የሃይማኖት የወደፊቱ ሁኔታ ካለፈው ታሪኩ አንጻር ሲታይ
ክፍል 13:- ከ476 እዘአ ወዲህ ከጨለማ ውስጥ “ቅዱስ” ነገር ተወለደ—“በጨለማ የተሠራ ኃጢአት በሰማይ እንደ እሳት ብራና ግልጽ ሆኖ ይታያል።” አንድ የቻይናውያን ተረት
በ1988 በሚያዝያ ወር ዋና ጸሐፊ የነበሩት ሚኻኤል ጎርባቾቭ መንግሥት ከቤተ ክርስቲያንና ከአባሎችዋ ጋር በነበረው ግንኘነት ረገድ የተሠሩት ስህተቶች መታረም እንደሚገባቸው በአደባባይ ሲናገሩ በመስማትዋ በሶቪየት ኅብረት የምትገኘው ቤተ ክርስቲያን በጣም ተደስታለች።
በተጨማሪም የሮማ ካቶሊክ ሊቀ ጳጳስ የሆኑት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ “ክርስቶስ የሚፈልገውንና የቤተ ክርስቲያን ባሕርይ መሠረት የሆነውን ፍጹም አንድነት የሺህ ዓመት ዕድሜ ካላት እህት ቤተ ክርስቲያን ጋር ለመመሥረት ልባዊ ፍላጎት” ያላቸው መሆኑን የሚገልጽ ሰላምታ በላኩ ጊዜ ሌላ ዓይነት መለያየት የሚወገድ መስሎ ታይቷል። ይሁን እንጂ መጀመሪያስ ቢሆን ‘በእህትማማች አብያተ ክርስቲያናት’ መካከል እንዴት መለያየት ሊፈጠር ቻለ?
ቀድሞውንም ያልነበረ አንድነት እንዴት ሊታጣ ቻለ?
ታላቁ ቆስጠንጢኖስ በአራተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ የሮማ አፄያዊ መንግሥት ንጉሠ ነገሥት ከሆነ በኋላ ዋና ከተማውን ከሮማ በቦስፖረስ የባሕር ዳርቻ ወደምትገኘውና ባይዛንቲየም ወደምትባለው የግሪክ ከተማ አዛወረ። ይህች ከተማ ስምዋ ተለውጦ ቁስጥንጥንያ የተባለች ሲሆን ዛሬ በቱርክ አገር ኢስታንቡል ትባላለች። የዋና ከተማ ዝውውር የተደረገው መገነጣጠል አስግቶት የነበረውን ግዛት አንድነት ለማስጠበቅ ታስቦ ነበር። እንዲያውም ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንደሚለው ከሁለተኛው መቶ ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ ጀምሮ “በግልጽ ሊታይ የሚችል አይሁን እንጂ ግዛቱ የሚከፋፈልበት እቅድ መነደፍ ጀምሮ ነበር።”
ክርስትና ከምዕራቡ የሮማ ግዛት ክፍል ይልቅ በምሥራቁ ክፍል በበለጠ ፍጥነትና በቀላሉ ተሰራጭቶ ነበር። በዚህም ምክንያት ቆስጠንጢኖስ አንድ ሁሉን አቀፍ (ካቶሊክ) ሃይማኖት የግዛቱን አንድነት ሊያስጠብቅለት የሚችል ኃይል ሊሆን እንደሚችል ተገነዘበ። ግዛቱ ከመሠረቱ የተከፋፈለ እንደነበረ ሁሉ ሃይማኖቱም አንድነት ያልነበረውና የተከፋፈለ ነበር። የምሥራቁ ቤተ ክርስቲያን ማዕከሉን ሮም ላይ ካደረገው ቤተ ክርስቲያን ይበልጥ ወግ አጥባቂ ነበረና ሮም ያመጣቻቸውን ሃይማኖታዊ ለውጦችና መሻሻሎች ተቃወመ። ዘ ኮሊንስ አትላስ ኦቭ ወርልድ ሂስትሪ እንደሚለው “እስከ አሥራ ሁለተኛው መቶ ዘመን ድረስ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት መካከል በርካታ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ውዝግቦች ነበሩ።”
ከእነዚህ ሃይማኖታዊ ውዝግቦች መካከል አንደኛው ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነውን የሥላሴ መሠረተ ትምህርት ለማዳበር ተብሎ የወጣውን የኒቂያ ድንጋጌ የሚመለከት ነበር። በመጀመሪያዎቹ ሦስት የቤተ ክርስቲያን አጠቃላይ ጉባኤዎች (ኒቂያ በ325 እዘአ፣ ቁስጥንጥንያ በ381 እዘአ፤ ኤፌሶን በ431 እዘአ) የተላለፈው ድንጋጌ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሲናገር “ከአብ የሚወጣው ቅዱስ መንፈስ . . .” ይል ነበር። የምዕራቡ ቤተ ክርስቲያን ግን በስድስተኛው መቶ ዘመን በተደረገ አንድ ጉባኤ ይህን ሐረግ ለውጦ “ከአብ እና ከወልድ የሚወጣ” ተብሎ እንዲነበብ አድርጓል። ይህ በፊሊዮኬ (በላቲንኛ “እና ወልድ” ማለት ነው) ምክንያት የተነሳው ክርክር ዛሬም እነኚህን “ክርስቲያን” እህትማማች አብያተ ክርስቲያናት ማወዛገቡ አልቀረም።
የምዕራቡ ግዛት በ476 እዘአ ጠፍቶ የጨለማው ዘመን ከገባ በኋላ በመካከላቸው የነበረው ልዩነት ይበልጥ ገሐድ ሆኖ ወጣ። የጨለማው ዘመን በእርግጥም በክርስትና ረገድ እውቀት የተዳፈነበትና ድንቁርና የሰፈነበት ዘመን ነበር። የክርስትና የወንጌል ብርሃን ለጊዜውም ቢሆን በሕዝበ ክርስትና ጨለማ ተሸነፈ።
ሃይማኖታዊ ጨለማ አንድነት ለመጠበቅ አይረዳም። የካንተርበሪ ገዳም አለቃ የነበሩት ኸርበርት ዋዳምስ እንደሚከተለው ብለዋል:- “የክርስቲያኑ ዓለም የተለያዩ ክፍሎች ፈጽሞ ሊያገኙ ያልቻሉትን አንድነት ሳያቋርጡ ይፈልጉ ነበር። በኋለኞቹ ዘመናት የፈረሰው አንድነት የተሟላ አንድነት አልነበረም።” አክለውም “ሕዝበ ክርስትና አንዲት የተባበረች ትልቅ ቤተ ክርስቲያን ነበረች የሚለው አስተሳሰብ ሐሳብ የወለደው ግምታዊ አስተሳሰብ ነው” ብለዋል።
አንድ “ሕፃን” ተወለደ
“ሕፃኑ” የተወለደው በ800 እዘአ በገና ዕለት ሲሆን ባደገ ጊዜም ቅዱስ ተብሎ ተጠርቷል። ይህ ሕፃን ሊቀ ጳጳስ ሊዮ ሳልሳዊ ከምሥራቃዊው ቤተ ክርስቲያን ከተገነጠሉና የፍራንኮች ንጉሥ የነበረውን ሻርለማይን ንጉሠ ነገሥት አድርገው ዘውድ ከጫኑለት በኋላ የተወለደውና እንደገና የተቋቋመው የምዕራቡ ግዛት ነው። የምዕራቡ ግዛት ለጥቂት ጊዜ ተቋርጦ ከቆየ በኋላ በ962 እዘአ እንደገና ተቋቋመና ቆየት ብሎ ቅዱሱ የሮማ መንግሥት በሚል የትዕቢት ስያሜ መጠራት ጀመረ።
እንደ እውነቱ ከሆነ የሮማ መንግሥት የሚለው አጠራር ትክክለኛ ስያሜ አልነበረም። ይህ መንግሥት የዘመናችንን ጀርመን፣ ኦስትሪያ፣ ምዕራባዊ ቼኮዝላቫኪያ፣ ስዊዘርላንድ፣ ምሥራቅ ፈረንሳይና የባሕር ጠረፍ አካባቢ አገሮች የሚያጠቃልል ስለነበረ በአብዛኛው ከኢጣልያ ውጭ ነበር። በዚህ ግዛት የበላይነት የነበራቸው የጀርመን አገሮችና ጀርመናውያን ገዥዎች ነበሩ። በዚህም ምክንያት የጀርመን ብሔር ስሙ ተለውጦ ቅዱሱ የሮማ መንግሥት ተብሏል።
ይህ መንግሥት የሃይማኖት ጉዳዮችን ከፖለቲካ የሚቀላቅል መንግሥት ነበር። ኮልየርስ ኢንሳይክሎፔድያ እንደሚገልጸው ዓላማውና እቅዱ “በመላው ምድር ሁሉን አቀፍ ከሆነው ሃይማኖት ጋር ተስማምቶና ከአምላክ ባገኘው የሥልጣን ክልል ተወስኖ የሚሠራ አንድ ብቸኛ ፖለቲካዊ ራስ እንዲኖር ነበር።” ይሁን እንጂ በቤተ ክርስቲያንና በመንግሥት መካከል ያለው የሥልጣን ድንበር ሁልጊዜ በግልጽ ያልተለየ መሆኑ ለብዙ ግጭቶች መን ስኤ ሆኖአል። በተለይ በ11ኛው መቶ ዘመንና በ13ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ መካከል በነበሩት ዘመናት ቤተ ክርስቲያንና መንግሥት የአውሮፓን የበላይ አመራር ለማግኘት እርስ በርሳቸው ይፎካከሩ ነበር። አንዳንዶች ሃይማኖት በፖለቲካ ጉዳዮች ውስጥ መግባቱ ተገቢና በራስ ወዳድነት ላይ ያልተመሠረተ ነው ይላሉ። ይሁን እንጂ ዋዳምስ የተባሉት ደራሲ “ለዚህ ሁኔታ ዋነኛ ምክንያት የሆነው ሊቃነ ጳጳሳት የነበራቸው የሥልጣን ጥማት ነበር” ብለዋል።
ይህ መንግሥት በሕልውና በቆየባቸው የመጨረሻ አንድ ተኩል መቶ ዘመናት፣ ከነበረው ደረጃ ዝቅ ብሎ በአንድ የጋራ ንጉሠ ነገሥት ደካማ ቁጥጥር ሥር የሚተዳደሩ የትናንሽ ብሔራት ስብስብ ሆኖአል። በዚህ የታሪክ ወቅት ላይ ቮልቴር የተባለው ጸሐፊ እንደተናገረው “ቅዱስም፣ ሮማዊም፣ አንድ መንግሥትም አልነበረም።” በመጨረሻም ይህ “ቅዱስ ሕፃን” ለቅድስና የሚያበቃው አንዳች ተግባር ሳይፈጽም አርጅቶ በ1806 ሞተ። በ1871 ይህ መንግሥት ሁለተኛው ራይኽ (በጀርመንኛ “አፄያዊ መንግሥት” ማለት ነው) ተብሎ እንደገና ቢቋቋምም 50 ዓመት ላልሞላ ጊዜ ከቆየ በኋላ በ1918 ፈራርሷል። በ1933 ደግሞ በአዶልፍ ሂትለር ይመራ የነበረው ሦስተኛ ራይኽ መላውን አውሮፓ ረጋግጦ ከግዛቱ ሥር ማድረግ ቢጀምርም በ1945 ከፍተኛ ውርደት ተቀብሎ ፍጻሜው በበርሊን ፍርስራሾች ውስጥ ሆኗል።
የጀርመናውያን ተጽእኖ በምዕራቡ ዓለም
መየርስ ኢሉስትርየርተ ቨልትጌሺክተ (የመየር ሥዕላዊ የዓለም ታሪክ) የተባለው የጀርመንኛ ማመሳከርያ መጽሐፍ “የመካከለኛው ዘመን አውሮፓ በሦስት አምዶች ላይ ማለትም . . . በግሪካውያንና በሮማውያን የጥንት የወግና የባሕል ቅርሶች ላይ በተመሠረተው የሮማውያን ወግ፣ በክርስትናና በመጨረሻም ጀርመናውያን ሕዝቦች ከቅድመ አያቶቻቸው በወረሷቸው ወጎች ላይ የተመሠረተ ነበር” ብሏል። ኤሚል ናክ የተባሉት ጀርመናዊ ደራሲ ይህን ሲያረጋግጡ እንዲህ ብለዋል:- “ታላቁ ሊቀ ጳጳስ ግሪጎሪ ብዙዎቹ አረማዊ በዓላት ወደ ክርስትና በዓልነት እንዲለወጡ ለቤተ ክርስቲያን ሐሳብ ካቀረቡበት ጊዜ ጀምሮ የጥንቶቹ ጀርመናውያን ዓመት በዓሎች የክርስትና በዓላት ሆነው ቀጥለዋል።”
ጀርመናውያን ሕዝቦች እነዚህን ሃይማኖታዊ በዓላት ማክበራቸው የጠለቀ ሃይማኖታዊ ስሜት ያላቸው መሆናቸውን የሚያመለክት አልነበረም። የጀርመን ሃይማኖት ጠቢብ የሆኑት ሟቹ አንድርያስ ሆይስለር እንደገለጹት ሃይማኖታቸው “ከምንም ነገር የማያግድ፣ በአፈ ታሪክ ላይ የተመሠረቱ ቀኖናዎችን ጨምሮ አስቸጋሪ የሆኑ ነገሮችን የማይጠይቅ ነበር። አንድ ሰው መሥዋዕት ካቀረበ፣ የቤተ መቅደስ ግብር ከከፈለ፣ መቅደሱን ካላረከሰና አማልክትን የሚዘልፍ ነገር ካልጻፈ ሃይማኖተኛ ሰው እንደሆነ ይቆጠር ነበር።” ጽሑፋቸውን ሲደመድሙ “ሃይማኖታዊ ግፊት ነው ለማለት አይቻልም። . . . የጀርመናውያን ዓላማና ግብ በሃይማኖታቸው ላይ የተመሠረተ አልነበረም” ብለዋል።
የጥንት ጀርመናውያን ሕዝቦች በአማልክት ያምኑ የነበረ ቢሆንም አማልክትን የፈጠረና ከአማልክት የበለጠ ሌላ ኃይል እንዳለ ይሰማቸው ነበር። ይህ ኃይል ደራሲው ናግ እንደሚያብራሩት “በመሥዋዕቶችም ሆነ በጸሎት የማይለመነው የዕድል ኃይል ነው።” ቢሆንም ይህ የዕድል ኃይል የሚሠራው ከተፈጥሮ ሕጎች ጋር ተስማምቶ ስለሆነ “በጭፍን የሚመራ” ኃይል ተደርጎ አይታይም ነበር። በዚህም ምክንያት ሰው “የዕድል ምርኮኛ ሳይሆን የራሱ ነፃ ምርጫ” እንዳለው ይታመን ነበር።
የጀርመናውያን ሃይማኖት በተፈጥሮ ላይ የተመሠረተ ነበር። አብዛኛውን ጊዜ መሥዋዕቶች ይቀርቡ የነበረው ከቤት ውጭ በደኖችና በቁጥቋጦዎች ውስጥ ነበር። አንድ የጀርመናውያን አፈ ታሪክ አማልክት በየቀኑ ችሎት የሚያስችሉበት ይግድራሲል የሚባል የጠፈር ዛፍ እንዳለ ይናገራል። ዘ ኢንሳይክሎፔድያ ኦቭ ሪልጅን እንዲህ በማለት ያብራራል:- “ጫፉ እስከ ሰማይ ይደርስና ቅርንጫፎቹም በመላው ምድር ላይ ይዳረስ ነበር። . . . የዚህ ዛፍ ምሳሌነት በሌሎች አፈ ታሪኮችም ተንጸባርቋል። ለምሳሌ ያህል በጥንቷ ባቢሎንያ አንድ ኪስካኑ የሚባል የጠፈር ዛፍ በአንድ ቅዱስ ቦታ በቅሎ ነበር። . . . በጥንትዋ ሕንድ መላው ጽንፈ ዓለም በጎባጣ ዛፍ ይመሰል ነበር። . . . ይሁን እንጂ የይግድራሲል ጽንሰ ሐሳብ ከአይሁዳውያንም ሆነ ከክርስትና እምነቶች ጋር ምን ዓይነት ዝምድና እንዳለው የሚያሳይ ማስረጃ አልተገኘም።”
ይህን ስንመለከት የጀርመናውያን ሃይማኖት ተጽእኖ በሚታይባቸው አገሮች የሚኖሩ ሰዎች በዕድል የሚያምኑ፣ በጣም ሃይማኖተኛ ያልሆኑና ‘የእኔ አምላክ ተፈጥሮ ነው!’ የሚሉ መሆናቸው አያስደንቅም። በተጨማሪም የጀርመናውያን ሃይማኖት ወደ ክርስትና ካስገባቸው የአረማውያን ልማዶች ብዙዎቹ በተፈጥሮ ላይ የሚያተኩሩ የሆኑበትን ምክንያት መረዳት አስቸጋሪ አይሆንም። በመብራቶችና በዛፍ ተቀጽላዎች እንደመጠቀም፣ ፍልጥ እንደማንደድና የገና ዛፍ እንደማዘጋጀት ያሉት በምሳሌነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።
በዚሁ ጊዜ በምሥራቁ ክፍለ ዓለም የተፈጸሙ ሁኔታዎች
ሁልጊዜ ከምዕራቡ ቤተ ክርስቲያን ጋር ይወዛገብ የነበረው የምሥራቁ ቤተ ክርስቲያን ከራሱም ጋር ቢሆን ስምምነት አልነበረውም። ለዚህም በሥዕሎችና በምስሎች አምልኮ ላይ የተነሳው ውዝግብ ምሳሌ ሊሆን ይችላል። ሃይማኖታዊ ሥዕሎችና ምስሎች በምዕራቡ ቤተ ክርስቲያን ከተለመዱት ሦስት ጊዜ ስፋት ያላቸው ቅርጾችና ሐውልቶች የተለዩ ሲሆኑ ጠፍጣፋ በሆኑ ገጾች ላይ የሚሳሉ ወይም የሚቀረጹ ናቸው። ሥዕሎቹ አብዛኛውን ጊዜ የሚያሳዩት ክርስቶስን፣ ማርያምን ወይም “ቅዱሳንን” ነው። በምሥራቁ ዓለም በጣም በመስፋፋታቸው ምክንያት የቤትስ ኮሌጅ ባልደረባ የሆኑት ጆን ኤስ ስትሮንግ እንዳሉት “የሚወክሏቸው አካላት ቀጥተኛ ነጸብራቅና ምስል ሆነው መታየት ጀምረው ነበር። . . . በዚህም ምክንያት ቅድስናና ተአምር የማድረግ ኃይል የተሞሉ እንደሆኑ ይታመን ነበር።” ይሁን እንጂ በስምንተኛው መቶ ዘመን ላይ ሳልሳዊ ሊዮ የተባሉት የባይዛንታይን ንጉሠ ነገሥት ሰዎች በሥዕሎችና በምስሎች እንዳይጠቀሙ አግደው ነበር። በመጨረሻም በዚህ ጉዳይ ላይ የተነሳው ውዝግብ በ843 እዘአ ላይ እልባት አግኝቶ በሥዕሎችና ምስሎች መጠቀም በምሥራቁ ቤተ ክርስቲያን የተፈቀደ ሆነ።
በምሥራቁ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለነበረው መለያየት ሌላ ምሳሌ ከግብጽ እናገኛለን። አንዳንድ ግብጻውያን ካቶሊኮች በግብጽ ቋንቋ የሚናገሩ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ በግሪክኛ ይናገሩ ነበር። ሁለቱ የቋንቋ ቡድኖች በክርስቶስ ባሕርይ ላይ የተለያየ አመለካከት ነበራቸው። የባይዘንታይን ባለሥልጣኖች ለመቀበል አሻፈረን ቢሉም በዚህ ምክንያት ሁለት የተለያዩ አብያተ ክርስቲያናት ሊገኙ ችለዋል። በዚህ ጊዜ ሁሉ እያንዳንዱ ቡድን የራሱ ጳጳስ የእስክንድርያ ፓትርያርክ እንዲሆን ጥረት ያደርግ ነበር።
ዛሬም ቢሆን የምሥራቁ ቤተ ክርስቲያን እንደተከፋፈለ ነው። ለምሳሌ ያህል የምሥራቁን ሥርዓተ አምልኮ ከሚቀበሉት አብያተ ክርስቲያናት መካከል ዩኒየትስ የሚባሉ አብያተ ክርስቲያናት የሮማን መንበረ ጵጵስና ሥልጣን ይቀበላሉ። የምሥራቅ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናትና ሌሎች አነስተኛ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት የሚባሉት ግን አይቀበሉም።
እንደ እሳት ብራና
ቅዱስ ያልሆነው፣ ሮማዊ ሊባል የማይችለውና እንድ የተባበረ መንግሥት ያልሆነው የሮማ መንግሥት ከመጥፋቱ ከረዥም ጊዜ በፊት አንግሊካን ቸርችማን ዋዳምስ እንዳሉት “ምሥራቃውያን ክርስቲያኖች ለሌሎች ክርስቲያኖች የጠለቀ ጥላቻ እንዲኖራቸው ተደርጎ ነበር።” በእርግጥም “ክርስቲያኖች ክርስቲያኖችን” በመጥላት የሠሩት ኃጢአት በጨለማ ውስጥ የተሠራ ቢሆንም በሰማያት እንደ እሳት ብራና ግልጽ ሆኖ ታየ እንጂ ተሰውሮ አልቀረም።
ከዚህም በላይ ሕዝበ ክርስትና የሠራችው እርስ በርስ የመከፋፈል ኃጢአት በምድር ሰዎች መታየቱ አልቀረም። ለምሳሌ ያህል አንድ በሰባተኛው መቶ ዘመን እዘአ ይኖር የነበረ፣ “ካደረጋቸው ጉዞዎችና በአካባቢው ከሚኖሩ ሰዎች ስለ ክርስትና በቀላሉ የማይገመት እውቀት ያተረፈ” እውቅ አረብ “በክርስቲያኖች መካከል የተመለከተው ውዝግብ እንዳሳዘነው” ዋዳምስ የተባሉት ቄስ ይናገራሉ። ይህ ሰው እርስ በርስዋ የተከፋፈለችው ሕዝበ ክርስትና ከምትሰጠው የተሻለ መንገድ ለማግኘት ፈልጎ ነበር። ታዲያ ይህ ሰው የተሻለ መንገድ አግኝቶ ይሆን? በ1989 ከዓለም ሕዝቦች 17 በመቶ የሚሆኑት ከዚህ ሰው ዓላማ በስተጀርባ ተሰልፈዋል። ይህ ሰው ማን እንደሆነና “ለአምላክ ፈቃድ ስለ መገዛት” ምን ተሰምቶት እንደነበረ በሚቀጥለው እትማችን ይብራራል።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
የሮማ መንግሥት በፈረሰበት (476 እዘአ) ጊዜ ሕዝበ ክርስትና እርስ በርሳቸው በሚፎካከሩ ስድስት ጳጳሳት ሥር ተከፋፍላ ነበር። እነርሱም ሮም፣ ቁስጥንጥንያ፣ አንጾኪያ፣ እስክንድርያ፣ ኢየሩሳሌምና ሳላሚስ (ቆጵሮስ) ናቸው
ሮም
ቁስጥንጥንያ
አንጾኪያ
ኢየሩሳሌም
እስክንድርያ
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የኢየሱስና የማርያም (ሃይማኖታዊ) ሥዕል
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.