አንዲት ሴት ተገዳ ብትደፈር ሁኔታውን መቋቋም የምትችለው እንዴት ነው?
ሜሪን አንድ ሰው በጩቤ አስፈራርቶ የደፈራት ከሠላሳ ሦስት ዓመት በፊት ነበር። አሁንም ቢሆን ሜሪ ስለ ሁኔታው ለመናገር ከሞከረች ልቧ በኃይል ይመታል፤ እጅዋንም ያልባታል። እንባ እየተናነቃት “አንዲት ሴት ሊያጋጥሟት ከሚችሉት ነገሮች ሁሉ በጣም የሚያዋርድ ነገር ቢኖር ተገዶ መደፈር ነው። በጣም አስቀያሚና አስከፊ ነው” ስትል ትናገራለች።
አንዲት ሴት በሕይወቷ ሊያጋጥሟት ከሚችሉ በጣም አደገኛና ጎጂ ሁኔታዎች መካከል አንዱ ተገዶ መደፈር ነው። እስከ ዕድሜ ልክ የሚቆይ አስከፊ ውጤቶችንም ሊያስከትል ይችላል። አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ቃለ ምልልስ ተደርጎላቸው ከነበሩት ተገደው የተደፈሩ ሴቶች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ራሳቸውን ለመግደል አስበው እንደነበር ሲገልጹ አብዛኞቹ ደግሞ የማይሽር ለውጥ ያስከተለባቸው መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም ሴትየዋ ጥቃት ያደረሰባትን ሰው የምታውቀው ከሆነ የሚያደርስባት ቁስል ይበልጥ የሚያሠቃይ ይሆንባታል። በምታውቀው ሰው የተደፈረች ሴት ከሌሎች ሰዎች እርዳታ ለማግኘት ያላት አጋጣሚ በጣም አነስተኛ ነው። ምክንያቱም ስለተፈጸመባት ድርጊት ለማንም አትናገርም። ብትናገርም የተደፈረችው ተገዳ ነው ብሎ የሚያምናት ሰው አይኖርም። ጉዳት ያደረሰባት እምነት የጣለችበት ሰው በመሆኑ ለድርጊቱ ራስዋ ተጠያቂ እንደሆነች አድርጋ እንድታስብ ወይም ሌሎች ሰዎችን ለመመዘን ባላት ችሎታ እንድትጠራጠር ያደርጋታል።
እርዳታ ተቀበይ
ተገደው የተደፈሩ ብዙ ሴቶች መጀመሪያ ላይ በጣም ይደነግጣሉ፤ ድርጊቱንም እንዳልተፈጸመባቸው አድርገው ለመርሳት ይሞክራሉ። አንዲት ሴት በጣም ወሳኝ የሆነ የኮሌጅ ፈተና ከመውሰዷ ትንሽ ቀደም ብሎ ተገዳ ተደፈረች። ፈተናዋን እስክትጨርስ ድረስ ተደፍራ የነበረ መሆኑን ጨርሶ ረሳች። ተገዳ የተደፈረች ሌላዋ ሴት ደግሞ እንዲህ አለች:- “የማውቀውና እተማመንበት የነበረው ሰው ዓይኔ እያየ ጥቃት ስለፈጸመብኝ ስለ ሁኔታው ማስታወስ አልፈልግም። በሚያውቁት ሰው መደፈር እንዳለ አላውቅም ነበር። የሚያውቁት ሰው አስገድዶ ሊደፍር ይችል ይሆናል ብሎ ማሰብ ቂልነት መስሎ ይታይ ይሆናል፤ ሆኖም ይህ ዓይነቱ አስተሳሰብ ያለ ተስፋ አስቀረኝ። ብቸኝነት በጣም ተሰማኝ።”
አንዳንድ ሴቶች ተገደው መደፈራቸውን ለማንም ባለመናገር ድርጊቱ እንዳልተፈጸመባቸው አድርገው ለማሰብ በመሞከር ቀጥለውበታል። መደፈራቸውን ለብዙ ዓመታት ምሥጢር አድርገው መያዛቸው ቁስሉ ቶሎ እንዳይሽርላቸው አድርጓል። ከዚህም በተጨማሪ በመደፈራቸው ምክንያት የተከሰቱ መሆናቸውን ያልተረዷቸው ስሜታዊ ችግሮች ደርሰውባቸዋል።
የደረሰብሽን ነገር ለሌሎች ካልተናገርሽ በስተቀር ከደረሰብሽ ጥቃት ቶሎ ማገገም አትጀምሪም። እምነት የምትጥይባት ወዳጅሽ የደረሰብሽ ነገር ወደሽ ያደረግሽው ወይም በራስሽ ጥፋት የመጣ ሳይሆን ሳትወጂ በግድ የተፈጸመብሽ መሆኑን እንድትገነዘቢ ልትረዳሽ ትችላለች። አንድ የቆየ ምሳሌ “ወዳጅ በዘመኑ ሁሉ ይወድዳል፤ ወንድምም ለመከራ ይወለዳል” ይላል። (ምሳሌ 17:17) በተጨማሪም መንፈሳዊ እረኞች “ከነፋስ እንደ መሸሸጊያ ከዐውሎ ነፋስም እንደ መጠጊያ” ሊሆኑ ይችላሉ። (ኢሳይያስ 32:2፤ 1 ተሰሎንቄ 5:14) ጥቃቱ የተፈጸመባቸው አንዳንድ ሴቶች ለሚሰሟቸው ነገሮች መፍትሔ ለማግኘት ተገደው ለተደፈሩ ሰዎች እርዳታ ለመስጠት ከተ ቋቋመ ማዕከል ወይም ምክር ሊሰጣቸው ከሚችል ባለሙያ ጋር ተገናኝተው መነጋገር ያስፈልጋቸው ይሆናል።
ተገደው የተደፈሩ ሴቶች፣ በተለይ በወቅቱ የፆታ ስሜታቸው ተነሣሥቶ ከነበረ የበደለኛነት ስሜት ስለሚሰማቸው የተደፈሩ መሆናቸውን ለሌሎች መናገር ይፈራሉ። ለደረሰባቸው ጥቃት ተነቃፊው አስገድዶ የደፈራቸው ሰው ቢሆንም እንደረከሱ ወይም ዋጋ የሌላቻው እንደሆኑ ይሰማቸው ወይም ራሳቸውን ይወቅሱ ይሆናል።
የደረሰባትን ነገር ለምታምናት ክርስቲያን ጓደኛዋ ያካፈለችው ሜሪ “ልትነግሩት የምትችሉ አንድ ጥሩ ጓደኛ መኖሩ ለውጥ ያመጣል” ስትል ተናግራለች። “ተገድጄ መደፈሬን ለጓደኛዬ ስነግራት እንደረከስኩና ጠባሳ እንዳለብኝ ሆኖ አልተሰማኝም።”
ድጋፍ ስጧት
ተገዳ ለተደፈረችው ሴት ጓደኞች የሆኑ ሰዎች ነገሩ እውነት መሆኑን ቢጠራጠሩ ወይም “በእርግጥ መደፈሯን” ለማረጋገጥ ቢሞክሩ ፍቅር የጎደለው አድራጎት ነው። ነገሩ አስደስቷት የነበረ መሆን አለመሆኑን መጠየቅ ወይም ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ነገር እንደፈጸመች መናገር ፈጽሞ አይገባም። እንዲረዳት የምትጠይቀው ወዳጅ የሆነ ሰው ማድረግ ያለበት ትልቁ ነገር የምትናገረውን አምኖ መቀበሉ ነው። አጽናኗት። መናገር ስትፈልግ አዳምጧት፤ ሆኖም ዝርዝር ሁኔታውን እንድትነግራችሁ አጥብቃችሁ አትጠይቁ።
አንዲት ሴት ተገዳ ከተደፈረች ብዙ ጊዜ ካልሆነ የሕክምና እርዳታ እንድታገኝና ለሕይወቷ በማያሰጋ ቦታ እንድትቆይ በማድረግ በኩል ጓደኞቿ ሊረዷት ይችላሉ። ተገዳ መደፈሯን ሪፖርት እንድታደርግ አበረታቷት፤ ሆኖም ውሳኔውን ለራሷ ተዉት። የመወሰን መብቷ ታቅቦና በሌላ ሰው ቁጥጥር ሥር ወድቃ ቆይታለች። ቀጥሎ ምን መደረግ እንዳለበት ራሷ እንድትመርጥ በማድረግ የመወሰን መብቷን መልሳ እንድታገኝ ፍቀዱላት።
የቤተሰባቸው አባል ተገዳ የተደፈረችባቸው ሰዎች በግልፍተኝነት ስሜት ተነሣሥተው የችኮላ እርምጃ ከመውሰድ መቆጠብ አለባቸው። ለደረሰው ጉዳት ሌላውን ሰው ለመወንጀል ወይም ለመበቀል ይፈልጉ ይሆናል። የትኛውም ቢሆን ጉዳት ለደረሰባት ሴት የሚያመጣላት አንዳችም ጥቅም የለም። (ሮሜ 12:19) አስገድዶ የደፈረውን እንጂ ሌላ ሰው መውቀስ አይጠቅምም፤ ለመበቀል መፈለግም አደገኛ ነው። ለመበቀል መሞከር ተገዳ የተደፈረችው ሴት ወደ ቀድሞ ሁኔታዋ እንዴት መመለስ እንደምትችል ከማተኮር ይልቅ ስለምታፈቅራቸው ሰዎች ደህንነት እንድትጨነቅ ሊያደርጋት ይችላል።
በተጨማሪም ብዙ ሴቶች ከተደፈሩ በኋላ ስለ ፆታ ግንኙነት ያላቸው አመለካከት እንደሚለወጥ ቤተሰቦቻቸው ሊገነዘቡላቸው ይገባል። ሩካቤ ሥጋ እንደ ማጥቂያ መሣሪያ ሆኖ ይታያቸዋል። ስለዚህ ከሚያፈቅሩትና ከሚተማመኑበት ሰው ጋርም ቢሆን የፆታ ግንኙነት ማድረግ ለጊዜው ይቸግራቸው ይሆናል። ስለዚህ አንድ ባል ሚስቱ ይህ ዓይነቱ ስሜት እስኪጠፋላት ድረስ የፆታ ግንኙነት እንድታደርግ ግፊት ሊያደርግባት አይገባም። (1 ጴጥሮስ 3:7) በአንዲት ወጣት ሴት ላይ የደረሰው ነገር ምንም ይሁን ምን የምትፈቀርና የምትከበር እንደሆነች በመግለጽ በራሷ የመተማመንን መንፈስ እንድትገነባ በማድረግ በኩል መላው ቤተሰብ ሊረዳት ይችላል። ተገዳ የተደፈረች ሴት ከደረሰባት ስሜታዊ ቁስል ለመዳን ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ ስለሚችል የቤተሰቡ አባሎች ያለማቋረጥ ድጋፋቸውን ሊሰጧት ያስፈልጋል።
ፍርሃትንና የመንፈስ ጭንቀትን መቋቋም
ተገደው የተደፈሩ ሴቶች በጣም እንደሚፈሩ ይናገራሉ። ተገዶ የመደፈር ጥቃት ከደረሰባቸው ሴቶች መካከል አብዛኞቹ ከጥቃቱ በኋላ በሕይወት የሚኖሩ አይመስላቻውም። ከተደፈሩም በኋላ ቢሆን ሁለተኛ ጊዜ እንዳይደፈሩ ይሰጉ ወይም አስገድዶ የደፈራቸውን ሰው ለማየት አንኳ ይፈሩ ይሆናል።
በተደፈሩበት ጊዜ የነበረውን የሚመስል ድምፅ፣ ሽታና ቦታ ሲያጋጥማቸው ተገደው በተደፈሩበት ጊዜ ተሰምቷቸው የነበረው የፍርሃት ስሜት እንደገና ሊቀሰቀስባቸው ይችላል። አንዲት ሴት የተደፈረችው ሰዋራ በሆነ መንገድ ከሆነ እንዲህ ባለው መንገድ መሄድ ያስፈራት ይሆናል። የተደፈረችው እቤቷ እያለች ከሆነ እዚያው ቤት መኖር አስተማማኝ መስሎ ስለማይሰማት ቤቱን ለቅቃ ለመሄድ ትገደድ ይሆናል። አስገድዶ የደፈራት ሰው ተቀብቶት የነበረው ሽቶ ከሸተታት እንኳ መጥፎ ትዝታዎች ሊቀሰቀሱባት ይችላሉ።
ተገደው በመደፈራቸው ምክንያት የሚያረግዙት ሴቶች በጣም ጥቂት ቢሆኑም ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው ሴቶች ብዙዎቹ አርግዘን ይሆን ብለው በጣም ይሰጋሉ። ሌሎች ደግሞ በፆታ ግንኙነት የሚተላለፍ በሽታ ይዞኝ ይሆን ብለው ይጨነቃሉ። እንዲህ ብለው ቢያስቡም አይፈረድባቸውም። ተገደው ከተደፈሩት መካከል ግማሾቹ ከበርካታ ሳምንታት እስከ ወራት የሚቆይ የመንፈስ ጭንቀት፣ ተስፋ የመቁረጥና የዋጋ ቢስነት ስሜት ይሰማቸዋል። እንዲሁም ከከባድ ፍርሃትና ከአእምሮ መረበሽ ስሜት ጋር ይታገሉ ይሆናል።
ሴቶች ተገዶ መደፈራቸውን ሊያስቀሩ የማይችሉት ነገር ቢሆንም እንኳ ጥቃቱ በተፈጸመባቸው ወቅት የነበራቸውን አስተሳሰብ፣ ስሜትና ሁኔታ ቀስ በቀስ መቆጣጠር ይችላሉ። ስለ ራሳቸው ያሏቸውን አፍራሽ አመለካከቶች ገንቢ በሆኑ አመለካከቶች መተካትን ሊማሩ ይችላሉ።
ሊንዳ ሌድሬይ ሪከቨሪንግ ፍሮም ሬፕ በተሰኘው መጽሐፋቸው ቀጥሎ ያለውን ምክር ጽፈዋል:- “ምን ያህል ደካማ፣ የማልረባ ወይም አቅመ ቢስ ነኝ ከማለት ይልቅ ጥቃቱ ከደረሰብሽ በኋላ ያከናወንሻቸውን ጥሩ ነገሮች አስቢ። በየዕለቱ ‘ሁኔታውን በመቆጣጠር ወደ ቀድሞው ሁኔታዬ እንዴት መመለስ እንደምችል እየተማርኩ ነው’ እያልሽ ለራስሽ ብትናገሪ በአእምሮሽ ውስጥ የሚጉላሉት አፍራሽ አስተሳሰቦችና ስሜቶች ይቀንሳሉ።”
የፍርሃትን ስሜትም ቢሆን መንስዔው ምን መሆኑን ለይቶ በማወቅ መቋቋም ይቻላል። ዓመፁ የተፈጸመባት ሴት የፍርሃቷ መንስዔ ምን እንደሆነ ካወቀች አሁን መፍራቴ ትክክል ነው? ብላ ራሷን ልትጠይቅ ትችላለች። ለምሳሌ አስገድዶ የደፈራትን የሚመስል ሰው ብታይ አስገድዶ የደፈራት ሰው እርሱ እንዳልሆነና ጉዳት የማያደርስባት መሆኑን ልታስብ ትችላለች።
ፍርሃት ለማስወገድ የሚረዳ ሌላው ዘዴ ደግሞ የፍርሃት ስሜት እንዲጠፋ ቀስ በቀስ ልምምድ ማድረግ ነው። ሴትየዋ የሚያስፈሯትን ነገሮች ወይም ሁኔታዎች ከቀላሉ እስከ ከባዱ ድረስ በቅደም ተከተል ትመዘግባለች። ከዚያም በኋላ ብዙም በማያስፈራት ሁኔታ ውስጥ እንዳለች አድርጋ በማሰብ የፍርሃት ስሜቷ እስኪጠፋላት ድረስ ትቆያለች። እንዲህ እያደረገች በሁሉም ሁኔታዎች ሥር ይሰማት የነበረው ፍርሃት እስኪጠፋ ድረስ ትለማመዳለች።
የተደፈረች አንዲት ሴት ከወዳጆቿ በምታገኘው እርዳታ በማታ ከቤት መውጣት ወይም ብቻዋን መሆንን የመሳሰሉ የዕለት ተለት ተግባሮች በማከናወን መሻሻል ልታሳይ ትችላለች። ቀስ በቀስ ፍርሃቷን በመቆጣጠር የየዕለቱን ተግባር ማከናወኗን ትቀጥላለች። ሆኖም በማታ መብራት በሌለው ሰዋራ ቦታ ብቻዋን እንደ መሄድ ያሉ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ብትፈራ አይፈረድባትም። በእነዚህ ሁኔታዎች ሥርም ቢሆን መፍራት የለብሽም ብሎ ለማደፋፈር መሞከር ምክንያታዊነት አይደለም።
የቁጣን አቅጣጫ ማስቀየር
ተገደው የተደፈሩ ሴቶች የቁጣ ወይም የንዴት ስሜት ይሰማቸዋል። ይህም መጀመሪያ በሁሉም ወንዶች ላይ እንዲቆጡ ያደርጋቸው ይሆናል። ከጊዜ በኋላ ግን ብዙውን ጊዜ ቁጣቸው የሚያነጣጥረው አስገድዶ በደፈራቸው ሰው ላይ ይሆናል። የተናደዱ ሰዎች ብዙውን ጊዜ የሚሠሩትን ስለማያውቁ እንደመሰላቸው ያደርጋሉ። ሌሎች ደግሞ ስሜታቸውን አፍነው ይይዛሉ። ያም ሆነ ይህ ተገዳ የተደፈረች ሴት ብትቆጣም ቁጣዋን ገንቢ ወደሆነ አቅጣጫ መቀየር ትችላለች። አንዲት ተገዳ የተደፈረች ሴት ስለ ቁጣዋ የምትወስደው እርምጃ ከደረሰባት ጉዳት በቶሎ እንድታገግም ሊረዳት ይችላል። ቅዱሳን ጽሑፎች “ተቆጡ ኃጢአትንም አታድርጉ” በማለት ይመክራሉ። — ኤፌሶን 4:26
በመጀመሪያ ደረጃ ተገደው የተደፈሩ ሴቶች የሚሰማቸውን ቁጣ ወይም ንዴት ከመግለጽ መፍራት የለባቸውም። ስለተሰማቸው ነገር ለሌሎች መናገር ይችላሉ። ሁኔታውን ለሕግ ማቅረብ ወይም በማስታወሻ መመዝገብ የንዴታቸውን አቅጣጫ የሚያስቀይሩበት መንገድ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም የመንፈስ ጭንቀትን ለመዋጋት በሚረዱ እንደ ሜዳ ወይም የጠረጴዛ ቴኒስ፣ የእጅ ኳስ፣ በእግር መንሸራሸር፣ ቀስ እያሉ መሮጥ፣ ብስክሌት መንዳት ወይም መዋኘት በመሳሰሉት የአካል እንቅስቃሴዎች በመዝናናት ንዴታቸውን ሊወጡ ይችላሉ።
እንዲህ በማድረግ ሕይወትሽን እንደ ወትሮው መምራት ትችያለሽ።
ተገዶ መደፈርን የሚያስቆመው ምን ይሆን?
ተገዶ መደፈርን ለማስቆም አስገድደው ከሚደፍሩ ወንዶች ከመራቅ ወይም ተገደው እንዳይደፈሩ ከመታገል የበለጠ ነገር ያስፈልጋል። ቲሞቲ ቤኔክ የተባሉ አንድ ሰው ሜን ኦን ሬፕ በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ “አስገድድው የሚደፍሩት ወንዶች ናቸው፤ ተገዶ መደፈርን ለማስቆም ኃይል ያላቸውም ወንዶች ናቸው” ሲሉ ጽፈዋል።
ወንዶች ሴቶችን እንደ ዕቃ አድርገው መመልከታቸውን እስካላቆሙና በሴቶችና በወንዶች መካከል ጥሩ ግንኙነት ሊኖር የሚችለው ሴቶችን በጉልበት ተጭኖ በመግዛት አለመሆኑን እስካልተማሩ ድረስ ተገዶ መደፈር አያቆምም። በግለሰብ ደረጃ የጎለመሱ ወንዶች ከሌሎች ወንዶች ጋር በመነጋገር አስተሳሰባቸውን ማስቀየር ይኖርባቸዋል። ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ስለ ፆታ ብልግና የሚነገሩ ቀልዶችን ባለመስማት፣ በማስገደድ የሚፈጸሙ የፆታ ዓመፅን የሚያሳዩ ፊልሞችን ባለማየት ወይም ዕቃ ለማሻሻጥ በፆታ የሚጠቀሙ ማስታወቂያዎችን ባለመደገፍ ዓመፅን እንደሚጸየፉ ማሳየት ይችላሉ። መጽሐፍ ቅዱስ “ለቅዱሳን እንደሚገባ ግን ዝሙትና ርኩሰት ሁሉ ወይም መመኘት በእናንተ ዘንድ ከቶ አይሰማ፤ የሚያሳፍር ነገርም የስንፍና ንግግርም ወይም ዋዛ የማይገቡ ናቸውና አይሁኑ፣ ይልቁንም ምስጋና እንጂ” በማለት ይመክረናል። — ኤፌሶን 5:3, 4
ወላጆች ለሴቶች ክብር በመስጠት በኩል ምሳሌ በመሆን ልጆቻቸውን ማስተማር ይችላሉ። ወላጆች ወንዶች ልጆቻቸው ሴቶችን ይሖዋ በሚመለከትበት መንገድ ማየትን እንዲማሩ ሊረዷቸው ይችላሉ። አምላክ በሰዎች መካከል አያዳላም። (ሥራ 10:34) ወላጆች ኢየሱስ እንዳደረገው ሴቶችን በወዳጅነት እንዲመለከቷቸውና ከሴቶች ጋር መሆን የማይከብዳቸው እንዲሆኑ ወንዶች ልጆቻቸውን ሊያስተምሩ ይችላሉ። የፆታ ግንኙነት አንድ ሰው ከትዳር ጓደኛው ጋር ብቻ የሚፈጽመው የፍቅር መግለጫ ድርጊት መሆኑን ለወንዶች ልጆቻቸው ሊያስተምሩ ይችላሉ። ወላጆች ዓመፅ በዝምታ የማይታለፍ መሆኑንና በሌሎች ላይ የኃይል ድርጊት መጠቀምም ጎጂ መሆኑን መግለጽ ይችላሉ። (መዝሙር 11:5) ወላጆች ልጆቻቸው ፆታን ስለሚመለከቱ ጉዳዮች ከእነርሱ ጋር በግልጽ እንዲወያዩና የፆታ ግፊቶችን መቋቋም እንዲችሉ ሊያበረታቷቸው ይችላሉ።
በቅርቡ ተገዶ መደፈር የሚያቆምበት ጊዜ ይመጣል
ሆኖም በዓለም ባለው ኅብረተሰብ ውስጥ ሥር ነቀል ለውጦች እስካልተካሄዱ ድረስ አስገድዶ የመድፈር ዓመፅ አይቆምም። ተመራማሪዋ ሊንዳ ሌድሬይ “ተገዶ መደፈር የአንድ ግለሰብ ችግር ሳይሆን የቤተሰብ፣ የኅብረተሰብና የአገር ችግር ነው” ብለዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ ‘ሰው ሰውን ለጉዳቱ መግዛቱ’ የሚያቆምበትና መላው የምድር ኅብረተሰብ ከዓመፅ ድርጊቶች እፎይታ የሚያገኝበት ጊዜ እንደሚመጣ ተስፋ ይሰጣል። (መክብብ 8:9፤ ኢሳይያስ 60:18) በቅርቡ ይሖዋ አምላክ አስገድዶ መድፈረን ጨምሮ በጉልበት አላግባብ መጠቀምን ዝም ብሎ የማይመለከትበት ጊዜ ይመጣል። — መዝሙር 37:9, 20
በዚያ የአዲስ ዓለም ኅብረተሰብ ውስጥ ሁሉም ሰዎች የፆታ፣ የዘር ወይም የብሔር ልዩነት ሳያደርጉ እርስ በእርስ መፋቀርንና አብሮ በሰላም መኖርን ይማራሉ። (ኢሳይያስ 54:13) በዚያ ጊዜ የሚኖሩ ገር ሰዎች የሚያውቋቸውንም ሆነ የማያውቋቸውን ሰዎች አይፈሩም። “በብዙም ሰላም ደስ ይላቸዋል።” — መዝሙር 37:11
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
ተገደሽ ብትደፈሪ
□ የሕክምና እርዳታ እንዲደረግልሽ አድርጊ
□ ተገደው ለተደፈሩ ሰዎች ምክር የሚሰጥ ባለሙያ ሰው በአካባቢው ካለ ስለ ሕክምናና ሕግ ነክ ጉዳዮች ምን ማድረግ እንደሚያስፈልግሽ እንዲረዳሽ (አብሮሽ እንዲሄድ) ጠይቂ
□ በተቻለ ፍጥነት ፖሊስ ጥሪ። ለራስሽም ሆነ ለሌሎች ሴቶች ደህንነት ስትይ ሪፖርት ማድረጉ አስፈላጊ እንደሆነ አማካሪዎች ይናገራሉ። ድርጊቱን ሪፖርት ማድረግና ወንጀለኛውን ሕግ ፊት ማቅረብ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ከጊዜ በኋላ ሕግ ፊት ለማቅረብ ብትፈልጊ እንኳ ቶሎ ሪፖርት ባለማድረግሽ ክስሽ ይዳክምብሻል።
□ ድርጊቱ መፈጸሙን የሚያስረዱ ሁኔታዎችን አታጥፊ። ገላሽን አትታጠቢ፣ ልብስሽን አትለውጪ፣ ፀጉርሽን አታበጥሪ ወይም አትታጠቢ፣ የእጁን ወይም የእግሩን አሻራ አታጥፊ።
□ የሕክምና ባለሙያዎች ማስረጃዎችን ሊያሰባስቡና የአባለዘር በሽታዎችና የእርግዝና ምርመራ ሊያካሂዱ ይችላሉ። ሐኪሞች ሞርኒንግ አፍተር ፒል በመባል እንደሚታወቀው ያሉ እርግዝናን የሚከላከሉ መድኃኒቶች የሚሰጡ ከሆነ ክርስቲያኖች እነዚህ መድኃኒቶች ጽንስ የሚያስወርዱ እንዳይሆኑ ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባቸዋል።
□ ከፍርሃት የሚያድንሽ መስሎ የተሰማሽን ነገር ሁሉ አድርጊ። ቁልፍ መቀየር፣ ወደ ጓደኛ ቤት ዘወር ብሎ መቆየት፣ በር መዝጋት ሊሆን ይችላል።
□ ከሁሉም በላይ መጽናናት ለማግኘት ቅዱሳን ጽሑፎችን ማንበብ፣ ወደ ይሖዋ መጸለይና በአደጋው ጊዜም ሆነ ከአደጋው በኋላ የይሖዋን ስም ጮክ ብሎ መጥራት ያስፈልጋል። ሽማግሌዎች ወይም በጉባኤው ውስጥ ያሉ ሌሎች የቅርብ ጓደኞች ምክር እንዲሰጡሽ ጠይቂ። የሚቻል ከሆነም በጉባኤ ስብስባዎች ተገኚ፤ እንዲሁም ከክርስቲያን ጓደኞችሽ ጋር አብረሽ ወደ አገልግሎት ሂጂ።