የወፎች ዝማሬ እንዲያው ለጆሮ የሚጥም ዜማ ብቻ ነውን?
ከሩቅ የበራው የመድረክ መብራት በመዘምራኑ ጓድ ላይ ፈንጥቋል። መዘምራኑ ለትርዒታቸው የሚስማማ ጽዱ ልብስ ለብሰው ቦታ ቦታቸውን መያዝ ጀምረዋል። እያንዳንዱ ዘማሪ ከሕፃንነቱ ጀምሮ በቤተሰቡ ወግና ልማድ መሠረት በሚገባ የሰለጠነ ስለሆነ አለምንም ችግር ከልቡ መዘመር ይችላል። እንዲያውም አንዳንዶቹ አለምንም ልምምድ በቅጽበት አዲስና የተለያዩ ዜማዎችን በመፍጠር የተካኑ ይመስላሉ።
ይህ ትርዒት የሚታየው የት ነው? በዓለም ዝነኛ በሆነ ትልቅ የሙዚቃ አዳራሽ አይደለም። ከዚህ ይልቅ የሌሊቱ የጨለማ መጋረጃ ይከፈትና በተለያየ ቀለም የተዋቡ ትናንሽ ባለ ላባ ፍጥረታት ይታያሉ። ብዙ ዓይነት ያላቸው ዘማሪ አእዋፍ በዛፎች፣ በአጥሮች በስልክ ሽቦዎች ላይ ሆነው ድምፃቸውን አንድ ላይ በማቀናጀት በመላው ዓለም ላይ ከሚገኙት ምርጥ ዝማሬዎች መካከል አንዱ የሆነውን ጣፋጭ ዝማሬ ያሰማሉ። የተለያዩት እንደ ፉጨት፣ ቃጭልና ዋሽንት የመሰሉት ድምፆች አዲስ ቀን መጥባቱን ያበስራሉ።
ይሁን እንጂ እነዚህ ድምፆች የሚያስደስቱ ከመሆናቸውም በላይ ጆሯችን ሊለየው ከሚችለው የበለጠ ትርጉም አላቸው። ወፎች የሚዘምሩት ለምንድን ነው? መዝሙሮቹ ትርጉም አላቸውን? ወፎቹ መዝሙራቸውን የሚማሩት እንዴት ነው? አዳዲስ መዝሙሮችንስ ይማራሉን?
ስውር የሆኑት መልእክቶች
ሙዚቃው የሚሟሟቀው ጠዋትና ምሽት ላይ ነው። በብዛት የሚሰማው የወንዶቹ ድምፅ ሊሆን ይችላል። መዝሙሮቹ ሁለት ዓይነት መልእክት ያስተላልፋሉ። አንደኛው ሌሎች ወንዶች ከድንበራቸው እንዳያልፉ ማስጠንቀቂያ የሚሰጥ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ለጋብቻ የደረሱ ተባቶች ነጠላ ለሆኑ እንስቶች የጓደኝነት ግብዣ የሚያቀርብ ነው። ዘማሪ አእዋፍ የሚለማመዱትና የሚያዳብሩት የየራሳቸውን አካባቢ ዝማሬ ነው። አንድ ቋንቋ የተለያዩ ቀበሌኛዎች እንደሚኖሩት ማለት ነው። በዓይነቱ የተለየ የሆነው የአንድ አካባቢ ዝማሬ የሚማርከው በዚያው አካባቢ ያለችውን እንስት ወፍ ነው። በጣም የተሟሟቀና የረቀቀ ዝማሬ የሚሰማው በመራቢያ ወራት ነው። ምክንያቱም ዝማሬዎቹ የሚሰሙት ወይዛዝርቱን አእዋፍ ለመማረክ ሲባል ነው።
ዘማሪው ወፍ በዝማሬው አማካኝነት ያለበትን አድራሻ ለጠላትም ሆነ ለወዳጅ ያሳውቃል። በዚህም ምክንያት ደማቅ ቀለም ያላቸውና ገላጣ መስክ የሚወዱ አእዋፍ ለጥቃት ሊጋለጡ ስለሚችሉ ጮክ ብለው አይዘምሩም። በሌላ በኩል ደግሞ በቀላሉ የማይታይ ቀለም ያላቸውና ጥቅጥቅ ባለ ደን ውስጥ የሚኖሩ አእዋፍ ምንም የሚያሰጋቸው ነገር ስለማይኖር እንደ ልባቸው ሊዘምሩ ይችላሉ።
አንዳንድ ጊዜ የምትሰሙት የባለ ክንፎቹን ወዳጆቻችን እውነተኛ ዝማሬ ላይሆን ይችላል። ባልና ሚስቶች እንዳይጠፋፉ ወይም የአንድ መንጋ አባላት እንዳይነጣጠሉ የሚሰማ የጥሪ ድምፅ ሊሆን ይችላል። አደጋ መምጣቱን የሚያስጠነቅቅ ማስጠንቀቂያ፣ አለበለዚያም አንድ ድመት ወይም ሌላ ያልተፈለገ እንግዳ ለማባረር የቀረበ የውጊያ ጥሪ ሊሆን ይችላል። አእዋፍ በድምፃቸው አማካኝነት መቆጣታቸውን፣ መፍራታቸውን፣ መረበሻቸውን እንዲሁም የትዳር ጓደኛ መፈለግና አለመፈለጋቸውን ያሳውቃሉ።
የተራቀቁና ጥሩ ተሰጥኦ ያላቸው ሙዚቀኞች
የዘማሪ አእዋፍ የድምፃዊነት ችሎታ በእርግጥም የሚያስደንቅ ነው። አንዳንዶቹ በአንድ ጊዜ ሦስት ወይም አራት ኖታ ሊዘምሩ ይችላሉ። ሌሎች ደግሞ በሴኮንድ እስከ 80 ኖታዎች ሊያሰሙ ይችላሉ። እነዚህ ድምፆች ለሰው ጆሮ ያልተቆራረጠ የአንድ ኖታ ድምፅ ሆነው ቢሰሙም ወፎች ግን በጣም የተራቀቀ የማዳመጥ ችሎታ ስላላቸው ለይተው ሊሰሟቸው ይችላሉ።
ተመራማሪዎች ወፎች ሙዚቃ የማጣጣምና የመለየት ችሎታ ይኖራቸውና አይኖራቸው እንደሆነ ለማወቅ ፈልገው ነበር። አእዋፍ በኦርጋን የተቀነባበረውን የባህ የሙዚቃ ድርሰት “ራይት ኦቭ ስፕሪንግ” ከተባለው የስትራቪንስኪ ሙዚቃ ለመለየት ይችሉ ይሆን? ተመራማሪዎቹ አራት ርግቦችን አሰልጥነው ከሁለት ቁልፎች መካከል አንዱን በመጠቆም ትክክለኛውን የሙዚቃ ደራሲ እንዲያመለክቱና የምግብ ሽልማት እንዲያገኙ አድርገው ነበር። ርግቦቹ ብዙም ሳይቆይ 20 ደቂቃ ከሚፈጀው የባህ ሙዚቃዊ ቅንብር ጥቂቱን ክፍል ብቻ ሰምተው ትክክለኛውን ቁልፍ ለመምረጥ ችለዋል። እንዲያውም ሌሎች የሙዚቃ ደራሲዎች ያቀነባበሯቸውን ተመሳሳይ ስልት ያላቸው ሙዚቃዎች ለመለየት ችለዋል።
አንዳንድ በሐሩር ክልል የሚኖሩ ወፎች በሁለት ተጫዋቾች የሚቀርቡ ሙዚቃዎችን ለማቀናበርና ለመጫወት ይችላሉ። ባልና ሚስት የሆኑ ወፎች ብዙ ልምምድ ካደረጉ በኋላ እየተፈራረቁ ወይም እንደ ጥያቄና መልስ እየተቀባበሉ የሚጫወቱት ወጥ የሆነ የሙዚቃ ድርሰት ይፈጥራሉ። ዝማሬያቸው በጣም የተስተካከለ በመሆኑ ላልሰለጠነ ጆሮ አንድ ወፍ ብቻውን ሆኖ የዘመረው ይመስላል። ሁለቱም እየተቀባበሉ ይዘምራሉ ወይም አንዳቸው ከሌሉ ሌላኛው ብቻውን ሆኖ ያዜማል። ይህ ልዩ የሆነ የአእዋፍ ችሎታ ወፎቹ ጥቅጥቅ ባለው ደን ውስጥ እርስ በርስ እንዳይጠፋፉና የትዳር ጓደኛቸውን ፈልገው እንዲያገኙ ያስችላቸዋል።
ሙዚቃ የሚደርሱና አስመስለው የሚጫወቱ
አእዋፍ ዝማሬያቸውን እንዴት እንደሚፈጥሩና እንደሚማሩ ገና በመጠናት ላይ ያለ ጉዳይ ቢሆንም አንድ የተረጋገጠ ነገር አለ:- የመማር ዘዴያቸው እጅግ በርካታና የተለያየ ነው። የሚከተሉት በአእዋፍ ዓለም ውስጥ ላሉት የመማር ዘዴዎች ለናሙና ያህል ብቻ የተጠቀሱ ናቸው።
ቻፊንች የተባለው ወንድ ወፍ የሚያዜመው ዜማ ቢያንስ በከፊል አእምሮው ውስጥ ተቀርጾ ይወለዳል። ከሌሎች አእዋፍ ሙሉ በሙሉ ተነጥሎ ቢያድግ እንኳን በጥቂቱ ለየት ይበል እንጂ ሌሎች ቻፊንቾች ከሚያዜሙት ዜማ ጋር እኩል የሆነ ኖታና ርዝመት ያለው ዜማ ያዜማል። ይሁን እንጂ ሙሉ በሙሉ አንድ ዓይነት የሆነ መዝሙር ለመዘመር እንዲችል ለመዘመር በሚያስችለው ዕድሜ ላይ ከመድረሱ በፊትና በሚቀጥለው የፀደይ ወር ላይ ሌሎች ወንድ ቻፊንቾች ሲዘምሩ በድጋሚ መስማት አለበት። ከዚያ በኋላ ግን ልክ አንድ የተራቀቀ ሙዚቀኛ እንደሚያደርገው ደግሞ ደጋግሞ በመለማመድ የወጣትነት ድምፁን በጭንቅላቱ ውስጥ ከተቀረጸው ዜማ ጋር እንዲጣጣም ያደርጋል።
ኦሬገን ጁንኮ የተባለው ወፍ የአካባቢውን ዜማ ካልሰማ የራሱን ዜማ ይፈጥራል። ቀላልና ግልጽ የሆነውን የጁንኮ ዜማ ከሰማ ግን የራሱን ዜማ መፍጠሩን ትቶ ሌሎች ጁንኮዎች የሚያዜሙትን ያዜማል። የአሪዞና ጁንኮ ግን አንድ ሙሉ ዕድሜ ላይ የደረሰ ጁንኮ የሚያዜመውን ዜማ ሲሰማ የፈጠራ ችሎታው ይቀሰቀሳል። የራሱ የሆነ የተለየ ዜማ ይፈጥራል እንጂ ያዳመጠውን አይቀዳም።
አንዳንድ ዜማዎች በዘር የሚተላለፉ ለመሆናቸው ጠንካራ ማስረጃ የሚሆኑን ሌላ ዓይነት ዝርያ ባላቸው ወፎች ተቀፍቅፈው የሚያድጉ ወፎች ናቸው። ለምሳሌ ያህል ኩኩ የተባለችው ወፍ እንቁላሎችዋን የጉዲፈቻ ወላጆች ሆነው በሚያሳድጉላት ሌሎች ዓይነት ወፎች ጎጆ ውስጥ ትጥላለች። የሚቀፈቀፈው የኩኩ ጫጩት ከጉዲፈቻ አባቱ በዘር የተለየ መሆኑንና እንደ ጉዲፈቻ አባቱ ማዜም እንደሌለበት የሚያውቀው እንዴት ነው? በሚወለድበት ጊዜ የኩኩዎች ዜማ በአንጎሉ ውስጥ ተቀርጾ ይወለዳል።
ስለዚህ በብዙ ሁኔታዎች የአእዋፍ ዝማሬ በዘር የሚወረስ ይመስላል። አንድ ወፍ የዘሮቹን ዝማሬ ለመማር ባይችል እንኳን የሌሎች ዘሮችን ዝማሬ አይቀዳም ወይም አይወስድም። አንዳንድ ተመራማሪዎች የዘሮቹ ዜማ በጣም ግልጽ ባይሆንም በአእምሮው ውስጥ ተቀርጾ ስለሚኖር ወፉ የሚሰማቸውን ዜማዎች አመዛዝኖ ከእርሱ ዜማ ጋር በጣም የሚመሳሰለውን ለመምረጥ ይችላል ብለዋል።
የአእዋፍ አንጎል በጣም የሚያስደንቅ ነው! ፌርናንዶ ነተቦም የተባሉት ሳይንቲስት የዘማሪ አእዋፍ አንጎል በቀኝና በግራ የተከፈለና እያንዳንዱም ክፍል የራሱ የሆነ የሥራ ድርሻ እንዳለው ተረድተዋል። በተጨማሪም የመዘመር ችሎታ የሚገኝበትን የአንጎል ክፍል ለይተው ለማወቅ ችለዋል። አንድ በማደግ ላይ የሚገኝ ካነሪ የሚባል ወፍ ለመጪው የመራቢያ ወራት አዲስ ዝማሬ መማር ካስፈለገው ይህ የአንጎሉ ክፍል እንደሚያድግና መማር በማያስፈልገው ጊዜ ግን እንደሚኮማተር ተደርሶበታል። ካነሪዎች መዝሙር መለማመድ የሚጀምሩት ገና በጨቅላነታቸው ቢሆንም እነዚህ የተዋጣላቸው ዘማሪዎች እንኳን የተራቀቁ መዘምራን መሆን የሚችሉት ስምንት ወይም ዘጠኝ ወር ከሞላቸው በኋላ ነው።
ሌሎች ዘማሪ ወፎች ደግሞ ልዩ ተሰጥኦዋቸው አንዱን ዝማሬ ወስደው እሱን ማበልጸግ፣ ማሻሻል ወይም የፊቱን ዜማ ወደኋላ የኋላውን ወደፊት ማዛወር ነው። እነዚህ አስመስለው የሚዘምሩ ወፎች፣ በተለይም “የመናገር” ወይም የሰዎችን ድምፅ የመቅዳት ችሎታ ያላቸው ወፎች የብዙዎቻችንን አድናቆትና ትኩረት ስበዋል። አስመስለው ከሚዘምሩ አእዋፍ መካከል ላይበርድ የሚባለው የአውስትራሊያ ወፍ፣ ማርሽ ዋርብለርና ስታርሊን የሚባሉት የአውሮፓ ወፎች፣ ባለ ቢጫ ደረት ቻት እና ሞኪንግበርድ የሚባሉት የሰሜን አሜሪካ ወፎች ይገኛሉ። ሞኪንግበርድ የተባለው በሙዚቃው ውስጥ በደርዘን የሚቆጠሩ ዜማዎችን፣ እንዲያውም የእንቁራሪትና የአንዳንድ ነፍሳትን ጩኸት ሊጫወት ይችላል። ሞኪንግ በርድ ከአእዋፍ ዓለም ያገኛቸውን ረቂቅ ሙዚቃዎች በሙሉ አቀላቅሎና አቀናብሮ ሲጫወት መስማት በእርግጥም በጣም የሚያስደንቅ ነው።
እነዚህ ባለ ክንፍ ፍጥረታት ጣፋጭ ዜማቸውን ሲያዜሙ መስማት ብቻ ሳይሆን በአድናቆት ተመስጠህ ማዳመጥ ትችላለህ። የነገው የመድረክ ትርዒት የሚጀምረው ማለዳ ጎህ ሲቀድ ነው። ታዳምጣቸዋለህን?
በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን
የተለመደ የስልክ ድምፅ
በብሪታንያ የሚኖር አንድ ሳይንቲስት ትረሽ የሚባሉት ወፎች ከሚያሰሟቸው መዝሙሮች ውስጥ በአንዱ የተለመደ የስልክ ጥሪ ድምፅ ይሰማል። መዝሙሩን ከቀዳ በኋላ በኤሌክትሮኒክ መሣሪያ ይመረምረዋል። ድምፁ ቴሌኮም የሚባለው የብሪታንያ የስልክ ኩባንያ የሚያከፋፍለው የስልክ መሣሪያ ከሚያሰማው የጥሪ ድምፁ ጋር አንድ እንደሆነ ይገነዘባል። ዘማሪዎቹ ወፎች የስልኩን ድምፅ ቀድተው በሙዚቃቸው ውስጥ አስገብተውታል ማለት ነው። የትራሾቹ ዝማሬ አንዳንድ እንግሊዛውያን ስልካቸው የሚጮህ መስሏቸው ወደ ስልካቸው እንዲሮጡ ሳያደርጋቸው አልቀረም።
Camerique/H. Armstrong Roberts
T. Ulrich/H. Armstrong Roberts