የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g93 4/8 ገጽ 4-8
  • የሞትን ሸክም ማቃለል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የሞትን ሸክም ማቃለል
  • ንቁ!—1993
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • እንዲደረግልህ የምትፈልገውን ነገር አስቀድመህ አስታውቅ
  • በሞት ሳቢያ የሚካሄደውን ንግድ መቋቋም
  • ሐዘንን መቆጣጠር
  • የክርስቲያኖች የቀብር ሥነ ሥርዓት​—ክብር ያለው፣ መጠነኛና አምላክን የሚያስደስት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2009
  • አንድ ክርስቲያን ከቀብር ሥነ ሥርዓት ጋር ለተያያዙ ልማዶች የሚኖረው አመለካከት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • የይሖዋ ምሥክሮች ስለ ቀብር ሥነ ሥርዓት ምን አመለካከት አላቸው?
    ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ብዙ ጊዜ የሚነሱ ጥያቄዎች
  • ሌሎች መርዳት የሚችሉት እንዴት ነው?
    የምትወዱት ሰው ሲሞት
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1993
g93 4/8 ገጽ 4-8

የሞትን ሸክም ማቃለል

የቀብር ወጎችና ልማዶች ከአገር ወደ አገር ከባሕል ወደ ባሕል በጣም ይለያያሉ። መንግሥት የሚያወጣቸው መመሪያዎች በቀብር ሥርዓት ወቅት ሊጠበቁ የሚገባቸውን ደንቦች ሊደነግጉ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ ትልቅ ሚና የሚጫወተው የቤተሰቡና የማኅበረሰቡ ሃይማኖታዊ እምነት ነው። “በሞት ጊዜ በሚከናወኑ ሥነ ሥርዓቶችና ወጎች ላይ የተደረገው ጥናት በሃይማኖታዊ እምነትና አንድ ሰው ሲሞት በሚደረገው የአካባቢ ልማድ መካከል ያለውን ዝምድና ጎላ አድርጎ ያሳያል” በማለት ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ገልጿል።

በሕንድ ውስጥ የሚከናወነውን የሂንዱ የቀብር ሥርዓት ተመልከት። አንድ የሃይማኖት ቡድን ሥርዓት በሚያዘው መሠረት አካሉ በእሳት ለመቃጠል ይዘጋጃል። ከጋንጀስ ወንዝ ቢመጣ የሚመረጥ “ፀበል” በወለሉ ላይ ይርከፈከፋል። ከዚያም አንድ ነጭ አንሶላ ይነጠፍና አስከሬኑ እዚያ ላይ እንዲያርፍ ይደረጋል። ንጹሕ መናፍስትን ወደ አካባቢው ይጠራል ተብሎ ስለሚታመን ጥሩ መዓዛ ያለው ዕጣን ይጤሳል። ፊቱን ከሰንደል እንጨት የተዘጋጀ የሚያጣብቅ ሙቅና ቀይ ዱቄት ይቀቡታል። አስከሬኑ ይታጠብና በነጭ ልብስ ይሸፈናል፤ ከዚያም አበባዎች ጣል ጣል ይደረግበታል። ከዚህ በኋላ አስከሬኑ ፊት ለፊት እንዲታይ ተደርጎ ከሸምበቆ በተሠራ ቃሬዛ ላይ ይደረግና ወደሚቃጠልበት ጋት (ወደ ሚቃጠልበት ሥፍራ) ይወሰዳል። እዚያ ሲደርስ እግሩ በማቃጠያው ጋት ፊት ለፊት እንዲሆን ቃሬዛውን ያዞሩታል። ይህም የወደፊቱን ሕይወት አሻግሮ እያየ መሆኑን እንዲያመለክት ተብሎ የሚደረግ ነው። አስከሬኑን ለማቃጠል የተከመረውን እንጨት የሚለኩሰው የመጀመሪያው ልጅ ነው፤ ይህ የሚደረገው የሟቹ “ነፍስ” ሰላም ማግኘት የምትችለው ይህ ከሆነ ብቻ ነው ተብሎ ስለሚታመን ነው። ከዚያ በኋላ አመዱ ይሰበሰብና ከሕንድ “ቅዱስ” ወንዞች በአንዱ ውስጥ እንዲጨመር ይደረጋል።

በፓፑዋ ኒው ጊኒ ዘመዶች አስከሬኑን በመሳም፣ እላዩ ላይ ሆኖ በማልቀስ፣ ቃል እንዲገባላቸው በመጠየቅና በሞተው ሰው ላይ የፈጸሙትን በደል ይቅር እንዲላቸው በመጠየቅ ሬሳው ላይ መንከባለላቸው የተለመደ ነው። ምርር ያለ ለቅሶ ይለቀሳል፤ አልቃሾቹ የሚያወጡት ሙሾ ደግሞ ሐዘኑን ይበልጥ ያባብሰዋል። አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ለሞተው ሰው “መንፈስ” አክብሮት ለመግለጽና ይኸው መንፈስ ሊያመጣ የሚችለውን ማንኛውንም የበቀል እርምጃ ለማስወገድ ቢያንስ ቢያንስ ሁለት ትላልቅ ድግሶች መደገሳቸው የተለመደ ነገር ነው።

ነፍስ አትሞትም የሚለው እምነት በአፍሪካ የቀብር ሥርዓት ልማዶችና ባሕሎች ውስጥ በጣም ጎልቶ ይታያል። የሞቱት ሰዎች በቤተ ዘመዶቻቸው ላይ ጉዳት እንዳያመጡ በመስጋት የሞቱትን ሰዎች ማስደሰት ያስፈልጋል በማለት ብዙ ነገር ያደርጋሉ። የሞተው ሰው በሕይወት ላሉት ሰዎች ሞገሱን ያሳያቸዋል ብለው ተስፋ በማድረግ ብዙ ገንዘብ ያፈስሳሉ፤ ብዙ መሥዋዕቶችንም ያቀርባሉ። ብዙዎች አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ሌላ ፍጡር ሆኖ እንደገና ይመጣል ብለው ያምናሉ፤ የሞተው ሰው የአምልኮ ክብር ለማግኘት እንስሳ ሆኖ ይመጣል፤ አለዚያም ደግሞ በአንድ በጸነሰች ሴት አማካኝነት ተወልዶ የሌላ ቤተሰብ አባል ይሆናል የሚል እምነት አላቸው። “በመሆኑም” ይላል አንድ ከናይጄሪያ የመጣ ሪፖርት “አንድን አስከሬን በሚያለብሱበት ጊዜ ሁሉም ነገር ትክክለኛ ቅርጹን የያዘ መሆኑን ለማረጋገጥ ልዩ ጥንቃቄ ይደረጋል። ለምሳሌ ያህል የሞተው ሰው በሬሳ ሳጥን ውስጥ ሲገባ እጁ ቀጥ ካላለ ሰውየው እንደገና ሲወለድ አካለ ጎዶሎ ሆኖ እንደሚወለድ ያሳያል ተብሎ ይታመናል። ወይም የሞተው ሰው በትክክል ካልለበሰ እንደገና ሲወለድ እብድ ይሆናል ብለው ያምናሉ።” የሞቱ ሰዎችን መፍራትና እነዚህ ሙታን ሕያዋንን ይቆጣጠራሉ የሚለው እምነት ብዙውን ጊዜ በአፍሪካውያን የቀብር ሥርዓቶች ላይ ትልቅ ሚና ይጫወታሉ።

በብዙዎቹ የግሪክ ገጠር ክፍሎች ውስጥ አንድ ሰው ከሞተ በኋላ ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆዩና ብዙ ዓይነት ሥነ–ሥርዓቶችን ያቀፉ የቀብር ሥርዓቶች ይካሄዳሉ። “ከዚያ ቀጥሎ ባሉት አምስት ዓመታት የሟቹ ሴት ዘመዶች ብዙ የሙት ዓመት አገልግሎቶችን ያከናውናሉ” በማለት ሳይንስ የተባለው መጽሔት ይገልጻል። “በሚስቶች፣ በእናቶችና በሴት ልጆች ዘንድ ለቅሶ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ነው። ሻማዎችን ለማብራት፣ የመቃብሩን ድንጋይ ለማጽዳት፣ ከሞተው ሰው ጋር ለመነጋገር፣ የሐዘን እንጉርጉሮ ለማንጎራጎርና ለማልቀስ በየዕለቱ ሌሊት ሌሊት ወደ መቃብሩ ቦታ ይሄዳሉ። እነዚህን ሥርዓቶች ሳያዛንፉ በትክክል መፈጸማቸው የሚያፈቅሩትን ሰው ነፍስ በሰማይ ይረዳል ብለው ያምናሉ።” በመጨረሻም የሟቹን አጥንቶች ቆፍረው ያወጡና በአንድ መንደር ውስጥ በሚገኝ የመቃብር ቤት ውስጥ ያስቀምጡታል።

በጃፓን ውስጥ የሚከናወኑ ብዙ የቀብር ሥርዓቶች የቡድሂስት ሃይማኖታዊ ሥነ–ሥርዓቶችን የተከተሉ ናቸው። አስከሬኑ ከታጠበና ልብስ ከለበሰ በኋላ በነጭ አንሶላ ይሸፈናል፤ ከዚያም ክፉ መናፍስትን ለመከላከል ቢላዋ ደረቱ ላይ ይደረጋል። ሻማዎች በሚበሩበትና ዕጣን በሚጤስበት ጊዜ አንድ ቄስ አልጋው አጠገብ ሆኖ ሱትራዎችን (እንደ ቅዱስ መጽሐፍ ተደርጎ በሚቆጠረው የቡድሂስት ጽሑፍ ላይ፤ የሚገኙ ምንባቦችን) ይደግማል። ለሟቹ ደግሞ ከመሞቱ በፊት ካከናወናቸው ሥራዎች ጋር የተያያዘ የቡድሂስት ስም ያወጣለታል፤ ባወጣው ስም ፊደላት ብዛት የሚወሰን ከፍተኛ ገንዘብም ይከፈለዋል። ከዚህ በኋላ አስከሬኑ ከእንጨት በተሠራና ቀለም ባልተቀባ የሬሳ ሳጥን ውስጥ ይገባል። ሙሉ ሌሊት ወይም ግማሽ ሌሊት ለሞተው ሰው ያለቅሳሉ፤ ነፍሱም እረፍት እንድታገኝ ይጸልያሉ። ቄሱ ሱትራዎችን በሚደግምበት ጊዜ አልቃሾች በየተራ እየገቡ በጣታቸው የቆነጠሩትን ዕጣን ያጤሳሉ። በሚቀጥለው ቀን በሚደረገው የቀብር ሥርዓት ላይም የሬሳ ሳጥኑ፣ የሟቹ ፎቶና ሌሎች የቡድሂስት ሃይማኖታዊ ሥነ–ሥርዓት መገልገያዎች በተቀመጡበት መሠዊያ ፊት ተመሳሳይ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች ይካሄዳሉ። ቀጥሎም ሕጉ በሚጠይቀው መሠረት ሬሳው ይቃጠላል። ከዚያ በኋላ ነፍሱ በሰው ላይ የምታደርሰው ተጽዕኖ አብቅቷል እንዲሁም ቀድሞ ወደነበረችበት ሁኔታ ተለውጣለች እስከሚባልበት ጊዜ ድረስ ለተወሰነ ጊዜ እየቆየ እየቆየ ዕጣን ይጤሳል፤ ቄሱም ሱትራዎችን ይደግማል።

እንዲደረግልህ የምትፈልገውን ነገር አስቀድመህ አስታውቅ

አንድ የሚያፈቅሩት ሰው ሲሞት የሚያስከትለውን ጭንቀት ከማቃለል ይልቅ እንደነዚህ ያሉ የቀብር ሥርዓት ልማዶች ብዙውን ጊዜ ተጨማሪ ሸክሞችን ያመጣሉ። ከእነዚህ ሸክሞች አንዱ ከፍተኛ ወጪ መጠየቁ ነው። ሰፊ የቀብር ሥርዓቶች በቀላል ወጪ አይሸፈኑም። አብዛኛውን ጊዜ ቄሶች ለሚሰጧቸው አገልግሎቶች ከፍተኛ ገንዘብ ይሰጠናል ወይም ይከፈለናል ብለው ይጠብቃሉ። ትላልቅ ድግሶችና የአከባበር ሥነ–ሥርዓቶችም ከፍተኛ ገንዘብ የሚፈስባቸው ናቸው። አልፎ ተርፎም ከሞተው ሰው ፍላጎት ውጪ የሆነ ነገር እንዲደረግ ወይም እርሱ የማያምንባቸው ሃይማኖታዊ ሥነ–ሥርዓቶች እንዲካሄዱ የሚገፋፋ ተጽዕኖ ሊኖር ይችላል። የቤተሰብ አባሎች ወይም ጓደኞች ሟቹ በማኅበረሰቡ ደንብ መሠረት ተገቢና ትክክለኛ የቀብር ሥርዓት አልተደረገለትም የሚል ተቃውሞ ሊያሰሙ ይችላሉ። በቀብር ሥርዓትህ ወቅት እንዲደረግልህ የምትፈልገው ነገር ካለ በጽሑፍ ማስፈርህና ሕጋዊ ሰነድ እንዲኖር ማድረግህ ጥበብ ይሆናል።

አንድ ጃፓናዊ የቤት እመቤት 85 ዓመት የሆናቸው አባቷ በሞቱባት ጊዜ ይህን ትምህርት አግኝታለች። አባቷ የቤተሰብ አባሎች ብቻ የሚገኙበት ቀላል የሆነ የቀብር ሥርዓት እንዲደረግላቸው የሚፈልጉ መሆናቸውን ገልጸው ነበር። ሆኖም ይህ ሁኔታ በኅብረተሰቡ ባህል የሚከናወነው የቀብር ሥርዓት ፕሮግራም እንዲካሄድ ይፈልጉ በነበሩት ሰዎች ብዙ ትችት አስከትሏል። ከጊዜ በኋላ የሰውየው ልጅ ቶኪዮ ውስጥ ለሚታተም አሳሂ ሺምበን ለተባለ ጋዜጣ የሚከተለውን ጽፋለች:- “አንድ ሰው ከሌሎች ለየት ያለ የቀብር ሥርዓት እንዲደረግለት ቢፈልግ ለእሱ ምክንያታዊ መስሎ ቢታየውም እንኳን ቤተሰቡ ዕለት ተዕለት በሚያደርገው የሐሳብ ልውውጥ ጉዳዩን አንስቶ ቢነጋገርበትና አንድ ስምምነት ላይ ቢደርስ የተሻለ ነው። አንድ ሰው ሊደረግለት የሚፈልገውን ነገር በጽሑፍ ላይ ማስፈሩም አስፈላጊ ነው፤ እንዲህ ከሆነ ዘመድ የሞተበት ቤተሰብ አባላት የሚመጣውን ትችት መቋቋም ይችላሉ።”

ከአካባቢው ልማድ ጋር የማይጣጣሙ ጥብቅ የሆኑ ሃይማኖታዊ እምነቶች ሲኖሩህም እንዲህ ማድረጉ ይበልጥ አስፈላጊ ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ በጃፓን የሚኖር ክርስቲያን እርሱ ከሞተ በኋላ ክርስቲያን ያልሆኑት ዘመዶቹ በቀብሩ ሥርዓት ወቅት በቡድሂስት መሰዊያ ፊት በሚቀርቡበት ጊዜ እንደሚያደርጉት አምልኮታዊ አክብሮት በመስጠት በሬሳ ሳጥኑ ፊት ወይም በፎቶው ፊት ሊደፉ ይችላሉ ብሎ ሊሰጋ ይችላል። ስለዚህ ሰዎች እቤት ከደረሱ በኋላ አስከሬኑ እንዲቃጠልና በኋላም የሬሳ ሳጥኑም ሆነ ፎቶው በሌለበት ቀለል ያለ የቀብር ሥርዓት መካሄድ እንዳለበት የሚገልጽ መመሪያ አስቀድሞ በጽሑፍ በማስፈር ጥብቅ ደንብ ሊያወጣ ይችላል። ችግሮችን ለማስወገድ አስቀድሞ ዘመዶች ቅደም ተከተሉን እንዲያውቁት መጠቆም ይቻላል።

በሞት ሳቢያ የሚካሄደውን ንግድ መቋቋም

ከአንድ መቶ ዓመታት በፊት እስከነበረው ጊዜ ድረስ አብዛኛዎቹ ሰዎች በቤተሰባቸውና በወዳጆቻቸው ተከበው እንዳሉ ይሞቱ ነበር። ሰዎች ለሞት በተቃረቡበት ወቅት በአጠገባቸው ልጆችም ይገኙ ስለነበር የሞትን ምንነት ያውቁ ነበር። በሰለጠነውና በኢንዱስትሪ የበለጸጉ አገሮችን ባቀፈው ዓለም ውስጥ ግን ይህ ሁሉ ነገር ተለውጧል። ብዙ ሰዎች ለሞት ሲቃረቡ ወዲያውኑ ወደ ሆስፒታል ይወሰዳሉ፤ ሕይወታቸውን ለማራዘምም ጥረት ይደረጋል። “ሐኪሞች ሞትን ተፈጥሯዊ የሆነ ነገር አድርገው ከማየት ይልቅ እንደ መጥፎና ባዕድ ነገር አድርገው እየተመለከቱት ነው። በሽታን ለመዋጋት በሚያደርጉት ጥረት የደረሰባቸው ሽንፈት አድርገው ይመለከቱታል። በሽታን ለማጥፋት የማይሞከር መሣሪያ የለም። ብዙውን ጊዜም ይህን ሲያደርጉ ለበሽተኛው ምንም ቦታ አይሰጡትም። አንዳንዴማ ‘ሰው’ መኖሩንም እስከናካቴው ይረሱታል” በማለት ዘ ኒው ኢንሳይክሎፒዲያ ብሪታኒካ ይገልጻል።

በአሁኑ ጊዜ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚካሄድ የቀብር ሥርዓት የመቃብሩን ቦታ ሳይጨምር ከ3,000 ዶላር በላይ ይፈጃል። አዛኝ ከሆነ የቀብር ሥርዓት ዲሬክተር ጋር በሚያደርጉት ግንኙነት ብዙ ሰዎች ሰውየው ገንዘብ ለማግኘት ሲል እየሠራ መሆኑን ይረሱታል። ቼንጂንግ ታይምስ የተባለው መጽሔት “ሬሳን ለቀብር በሚያዘጋጁት ሰዎች ዘንድ ትርፍ የማግኘቱ ሐሳብ ይበልጥ ይንጸባረቃል፤ እንዲሁም በየትኛውም የንግድ ዓለም እንደሚታየው አጭበርባሪ የሆነ ነጋዴ ገዢውን ሊያምታታው፣ ሊያጭበረብረው፣ ከዋጋ በላይ ሊያስከፍለው ወይም መልስ በሚሰጥበት ጊዜ መስጠት ከሚገባው አሳንሶ ሊሰጠው ይችላል። እንዲያውም ብዙዎቹ የሚገዙት ለመጀመሪያ ጊዜ ስለሆነ በዚህ መንገድ የመጭበርበራቸው አጋጣሚ የሰፋ ነው። ዘመድ የሞተባቸው ስለሆኑ ጉዳዩን ባፋጣኝ መፈጸም አለባቸው” በማለት ይናገራል።

ይሁን እንጂ ሌሎች አማራጮች አሉ። አንዱ መንገድ ለቀብር ሥርዓትህ የሚሆን ገንዘብ ራስህ ማስቀመጥ ነው። ይህም በሕይወት ላለ ሰው እንዲሰጥ በሚያዝ አሠራር በባንክ በማስቀመጥ ሊከናወን ይችላል። በአሜሪካ የባንክ ሕግ መሠረት በዚህ መንገድ የተቀመጠውን ገንዘብ (ቶተን ትረስት ተብሎ ይጠራል) ተቀባዩ የሟቹን መታወቂያ ወረቀትና መሞቱን የሚያረጋግጥ ማስረጃ በማሳየት ከባንክ ሊያወጣው ይችላል። እስከዚያ ድረስ ግን ገንዘቡ በአንተ ቁጥጥር ሥር ይቆያል። አስተማማኝ ከሆነና ጥሩ ስም ካለው የሕይወት መድን ኩባንያ ጋር ውል መፈራረም ሌላው አማራጭ ነው። ያገባህ ከሆንክ የትዳር ጓደኛህ ይህንን በተለይም ደግሞ ገንዘብ ነክ ጉዳዮችን ማወቋን ወይም ማወቁን አረጋግጥ(ጭ)። ኑዛዜም በጣም ጠቃሚ ነው። ሁለታችሁም በአንድ ቀን የመሞታችሁ አጋጣሚ የመነመነ ነው። በአብዛኛው ባሎች ከሚስቶቻቸው ቀድመው ይሞታሉ። ብዙውን ጊዜ ሚስቶች እነዚህን ነገሮች ሳያውቁ በመቅረታቸው ሐዘናቸውና ጭንቀታቸው ይባባሳል። ሞት ድንገት ከተፍ ሊል ስለሚችል በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ከቤተሰብህ ጋር የምታደርገውን ውይይት ነገ ዛሬ እያልክ አታዘግየው።

ሐዘንን መቆጣጠር

የሚወደውን ሰው በሞት ያጣ አንድ ግለሰብ በጣም ያዝናል። ሞቱን አምኖ እስከሚቀበለው ድረስ ምንጊዜም መጮኽና ማልቀስ ይኖራል። የሐዘኑ ርዝማኔ ከሰው ወደ ሰው ይለያያል። አንዳንዶች ብዙም ሳይቆዩ ስለሞተው ሰው ተገቢ አመለካከት በመያዝ ይስተካከላሉ፤ ሌሎቹ ግን ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ሊወስድባቸው ይችላል። ጥቂቶች ደግሞ በሐዘን እንደ ተቆራመዱ ይኖራሉ። አንድ ሰው ይህን ችግር መቋቋምን መማር የሚችለው እንዴት ነው?

ከኅብረተሰቡ ከመራቅና ራስህን ከማግለል መቆጠብህ አስፈላጊ ነው። ወደተለመደው የዕለት ተዕለት ኑሮ መመለስና ጓደኞችንና ዘመዶችን በስልክም ሆነ ቤታቸው ድረስ ሄዶ መጠየቅ ከሐዘን ለመላቀቅ በጣም አስፈላጊ ነው። ብቻህን መሆን የምትፈልግባቸው ጊዜያት ቢኖሩም ብቸኝነቱ ልማድ ሊሆንብህ አይገባም። ሰዎችን በመቅረብ እነርሱም አንተን እንዲቀርቡህ እርዳቸው።

ለረጅም ጊዜ በካንሰር ትሰቃይ የነበረችውን የ41 ዓመት ውድ ሚስቱንና እናቱን ጨምሮ አምስት የቅርብ ዘመዶቹን በሶስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ያጣ አንድ ሰው አንዳንድ ጥሩ ምክሮችን ለግሷል። “እርግጥ ማዘኔ አልቀረም። አንዳንዴም አለቅሳለሁ። ሆኖም ሕይወትን በእውነታ ላይ ተመርኩዘህ ማየት ይኖርብሃል። ሕይወትን አንተ በምትሻው መንገድ ሳይሆን ባለበት መልኩ መቀበል አለብህ። ሁልጊዜ በሐዘን ከመዋጥ ይልቅ መከራውን መልመድና የሞትን መኖር መቀበል ያስፈልግሃል” በማለት ሐሳብ ሰጥቷል።

ላዘኑ ሰዎች እርዳታና ማበረታቻ መስጠት አስፈላጊ ነው። ብዙዎቻችን ግን ለዚህ አልታደልንም። ይህን ለማድረግ ብቃት እንደሌለን ሆኖ ይሰማናል፤ የምንለውም ይጠፋናል። አልፎ ተርፎም የሐዘን ስሜት ሲያሳዩ እናፍር ይሆናል። ስለዚህ ያዘነው ሰው የእኛን ማጽናኛ ይበልጥ በሚፈልግበት ወቅት ጥለነው የመሄድ ዝንባሌ እናሳያለን። አንዳንዶች ዘመድ ከሞተበት ሰው ጋር እያወሩ ላለመሄድ መንገድ አቋርጠው በሌላ መንገድ ይሄዳሉ ተብለው ይወቀሳሉ። አንድ ባሏ የሞተባት ሴት “ብቻዬን በሐዘን ተቆራምጃለሁ። ከሌሎች ጋር ለመነጋገር ብጓጓም የሚያዳምጠኝ አንድም ሰው የለም” ስትል ተናግራለች።

አንድ ሰው በሚሞትበት ጊዜ ነገሩን በጥሞና ሳያስቡበት በችኮላ እርዳታ የሚያደርጉ ሰዎች ደግሞ ብዙውን ጊዜ የሚያደርጉትን እርዳታ ወዲያውኑ ያቋርጣሉ። “አንድ ሰው ከሞተ በኋላ አንዳንድ ጊዜ ዘመድ የሞተበት ሰው መጀመሪያ ላይ የተሰማውን ድንጋጤ ለመቆጣጠር ሳምንታት ወይም ወራት ሊወስድበት ይችላል። ከምንጊዜውም ይበልጥ ድጋፍ የሚያሻበትና ድጋፉ በጥቂቱ የሚገኝበት ወቅት ያ ወቅት ነው” ሲሉ የአእምሮ ሕክምና ጠበብት የሆኑት ፕሮፌሰር ፓትሪካ ሚኔስ ተናግረዋል። ጥልቅ የሆነ ሐዘን የማያሳዩ ሰዎች ደንታ ቢስና ፍቅር የሌላቸው ስለሆኑ ሰው የሞተባቸው አይመስሉም ወይም የደረሰባቸውን ሐዘን ተቋቁመውታል ብሎ መደምደምም ስህተት ነው። አንዳንዶች ሐዘናቸውን ለመቋቋም የሚያስችል የተሻለ ውስጣዊ ጥንካሬ ሊኖራቸው ይችላል፤ እነርሱም ቢሆኑ ግን ማጽናኛና እርዳታ ያስፈልጋቸዋል።

ወዳጆቹ አንዳንድ ጉዳዮችን በማስፈጸምና አስፈላጊ የሆኑ ሰነዶችን ተሯሩጦ ለማግኘት ዘመድ የሞተበትን ሰው በመርዳት ሲደክሙ ማየት ምንኛ ያስደስታል! የቀብር ዝግጅቶች በሚደረጉበት ጊዜ የማያቋርጥ እርዳታና ድጋፍ እንዲሁም አሳቢነት ማግኘት ምንኛ የሚያጽናና ነው! አንድ ሰው የሟቹን ልጆች ሲረዳና ለቅሶ ለመድረስ ለሚመጡት ዘመዶችና ወዳጆች የሚያስፈልጋቸውን ነገር ሲያደርግላቸው ማየቱ ምንኛ የሚያስደስት ነው! ወዳጆችና ጎረቤቶች በየዕለቱ ምግብ ማምጣታቸውና መሠራት ያለባቸውን ሥራዎች ለመሥራት ወይም ያዘኑትን ሰዎች ወደሚፈልጉበት ቦታ ለመውሰድ ፈቃደኛ መሆናቸው እንዴት ያለ አሳቢነት ነው! ያዘኑት ሰዎች የሚሰማቸውን ነገር የሚያወያያቸው ማግኘታቸው እንዴት የሚያስደስት ነው! የሚያበረታቱ ቃላትን መስማትና አይዞህ ባይ ማግኘቱ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ወራት ካለፉም በኋላ እንኳን ሐዘን የደረሰባቸው ሰዎች እንዴት እንደሆኑ መጠየቅና ፍቅርን የሚገልጹ ቃላትን መሰንዘር እንዴት ጥሩ ነው!

ይሁን እንጂ ከሁሉም በላይ የሚረዳው ተስፋ ማግኘት ነው። እንደዚህ ዓይነት ተስፋ ይኖር ይሆን?

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

“ሕይወትን አንተ በምትሻው መንገድ ሳይሆን ባለበት መልኩ መቀበል አለብህ”

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]

ለልጆቻችን ምን ብለን እንንገራቸው?

የመረዳት ችሎታቸው የሚፈቅድላቸውን ያህል እውነቱን ንገሯቸው። ስለሞትና ስለአሟሟት በመጠኑ ግለጹላቸው፤ ግራ የሚያጋቡ ቃላትን አትጠቀሙ። “አያትህ ሄዷል” ወይም “አያትህን አጣነው” ብትሉት ልጁ አያቱ ተመልሶ እንደሚመጣ ወይም አያቱን “እንደሚያገኝ” አድርጎ ሊጠብቅ ይችላል። ልጁ ሞት ማለት ምን ማለት እንደሆነ በትክክል እንዲገባው እርዱት፤ የሚያቀርባቸውንም ጥያቄዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ በማቅረብ መልሱለት። አንድ ልጅ ሞት ምን ማለት እንደሆነ እንዲገባው ለመርዳት ተፈጥሮን መጠቀም ይቻላል። የእንስሳትን፣ የአዕዋፍን ወይም የጥቃቅን ነፍሳትን ሞት በመጥቀስ ልታስረዱት ትችላላችሁ። ታጋሾች ሁኑ፤ ልጁ ከቴሌቪዥን ወይም ከፊልሞች የቀሰማቸው የተሳሳቱ ትምህርቶች ካሉ ስህተቱን አርማችሁ ትክክለኛውን ነገር አስጨብጡት። ለልጆች ስለሞት አንዳችም ነገር አለመንገር በማያወቁት ነገር ላይ የቁጣ ስሜት እንዲያድርባቸው ወይም ፍርሃት እንዲሰማቸው ሊያደርግ ይችላል።

አንድ ልጅ በተለይ በሞተው ሰው ላይ ቅሬታ የነበረው ከሆነ ለሞቱ ተጠያቂው እሱ እንደሆነ ሊሰማው ይችላል። የተሰማውን የጥፋተኛነት ስሜት ማስወገድ እንዲቻል ልጁ ምንም የፈጸመው ስህተት እንደሌለ እንዲገነዘብ እርዱት።

ወላጃቸውን በሞት ያጡ ልጆች የተጣልን እንሆናለን የሚል ስጋት ያድርባቸዋል። በተቻለ መጠን እንዲረጋጉ አድርጓቸው፤ የሚፈቀሩና እንክብካቤ የሚደረግላቸው መሆኑንም እንዲያውቁ አድርጉ። በተጨማሪም አንድ ልጅ የቁጣ ስሜት ሊሰማው ይችላል። ወላጅህን የወሰደው አምላክ ነው ተብሎ ከተነገረው በአምላክ ላይ ጥላቻ ሊያድርበት ይችላል። በእነዚህ ነገሮች ረገድ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ማወቁ ይጠቅማል። ልጁን አጽናኑት። ፍቅራችሁን ግለጹለት፤ እንዲሁም ድጋፋችሁን አትንፈጉት።

[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ያዘኑትን ሰዎች ከማጽናናትና ከማበረታታት ወደ ኋላ አትበል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ