የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g94 4/8 ገጽ 20-22
  • የአንድ ቀን ውሎ በቢራቢሮ ሕይወት ውስጥ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የአንድ ቀን ውሎ በቢራቢሮ ሕይወት ውስጥ
  • ንቁ!—1994
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የፀሐይ ቁርስ
  • “ገና እንደተያዩ መፋቀር”
  • የአበባ ማር መቅመስ
  • ራስን ከአደጋ መጠበቅ
  • የመጨረሻው ጉዞ
  • ትልቁና ትንሹ
    ንቁ!—2000
  • ካቤጅ ኋይት ቢራቢሮ ክንፏን የምትዘረጋበት መንገድ
    ንድፍ አውጪ አለው?
  • አስገራሚ የሆነው የቢራቢሮ ክንፍ
    ንቁ!—2012
  • በቢራቢሮዎች፣ በዕፅዋትና በጉንዳኖች መካከል ያለ ወሳኝ ትስስር
    ንቁ!—2001
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1994
g94 4/8 ገጽ 20-22

የአንድ ቀን ውሎ በቢራቢሮ ሕይወት ውስጥ

በየቀኑ የምትሠራው ሥራ ከባድና አሰልቺ መስሎ ከታየህ ለአንድ አፍታ ቆም በልና የታታሪዋን ቢራቢሮ አኗኗር ተመልከት። ላይ ላዩን ስትመለከተው የቢራቢሮ የሥራ ፕሮግራም የተንደላቀቀና ዕረፍት የበዛበት መስሎ ሊታይህ ይችላል። ከአበባ ወደ አበባ እየተዘዋወረች ትቀስማለች፣ በፈለገችው ጊዜ ክንፏን ዘርግታ ፀሐይ ትሞቃለች። የቢራቢሮ ኑሮ ምንም ዓይነት ውጣ ውረድ ያለበት አይመስልም።

ይሁን እንጂ የበራሪ ነፍሳት ሕይወት ከውጭ እንደሚታየው ቀላል ሆኖ አይገኝም። ቢራቢሮዎች ከንጋት እስከ ምሽት ሳይታክቱ የሚሠሩና በጣም ከፍተኛ የሆነ አገልግሎት የሚሰጡ ታታሪ ፍጥረቶች ናቸው። አሁን የአንዲት ቢራቢሮ የሥራ ቀን ምን እንደሚመስል እንመል⁠ከት።

የፀሐይ ቁርስ

ከእንቅልፍህ ስትነሣ መንቀሳቀስ እስከማትችል ድረስ ድክምክም ብሎህ ያውቃልን? የማለዳ ድካምና መፍዘዝ በቢራቢሮዎች ዘንድ በጣም የተስፋፋ ችግር ነው። በአንዳንድ ጠዋቶች ፈጽሞ መንቀሳቀስ እንኳን ያቅታቸዋል። ችግራቸው እንደ አካባቢው የአየር ሁኔታ የሚለዋወጠው የሰውነታቸው ሙቀት ነው። ሌሊቱን አንድ ቅጠል ሥር ተለጥፈው ስለሚያሳልፉ ደማቸው በጣም ከመቀዝቀዙ የተነሣ መብረር ይቅርና መንቀሳቀስ አንኳን ያቅታቸዋል። በዚህ ምክንያት የፀሐይዋን መውጣት ለመጠባበቅ ይገደዳሉ።

ፀሐይ ስትወጣ ቢራቢሮዋ ክንፎችዋን ትከፍትና የፀሐይዋን ጨረር ሙሉ በሙሉ ለማግኘት ወደሚያስችላት አቅጣጫ ታዞራለች። የተዘረጋው ክንፍዋ የፀሐይዋን ሙቀት ቶሎ ብሎ ስለሚሰበስብላት ቢራቢሮዋ ወዲያው መብረር ትጀምራለች። ይሁን እንጂ ሰማዩ ደመናማ ከሆነስ? ቀዝቀዛ በሆኑት አካባቢዎች ፀሐይ እስኪወጣላት ድረስ አመቺ በሆነ ቅርንጫፍ ወይም አበባ ላይ ተለጥፋ ሳትነቃነቅ ትቆያለች። ይህን የምታደርገው በስንፍና ምክንያት ሳይሆን ግዴታ ስለሆነባት ነው።

የቀኑ ሙቀት አነስተኛ ከሆነ በየጊዜው ቆም እያለች የፀሐይ ሕክምና ትወስዳለች። አንድ መኪና ወደ ነዳጅ ማደያ ጎራ ብሎ ነዳጅ እንደሚሞላ ቢራቢሮዋም ራስዋን በፀሐይ ኃይል መሙላት ያስፈልጋታል። በሞቃታማ አካባቢዎች ፀሐይ መሞቅ የሚያስፈልጋት ጠዋት ብቻ ወይም ዝናብ ከዘነበ በኋላ ብቻ ነው። በአጠቃላይ የአየሩ ሁኔታ በቀዘቀዘ መጠን ፀሐይ በመሞቅ የምታሳልፈው ጊዜ ይጨምራል። የሚያስፈልጋትን ጉልበት ካገኘች በኋላ ግን ከፊትዋ የሚጠብቃትን ሥራ ማከናወን ትጀምራለች።

“ገና እንደተያዩ መፋቀር”

በጣም አስቸኳይ የሆነው ሥራ የጾታ ጓደኛ ማግኘት ነው። የቢራቢሮ ዕድሜ ከጥቂት ሳምንታት ስለማይዘልል በዚህ ረገድ የሚባክን ጊዜ አይኖርም። በቢራቢሮዎች ዓለም ውስጥ ደግሞ የጾታ ጓደኛ ማግኘት ቀላል ነገር አይደለም። ከፍተኛ ትዕግሥትና ጽናት የሚጠይቅ ጉዳይ ነው።

በቢራቢሮዎች ዓለም ውስጥ ገና እንደተያዩ መፋቀር ፈጽሞ አይታወቅም። ከርቀት የማየት ችሎታቸው በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ብዙ ጊዜ ሌላው ዓይነት የቢራቢሮ ዝርያ የራሳቸው ዓይነት ዝርያ ይመስላቸዋል። በዚህ ምክንያት ወንዱ ቢራቢሮ ከራሱ ዝርያ የተለየችውን ዝርያ ሲያሳድድ ከዋለ በኋላ ዓይኑ እንዳታለለው በሚገነዘብበት ጊዜ ድካሙ ሁሉ ከንቱ ይሆንበታል።

እንስቷ ቢራቢሮ ቶሎ ብላ ፈቃደኛ አለመሆኗ ደግሞ የወንዱን ቢራቢሮ ሕይወት ይበልጥ ያከብድበታል። በስሜት የተቃጠለው ቢራቢሮ ሴቲቱን ቢራቢሮ እሺ ለማሰኘት በአየር ላይ ዝግተኛ ዳንስ በሚመስል አበራረር ተስፋ ሳይቆርጥ ይከታተላታል። ይሁን እንጂ ይህ አስደናቂ የሆነ የቢራቢሮ ዳንስ እንስቷ ተባዕቱን ጥላ ስትሄድ በድንገት ይቆማል። ያልታደለው ቢራቢሮ ሌላ እንስት ፍለጋ ይዳክራል።

የተባዕት ቢራቢሮው የተዋበ ቀለም እንስትዋን እምብዛም አይማርካትም። ዳርዊን የቢራቢሮዎች ደማቅ ቀለም ‘የኢቮሉሽን ጥቅም’ አስገኝቶላቸዋል ብሎ ቢገምትም ይህን የሚያረጋግጥ ማስረጃ አልተገኘም። በአንድ ሙከራ አናርቲያ አማቲያ የተባሉት የሰሜን አሜሪካ እንስት የቢራቢሮ ዘሮች የደማቅ ቀይና የጥቁር ቡራቡሬ የሆነው ክንፋቸው ጥቁር ቀለም ከተቀባላቸው ተባዕት ቢራቢሮዎች ጋር በደስታ የጾታ ግንኙነት ፈጽመዋል። እንስቶቹ ይበልጥ የሚማረኩት በተባዕቱ አበራረር፣ ተስፋ ባለ መቁረጡና ከሁሉ በላይ ደግሞ ልዩ በሆነው “የፍቅር አቧራ” ነው።

ተባዕቱ ድል እንዲያደርግ የሚያስችለው በፍቅር አቧራ ውስጥ የሚገኘው ፈሮሞን የተባለው ስሜት ቀስቃሽ ቅመም ነው። ይህ ቅመም የራሱ ዝርያ የሆኑትን እንስት ቢራቢሮዎች ስሜት ብቻ እንዲቀሰቅስ ሆኖ የተዘጋጀ ነው። እንስቷን በሚከታተልበት ጊዜ በዚህ “ልዩ ሽታ” ሊያጥናት ይሞክራል። የፍቅር አቧራው ለሴቲቱ መሸነፍ ዋስትና ሊሆን ባይችልም ፈቃደኛ እንስት በም⁠ትገኝበት ጊዜ አስደናቂ ውጤት ያስገኛል።

የአበባ ማር መቅመስ

የጾታ ጓደኛ ለማግኘት የባከነው ይህ ሁሉ ጉልበት መተካት ይኖርበታል። ለዚህም ቢራቢሮዎች ያበባ ማርን ይመጥጣሉ። አበቦች ማራኪ በሆነው ቀለማቸውና ቅርጻቸው ይህ ጉልበት ሰጪ ምግብ በውስጣቸው የሚገኝ መሆኑን ያበስራሉ። ቢራቢሮው አበባው ላይ ከተቀመጠ በኋላ ቀሰም የመሰለ ረዥም አፉን ወደ አበባው ሰድዶ ይመጥጣል።

ቢራቢሮው የአበባውን ማር በሚቀስምበት ጊዜ የአበባው ብናኝ ወይም ፖለን ፀጉራማ በሆነው አካሉ ላይ ያርፋል። በዚህ መንገድ ፖለኑን ቀጥሎ ወደሚጎበኘው አበባ ወስዶ ያራግፈዋል። በአንድ የሥራ ቀን ውስጥ በመቶ የሚቆጠሩ አበቦች በፖለን ይዳብራሉ። ይሁን እንጂ በምድር ወገብ በሚገኙ ሞቃት አካባቢዎች ብዙ አበቦች አይገኙም። ታዲያ በዚህ አካባቢ የሚኖሩ ቢራቢሮዎች ምን ይመ ጥጣሉ?

በምድር ወገብ አካበቢ በሚገኙ ሞቃት አካባቢዎች የሚኖሩ ቢራቢሮዎች የበሰበሰ ፍራፍሬ ከመመገብ የበለጠ የሚወዱት ነገር የለም። በጣም በስሎ መሬት ላይ ከሚወድቀው ፍሬ በርካታ ኃይል ሰጪ ስኳር ያገኛሉ።

ቢራቢሮዎች ጨውም ይወዳሉ። እርጥብ ከሆነ መሬት የሚወጣውን ጨዋማ እርጥበት፣ አልፎ አልፎም በአድናቆት ሊመለከታቸው በያዛቸው ሰው እጅ ላይ የሚያገኙትን ላብ ይመጥጣሉ። እንዲያውም ደፋር የሆነችው አብሪ ቢራቢሮ የአዞዎችን እንባ ስታደርቅ ታይታለች።

ባለ ክንፉ ወዳጃችን የጾታ ጓደኛ ፍለጋ፣ አበቦችን በማዳበርና ራሱን በመመገብ ሲባዝን የሚውል ቢሆንም ራሱን ከጠላቶች መጠበቅ ያስፈልገዋል። ምንም ዓይነት መከላከያ ያለው መስሎ ባይታይም ራሱን የሚጠብቅባቸው ብዙ ዘዴዎች አሉት።

ራስን ከአደጋ መጠበቅ

ብርቅርቅ ባሉ ቀለማት አሸብርቆ በአውላላ ሜዳ ላይ የሚበርረው ቢራቢሮ ነፍሳትን አሳድዳ ለምትበላ ወፍ ጣፋጭ ጉርሻ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ቢራቢሮው ቀጥተኛ ባልሆነና ወጣ ገባ በሆነ መስመር ስለሚበርር ወፍዋ ለመያዝ በጣም ትቸገራለች። አብዛኞቹ ወፎች ቢራቢሮ ለመያዝ ጥቂት ሙከራ ካደረጉ በኋላ ተስፋ ቆርጠው ይተዋሉ። ተሳክቶላቸው ቢይዙት እንኳን ክንፉን አፋቸው ውስጥ ትቶላቸው ሊያመልጥ ይችላል።

ሌላው ራሱን እንዲጠብቅ የሚያስችለው መሣሪያ ዓይኑ ነው። ቢራቢሮዎች ከርቀት የማየት ችሎታቸው አነስተኛ ቢሆንም የብዙ ዓይኖች ውህድ የሆነው ዓይናቸው በአካባቢ የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን የመለየት ከፍተኛ ችሎታ አላቸው። ቢራቢሮዎችን ፎቶግራፍ ለማንሣት የሞከረ ሰው ሁሉ እንደሚያውቀው አደጋ የሚመጣባቸው ከመሰላቸው ወዲያው ይሸሻሉ።

አንዳንድ የበረራ ፍጥነት የሌላቸው ቢራቢሮዎች ሌላ ዓይነት ራሳቸውን የሚጠብቁበት መሣሪያ አላቸው። እርሱም መጥፎ ሽታቸው ነው። ይህን ሽታ የሚያገኙት እጭ በነበሩበት ጊዜ ከሚመገቡአቸው መርዛማ ዕፅዋት ነው። አንድ ወፍ ይህችን ባለ መጥፎ ሽታ ቢራቢሮ ቀምሶ ካየ ሁለተኛ ያችን ዓይነት ቢራቢሮ ለመብላት አይደፍርም። ብዙ ጊዜ እንደነዚህ ያሉት ባለ መጥፎ ሽታ ቢራቢሮዎች ቀለማቸው በጣም ደማቅ ነው። ይህም ለወፎቹ ጥሩ ማስጠንቀቂያ ይሆናቸዋል።

የመጨረሻው ጉዞ

ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ አብዛኞቹ ቢራቢሮዎች ከጥቂት ሳምንታት የበለጠ ዕድሜ ባይኖራቸውም አንዳንዶቹ ዝርያዎች እስከ 18 ወር የሚደርስ ዕድሜ እንዳላቸው ይናገራል። አንዳንዶቹ በቀዝቃዛዎቹ የክረምት ወራትና በሐሩር አካባቢ አገሮች ደግሞ በደረቆቹ ወራት ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ ሳያደርጉ ተኝተው ይቆ⁠ያሉ።

ቢራቢሮዎች ዕድሜያቸው አጭር ቢሆንም አስደናቂ ሥራ ያከናውናሉ። ባለፈው መቶ ዘመን ሞናርክ የተባለው የቢራቢሮ ዘር የአትላንቲክ ውቅያኖስን አቋርጦ በአፍሪካ ዳርቻ በሚገኙት የካነሪ ደሴቶች ሊሰፍር ችሏል። ፔይንትድ ሌዲ የተባለችው የረዥም ርቀት ተጓዥ የቢራቢሮ ዘር ደግሞ በየዓመቱ በበጋ ወራት ከሰሜን አፍሪካ ወደ ሰሜን አውሮፓ ትጓዛለች።

ደከመኝ የማይሉት ቢራቢሮዎች በአጭሩ የሕይወት ዘመናቸው አበቦች፣ ቁጥቋጦዎችና የፍራፍሬ ዛፎች እንዲራቡ በማድረግ በጣም አስፈላጊ የሆነ አገልግሎት ይሰጣሉ። ከዚህም በላይ የቢራቢሮዎች መኖር ራሱ ለገጠሩ አካባቢ ልዩ የሆነ ውበትና ደስታ ይሰጣል። ቢራቢሮዎች ካልኖሩ በጋ በጋ ሊሆን አይችልም።

[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በጠዋት ፀሐይ መሞቅ

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

አበባ መቅሰም

[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ከመሬት እርጥበት መምጠጥ

[ምንጭ]

Courtesy of Buckfast Butterfly Farm

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ