ከአልኮል ሱስ መላቀቅ ይቻላል
“ከፊታችን የተደቀነው አንድ ምርጫ ብቻ ነው። መጠጥ አቁሞ ከአልኮል ሱስ መላቀቅ፤ አለዚያ አልኮል እየተጋቱ መሞት።”— ከአልኮል ሱስ የተላቀቀ ሰው
አንድ ቀን ሌሊት ከእንቅልፍህ ስትባንን ቤትህ በእሳት ተያይዞ አገኘህ እንበል። ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ሰዎች በቦታው ደርሰው ባደረጉት ርብርቦሽ እሳቱ ጠፋ። ቤትህ ውስጥ ተመልሰህ በመግባት ምንም ነገር እንዳልደረሰብህ ሆነህ ለመታየት ትሞክራለህን? እንደዚህ እንደማታደርግ የታወቀ ነው። ቤቱ እንዳልነበረ ሆኗል፤ ስለዚህ የተለመደውን ዕለታዊ ኑሮ ለመምራት በቅድሚያ ቤቱን እንደገና መገንባት ያስፈልግሃል።
የአልኮል ሱሰኛ የሆነ ሰውም ከሱሱ ለመላቀቅ ጥረት ማድረግ ሲጀምር ተመሳሳይ የሆነ አስቸጋሪ ሁኔታ ከፊቱ ይደቀናል። በአልኮል ጦስ ኑሮው ተበላሽቷል፤ ምናልባትም ሱሰኝነቱ ለበርካታ ዓመታት የቆየ ሊሆን ይችላል። አሁን ግን ከአልኮል ጋር ተቆራርጧል። “እሳቱ” ጠፍቷል፤ ሆኖም የአልኮል ሱሰኛው ከመጠጥ እንደተቆራረጠ መቀጠል እንዲችል አመለካከቱ፣ የአኗኗር ዘይቤውና ጠባዩ የግድ መታደስ ይኖርበታል። የአልኮል ሱሰኛ የነበረ ሰው ለዘለቄታው በዚህ አቋሙ እንዲቀጥል የሚከተሉት ሐሳቦች ሊረዱት ይችላሉ።
1.ጠላትህን ለይተህ እወቅ
መጽሐፍ ቅዱስ የሥጋ ምኞቶች ‘ነፍስን እንደሚዋጉ’ ይገልጻል። (1 ጴጥሮስ 2:11) ‘መዋጋት’ ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ጥሬ ትርጉሙ “ወታደራዊ አገልግሎት ማከናወን” ማለት ሲሆን ከፍተኛ ጥፋት የሚያስከትል ውጊያን የሚያመለክት ትርጉም አለው።— ከሮሜ 7:23-25 ጋር አወዳድር።
ማንኛውም ጎበዝ ወታደር ጊዜ ወስዶ የጠላቱን ስልቶች በጥንቃቄ እንደሚያጠና ሁሉ የአልኮል ሱሰኛ የነበረ ሰውም የአልኮል ሱስን ጠባይና ይህ ሱስ እሱንም ሆነ አብረውት ያሉትን ሰዎች እንዴት እንደሚጎዳ በሚገባ ማወቅ አለበት።a— ዕብራውያን 5:14
2.የመጠጥ ልማድህንም ሆነ አስተሳሰብህን ለውጥ
አንድ ሐኪም “ከአልኮል ሱስ መላቀቅ ማለት ከመለኪያም ሆነ ከልጅነት ጠባይ መራቅ ማለት ነው” ሲሉ ተናግረዋል። በሌላ አባባል የአልኮሉ ልማድ ብቻ ሳይሆን ውስጣዊውም ሰው መለወጥ አለበት ማለት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ “በልባችሁ መታደስ ተለወጡ” በማለት ጥበብ የተሞላበት ምክር ይሰጣል። (ሮሜ 12:2) ‘አሮጌውን ሰውነት ከሥራው ጋር ገፋችሁ ጣሉት።’ (ቆላስይስ 3:9) የአልኮል ሱሰኛ የነበረ ሰው ድርጊቱን ቢተውም ባሕርይው እስካልተለወጠ ድረስ ሌላ ጎጂ ሱስ ማፍራቱ ወይም ወደ ቀድሞ ልማዱ መመለሱ አይቀርም።
3.ችግርህን የምታወያየው አሳቢ የሆነ ጓደኛ ይኑርህ
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ እንዲህ ይላል:- “መለየት የሚወድድ ምኞቱን ይከተላል፣ መልካሙንም ጥበብ ሁሉ ይቃወማል።” (ምሳሌ 18:1) የአልኮል ሱሰኛ የነበረ ሰው ከሱሱ ከተላቀቀም በኋላ ሰበብ የመፈለግ ዝንባሌ ይኖረዋል። ስለዚህ አሳቢ የሆነና ጠንካራ አቋም ያለው የምሥጢር ጓደኛ ያስፈልገዋል። የምሥጢር ጓደኛ የሆነው ሰው ራሱ የአልኮል ሱሰኛ የነበረና ከአልኮል ሱስ መላቀቅ የሚጠይቀውን ትግል በተሳካ ሁኔታ መወጣት የቻለ ሰው ቢሆን በጣም ጠቃሚ ይሆናል። (ከምሳሌ 27:17 ጋር አወዳድር።) እንዲህ ዓይነቱ የምሥጢር ጓደኛ የአልኮል ሱሰኛ የነበረው ሰው የሚያምንባቸውን ጠንካራ ሃይማኖታዊ እምነቶች የሚያከብር እንዲሁም የራሱን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግና ረዘም ላለ ጊዜ የሚቀጥል እርዳታ መስጠት የሚችል መሆን አለበት።— ምሳሌ 17:17
4.ታጋሽ ሁን
ከአልኮል ሱስ ፈጽሞ መላቀቅ የሚቻለው ቀስ በቀስ ነው። የአልኮል ሱሰኛ የነበረው ሰው ሕይወቱን መልሶ ለመገንባት ጊዜ ይወስድበታል። ገንዘብ ነክ ችግር፣ የሥራ ውጥረትና በቤተሰቡ ውስጥ አንዳንድ የተመሰቃቀሉ ሁኔታዎች ሊያጋጥሙት ይችላሉ። ከአልኮል ሱስ መላቀቅ ማለት ከማንኛውም ዓይነት ችግር መላቀቅ ማለት አይደለም። ከአልኮል ሱስ የተላቀቀው ሰው ‘ችግሩን የሚፈታበት’ ኬሚካላዊ ምርኩዝ ሳይኖረው የሕይወትን ውጣ ውረድ ፊት ለፊት መጋፈጥ ሲጀምር ጭንቀት ሊሰማው ይችላል። አንድ ከአልኮል ሱስ የተላቀቀ ሰው እንዲህ ዓይነቱን የጭንቀት ስሜት ሊወጣ እንደማይችል ሲሰማው መዝሙራዊው የተናገረውን የሚከተለውን አጽናኝ ቃል ማስታወስ ይኖርበታል:- “ትካዜህን በእግዚአብሔር ላይ ጣል፣ እርሱም ይደግፍሃል፤ ለጻድቁም ለዘላለም ሁከትን አይሰጠውም።”— መዝሙር 55:22
5.ጤናማ ባልንጀሮች ይኑሩህ
የአልኮል ሱሰኛ የነበረ ሰው በሐቀኝነት ራሱን እንዲህ ብሎ መጠየቅ ይኖርበታል:- ‘ባልንጀሮቼ ከአልኮል ሱስ መላቀቄን የሚደግፉ ናቸው ወይስ ዘወትር “የቀድሞዎቹን ጥሩ ጊዜያት” በማውሳት ጥሩ ነገር እንደቀረብኝ እንዲሰማኝ የሚያደርጉ ናቸው?’ ምሳሌ 18:24 (አዓት) እንዲህ ይላል:- “አንዳቸው ሌላውን የማነካከት ዝንባሌ ያላቸው ጓደኛሞች አሉ፤ ነገር ግን ከወንድም አብልጦ የሚጠጋጋ ጓደኛ አለ።” እውነተኛ ጓደኞች የትኞቹ እንደሆኑና ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉት የትኞቹ እንደሆኑ ለማወቅ አስተዋይ መሆን ያስፈልጋል።
6.ከመጠን በላይ በራስህ አትታመን
“አሁን በጣም ደስ ብሎኛል፤ የመጠጣት ፍላጎቱ እንኳ የለኝም!” እንዲህ ብሎ የሚናገር የአልኮል ሱሰኛ የነበረ ሰው ባደረገው መሻሻል ከመጠን በላይ የሚኩራራና ሱሱን አቅልሎ የሚመለከት ሰው ነው። ከአልኮል ሱስ እንደተላቀቀ የሚሰማው ደስታና እርካታ እንደ ጉም በንኖ ሊጠፋ ይችላል። “ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖርህ ከፍተኛ ጥረት አድርግ” በማለት ዊልፓወርስ ኖት ኢነፍ የተባለው መጽሐፍ ይመክራል። “አለበለዚያ ራስህን ለውድቀት ታመቻቻለህ፤ አወዳደቅህ ደግሞ የከፋ ይሆናል።”— ከምሳሌ 16:18 ጋር አወዳድር።
7.በምትኩ ሌላ ሱስ እንዳይዝህ ተጠንቀቅ
ብዙዎች የመጠጥ ልማዳቸውን ያቆማሉ፤ ሆኖም በምትኩ የተዛባ የአመጋገብ ልማድ ያዳብራሉ ወይም የሥራ ሱሰኞች፣ የቁማር ሱሰኞች ወዘተ ይሆናሉ። ከአልኮል ሱስ የተላቀቀው ሰው ‘ታዲያ ይህ ምን ጉዳት አለው? ቢያንስ ቢያንስ መጠጥ አቁሜያለሁ’ የሚል ምክንያት ሊያቀርብ ይችላል። እርግጥ በአንዳንድ ነገሮች ራስን ማስጠመዱ ጥሩ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ በማንኛውም ነገር ወይም ሥራ ተጠቅመህ ስሜቶችህን ስታደነዝዝ ጊዜያዊ የሆነና የይስሙላ የተረጋጋ መንፈስ እንዲሰማህ ከማድረግ ሌላ የምታገኘው ዘላቂ ጥቅም አይኖርም።
8.አዳዲስ የቤተሰብ ኃላፊነቶችን ለመወጣት ራስህን ዝግጁ አድርግ
ብዙ የአልኮል ሱሰኞች ሁሉ ነገር ተስተካክሎ መስመር ከያዘ በኋላ እንደገና ወደተዉት ሱስ የሚመለሱበትን መንገድ ይፈጥራሉ! ለምን? ከአልኮል ሱስ ከተላቀቁ በኋላ የሚመሩት ሕይወት አዲስ ስለሚሆንባቸው ነው። የአልኮል ሱሰኛ የነበረው ሰው የለመደው የቀድሞ አኗኗሩ የተሻለ ሆኖ ሊታየው ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ የአልኮል ሱሰኛ የነበረው ሰው ከሱሱ መላቀቁ የመላውን ቤተሰብ የአኗኗር ዘይቤ ሊያናጋ ይችላል። በዚህ ምክንያት እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የሥራ ድርሻውን ለመለወጥ ይገደዳል። ሪከቨሪ ፎር ዘ ሆል ፋሚሊ የተባለው ቡክሌት “የመላው ቤተሰብ የሥራ ክፍፍል ተለውጦ እንደገና በአዲስ መልክ መደራጀት ይኖርበታል” ሲል ይገልጻል። የአልኮል ሱሰኛ የነበረ ሰው ከሱሱ መላቀቁ መላውን ቤተሰብ የሚነካ የጋራ ጉዳይ ነው መባሉ ትክክል ነው።— ከ1 ቆሮንቶስ 12:26 ጋር አወዳድር።
9.ሱሱ እንዳያገረሽብህ ተጠንቀቅ
ከመጠን በላይ በራስ መታመን፣ ጤናማ ያልሆነ ጓደኝነት፣ በምትኩ ሌላ ሱስ ማዳበርና ራስን ማግለል ሱሱ እንዲያገረሽብህ ሊያደርጉ የሚችሉ ነገሮች ናቸው። እንደነዚህ ስላሉት ዝንባሌዎች ከምሥጢር ጓደኛህ ጋር በግልጽ ተወያይ።
አንድ ከአልኮል ሱስ የተላቀቀ ሰው እንዲህ ብሏል:- “የአልኮል ሱሰኞች ሁሉ መጠጥ ማቆማቸው የማይቀር ነገር ነው። አንዳንዶቻችን ግን ከመሞታችን በፊት መጠጥ ማቆም በመቻላችን ዕድለኞች ነን።”
[የግርጌ ማስታወሻ]
a እንዲህ ዓይነቱን እውቀት የሚሰጡ ብዙ የሕክምና ማዕከሎች፣ ሆስፒታሎችና ከዚህ ሱስ ለመላቀቅ የሚረዱ ፕሮግራሞች አሉ። ንቁ! መጽሔት የተሻለ የሕክምና ዘዴ ይኼኛው ነው ብሎ ሐሳብ አያቀርብም። ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ቅዱስ ጽሑፋዊ ሥርዓቶችን የሚያስጥሱ ነገሮችን እንዳይፈጽሙ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። የይሖዋ ምሥክር የሆነ ሰው በግንቦት 1, 1983 የእንግሊዝኛ መጠበቂያ ግንብ ገጽ 8-11 ላይ ጠቃሚ ምክሮች ማግኘት ይችላል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የሕክምና እርዳታ የግድ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ
አልኮል ያለበት ማንኛውም መድኃኒት የአልኮል ፍላጎትን እንደገና ሊቀሰቅስና የቀድሞ ሱስ እንዲያገረሽ ሊያደርግ ይችላል።
ዶክተር ጀምስ ደብልዩ ስሚዝ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “አንድ የአልኮል ሱስ የነበረበት ሰው ከአልኮል ሱስ ከተላቀቀ ከብዙ ዓመታት በኋላ ሐኪም ሳያማክር አልኮል ያለው የሳል ሽሮፕ በመውሰዱ ምክንያት የአልኮል ሱሱ እንደገና ማገርሸቱ ያልተለመደ ነገር አይደለም።” የአልኮል ሱሰኛ የነበረ ሰው ሰውነት የማደንዘዝ ጠባይ ባላቸው መድኃኒቶች በሙሉ በቀላሉ ይነካል። ሰውነት የማደንዘዝ ጠባይ ያላቸውን መድኃኒቶች መውሰድ የግድ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ የአልኮል ሱሰኛ የነበረ ሰው የሚከተሉትን ነገሮች ማድረግ ይኖርበታል:-
1. መድኃኒቱን መውሰዱ ምን ጉዳት ሊያስከትል እንደሚችል ለማወቅ ፋርማሲስት አማክር።
2. ሁኔታውን ለምሥጢር ጓደኛህ አሳውቀው፤ የሚቻል ከሆነም ሁልጊዜ መድኃኒቱን ከመውሰድህ በፊት ደውልለት።
3. እያንዳንዱን የምትወስደውን መድኃኒት መጠን መዝግበህ ያዝ።
4. መድኃኒቱን በተቻለ ፍጥነት ለማቆም ሞክር።
5. የሚያስፈልግህን ያህል ከወሰድክ በኋላ የተቀረውን መድኃኒት አስወግድ።