“ይሖዋ ሆይ፣ ልጄ ታማኝነቷን እንድትጠብቅ እርዳት!”
የተወለድኩት በ1930 በፈረንሳይ አገር በአልሴስ ከተማ ከአንድ የአርቲስት ቤተሰብ ነው። ማታ ማታ አባቴ በሳሎን ወንበሩ ላይ ተዝናንቶ ይቀመጥና የጂኦግራፊ ወይም የአስትሮኖሚ መጻሕፍት ያነብ ነበር። ውሻዬ እግሩ ሥር ይተኛል። እማማም አባባ ካነበበው ነገር ዋና ዋና ሐሳቦችን ሲነግራት ሹራብ እየሠራች ታዳምጣለች። እነዚያ ምሽቶች ምንኛ ደስ የሚያሰኙ ነበሩ!
ሃይማኖት በሕይወታችን ውስጥ ትልቅ ቦታ ነበረው። አጥባቂ ካቶሊኮች ነበርን። እሑድ እሑድ ጠዋት ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንሄድ የሚያዩን ሰዎች “ሦስት ሰዓት ሆኗል። የአርልኖድ ቤተሰቦች ወደ ቤተ ክርስቲያን እየሄዱ ነው” ይሉን ነበር። ትምህርት ቤት ከመሄዴ በፊት በየቀኑ ቤተ ክርስቲያን እየሄድኩ እሳለም ነበር። ሆኖም ቄሶቹ ምግባረ ብልሹ ስለነበሩ እናቴ ብቻዬን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዳልሄድ ከለከለችኝ። በዚያ ጊዜ ስድስት ዓመቴ ነበር።
እናቴ በቢብልፎርሽር (አሁን የይሖዋ ምሥክሮች በመባል በሚታወቁት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች) የታተሙ ሦስት ቡክሌቶችን ካነበበች በኋላ ከቤት ወደ ቤት እየሄደች መስበክ ጀመረች። አባባ በዚህ በጣም ተናደደ። በእኔ ፊት ምንም ዓይነት ሃይማኖታዊ ውይይት እንዳይደረግ አገደ። ‘ያን ነገርሽን እፊቷ እንዳታነቢ!’ አላት። እናቴ ግን ለእውነት ከፍተኛ ቅንዓት ስለነበራት አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦችን ልታነብልኝ ወሰነች። አንድ የካቶሊክ መጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ገዛችና በየቀኑ ጠዋት ጠዋት ታነብልኝ ነበር። አባባን ለመታዘዝ ስትል ግን በምታነበው ላይ ምንም ሐሳብ አትሰጥም።
አንድ ቀን “የአሕዛብ ጣዖታቶች የወርቅና የብር፣ የሰው እጅ ሥራ ናቸው። . . . የሚሠሩአቸውም የሚያምኑባቸውም ሁሉ እንደ እነርሱ ይሁኑ” የሚለውን መዝሙር 115:4–8ን አነበበችልኝ። ከዚያም “የተቀረጸውንም ምስል ለአንተ አታድርግ” ከሚለው ከሁለተኛው ትእዛዝ ጋር አያያዘችው። (ዘጸአት 20:4–6) ወዲያው ብድግ አልኩና በክፍሌ ውስጥ የነበሩትን የግሌን ሥዕላ ሥዕሎች አውርጄ ሰባበርኳቸው።
ትምህርት ቤት ስሄድ በየቀኑ ከመጽሐፍ ቅዱስ ስለማነበው ነገር ካቶሊክ ለሆኑት የክፍል ጓደኞቼ እነግራቸው ጀመር። ይህም በትምህርት ቤት ትልቅ ረብሻ ፈጠረ። ብዙ ጊዜ ልጆች መንገድ ለመንገድ እየተከተሉ አንቺ “የገማሽ አይሁድ!” ይሉኝ ነበር። ይህ የሆነው በ1937 ነበር። ይህ ሁኔታ አባቴ የምማረውን ነገር እንዲመረምር አደረገው። አባቴ በይሖዋ ምሥክሮች የታተመውን ፍጥረት የተባለ መጽሐፍ አገኘ። መጽሐፉን አነበበና ራሱም የይሖዋ ምሥክር ሆነ!
የጀርመን ሠራዊት በቤልጅየም ድንበር በኩል አድርጎ ፈረንሳይ እንደገባ ወዲያውኑ የናዚ አርማ (ስዋስቲካ) ያለባቸው ባንዲራዎች በየቤተ ክርስቲያኖች ላይ ሲውለበለቡ ማየት ጀመርን። የፈረንሳይ ባንዲራ ግን ገና ከከተማው ምክር ቤት ሕንፃ አልወረደም ነበር። የፈረንሳይ መንግሥት የመንግሥት አዳራሻችንን ዘግቶና የይሖዋ ምሥክሮችን ሥራ አግዶ ስለነበር የጀርመን ሠራዊት አገሪቷን መቆጣጠር በጀመረበት ጊዜ በድብቅ እንቀሳቀስ ነበር። ምሥክሮቹን ለማጥፋት ይደረግ የነበረው ጥረት እየተጠናከረ መጣ። ከሁለት ዓመት በኋላ በ11 ዓመቴ ተጠመቅሁ።
ከአንድ ወር በኋላ መስከረም 4, 1941 ከሰዓት በኋላ በስምንት ሰዓት የበራችን ደወል ተደወለ። አባባ ከሥራ የሚመለስበት ጊዜ ነበር። ዘልዬ ተነሥቼ እየሮጥኩ ሄድኩና በሩን ከፍቼ ተጠመጠምኩበት። ከኋላው የነበረው ሰው ‘ሃይል ሂትለር!’ ብሎ ጮኸ። ቀጥ ብዬ ስቆም የተጠመጠምኩበት ሰው የኤስ ኤስ ወታደር መሆኑን ተገነዘብኩ! ወደ መኝታ ቤቴ እንድሄድ አደረጉና እናቴን ለአራት ሰዓት ያህል ሲመረምሯት ቆዩ። ሲሄዱም ከመካከላቸው አንዱ “ከዚህ በኋላ ባልሽን አታይውም! አንቺና ልጅሽም መጨረሻችሁ ያው ነው!” ሲል ጮኾ ተናገረ።
አባባ የታሰረው የዚያን ዕለት ጠዋት ነበር። ደሞዙን ተቀብሎ በኪሱ አንዳስቀመጠ ነበር። የኤስ ኤስ ወታደሮች የባንክ ሒሳቡን ዘጉበት፤ እናቴም ሥራ ለማግኘት የሚያስፈልጓትን ሰነዶች በሙሉ ከለከሏት። በወቅቱ የነበራቸው ፖሊሲ “እነዚህ አይጦች ምንም ዓይነት መተዳደሪያ ማግኘት የለባቸውም!” የሚል ነበር።
በትምህርት ቤት የደረሰብኝ ስደት
በዚህ ጊዜ እማርበት በነበረው ለኮሌጅ የሚያዘጋጅ ትምህርት ቤት ይደርስብኝ የነበረው ተጽዕኖ እየጨመረ መጣ። አስተማሪ ወደ ክፍላችን በመጣ ቁጥር 58ቱም ተማሪዎች በሙሉ ይቆሙና እጃቸውን ወደ ላይ አንሥተው “ሃይል ሂትለር” ይሉ ነበር። ቄሱ ሃይማኖታዊ ትምህርት ለመስጠት ሲመጡ እንደገቡ “ሃይል ሂትለር —በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው” ይላሉ። የክፍሉ ልጆችም “ሃይል ሂትልር —አሜን!” ብለው ይመልሳሉ።
እኔ ግን “ሃይል ሂትለር” አልልም ነበር፤ ይህም በትምህርት ቤቱ ዲሬክተር ዘንድ ታወቀ። “አንዲት ተማሪ የትምህርት ቤቱን ሕጎች አትታዘዝም። በሳምንት ጊዜ ውስጥ ለውጥ የማታሳይ ከሆነ ይህች ተማሪ ትምህርት ቤቱን ለቃ መውጣት አለባት” የሚል የማስጠንቀቂያ ደብደቤ ተጻፈልኝ። ከደብዳቤው ግርጌ ከ20 በሚበልጡ ክፍሎች መነበብ እንዳለበት ተጽፏል።
ውሳኔዬን በክፍሌ ልጆች ፊት ወጥቼ የማሳውቅበት ቀን ደረሰ። ዲሬክተሩ ሃይል ሂትለር ለማለት ወይም የትምህርት ቤት መልቀቂያ ወረቀቴን ይዤ ለመውጣት የምመርጥበት ተጨማሪ አምስት ደቂቃ ፈቀደለኝ። እነዚያ አምስት ደቂቃዎች በጣም ረዥም ሆኑብኝ። እግሮቼ ዛሉ፣ ራሴ ከበደኝ፤ የልቤም ትርታ በጣም ጨመረ። ከክፍሉ ልጆች “ሃይል ሂትለር” የሚል ጩኸት ሲሰማ የክፍሉ ፀጥታ ተቋረጠ፤ ሦስት ጊዜ በመደጋገም ‘ሃይል ሂትለር’ አሉ። ወደ ዴስኩ ሮጬ ሄድኩና ወረቀቴን ይዤ ሮጬ ወጣሁ።
በሚቀጥለው ሰኞ ሌላ ትምህርት ቤት እንድገባ ተፈቀደልኝ። በዚህ ትምህርት ቤት ለመማር የሚፈቀድልኝ ከነበርኩበት ትምህርት ቤት ለምን እንደተባረርኩ ለማንም እስካልተናገርኩ ድረስ ብቻ እንደሆነ ዲሬክተሩ ነገረኝ። የክፍሌ ልጆች ከትምህርት ቤት የተባረርኩት ሌባና ዱርዬ በመሆኔ እንደሆነ እየተናገሩ ይሰድቡኝ ነበር። እውነተኛውን ምክንያት ለማስረዳት አልችልም ነበር።
የምቀመጠው ከኋላ ነበር። ከኔ አጠገብ ትቀመጥ የነበረችው ልጅ “ሃይል ሂትለር” ብዬ ሰላምታ እንደማልሰጥ አስተዋለች። እርሷም ፍሬንች ሬዚዝተር በመባል የሚታወቀውና በሕቡዕ ይሠራ የነበረው የፈረንሳይ የፖለቲካ ቡድን አባል እንደሆንሁ አድርጋ ቆጠረችኝ። ስለዚህ ሃይል ሂትለር የማልልበትን ምክንያት በግልጽ ማስረዳት ነበረብኝ። “‘መዳን በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች የለምና’ በሚለው በሥራ 4:12 መሠረት አዳኛችን ክርስቶስ ብቻ ነው። ‘ሃይል’ የሚለው ቃል ‘እገሌ አዳኝ ነው’ የሚል ትርጉም ያለው በመሆኑ ማንም ሰው ሂትለርም ጭምር መዳን ያስገኛል ማለት አልችልም” አልኳት። ይህቺ ልጅና እናቷ ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ጀምረው የይሖዋ ምሥክሮች ሆነዋል!
ድብቅ እንቅስቃሴ
በነዚህ ጊዜያት ሁሉ በድብቅ መስበካችንን ቀጥለን ነበር። በየወሩ የመጀመሪያ እሑድ በፈረንሳይ ቋንቋ የሚታተመውን የመጠበቂያ ግንብ ቅጂ ለማግኘትና ወደ ጀርመንኛ ለመተርጎም ወደ ተራራማ የእርሻ ቦታዎች እንሄዳለን። እማማ መጠበቂያ ግንብ ደብቆ መያዝ የሚያስችል የፕላስቲክ ኪስ ያለው ልዩ ቀበቶ ሰፋችልኝ። አንድ ቀን ሁለት ወታደሮች አስቆሙን፤ ወደ ተራራው ተወስደን ተፈተሽን። በዚህ ጊዜ በጣም ስለታመምኩ በሣር ድርቆሽ ላይ እንድተኛ አደረጉ። በዚህ ምክንያት መጠበቂያ ግንቡን ማግኘት አልቻሉም። ሁልጊዜም ይሖዋ በአንድ ዓይነት መንገድ ያድነኝ ነበር።
አንድ ቀን ወደ “ሥነ አእምሮ ሐኪም” መሄድ እንዳለብኝ የሚገልጽ ጥሪ ደረሰኝ። ሐኪም የተባሉት ሁለት የኤስ ኤስ ወታደሮች ሆነው ተገኙ። የይሖዋ ምሥክር የሆኑ ሌሎች ወጣቶችም እዚያው ነበሩ። እንድገባ የተጠራሁት በመጨረሻ ነበር። ሁለቱ “ዶክተሮች” ከአንድ ጠረጴዛ ኋላ ተቀምጠዋል። እንደተቀመጥኩ በፊቴ ላይ ኃይለኛ ብርሃን የሚያንጸባርቅ መብራት በርቶ መስቀለኛ ጥያቄው ጀመረ። አንዱ “ዶክተር” የጂኦግራፊ ወይም የታሪክ ጥያቄዎች ጠይቆኝ ገና መልስ ሳልሰጠው ሌላው ጣልቃ ይገባና በድብቅ ስለምናካሂደው ሥራ ይጠይቃል። የሌሎች ምሥክሮችን ስም እንድነግረው ጭምር ጠይቆኝ ነበር። በምርመራው ልሸነፍ ስደርስ ድንገት ስልክ ተደወለና ጥያቄያቸው ተቋረጠ። ሁልጊዜም ቢሆን የይሖዋ እርዳታ የሚደርስበት መንገድ በጣም አስደናቂ ነው።
የትምህርት ቤቱ ዲሬክተር ከክፍሌ ልጆች መካከል ለአንዷ ስለ እምነታችን እንዳብራራሁላት ሲያውቅ ተያዝኩና ፍርድ ቤት ቀረብኩ። ዳኛው “ጠባይ ማረሚያ ቤት” እንድገባ ፈረዱብኝ። የፍርዱ ውሳኔ እንዲህ ይል ነበር:- ‘ያደገችው በሕግ በተከለከለው በዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ትምህርት ነው። ስለዚህ ብልሹ ባሕርይ ያላት ስለሆነች ለሌሎች ልጆች አደገኛ ናት።’ በዚያ በፍርሃት በሚያስርድ የፍርድ ቤት ክፍል ውስጥ ይህን ብያኔ ማዳመጥ ለ12 ዓመት ልጅ በጣም የሚያስፈራ ነበር። ይሁን እንጂ በአስተዳዳር ክፍሉ ውስጥ የሚሠራ አንድ ርኅሩኅ ወዳጃችን ባደረገልኝ እርዳታ የተፈረደብኝ ፍርድ ወዲያው አልተፈጸመብኝም።
አንድ ወር ያህል ቀይቶ የእኛ ክፍል ለሁለት ሳምንት ያህል ወደ ሂትለር የወጣቶች ማሠልጠኛ ካምፕ እንዲሄድ ተመረጠ። ስለዚህ ጉዳይ አንዲትም ቃል ለእናቴ አልተናገርኩም። እዚያ ላለመሄድ ለማደርገው ውሳኔ ኃላፊነቱን እንድትሸከም አልፈለግሁም። የመሄጃው ቀን ከመድረሱ በፊት የትምህርት ቤቱ ዲሬክተር “ሰኞ ጠዋት በባቡር ጣቢያው ባትገኚ ወይም ቢሮዬ ባትመጪ በፖሊስ አስይዝሻለሁ!” ሲል አስጠነቀቀኝ።
ስለዚህ ሰኞ ጠዋት ወደ ትምህርት ቤት ለመሄድ በባቡር ጣቢያው በኩል አለፍኩ። የክፍሌ ልጆች በሙሉ ከእነርሱ ጋር እንድሄድ ይጠሩኝ ነበር። እኔ ግን ወደ ዲሬክተሩ ቢሮ ለመሄድ ወስኜ ነበር። እዚያ የደረስኩት ዘግይቼ ስለነበር ከሌሎች ተማሪዎች ጋር በባቡር ሄዳ ይሆናል ብሎ ገምቶ ነበር። ባየኝ ጊዜ በጣም ተናደደ። ወደሚያስተምርበት ክፍል ከወሰደኝ በኋላ የክፍሉን ልጆች በጠቅላላ ለአራት ሰዓት ያህል አሠቃያቸው። ለምሳሌ እያንዳንዱን ልጅ ወጥቶ እፊት እንዲቆም ይጠይቅና ደብተራቸውን በእጃቸው ከመስጠት ይልቅ በደብተራቸው ፊታቸውን ይመታ ነበር። ከዚያም “ይህ ሁሉ የደረሰባችሁ በእርሷ ምክንያት ነው!” ይል ነበር። የአሥር ዓመት ዕድሜ ያላቸውን 45 ልጆች በእኔ ላይ አንዲነሡብኝ ለማድረግ ሞከረ። ሆኖም የትምህርቱ ክፍለ ጊዜ እንዳበቃ የውትድርና መዝሙሮችን አልዘምርም በማለት በአቋሜ በመጽናቴ እንኳን ደስ አለሽ ለማለት ሁሉም ወደ እኔ መጡ።
ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደግሞ ወረቀት፣ ጣሳና አጥንት እየለቀምኩ ለያይቼ እንዳስቀምጥ ታዘዝኩ። ጣሳዎቹ ለውትድርና አገልግሎት የሚውሉ ስለነበሩ ይህን አላደርገውም አልኩ። ራሴን ስቼ እስክወድቅ ድረስ ተደበደብኩ። በኋላም አብረውኝ የሚማሩት ልጆች ረድተውኝ ቆሜ ለመሄድ ቻልኩ።
ተመልሼ ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ ያልጠበኩት ነገር አየሁ። 800 የሚያክሉት የሁሉም ክፍል ልጆች ከየክፍሎቻቸው ወጥተው በባንዲራ መስቀያው ዙርያ ቆመዋል። ከልጆቹ መካከል እንድቆም ተደረገ። ስለ ነፃነትና ከሃዲዎች ስለሚደርስባቸው ሁኔታ ረጅም ገለፃ ተሰጠ። በመቀጠልም ዚግ ሃይል! (ድል እና መዳን) የሚሉ ሦስት ጩኸቶች ተሰሙ። ብሔራዊ መዝሙሩ ሲዘመር እንደ እንጨት ድርቅ ብዬ ቆሜ እንቀጠቀጥ ነበር። ይሖዋ ደግፎ ስላቆመኝ ፍጹም አቋሜን መጠበቅ ቻልኩ። ከዚያም ተመልሼ እንኖርበት ከነበረው አፓርታማ እንደገባሁ ልብሶቼ አልጋ ላይ ተቀምጠው ነበር። “ሲሞን አርኖልድ ነገ ጠዋት በባቡር ጣቢያው እንድትገኝ” የሚል መልእክት የተጻፈበት ወረቀትም ነበረ።
ወደ ጠባይ ማረሚያ ቤት ተወሰድኩ
በማግስቱ ጠዋት እኔና እናቴ በባቡር ጣቢያው ተገኘን። በሁለት ሴቶች ቁጥጥር ሥር ሆንኩ። በባቡር እየተጓዝን ሳለ እናቴ ማሳየት ስለሚገባኝ ጠባይ ደጋግማ ትመክረኝ ነበር። “የፍትሕ መጓደል ቢያጋጥምሽም እንኳ ሁልጊዜ ትሑት፣ ደግና ጨዋ ሁኚ። እልከኛ መሆን ፈጽሞ የለብሽም። መጥፎ ወይም ኃይለ ቃል መናገር የለብሽም። ጽናት እልከኛ ከመሆን ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው አስታውሽ። ይሖዋ መከራ እንዲደርስብን የሚፈቅደው ለወደፊቱ ጊዜ ስለሚጠቅመን ነው። አንቺ ደግሞ ለዚህ በሚገባ ተዘጋጅተሻል። ልብስ መስፋት፣ ወጥ መሥራት፣ ልብስ ማጠብና የጓሮ አትክልት መንከባከብ ትችያለሽ። አሁን ትልቅ ልጅ ሆነሻል።”
በዚያው ምሽት ካረፍንበት ሆቴል ውጭ ባለው የወይን አትክልት ውስጥ ሆነን እኔና እናቴ በጉልበታችን ተንበርክከን ስለ ትንሣኤ የሚናገረውን የመንግሥቱን መዝሙር ከዘመርን በኋላ ጸለይን። እናቴ ድምፅዋን ከፍ አድርጋ “ይሖዋ ሆይ፣ ልጄ ታማኝነቷን እንድትጠብቅ እርዳት!” ብላ ስለ እኔ የምልጃ ጸሎት አቀረበች። እማማ አልጋው ላይ አመቻችታ አስተኛችኝና ለመጨረሻ ጊዜ ሳመችኝ።
በሚቀጥለው ቀን ጠባይ ማረሚያው ቤት እንደደረስን በነበረው ጥድፊያ እማማን ለመሰናበት እንኳ ዕድል አላገኘሁም። አንዲት ልጅ ከስንዴ ገለባ የተሠራ ፍራሽ ያለው አልጋ አሳየችኝ። ጫማዬ ተወሰደ። እስከ ኅዳር 1 ድረስ በባዶ እግራችን እንድንሄድ ተፈርዶብን ነበር። በመጀመሪያው ቀን የቀረበልኝን ምሳ ለመብላት አልቻልኩም ነበር። ስድስት የእግር ሹራቦች እንድሰፋ ተሰጠኝ። የእግር ሹራቦቹን ካልሰፋሁ በስተቀር ምንም የሚበላ ነገር ማግኘት አልችልም። ለመጀመሪያ ጊዜ ማልቀስ ጀመርኩ። የእግር ሹራቦቹ በእንባ ራሱ። ሌሊቱን ሙሉ ሳለቅስ አደርኩ።
በማግስቱ ከሌሊቱ በ11:30 ተነሣሁ። የተኛሁበትን አልጋ ደም ነክቶታል። የወር አበባዬ ከዚህ ትንሽ ቀደም ብሎ ጀምሮ ነበር። በፍርሃት ተንቀጠቀጥኩ። መጀመሪያ ወዳገኘኋት አስተማሪ ወደ ሚስ ሜሲንገር ሄድኩ። አንሶላዬን በቀዝቃዛ ውኃ እንዴት ማጠብ እንዳለብኝ የምታሳየኝ አንዲት ልጅ ጠራችልኝ። የድንጋዩ ወለል ይቀዘቅዝ ነበር፤ ሕመሙም ጠነከረብኝ። እንደገና ማልቀስ ጀመርኩ። ከዚያም ሚስ ሜሲንገር በአሽሙር ፈገግታ “አንሶላሽን እንዲያጥብልሽ ለይሖዋሽ ንገሪዋ!” አለችኝ። ይህን እንደሰማሁ ዓይኖቼን ጠራረግሁ። ከዚያ በኋላ አንድም ቀን አላለቀስኩም።
ሁላችንም ማለዳ 11:30 ላይ ተነሥተን ቤቱን ካፀዳን በኋላ በ2 ሰዓት ቁርስ እንበላለን። ቁርሳችን አንድ ሣህን ሾርባ ነበር። በቤቱ ውስጥ ለሚኖሩት ከ6 እስከ 14 ዓመት ዕድሜ ላላቸው 37 ልጆች ትምህርት ይሰጥ ነበር። ከሰዓት በኋላ ልብስ ማጠብ፣ መስፋትና የጓሮ አትክልት መኮትኮት አለብን። ከበድ ያሉ ሥራዎችን የሚሠሩልን ወንዶች አልነበሩም። በ1944/45 የክረምት ወራት ከአንዲት ልጅ ጋር ሆኜ 60 ሴንቲ ሜትር ውፍረት ያላቸውን ዛፎች በእጅ መጋዝ እቆርጥ ነበር። በጠባይ ማረሚያው ያለነው ልጆች እርስ በርስ መነጋገርም ሆነ ብቻችንን መሆን አይፈቀድልንም። ወደ ሽንት ቤትም እንኳ ብቻችንን አንሄድም ነበር። በዓመት ሁለት ጊዜ ገላችንን አንዴ ደግሞ ፀጉራችንን እንታጠባለን። ካጠፋን የሚደርስብን ቅጣት ምግብ መከልከል ወይም መደብደብ ነበር።
የሚስ ሜሲንገርን ክፍል እንዳፀዳ ታዘዝኩ። በየቀኑ አልጋ ሥር እየገባሁ የአልጋውን ሽቦ ማፅዳት እንዳለብኝ ነገረችኝ። ወደ ጠባይ ማረሚያው ደብቄ ያስገባኋት ትንሽ መጽሐፍ ቅዱስ ስለነበረችኝ ይህችን መጽሐፍ በሽቦዎቹ መካከል መደበቅ ችዬ ነበር። ከዚያ በኋላ ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን በየቀኑ ማንበብ ቻልኩ። ከልጆቹ ሁሉ ቀርፋፋዋ ልጅ ተብዬ መጠራቴ አያስገርምም!
የፕሮቴስታንት እምነት ተከታይ የሆኑት ልጃገረዶች እሑድ እሑድ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄዱ ነበር። ካቶሊክ የሆኑት ሦስቱ ልጃገረዶችም እንዲሁ ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው ሲሄዱ እኔ ግን ለ37ቱም ልጆች የሚበቃ ምግብ አበስል ነበር። በጣም ትንሽ ስለነበርኩ ሾርባውን ለማማሰል በአግዳሚ ወንበር ላይ መቆምና ማማሰያውን በሁለቱም እጆቼ መያዝ ያስፈልገኝ ነበር። ለአራቱ አስተማሪዎቻችን ደግሞ ሥጋ ወጥ መሥራት፣ ኬክ መጋገርና የአትክልት ምግብ ማዘጋጀት ነበረብኝ። እሑድ ከሰዓት በኋላ ጥልፍ መጥለፍ ነበረብን። የመጫወቻ ጊዜ አልነበረም።
አንድ አራት ወራት ካለፉ በኋላ ሚስ ሜሲንገር ፊቷ ላይ የደስታ ስሜት እየተነበበ ውዷ እማማ ተይዛ በእስረኞች ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ መሆኗን ነገረችኝ።
በ1945 ጦርነቱ አበቃ። የእስረኛ ማጎሪያ ካምፓች ስለ ፈረሱ በውስጡ ሲሠቃዩ የነበሩት እስረኞች ወጥተው አገሩን አጥለቀለቁት። በብዙ ሺህ የሚቆጠሩትም ከቤተሰቦቻቸው በሕይወት የተረፉ ካሉ ለማግኘት በየቦታው መፈለግ ጀመሩ።
በአሳዛኝ ሁኔታ እንደገና መገናኘት
እናቴ የት እንዳለሁ አውቃለች። እኔን ለመፈለግ በመጣችበት ጊዜ ግን አላወቅኋትም። በደረሰባት መከራ ምክንያት እርሷን ለይቼ ለማወቅ አለመቻሌ አያስደንቅም! እማማ እንደተያዘች የተወሰደችው የሴቶች ማጎሪያ መሆኑ ነው እንጂ አባባ ወደ ነበረበት ወደ ሽርሜክ ማጎሪያ ካምፕ ነበር። የወታደሮችን የደንብ ልብስ አልጠግንም ስላለች ከመሬት በታች ባለ በአንድ ክፍል ውስጥ ለብዙ ወራት ብቻዋን ታስራ ነበር። ቀጥሎም በሽታ እንዲጋባባት ብለው ቂጥኝ ያለባቸው ሴቶች ወደታሰሩበት ክፍል አዛወሯት። ወደ ራቨንስብሩክ በመወሰድ ላይ እንዳለች የሳል በሽታ ስለያዛት በጣም ተዳክማ ነበር። በዚያን ጊዜ ጀርመኖች አገሩን ጥለው ሸሹ። ወደ ራቨንስብሩክ በመጓጓዝ ላይ የነበሩት እስረኞች ሳይታሰብ ነፃ ሆኑ። እናቴም ከእነዚህ እስረኞች መካከል ነበረች። በቀጥታ እኔ ወዳለሁበት ወደ ኮንስተንስ አመራች። ከአየር ይጣል የነበረው ቦምብ ፍንጣሪ ፊቷን ቆራርጧትና አድምቷት ነበር።
እናቴ ወደነበረችበት ክፍል ተጠራሁ። በጣም ተለውጣ ነበር። ከረሃብ የተነሣ መንምናለች፣ የታመመች መሆኗ በግልጽ ይታያል፣ ፊቷ የተቀጠቀጠና ደም የጎረሰ ነበር። ስትናግርም ድምፅዋን መስማት የሚቻለው ትንሽ ትንሽ ብቻ ነው። በጎብኝዎች ፊት ጎንበስ ብዬ እጅ እንድነሣና የሠራኋቸውን ጥልፎችና የሰፋኋቸውን ልብሶች እንዳሳይ ማሠልጠኛ ተሰጥቶኝ ነበር። ምክንያቱም አንዳንድ የቤት እመቤቶች የቤት ሠራተኛ ለመቅጠር ወደ ጠባይ ማረሚያው ቤት ይመጡ ስለነበር ነው። ምስኪኗን እናቴን ያስተናገድኳት በዚህ መንገድ ነበር! እኔን ወደ መኖሪያ ቤታችን ለመውሰድ ሕጋዊ መብት እንዲሰጣት ወደ ዳኛ ስትወስደኝ ነበር ሴትየዋ እናቴ እንደሆነች ያወቅኋት! ላለፉት 22 ወራት በውስጤ አምቄው የነበረው እንባ ከቁጥጥሬ ውጭ በሆነ መንገድ ገንፍሎ ፈሰሰ።
የጠባይ ማረሚያ ቤቱን ለቅቀን ስንሄድ የዲሬክተሯ የሚስ ሌደርል አነጋገር ለእማማ እንደሚያርስ ዘይት ሆኖላት ነበር። “ልጅሽን ስትመጣ የነበራትን የአእምሮ ዝንባሌ እንደያዘች አስረክቤሻለሁ” አለቻት። ከጠባይ ማረሚያ ቤቱ ስወጣ የነበረኝ አቋም እንደ መጀመሪያው ነበር። አፓርታማችንን ስላገኘን እዚያው መኖር ጀመርን። አሁን የሚያሳዝነን ነገር ቢኖር የአባባ መጥፋት ብቻ ነው። ሞተዋል ተብለው በቀይ መስቀል ከተመዘገቡት ሰዎች መካከል አንዱ አባባ ነበር።
በ1945 የግንቦት ወር አጋማሽ ላይ በር ተንኳኳ። አሁንም በሩን ለመክፈት ሮጬ የሄድኩት እኔ ነበርኩ። በሩን ያንኳኳችው ማሪያ ኮኤል የተባለች ወዳጃችን ነበረች። እርሷም “ሲሞን ብቻዬን አይደለሁም። አባትሽ ደረጃውን እየወጣ ነው” አለች። አባባ ደረጃዎቹን የወጣው በጭንቅ ነበር። ጆሮውም ደንቁሯል። በአጠገቤ አልፎ በቀጥታ ወደ እማማ ሄደ! ከዚህ በፊት ያውቃት የነበረችው የ11ዓመት ልጃገረድ አሁን በእነዚህ ወራት ውስጥ አድጋ ዓይነ አፋር ወጣት ሆናለች። የዚችን አዲስ ልጃገረድ ማንነት እንኳን መለየት አልቻለም ነበር።
የደረሰበት መከራ ክፉኛ ጎድቶታል። መጀመሪያ ልዩ ካምፕ ወደነበረው ወደ ሽርሜክ ከዚያም ወደ ዳካው ተወስዷል። በዳካው እያለ የተስቦ በሽታ ይዞት ስለነበር ለ14 ቀናት ያህል ራሱን ስቶ ነበር። ቆይቶም የሕክምና መሞከሪያ ሆኗል። ከዚያም ከዳካው የከፋ ጉዳት ወደ ደረሰበትና ብዙ ሰዎች ወዳለቁበት ካምፕ ወደ ማውታውሰን ተላከ። በዚያ ከባድ የጉልበት ሥራ ይሠራ የነበረ ከመሆኑም በላይ ብዙ ጊዜ ይደበደብ እንዲሁም የፖሊስ ውሾች አንዲቦጫጭቁት ይደረግ ነበር። ሆኖም ከዚህ ሁሉ ተርፎ በመጨረሻ ወደ ቤቱ መመለስ ቻለ።
ወደ ይሖዋ ምሥክሮች የሙሉ ጊዜ አገልግሎት የገባሁት 17 ዓመት ሲሆነኝ ነው። ከዚያም በዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው የጊልያድ የሚስዮናውያን ማሠልጠኛ ትምህርት ቤት ገባሁ። በማኅበሩ ዋና መሥሪያ ቤት፣ በአንድ የሂትለር የማጎሪያ ካምፕ እያለ የይሖዋ ምሥክር የሆነውን ጀርመናዊ አይሁድ ማክስ ሌብስተርን ተዋወቅሁ። በ1956 ተጋባን። በአምላካችን በይሖዋ እርዳታ በፈረንሳይ ልዩ አቅኚዎች ሆነን እስካሁን ድረስ በሙሉ ጊዜ በማገልግል ላይ እንገኛለን።
ከብዙ ዓመታት በፊት እማማ በጠባይ ማረሚያው ቤት ትታኝ ከመሄዷ በፊት በነበረው ምሽት “ይሖዋ ሆይ፣ ልጄ ታማኝነቷን እንድትጠብቅ እንድትረዳት እማጸንሃለሁ!” ብላ በጸሎቷ የጠቀሰቻቸው ቃላት ምንኛ ተገቢ ነበሩ!
እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስም ይሖዋ ይህን የእናቴን ጸሎት መልሶልኛል። —ሲሞን አርኖልድ ሌብስተር እንደተናገረችው።
[በገጽ 40 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሲሞን አርኖልድ ሌብስተር እና ባለቤቷ ማክስ ሌብስተር