የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 4/8 ገጽ 26-29
  • አዲስ ትምህርት ቤት በአፍሪካ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አዲስ ትምህርት ቤት በአፍሪካ
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የትምህርት ቤቱ ዓላማ
  • በዓይነቱ ብቸኛ የሆነ ሥልጠና
  • ከመስክ የተገኙ አስተያየቶች
  • በትምህርት ቤቱ ለመካፈል ብቃት ያላቸው እነማን ናቸው?
  • የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት —ታላቅ የሥራ በር
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2004
  • በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ሰዎች በረከት የሚሆኑ ተማሪዎችን የሚያሠለጥን ትምህርት ቤት
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
  • የመንግሥቱን አገልጋዮች ማሠልጠን
    የአምላክ መንግሥት እየገዛ ነው!
  • የይሖዋ ፍቅር መገለጫ የሆኑት ቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 4/8 ገጽ 26-29

አዲስ ትምህርት ቤት በአፍሪካ

በናይጄርያ የሚገኝ የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

በሐምሌ 1990 በኢግዱማ፣ ናይጄርያ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ የሚኖሩትንና ፈቃደኛ ሠራተኞች የሆኑትን ከ400 የሚበልጡ የይሖዋ ምሥክሮች ያስፈነደቀ አንድ ደብዳቤ ተነበበ። በ1987 በዩናይትድ ስቴትስ የተጀመረው የአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ወደ አፍሪካ ሊመጣና የመጀመሪያው ኮርስ በኢግዱማ ሊደረግ ነበር።

ከዚያ በኋላ በነበሩት ወራት የቤቴል ቤተሰቡ ለኮርሱ የሚያስፈልጉትን ዝግጅቶች አደረገ።a ተማሪዎቹና አስተማሪዎቹ የመኖሪያ ቦታ ሊያስፈልጋቸው ነው። ያሉት የእንግዳ ማረፊያ ክፍሎች በቂ ስለማይሆኑ 15 ተጨማሪ ክፍሎችን ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆነ። ስለዚህ ምሥክሮቹ በመጋዘንነት ያገለግሉ የነበሩ ክፍሎችን ማራኪ ወደሆኑ የመኖሪያ ክፍልነት መለወጥ ጀመሩ። ወለሎችን ማንጠፍ፣ ግድግዳዎችን ቀለም መቀባትና መጋረጃዎችን መስቀል ነበረባቸው። የአናጺ ክፍሉ አልጋዎችን፣ ቁም ሳጥኖችንና ጠረጴዛዎችን ሠርቶ በየክፍሉ አስገባ። በመጨረሻም ወንበሮች፣ የንባብ መብራቶችና የመጻሕፍት መደርደሪያዎች እንዲገቡ ተደረገ። መደርደሪያዎቹ በቲኦክራሲያዊ ጽሑፎች ተሞሉ።

በተጨማሪም የቤተሰቡ ሳሎን ለተማሪዎቹ የመማሪያ ክፍልና ቤተ መጻሕፍት ሆኖ እንዲያገለግል ተደረገ። ከሕክምና ክፍሎች አንዱ ለአስተማሪዎቹ ጊዜያዊ ቢሮ ሆኖ እንዲያገለግል ስለተደረገ ጠረጴዛዎች፣ ወንበሮችና ሌሎች የቢሮ ዕቃዎች ገቡለት። ይህ ሁሉ ዝግጅት በመደረግ ላይ እንዳለ በአገሪቱ በሙሉ በተደረጉ የይሖዋ ምሥክሮች የአውራጃና የወረዳ ስብሰባዎች ላይ ስለ ትምህርት ቤቱ መከፈት ሲነገር በመቶ የሚቆጠሩ አመልካቾች በትምህርት ቤቱ ለመካፈል ማመልከቻቸውን መላክ ጀመሩ።

በ1992 በየካቲት ወር የመጀመሪያ ሳምንት ዝግጅቱ በሙሉ ተጠናቅቆ አለቀ። ማይክል ፐብሪክ እና ፒተር ኒከልስ የተባሉ ሁለት አስተማሪዎች የመጀመሪያውን ኮርስ ለመስጠት ከብሪታንያ መጡ። ከ22ቱ ተማሪዎች በተጨማሪ ወደፊት በአስተማሪነት የሚያገለግሉ አይዛያ ምዌ፣ አይዛያ ኦላቦድ እና ፓየስ ኦፓራች የተባሉ ወንድሞች መጡ። እነዚህ ናይጄርያውያን ምሥክሮች ወደፊት በሚሰጡት ኮርሶች ላይ በአስተማሪነት እንዲያገለግሉ የሚያስችላቸውን ሥልጠና ለማግኘት የመጡ ነበሩ።

የትምህርት ቤቱ ዓላማ

በመላው ቤቴል የጉጉትና የደስታ መንፈስ ሰፍኖ ነበር። ለምን? ትምህርት ቤቱ በናይጄርያ በሚከናወነው ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ላይ በጎ ተጽእኖ ስለሚያሳድር ነው። ይሖዋ ከረዥም ዘመናት በፊት ‘የሰዎች ስጦታ’ እንደሚሰጥ ቃል ገብቶ ነበር። (መዝሙር 68:18) ሐዋርያው ጳውሎስ ኤፌሶን 4:8-11 ላይ እንደጻፈው ይህን ቃሉን በሐዋርያት ዘመን ፈጽሟል። ዛሬም ቢሆን ይሖዋ የሰዎችን ስጦታ በመስጠት ላይ ነው። የአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ከእነዚህ ሰዎች አንዳንዶቹ ተጨማሪ የሆኑ ድርጅታዊ ኃላፊነቶችን እንዲሸከሙ የሚያስችል ፍቅራዊ ዝግጅት ነው።

በአገሪቱ ውስጥ ከ3,900 በሚበልጡ ጉባኤዎችና ከ200,000 በላይ የሚሆኑ ምሥክሮች አሉ። ከእነዚህ ጉባኤዎች አንዳንዶቹ አንድ ወይም ሁለት ሽማግሌ፣ እንዲሁም ጥቂት የጉባኤ አገልጋዮች ብቻ ያላቸው ናቸው። ሌሎች ጉባኤዎች ደግሞ ምሥራቹ በበቂ ሁኔታ ባልተዳረሰባቸው ሰፊ ክልሎች የሚገኙ ናቸው። በዚህ ምክንያት በወንጌላዊነቱ ሥራ በግንባር ቀደምትነት የሚሰማሩ ብቻ ሳይሆን መንጋውን ለመጠበቅና በጉባኤ ውስጥ ለማስተማር ብቃት ያላቸው ወንዶች አስፈልገዋል።

የአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ዓላማ እነዚህን ኃላፊነቶች የሚሸከሙ ወንድሞችን ማሠልጠን ነው። አንዳንዶቹ ተማሪዎች ከተመረቁ በኋላ የልዩ አቅኚነት አገልግሎት ወይም የተጓዥ የበላይ ተመልካችነት አገልግሎት ይጀምራሉ። በሁለቱም የአገልግሎት መስኮች በናይጄርያ ተጨማሪ አገልጋዮች በጣም ያስፈልጋሉ። ሌሎች ደግሞ ወደ ጉባኤዎቻቸው ተመልሰው ለወንድሞቻቸው እርዳታና ማበረታቻ ይሰጣሉ። እነዚህ ጥሩ ብቃት ያላቸው ወንድሞች ለሚያገለግሉባቸው ጉባኤዎች ትልቅ በረከት ናቸው!

በዓይነቱ ብቸኛ የሆነ ሥልጠና

የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት፣ ሚስዮናውያንን ለውጭ አገር አገልግሎት የሚያሰለጥነው የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ቅጥያ ቢሆንም ሥርዓተ ትምህርቱ የተለየ ነው። ተማሪዎቹ በሥልጠና ላይ በሚቆዩባቸው ስምንት ሳምንታት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን በጥልቀት ያጠናሉ። የእረኝነት ኃላፊነቶችን ስለመወጣትና በክርስቲያናዊ ሕይወት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ስለመቋቋም የሚሰጡ ምክሮችን ጨምሮ በጣም ሰፊ የሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ይመረምራሉ። በተጨማሪም ቅዱሳን ጽሑፎች ስለ አስተዳደራዊ፣ ስለ ድርጅታዊና ስለ ፍርድ ነክ ጉዳዮች የሚሰጡትን ትምህርት ይማራሉ። የሕዝብ ንግግር ስለ መስጠት ልዩ የሆነ ሥልጠና የሚሰጣቸው ከመሆኑም በላይ በመንፈሳዊ ዕድገታቸው ረገድ በአሳቢነት ከሚረዷቸው አስተማሪዎች በየግላቸው እርዳታ ያገኛሉ።

በአጠቃላይ አንድ ተማሪ 45 የክፍል ሥራዎች ሲሰጡት በክፍል ውስጥ ከሚያሳልፋቸው 256 የትምህርት ሰዓቶች ብዙ ጥቅም ያገኛል። በተጨማሪም 140 ሰዓቶች የቤት ሥራውን በመሥራትና 14 ሰዓቶች ፈተና በመሥራት ያሳልፋል።

ዋነኛው የትምህርት መጽሐፍ መጽሐፍ ቅዱስ ቢሆንም እያንዳንዱ ተማሪ ለግሉ 16 የሚያክሉ በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የታተሙ የመጽሐፍ ቅዱስ ማጥኛ መጻሕፍትን ይዞ እንዲመጣ ይጠየቃል። ተማሪዎቹ በኮርሱ ወቅት በሚገባ በተደራጀው የቤቴል ቤተ መጻሕፍት ከሚገኙ ሌሎች ጽሑፎች ጥልቅ ምርምር እንዲያደርጉ ይጠየቃሉ። ጥሩ አስተማሪዎች መሆን እንደሚያስፈልጋቸው ግልጽ ነው።

ተማሪዎች ከትምህርታቸው በተጨማሪ በየቀኑ ለ45 ደቂቃ ከስምንቱ የቤቴል የሥራ ክፍሎች በአንዱ ይሠራሉ። እነዚህም የጽዳት፣ የምግብ ቤት፣ የቅጥር ግቢ አያያዝ፣ የመኖሪያ ቤት አያያዝ፣ የወጥ ቤት፣ የልብስ ንጽሕና፣ የጽሑፍ መላኪያና የማጓጓዣ ክፍሎች ናቸው። እያንዳንዱ ተማሪ በቤቴል በሚቆይባቸው ስምንት ሳምንቶች በእያንዳንዱ ክፍል በዙር በመሥራት በሁሉም ሥራ ስልጠና ያገኛል። አንድ ተማሪ “በተለያዩ የሥራ ምድቦች መሥራቴ የሥራው የበላይ ተቆጣጣሪ ይሖዋ መሆኑን እንድረዳ አስችሎኛል” በማለት አስተያየቱን ሰጥቷል። ሌላው ደግሞ “የበላይ ተመልካቾቹ በፍቅር ለማረምና ለማስተማር የተዘጋጁ ናቸው” ብሏል። አሁንም ሌላው ተማሪ “የቤቴል ሥራ፣ ሁሉ ሰው ሊቀምሰውና በጣም ጥሩ መሆኑን ሊያየው የሚገባ ነው” ብሏል።

ወንድሞች ስለተሰጣቸው ሥልጠና ምን ተሰማቸው? አንደኛው “የትምህርት ቤቶች ሁሉ ትምህርት ቤት ነው” ብሏል። ሌላው በጋለ ስሜት “እንዴት ያለ ድንቅ ዝግጅት ነው!” በማለት አድናቆቱን ገልጿል። የመጀመሪያው ኮርስ ሰልጣኞች ልባቸው በአድናቆትና በደስታ ተሞልቶ በጻፉት ደብዳቤ ላይ “ቁርጥ ውሳኔያችን . . . መላው ሕዋሳችን በምሥራቹ መልእክት ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ነው” ብለዋል።

ከመስክ የተገኙ አስተያየቶች

በ1992 እና በ1993 የመጀመሪያ ወራት በናይጄርያ የመጀመሪያዎቹ አራት የአገልጋዮች ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ኮርሶች ተሰጥተዋል። የሁለተኛው ኮርስ ተማሪዎች ለአስተዳደር አካሉ በጻፉት የአድናቆት ደብዳቤ ላይ እንደሚከተለው ብለዋል:- “በእርግጥ ከዚህ የተሻለ ትምህርት ቤት አጋጥሞን አያውቅም። ይህ ኮርስ ከዩኒቨርሲቲ ኮርስ በእጅጉ ይበልጣል። በዚህም ምክንያት ዊልያም ፌልፕስ ‘የኮሌጅ ትምህርት አግኝቶ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ከማጣት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት አግኝቶ የኮሌጅ ትምህርት ማጣት ይሻላል’ ሲል ከተናገረው መስማማት ቀላል ሆኖልናል። በእነዚህ ነገሮች ሁሉ ከልብ የምታስቡልን መሆኑ ግልጽ ሆኖልናል። ስለዚህም የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን የዕድሜ ልክ ሥራችን ለማድረግ ቆርጠናል።”

ሰልጣኞቹ በየተመደቡባቸው ቦታዎች እንዴት ያለ አቀባበል አገኙ? አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ከመጀመሪያው ኮርስ ስለተመረቁና በልዩ አቅኚነት በማገልገል ላይ ስለሚገኙ ሁለት ወንድሞች ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:- “አሁን ስብሰባዎች ይበልጥ ማራኪ፣ ይበልጥ አበረታች፣ ይበልጥ አስደሳችና ጥልቅ ትርጉም ያላቸው ሆነዋል። የመስክ አገልግሎት እንቅስቃሴዎች ጨምረዋል። . . . ጉባኤው በደስታ እየተፍለቀለቀ ነው። . . . አንዳንድ ወንድሞችን ስለነዚህ ልዩ አቅኚዎች ስጠይቅ ሰብሳቢ የበላይ ተመልካቹ የደስታ እንባ እየተናነቀው ‘እነዚህ ጠንካራና ፍሬያማ ረዳቶች ወደ ጉባኤያችን ስለተላኩ ይሖዋንና ድርጅቱን ከልብ እናመሰግናለን’ ብሎኛል።”

በትምህርት ቤቱ ለመካፈል ብቃት ያላቸው እነማን ናቸው?

በማንኛውም አገር በሚደረግ የአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ለመካፈል መቻል በጣም አስደናቂ የሆነ የአገልግሎት መብት ከመሆኑም በላይ ከይሖዋ የሚገኝ ትልቅ በረከት ነው። ይህ ሥልጠና ተማሪዎች መንፈሳዊነታቸውን እንዲያጎለብቱና ይሖዋ በይበልጥ እንዲገለገልባቸው የሚያስችላቸውን ብቃት እንዲያገኙ የሚያስችላቸው እንደሆነ አያጠራጥርም።

በዚህ ትምህርት ቤት ለመካፈል የሚያስፈልገው ብቃት ከፍተኛ መሆኑን መረዳት አያዳግትም። አመልካቾች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ሽማግሌዎች ወይም የጉባኤ አገልጋዮች ሆነው ቢያንስ ለሁለት ዓመታት ያገለገሉ መሆን አለባቸው። በዘወትር አቅኚነት አገልግሎት ውስጥ ያሉ ይበልጥ ተመራጭነት ይኖራቸዋል። ሁሉም ነጠላ የሆኑና ከ23 እስከ 50 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ መሆን አለባቸው። ባለፉት አምስት ዓመታት የፍርድ ወቀሳ ያልተሰጣቸውና ያልተወገዱ መሆን አለባቸው። አመልካቾች እንግሊዝኛ አጣርተው የሚያነቡ፣ የሚናገሩና የሚጽፉ መሆን አለባቸው። በተጨማሪም ጥሩ ጤንነት ያላቸውና ልዩ የሆነ የአመጋገብ ወይም ሌላ ጥንቃቄ የማያስፈልጋቸው መሆን ይኖርባቸዋል።

በዚህ ትምህርት ቤት ለመካፈል ፈቃደኛ የሆኑ ሁሉ በሚፈለጉበት ማንኛውም ቦታ ለማገልገል ዝግጁና ፈቃደኛ መሆን ይገባቸዋል። ይህም የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ጠንካራ ፍላጎት እንዲኖራቸው ብቻ ሳይሆን “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” በማለት ልዩ የሆነ ሥራ ለመሥራት ራሱን በጉጉት እንዳቀረበው እንደ ኢሳይያስ ያለ መንፈስ ይጠይቅባቸዋል።—ኢሳይያስ 6:8

አንተስ ይህን የመሰለ መንፈስ አለህ? ይህን የአገልግሎት መብት ለማግኘት በሚያስችል ሁኔታ ላይ ትገኛለህ? በዚህ መስክ የተሰማሩ ሁሉ የሚጸጸቱበት ምክንያት አላጋጠማቸውም። በአሁኑ ጊዜ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ በማገልገል ላይ የሚገኝ አንድ የትምህርት ቤቱ ምሩቅ እንዲህ ብሏል:- “ለእኔ የአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ምንም ተወዳዳሪ የማላገኝለት ስጦታ ነው። የመንፈሳዊ ሕይወቴ ጉልላት ሆኖልኛል። እንደገና የመኖር ዕድል ባገኝ ከዚህ የተለየ አኗኗር አልመርጥም።”

[የግርጌ ማስታወሻ]

a “ቤቴል” በዕብራይስጥ “የአምላክ ቤት” ማለት ሲሆን እያንዳንዱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮ የሚጠራበት ስም ነው።

[በገጽ 26, 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አይዛያ ምዌ እና ፓየስ ኦፓሮች የተባሉት አስተማሪዎች

በክፍል ውስጥ የሚሰጥ ትምህርት

በክፍል ውስጥ የሚደረግ የቡድን ውይይት

በቤተ መጻሕፍት ውስጥ ምርምር ማድረግ

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በልብስ ንጽሕና መስጫ ክፍልና በጽሑፎች መላኪያ ክፍል መሥራት

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ