱ ፍርድ ቤት ቀርቦ እንዲመሠክር ያዛሉ። ተባባሪው በቀቀን በታዛዥነት ቀደም ሲል ‘በቀቀናችን ጠፋ’ በማለት ሪፖርት አድርጎ በነበረው ቤተሰብ ውስጥ ያሉትን ልጆች ስም በመጥራት ወሳኝ የሆነ ምሥክርነት ሰጥቷል። ለታማኙ በቀቀን ምስጋና ይግባውና የአውራጃው ፍርድ ቤት ዳኛ የበቀቀኑ ባለቤት ይኸው ቤተሰብ ነው በማለት ፈርደዋል።
ለሕይወት ማዳኛ የሚሆን ገንዘብ ታጣ
ምንም እንኳን የሳምባ ምች (ኒሞኒያ) እና ተቅማጥ ሊፈወሱ የሚችሉ በሽታዎች ቢሆኑም በየዓመቱ 7.5 ሚልዮን ልጆችን ይገድላሉ ሲል አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የተባለው የዜና አገልግሎት ዘግቧል። በዓለም ዙሪያ ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ 40 ሚልዮን ሕፃናት በሳምባ ምች ሲለከፉ ከአንድ ቢልዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ በተቅማጥ ይያዛሉ። ይሁን እንጂ በዓለም የጤና ድርጅት ውስጥ የሚሠሩት ዶክተር ራልፍ ሄንደርሰን እንዳሳወቁት እነዚህ በሽታዎች “ቀላል በሆነና ብዙ ወጪ በማይጠይቅ ሕክምና” ሊድኑ የሚችሉ ነበሩ። የሚያሳዝነው ግን የዓለም የጤና ድርጅት እነዚህን ሁለት በሽታዎች ለመዋጋት የነደፋቸው እቅዶች በገንዘብ እጥረት ምክንያት መሠረዝ አለዚያም ላልተወሰነ ጊዜ መተላላፍ ነበረባቸው። እንደ ዓለም የጤና ድርጅት አባባል ገንዘብ ቢኖር ኖሮ በተቅማጥ ምክንያት ከሚሞቱት ገሚሱ እንዲሁም በሳምባ ምች ሳቢያ ከሚሞቱት መካከል ሲሶው ሊድኑ ይችሉ ነበር።
የንባብ ፍላጎት አሽቆልቁሏልን?
“መጽሔቶችና ጋዜጦች ብዙም አንባቢ የላቸውም” በማለት ጋዜታ መርካንቲል ገልጿል። ይኸው የብራዚል ጋዜጣ እንደዘገበው ዓለም አቀፍ የጋዜጣ አሳታሚዎች ፌዴሬሽን በጀርመን አገር በበርሊን ከተማ ባካሄደው 46ኛው ጉባኤ ላይ የተገኙት ልዑካን “ሰዎች የታተሙ ጽሑፎችን ለማንበብ ያላቸው ፍላጎት በፍጥነት እያሽቆለቆለ የመሄዱና ድምፅና ምስልን አንድ ላይ የሚያስተላለፉ መገናኛ ብዙኃንን ማዳመጥ የሚመርጡ የመሆናቸው” ጉዳይ አሳስቧቸዋል። የኢንተር አሜሪካ የጽሑፍ አሳታሚዎች ማኅበር ፕሬዘዳንት በሆኑት በአሌጃንድሮ ጁንኮ ደ ላ ቬጃ አመለካከት ብዙ ሰዎች “ታትመው ስለሚወጡ ጽሑፎች ግድ የላቸውም። . . . ብዙዎች እስካሁን የሚያምኑት ለነሱ ይበልጥ የሚስማማቸው ቴሌቪዥን እንደሆነ ነው።” በማያሚ የሚታተመው ላስ አሜሪካስ የተባለ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ “በዓለም ዙሪያ እየተፈጸሙ ስላሉት ክንውኖች ሰፊ ገለጻ የሚያቀርቡት” ጋዜጦች ናቸው ሲሉ የተናገሩ ሲሆን በዚህም ብዙ የጋዜጣ አዘጋጆች ሳይስማሙበት እንደማይቀሩ አያጠራጥርም።
በምግብ ውስጥ የሚገኝ ገዳይ
የተፍትስ ዩኒቨርሲቲ ያወጣው ሪፖርት እንደሚገልጸው በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በየዓመቱ ወደ 80 ሚልዮን የሚጠጉ ሰዎች የተመረዘ ምግብ በመብላታቸው ምክንያት ይታመማሉ። ሪፖርቱ እንደገለጸው “ብዙውን ጊዜ ሰዎቹ በሽታቸው አይታወቅላቸውም፤ ምክንያቱም የበሽታው ምልክቶች ብርድ ብርድ የማለት፣ ትኩሳት፣ ማቅለሽለሽ፣ ቁርጠት፣ ማስቀመጥ፣ ማስመለስ በመሆናቸው ከኢንፍሉዌንዛ ምልክቶች ጋር ይመሳሰላሉ።” አንዳንድ ጊዜ በምግብ ምክንያት የሚመጡት እነዚህ በሽታዎች ገዳይ ናቸው። በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ እንኳን በየዓመቱ 9,000 ሰዎች የተመረዘ ምግብ በመመገባቸው ምክንያት ይሞታሉ። “ሰዎች በየቤታቸው በቅድሚያ መወሰድ የሚገባቸውን ጥንቃቄዎች ቢያደርጉ ኖሮ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከሎች እንደገመቱት በምግብ የተነሣ ከሚመጡት በሽታዎች 85 በመቶ የሚሆኑትን መከላከል ይቻል ነበር” ሲል የተፍትስ ዩኒቨርሲቲ ዳይት ኤንድ ኒዩትሪሽን ሌተር አትቷል። በቅድሚያ መወሰድ ካለባቸው ጥንቃቄዎች መካከል ማንኛውም ምግብ ከተሠራ በኋላ ሳይበላ እስከ ሁለት ሰዓት ያህል የሚቆይ ከሆነ ማቀዝቀዣ ውስጥ ማስቀመጥ እንዲሁም ማናቸውንም አትክልትና ፍራፍሬ ከመመገብ በፊት በደንብ ማጠብ ይገኙበታል።