ሴቶች፣ በቤታቸው ውስጥ ይከበራሉን?
“ሴቶቹ አንድ በአንድ በሚዘገንን ሁኔታ ተገደሉ። . . . የተገደሉበት ሁኔታ የተለያየ ቢሆንም ከግድያው በስተጀርባ ያለው ምክንያት አንድ ነበር። ሁሉም ሴቶች የተገደሉት በአሁኑ ወይም በቀድሞ ባላቸው ወይም በወንድ ወዳጃቸው ነው ይላል የኩቤክ [ካናዳ] ፖሊስ ጽሕፈት ቤት። በጠቅላላው በዚህ ዓመት [በ1990] በኩቤክ የተገደሉት ሴቶች ቁጥር 21 ሲሆን ሁሉም በጋብቻ ክልል ውስጥ ለሚፈጸም የኃይል አድራጎት ተጠቂዎች ሆነዋል።”— ማክሊንስ ጥቅምት 22, 1990
አንዳንዶች “የቤተሰብ ሕይወት ጥቁር ገጽታ” ብለው የሚጠሩት በቤተሰብ ክልል ውስጥ የሚፈጸም የኃይል አድራጎት የቤተሰብ መበታተንና ስለ ጋብቻ ግንኙነት የተጣመመ አመለካከት ያላቸው ልጆች ያስከትላል። ልጆች አባታቸው እናታቸውን የሚደበድብበት ምክንያት ግራ ስለሚገባቸው ከአባታቸውና ከእናታቸው ማናቸውን እንደሚደግፉ ይቸገራሉ። (እናቴ ለአባቴ ይህን ያህል ክፉ የምትሆነው ለምንድን ነው? የሚለው ጥያቄ ብዙ ጊዜ አያጋጥምም) በቤተሰብ ውስጥ የሚፈጸም የኃይል አድራጎት ብዙዉን ጊዜ ሲያድጉ ሚስቶቻቸውን የሚደበድቡ ልጆችንም ያፈራል። ከአባታቸው የሚቀረጽባቸው ባሕርይ ከባድ የሆነ የሥነ ልቦና እና የባሕርይ ችግር ያስከትልባቸዋል።
ዘ ወርልድስ ዉሜን— 1970–1990 የተባለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጽሑፍ እንዲህ ይላል:- “ወንዶች በቤታቸው ውስጥ በሴቶች ላይ የሚፈጽሙት ጥቃት ከሁሉ ዓይነት ወንጀሎች ባነሰ መጠን ሪፖርት የሚደረግ ወንጀል እንደሆነ ይታሰባል። ይህም የሆነው በከፊል እንዲህ ያለው ጥቃት እንደ ማኅበረሰባዊ ችግር እንጂ እንደ ወንጀል ስለማይታይ ነው።”
በዩናይትድ ስቴትስ በትዳር ጓደኛ ላይ የሚፈጸም ጥቃት ምን ያህል የተስፋፋ ነው? ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ላይ የተጠቀሰው የምክር ቤት ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “‘በቤተሰብ ክልል ውስጥ የሚፈጸም የኃይል አድራጎት’ የሚለው አነጋገር ልዝብ አነጋገር ሆኖ ሊታይ ይችላል። ይሁን እንጂ በዚህ አባባል የሚገለጸው ባሕርይ ከልዝብነት ፈጽሞ የራቀ ነው። የስታትስቲክስ ማስረጃዎች በትዳር ጓደኛ ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች ምን ያህል ከባድ ሊሆኑና እስከ ግድያ ሊደርሱ እንደሚችሉ ያሳያሉ። በየዓመቱ ከ2,000 እስከ 4,000 የሚደርሱ ሴቶች በሚደርስባቸው ጥቃት ምክንያት ይሞታሉ። . . . በትዳር ጓደኛ ላይ የሚፈጸመው ጥቃት ተደጋጋሚና ሥር የሰደደ በመሆኑ ከሌሎች ወንጀሎች ይለያል። በአካል ላይ የሚፈጸም ተደጋጋሚና የማያባራ ጥቃት ነው።”
ወርልድ ሄልዝ መጽሔት እንዲህ ይላል:- “በሴቶች ላይ የሚፈጸም የኃይል አድራጎት በሁሉም አገር፣ በሁሉም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መደብ ይታያል። በብዙ ባሕሎች ሚስት መደብደብ የወንዶች መብት እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል። አብዛኛውን ጊዜ ሴቶችንና ልጃገረዶችን መደብደብና አስገድዶ በሩካቤ ሥጋ መድፈር ሌሎች ሰዎችን፣ የሕግ ባለ ሥልጣኖችንም ሆነ የጤና ባለሞያዎችን የማይመለከት ‘የግል ጉዳይ’ እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠራል።” ይህ በቤተሰብ ክልል ውስጥ የሚፈጸም የኃይል አድራጎት በቀላሉ ወደ ትምህርት ቤቶችም ሊዛመት ይችላል።
ይህንንም በአንድ የኬንያ የወንዶችና ሴቶች አዳሪ ትምህርት ቤት ውስጥ በሐምሌ ወር 1991 ከተፈጸመው መመልከት ይቻላል። “71 የሚያክሉ በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ተማሪ ልጃገረዶች በወንድ ተማሪዎች ተገደው ሲደፈሩ 19 ልጃገረዶች . . . ሙሉ ሌሊት በቆየው መምህራንም ሆኑ የአካባቢው ፖሊሶች ሊቆጣጠሩ ባልቻሉት በተማሪዎቹ መኝታ ክፍሎች በተካሄደው ጠብ ተገድለዋል” በማለት ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ዘግቧል። እንዲህ ላለው ፍትወታዊ እብደት ምክንያቱ ምን ሊሆን ይችላል? ዘ ዊክሊ ሪቪው የተባለው ሰፊ ተነባቢነት ያለው የኬንያ መጽሔት ዋና አዘጋጅ የሆኑት ሂለሪ ንግዌኖ “ይህ አሳዛኝ ክስተት በኬንያ ማኅበራዊ ኑሮ ውስጥ የተንሰራፋውን አስነዋሪ የወንዶች እብሪተኝነት በገሐድ ያሳያል” ሲሉ ጽፈዋል። “ሴቶቻችንና ልጃገረዶቻችን የሚያጋጥማቸው ዕጣ በጣም የሚያሳዝን ነው። . . . ወንዶች ልጆቻችንን ለሴቶች ልጆች ምንም ያህል አክብሮት እንዳይኖራቸው አድርገን እናሳድጋለን።”
በዓለም ዙሪያ ዋናው ችግር ያለው እዚህ ላይ ነው። ወንዶች ልጆች አብዛኛውን ጊዜ ልጃገረዶችንና ሴቶችን ዝቅተኛ እንደሆኑና ሊጨቆኑ እንደሚገባቸው ፍጡሮች አድርገው እንዲመለከቱ ተደርገው ያድጋሉ። ሴቶች ደካማ እንደሆኑና በቀላሉ የበታች ሆነው ሊገዙ እንደሚችሉ ተደርገው ይታያሉ። እንዲህ ያለ ዝንባሌ ኖሯቸው የሚያድጉ ወንዶች ሴቶችን በንቀት ለመመልከትና እብሪተኝነት ለማሳየት አይከብዳቸውም። የሚያውቋትን ወይም የተቀጣጠሯትን ሴት አስገድደው ለመድፈር ወደኋላ አይሉም። አስገድዶ በመድፈር ረገድ “የተፈጸመው ጥቃት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚያበቃ ቢሆንም በጥቃቱ ምክንያት የሚሰማው ቁስል ዕድሜ ልክ የሚቆይ መሆኑን” መዘንጋት አይገባም።— የምክር ቤቱ ሪፖርት
ብዙ ወንዶች በሴቶች ላይ የጉልበት ጥቃት የማድረስ ዝንባሌ የማያሳዩ ቢሆኑም ለሴቶች ስውር የሆነ ውስጣዊ ጥላቻ ሊኖራቸው ይችላል። ጠብ ፈጥረው አካላዊ ጥቃት ከመፈጸም ይልቅ ሥነ ልቡናዊ ጥቃት ወይም ውርደት ሊያደርሱባቸው ይችላሉ። ዶክተር ሱዛን ፎርዋርድ ሜን ሁ ሄት ዉሜን ኤንድ ዘ ዉሜን ሁ ላቭ ዜም (ሴቶችን የሚጠሉ ወንዶችና እነርሱን የሚወዱ ሴቶች) በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ ብለዋል:- “[እነዚህ ወንዶች] በተጓዳኞቻቸው ገለጻ መሠረት አብዛኛውን ጊዜ ደስ የሚሉና እንዲያውም አፍቃሪዎች ናቸው። ይሁን እንጂ በቅጽበት ተለውጠው ጨካኞች፣ ተጨቃጫቂዎችና ተሳዳቢዎች ሊሆኑ ይችላሉ። የሚያሳዩት ባሕርይ ፊት ለፊት ከመዛትና ከማስፈራራት አንስቶ ለረዥም ጊዜ እስከ ማኩረፍና የሚያስመርር ቃል እስከ መናገር ሊደርስ ይችላል። የጥቃቱ ዓይነት የተለያየ ይሁን እንጂ የሚያስከትለው ውጤት ግን አንድ ነው። ወንዱ ሴቲቱን በመርገጥ በበላይነት ይቆጣጠራል። በተጨማሪም እነዚህ ወንዶች የፈጸሙት ጥቃት በተጓዳኞቻቸው ላይ ላደረሰው የስሜት ጉዳት ኃላፊነት ለመውሰድ እምቢተኞች ናቸው።”
ካገባች 15 ዓመት የሆናት ያሱኮa የተባለች ደቃቃ ሰውነት ያላት ጃፓናዊት ሴት ለንቁ! መጽሔት እንዲህ በማለት የቤተሰብዋን ተሞክሮ ተናግራለች:- “አባቴ ሁልጊዜ እናቴን ይደበድባትና ግፍ ይፈጽምባት ነበር። በእርግጫ ይመታት፣ ይገፈትራት፣ ፀጉሯን ጨምድዶ ይጎትታትና ድንጋይ ሳይቀር ይወረውርባት ነበር። ይህን ሁሉ የሚፈጽምባት ለምን ነበር? ከሌላ ሴት ጋር ማመንዘሩን ለመቃወም በመድፈርዋ ነበር። በጃፓናውያን ባሕል አንዳንድ ወንዶች ቅምጥ ቢኖራቸው እንደ ነውር አይታይም ነበር። እናቴ ግን ትኖርበት ከነበረው ዘመን የመጠቀ አስተሳሰብ ስለነበራት የባልዋን ምንዝር ለመቀበል ፈቃደኛ አልሆነችም። ከ16 ዓመት የጋብቻ ዘመንና አራት ልጆች ከወለደች በኋላ ፈታችው። አባቴ ለልጆቹ ማሳደጊያ ምንም ዓይነት እርዳታ አይሰጣትም ነበር።”
የሚስቶች መደብደብ ለአቤቱታ ሰሚ ባለ ሥልጣናት በሚቀርብበት ጊዜም እንኳን ቢሆን አቤቱታ መቅረቡ ለበቀል የተነሳሱ ባሎችን ሚስቶቻቸውን ከመግደል አላገዳቸውም። እንደ ዩናይትድ ስቴትስ ባሉት አገሮች በብዙ አጋጣሚዎች ሕጉ የተዛተባትንና ጥቃት የተቃጣባትን የትዳር ጓደኛ ለመከላከል ሳይችል ቀርቷል። “አንድ ጥናት እንዳመለከተው ሚስቶች በባሎቻቸው በተገደሉባቸው ሁኔታዎች ከግማሽ የሚበልጡት ግድያዎች ሲፈጸሙ ከግድያው በፊት በነበረው ዓመት ውስጥ ፖሊሶች በቤት ውስጥ የተፈጠረውን ጠብ እንዲመረምሩ አምስት ጊዜ ያህል ተጠርተው ነበር።” (የምክር ቤቱ ሪፖርት) በአንዳንድ ያልተለመዱ ሁኔታዎች ሚስቶች ራሳቸውን ከሌላ ተጨማሪ ጥቃት ለማዳን ሲሉ ባሎቻቸውን ገድለዋል።
አብዛኛውን ጊዜ ሴቶች ተጠቂ የሚሆኑባቸው የቤት ውስጥ ጠቦች በተለያዩ ዓይነት መልኮች ሊገለጹ ይችላሉ። በሕንድ አገር በጥሎሽ ምክንያት (ባሎች የሚስታቸው ቤተሰቦች በከፈሉት ጥሎሽ ባለመርካታቸው ምክንያት በባሎቻቸው የሚገደሉ ሴቶች) የሚሞቱ ሴቶች ብዛት በ1988 ከነበረው 2,209 ተነስቶ በ1990 ወደ 4,835 አሻቅቧል። ይሁን እንጂ ከሚስቶች ሞት ብዙዎቹ አብዛኛውን ጊዜ ለማገዶ በሚያገለግል ጋዝ በመቃጠል የተፈጸመ የቤት ውስጥ አደጋ ነው ተብሎ ስለሚታለፉ ይህን ቁጥር የተሟላ ወይም ትክክል ነው ማለት አይቻልም። በቤታቸው ውስጥ የሚደርስባቸውን መከራ መቋቋም አቅቷቸው ራሳቸውን የሚገድሉ ሚስቶች ቁጥርም ከዚህ ላይ የሚጨመር ነው።
ወንድ ወይም ሴት ልጅ በሚመረጥበት ጊዜ
ሴቶች ከተወለዱበት ጊዜ ጀምሮ፣ እንዲያውም ከመወለዳቸው በፊት ጀምሮ አድልዎ ይፈጸምባቸዋል። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? ንቁ! መጽሔት በሕንድ አገር በቦምቤ ለምትኖረው ለማዱ ይህን ጥያቄ አቅርቦ የሰጠችው መልስ የሚከተለው ነበር:- “በአንድ የሕንድ ቤተሰብ ውስጥ ወንድ ልጅ ሲወለድ ትልቅ ደስታ ይሆናል። የእናትዬዋ ጭንቀት ያበቃል። ወላጆቹ በሚያረጁበት ጊዜ የሚጦራቸው ወንድ ልጅ አግኝተዋል። ‘ማኅበራዊ ዋስትናቸው’ ተረጋገጠላቸው ማለት ነው። እናትዬዋ ሴት ልጅ ብትወልድ ግን ድካምዋ ሁሉ ብላሽ እንደሆነ ይቆጠራል። ሌላ ተጨማሪ ሸክም እንዳመጣች ይታሰባል። ወላጆቹ ይህችን ሴት ልጃቸውን ለመዳር ከፍተኛ ጥሎሽ ለመክፈል ሊገደዱ ነው። እናቲቱ ደጋግማ ሴት ልጅ የምትወልድ ከሆነ ከፍተኛ ኪሣራ እንዳስከተለች ይቆጠራል።”b
ኢንዲያን ኤክስፕሬስ የተባለው ጋዜጣ ስለ ሕንዳውያን ልጃገረዶች “ሕልውናቸው ለቤተሰባቸው ሕልውና አስፈላጊ እንደሆነ ተደርጎ አይቆጠርም” ብሏል። ይኸው ጋዜጣ በቦምቤ በተደረገ ጥናት “ጾታቸውን ለመለየት ምርመራ ከተደረገላቸው በኋላ እንዲገደሉ ከተደረጉት 8,000 የሚያክሉ ጽንሶች መካከል 7,999 የሚሆኑት ሴቶች መሆናቸው” እንደተረጋገጠ ገልጿል።
ኤልዛቤት ቡሚለር እንደሚከተለው በማለት ጽፈዋል:- “አንዳንድ የሕንድ ሴቶች የሚኖሩበት ሁኔታ በጣም ጎስቋላ በመሆኑ የሚደርስባቸው መከራ በሌሎች የዓለም ክፍሎች የሚኖሩ አናሳ ጎሣዎችና ብሔሮች ያገኙትን ትኩረት ያህል ቢያገኝ ኖሮ ችግራቸው የሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎችን ድጋፍ ያገኝ ነበር።”— ሜይ ዩ ቢ ዘ ማዘር ኦቭ ኤ ሃንድረድ ሳንስ
“የሴት ሥራ ማለቂያ የለውም”
“የሴት ሥራ ማለቂያ የለውም” የሚለው አባባል የአነጋገር ፈሊጥ ብቻ እንደሆነ ተደርጎ ሊታይ ይችላል። ይሁን እንጂ ወንዶች ብዙዉን ጊዜ ችላ የሚሉትን እውነታ የሚገልጽ አነጋገር ነው። አንዲት የልጆች እናት የሆነች ሴት እንደ ብዙዎቹ ወንዶች ከሦስት ሰዓት እስከ አሥራ አንድ ሰዓት የሚቆይ የተወሰነ የሥራ ሰዓት የላትም። ሌሊት ሕፃን ልጅ ቢያለቅስ አብዛኛውን ጊዜ ተነስቶ የሚያባብለው ማን ነው? ቤት የሚያጸዳው፣ ልብስ የሚያጥበውና የሚተኩሰው ማን ነው? ባል ከሥራ ሲመለስ ምግብ አዘጋጅቶ የሚያቀራርበው ማን ነው? ምግቡ ተበልቶ ካለቀ በኋላ ዕቃዎቹን የሚያጣጥበውና ልጆቹን አዘጋጅቶ የሚያስተኛው ማን ነው? በብዙ አገሮች ደግሞ ከእነዚህ ሥራዎች ሁሉ በተጨማሪ ውኃ መቅዳትና ልጅዋን ጀርባዋ ላይ አዝላ በእርሻ ቦታ ስትሠራ መዋል የሚኖርባት ማን ነች? አብዛኛውን ጊዜ እናት ነች። የሥራ ሰዓትዋ በቀን ውስጥ 8 ወይም 9 ሰዓት ሳይሆን ብዙ ጊዜ ከ12 እስከ 14 ሰዓት ወይም ከዚያ በላይ ነው። ይሁን እንጂ ለዚህ ሁሉ የትርፍ ሰዓት ክፍያ አይታሰብላትም፣ አብዛኛውን ጊዜ የምስጋና ቃል እንኳን አታገኝም!
ወርልድ ሄልዝ መጽሔት እንደገለጸው በኢትዮጵያ ብዙ “ሴቶች በቀን ከ16 እስከ 18 ሰዓት እንዲሠሩ ይጠበቅባቸዋል። የገቢያቸው መጠን በጣም አነስተኛ በመሆኑ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ማኖር አስቸጋሪ ይሆንባቸዋል። . . . ለእነርሱ ረሃብ ዕለታዊ ክስተት ነው። አብዛኛውን ጊዜ [የማገዶ እንጨት ለቃሚዎቹና ተሸካሚዎቹ ሴቶች] በቀን የሚያገኙት አንድ ያልተሟላ ምግብ ሲሆን ከቤታቸው የሚወጡት አለምንም ቁርስ ባዶ አፋቸውን ነው።”
የሆንግ ኮንግ ተወላጅ የነበረችውና አሁን ካገባች 20 ዓመት የሆናት ሴት እንዲህ ትላለች:- “በቻይናውያን የአኗኗር ልማድ ወንዶች ሴቶችን አሳንሰው የመመልከት ዝንባሌ አላቸው። ሴቶችን የሚመለከቱት በቤት ውስጥ ሥራ እንዲረዱ ወይም ልጆች እንዲወልዱ ብቻ እንደተፈጠሩ አድርገው፣ እንዲያውም በአንዳንድ ሁኔታዎች እንደ ጣዖት፣ እንደ አሻንጉሊት ወይም እንደ ወሲባዊ ስሜት ማርኪያ ዕቃ አድርገው ነው። እኛ ሴቶች ግን የምንፈልገው የማሰብ ችሎታ እንዳለን ፍጡራን ተደርገን እንድንታይ ነው። ወንዶች ምንም እንደማናውቅ አሻንጉሊቶች እንዲመለከቱን ሳይሆን በምንናገርበት ጊዜ እንዲያዳምጡን እንፈልጋለን!”
ሜን ኤንድ ዉሜን የተባለው መጽሐፍ እንደሚከተለው ማለቱ አያስደንቅም:- “በየትም ቦታ፣ ለሴቶች ከፍተኛ ግምት ቢሰጥም እንኳን ለሴቶች የሥራ ክንውን የሚሰጠው ዋጋ ከወንዶች ያነሰ ነው። በዚህ ረገድ ማኀበረሰቡ ለወንዶችና ለሴቶች የሚመድባቸው የሥራ ዓይነቶችና የተግባር ድርሻዎች ልዩነት አያመጡም። ወንዶች የሚሠሯቸው ሥራዎች በማኅበረሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ዋጋ ማግኘታቸው አይቀርም።”
ሴቶች በቤት ውስጥ ለሚፈጽሟቸው ተግባሮች ምንም ዓይነት ዋጋ የማይሰጥ መሆኑን መካድ አይቻልም። በዚህ ምክንያት ዘ ወርልድስ ዉሜን—1970–1990 የተባለው ጽሑፍ መቅድም እንዲህ ይላል:- “የሴቶች የኑሮ ሁኔታም ሆነ ለቤተሰብ፣ ለጠቅላላው ምጣኔ ሀብትና ለቤታቸው የሚያበረክቱት አስተዋጽዖ በጉልህ የማይታይ ሆኖ ቆይቷል። አብዛኞቹ የስታትስቲክስ መረጃዎች የሚዘጋጁት የወንዶችን እንጂ የሴቶችን የኑሮ ሁኔታና አስተዋጽዖ እንዲያንጸባርቁ ተደርገው አይደለም። አብዛኛውን ጊዜ በሁለቱ ጾታዎች መካከል ያለውን ልዩነት ችላ ብለው ያልፋሉ። . . . ሴቶች ከሚያከናውኗቸው ሥራዎች ብዙዎቹ አሁንም የሚታዩት ምንም ዓይነት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንደሌላቸው ተደርገው ነው። ጭራሹንም ግምት ውስጥ አይገቡም።”
በ1934 የሰሜን አሜሪካው ዠራልድ ደብልዩ ጆንሰን የተባሉ ደራሲ፣ ሴቶች በሥራ ቦታቸው ስለሚያጋጥሟቸው ሁኔታዎች ያላቸውን አስተያየት እንዲህ በማለት ጽፈው ነበር:- “የወንዶች ሥራ ለሴቶች የሚሰጥባቸው ጊዜያት ብዙ ቢሆኑም የወንዶችን ደመወዝ የሚያገኙበት አጋጣሚ ግን በጣም ጥቂት ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ማንም ወንድ ቢሆን ከአንዲት ሴት በተሻለ ሁኔታ ሊሠራ የማይችለው ሥራ ይኖራል ተብሎ ስለማይታሰብ ነው። በጣም እውቅ የሆኑ የወይዛዝርት ልብስ ሰፊዎችና ባርኔጣ ሠሪዎች ወንዶች ናቸው። . . . ምን ጊዜም ታላላቆቹ ወጥ ቤቶች ወንዶች ናቸው። . . . ማንኛውም አሠሪ ማንኛውንም ሥራ ወንዱ ከሴትዋ አስበልጦ እንደሚሠራ ስለሚያምን ለሴትዋ ከሚከፍላት የበለጠ ገንዘብ ለወንዱ ለመክፈል ፈቃደኛ መሆኑ ሊታበል የማይችል ሐቅ ነው።” ይህ አስተያየት ከመጠን በላይ የተጋነነ ሊሆን ቢችልም በዘመኑ የነበረውንና አሁንም ቢሆን ከብዙ ወንዶች አእምሮ ያልወጣውን የተዛባ አመለካከት ያንጸባርቃል።
ሴቶችን አለማክበር በመላው ዓለም የተስፋፋ ችግር ነው
እያንዳንዱ ባሕል ሴቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ሊኖራቸው ስለሚገባው ድርሻ የየራሱን አመለካከት፣ የተዛባ አስተያየትና ምክንያት የለሽ ጥላቻ አዳብሯል። ይሁን እንጂ መልስ ማግኘት የሚኖርበት ጥያቄ እነዚህ አመለካከቶች ለሴቶች ክብር ተገቢውን ግምት ይሰጣሉ? ወይስ ባለፉት መቶ ዘመናት አብዛኛውን ጊዜ ወንዶች ባላቸው የጉልበት ብልጫ ምክንያት ተንሰራፍቶ የኖረውን የወንድ የበላይነት ያንጸባርቃሉ? የሚለው ነው። ሴቶች እንደ ባሪያ ወይም መበዝበዝ እንዳለባቸው ፍጥረቶች የሚታዩ ከሆነ ተገቢ ክብር ተሰጥቷቸዋል ሊባል ይችላልን? አብዛኞቹ ባሕሎች መጠኑ ይነስ ይብዛ እንጂ ሴቶች በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን የሥራ ድርሻ ማቃለላቸውና ሰብዓዊ ክብራቸውን መዳፈራቸው አልቀረም።
የሚከተለው ከአፍሪካ የተገኘ ምሳሌ በመላው ዓለም ላይ በሴቶች ላይ ለሚደርሰው ውርደት አንድ ምሳሌ ይሆነናል። “የዮሩባ ሴቶች [ናይጄሪያ] በባሎቻቸው ፊት ምንም እንደማያውቁ መስለው መታየትና ዝም ማለት አለባቸው። ምግብ በሚያቀርቡበት ጊዜም በባሎቻቸው እግር ሥር እንዲንበረከኩ ይጠበቅባቸዋል።” (ሜን ኤንድ ዉሜን) በሌሎች የዓለም ክፍሎችም ይህ ሴቶች የሚሰጣቸው የሎሌነት ደረጃ በተለያዩ መንገዶች ሊገለጥ ይችላል። ሚስት ከባልዋ ኋላ በተወሰነ ርቀት ተከትላ እንድትሄድ፣ ወይም ወንዱ ባዶ እጁን ሆኖ ሴትዋ ሸክም ተሸክማ እንድትሄድ፣ ወይም ባልዬው ፈረስ ወይም በቅሎ ላይ ተቀምጦ እርስዋ በእግርዋ እንድትጓዝ፣ ወይም ብቻዋን እንድትበላ ይደረጋል።
በጃፓን አገር ተወልደው ያደጉት ኤድዊን ራይሻወር ዘ ጃፓኒዝ በተባለው መጽሐፋቸው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በጃፓን አገር የወንዶችን ትምክህተኝነት የሚያሳዩ ዝንባሌዎች በገሐድ ይታያሉ። . . . አሁንም በዝሙት ረገድ ወንዱ እንዳሻው ለመሆን የሚችልበትና የሴትዋ ነጻነት ግን በጣም የተገደበበት ሁኔታ በጣም የተስፋፋ ነው። . . . ከዚህም በላይ ያገቡ ሴቶች በጋብቻቸው ላይ እንዳይወሰልቱ ከወንዶች ይበልጥ ይጠበቅባቸዋል።”
በተጨማሪም በጃፓን አገር እንደ ብዙዎቹ አገሮች፣ በተለይ በሰዎች በተጨናነቁ በምድር ውስጥ ለውስጥ በተሠሩ መንገዶች የሚሄዱ ሴቶችን በፍትወት ስሜት መዳፈር በጣም የተስፋፋ ችግር ሆኗል። ከቶኪዮ ወጣ ብሎ በሚገኘው የሂኖ ከተማ የምትኖረው ያሱኮ ለንቁ! መጽሔት እንዲህ ብላለች:- “ወጣት ሴት በነበርኩበት ጊዜ በየቀኑ ወደ ቶኪዮ እመላለስ ነበር። በዚህ ጊዜ አንዳንድ ወንዶች ስለሚቆናጠጡና መላ አካላቴን ስለሚደባብሱ በጣም ያሳፍረኝ ነበር። እኛ ሴቶች ችለን ከማሳለፍ በስተቀር ምንም ማድረግ አንችልም። ይሁን እንጂ በጣም የሚያሳፍር ድርጊት ነው። ጥድፊያ በሚበዛባቸው የማለዳ ሰዓቶች ሴቶች እንዲህ ካለው አዋራጅ ድርጊት እንዲድኑ የሚጓጓዙበት የተለዩ ተሽከርካሪዎች ይመደባሉ።”
ቀድሞ ጃፓን ትኖር የነበረችው ሱ የተባለች ሴት ራስዋን እንዲህ ካለው የወንዶች ድፍረት የምትከላከልበት መንገድ ነበራት። ጮክ ብላ “ፉዛኬናይ ደ ኩዳሳይ! ” ትላለች። “አትነካካኝ!” ማለት ነው። “ይህ ጩኸቴ አፋጣኝ ትኩረትና ውጤት ያስገኝልኝ ነበር። ማንም ሰው በሌሎች ፊት ለመዋረድ አይፈልግም። ማንም ሰው ሳይነካኝ አልፋለሁ!” ብላለች።
ሴቶች በቤተሰብ ክልል ውስጥ የሚገባቸውን ክብር አለማግኘታቸው በመላው ዓለም የተስፋፋ ችግር እንደሆነ ግልጽ ነው። ሴቶች በሥራ ቦታቸው የሚሰጣቸው የሥራ ድርሻስ? በሥራ ቦታቸው ከቤታቸው የበለጠ አክብሮትና ተቀባይነት ያገኛሉን?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው ሰዎች ስማቸው እንዳይገለጥ ጠይቀዋል። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የተጠቀሱት ስሞች በሙሉ ተለዋጭ ስሞች ናቸው።
b ባሎች አብዛኛውን ጊዜ ሴት ልጅ በመወለዱ ጥፋተኛ የሚያደርጉት ሴቶችን ነው። የዘር ውርሻ ሕግ ወደ አእምሯቸው አይመጣላቸውም። (በዚህ ገጽ ላይ ያለውን ሣጥን ተመልከት።)
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መኖሪያ ቤት ቢኖራቸውም እንኳ የቧንቧ ውኃ፣ የቆሻሻ ማስወገጃ ወይም ኤሌክትሪክ የላቸውም