የይሖዋ ምሥክሮችና የሕክምና ባለሙያዎች ተባብረው ይሠራሉ
የይሖዋ ምሥክሮች ደም መውሰድ ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ የደም አጠቃቀም መሆኑን ያስተዋሉት በ1945 ነበር። በሙሴ ሕግ ከተጠቀሰው በተጨማሪ በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችም ውስጥ ደም መብላትን አጥብቆ የሚከለክል ሕግ ተላልፏል። ሥራ 15:28, 29 እንዲህ ይላል:- “ለጣዖት ከተሠዋ፣ ከደምም፣ ከታነቀም፣ ከዝሙትም ትርቁ ዘንድ ከዚህ ከሚያስፈልገው በቀር ሌላ ሸክም እንዳንጭንባችሁ እኛና መንፈስ ቅዱስ ፈቅደናልና፤ ከዚህም ሁሉ ራሳችሁን ብትጠብቁ በመልካም ትኖራላችሁ። ጤና ይስጣችሁ።” (ዘሌዋውያን 17:10–12 ተመልከት።) ምሥክሮቹ ደም አንወስድም ማለታቸው ከአንዳንድ የሕክምና ባለሙያዎች ጋር ብዙ ውዝግቦችን ፈጥሮባቸዋል።
የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች
የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል ምሥክሮቹ ደም አንወስድም የሚል አቋም የወሰዱበትን ምክንያት በግልጽ ለማስረዳት፣ ሐኪሞችና ሆስፒታሎች ለምሥክሮቹ ያላቸውን የተሳሳተ አመለካከት ለማስወገድ፣ ምሥክር በሆኑ ሕሙማንና በሕክምና ተቋማት መካከል ይበልጥ ተግባብቶ የመሥራት መንፈስ እንዲኖር ለማድረግ በማሰብ የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎችን አቋቁሟል። የጎለመሱ እንዲሁም ከሐኪሞችና ከሆስፒታሎች ጋር መግባባት የሚያስችል ሥልጠና ያገኙ ወንድሞች የሚገኙባቸው እነዚህ ኮሚቴዎች አለመግባባቶችን ለማስወገድና ይበልጥ ተባብሮ የመሥራት መንፈስ ለማስገኘት አስችለዋል። በ1979 እንዲህ ያሉት ኮሚቴዎች በጣት የሚቆጠሩ ብቻ ነበሩ። ዛሬ ግን በ65 አገሮች 850 የሚያክሉ ኮሚቴዎች አሉ። በአሁኑ ጊዜ 3.5 ሚልዮን የሚሆኑ የይሖዋ ምሥክሮች ኮሚቴዎቹ ከሚሰጡት አገልግሎት ተጠቃሚዎች ለመሆን ችለዋል።
ሐኪሞች ደም ሳይሰጡ በሽተኞቻቸውን ማከም የሚያስችሏቸውን ዘዴዎች በሙሉ ከሕክምና ጽሑፎች መመልከት እንዲችሉ ለመርዳት በይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ ከ4, 500 በላይ የሆኑ ሽማግሌዎች ከሐኪሞች ጋር ለመወያየት የሚያስችላቸውን ሥልጠና አግኝተዋል። ሐኪሞች ምሥክሮችን ያለ ደም ለማከም ልዩ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ አስፈላጊዎቹ ጽሑፎች በቀጥታ ወደ ሆስፒታሉ በፋክስ ይላካሉ። አለዚያም ኮሚቴዎቹ ደም አልባ ሕክምና ወይም ቀዶ ሕክምና ለማድረግ የሚስችሉ ዘዴዎችን ያዳበሩና ለመርዳት ፈቃደኛ የሆኑ ሐኪሞችን ማማከር የሚቻልበትን ዝግጅት ያደርጋሉ።
ለምሳሌ ሐኪሞች በከባድ የደም ማነስ ሕመም የተጠቁ ሰዎችን ቀይ የደም ሴሎች ቁጥር ከፍ ለማድረግ ደም መውሰድ የግድ አስፈላጊ ነው ብለው በተናገሩባቸው በጣም በርካታ በሆኑ አጋጣሚዎች ላይ የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ አባላት ኤሪትሮፖየቲን (ኢፒኦ) የሚባል ሰው ሠራሽ ቅመም ተፈላጊውን ውጤት ለማስገኘት ፍቱን መሆኑን የሚገልጹ በሕክምና ጽሑፎች ላይ የወጡ ማብራሪያዎችን ለሐኪሞች ለማሳየት ችለዋል። ይህ ሰው ሠራሽ ቅመም በአጥንት ውስጥ ያለው ቅልጥም አዲስ ቀይ የደም ሴሎችን ሠርቶ ወደ ደም እንዲልክ የሚቀሰቅሰው በኩላሊት ውስጥ በተፈጥሮ የሚገኝ ኤሪትሮፖየቲን የተባለ ሆርሞን የሚያከናውን ዓይነት ተግባር ያከናውናል።
አንዳንድ ሐኪሞች ኢፒኦ የሚፈለገውን ያህል በፍጥነት እንደማይሠራ ይሰማቸው ነበር። ሆኖም በፍጥነት ጥሩ ውጤት የሚያስገኝ መሆኑ የይሖዋ ምሥክር በሆኑ ብዙ ሕሙማን ላይ ታይቷል። ይህን ለማረጋገጥ በተደረገ አንድ ሙከራ ላይ እንደታየው ለሕመምተኛው ኢፒኦ በተሰጠበት ቀን ላይ የአዳዲስ የደም ሴሎች ብዛት ከጤነኛ ሰው በአራት እጥፍ ይበልጥ ነበር! በሚቀጥለው ቀን የሕመምተኛው የውስጥ አሠራር ተስተካከለ። በአራተኛው ቀን ሙሉ እድገት ያላቸው የቀይ ደም ሴሎች ቁጥር ከፍ ማለት ጀመረ። ከጥቂት ቀናት በኋላ የቀይ የደም ሴሎች ቁጥር በፍጥነት ጨመረ። በሽተኛው ከሞት ተረፈ። በዚህ መንገድ ሐኪሞችም ሆነ በሽተኛው የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴው በሚያደርጋቸው የሥራ እንቅስቃሴዎች ተጠቅመዋል።
በአውስትራሊያ የሚገኙ ሐኪሞች እምብዛም በማይከሰት የሀሩር አካባቢ በሽታ የተያዘን አንድ ምሥክር ያለ ደም ሕይወቱን ማትረፍ እንደማይችሉ በተሰማቸው ጊዜ ደም አልባ የሆነ ሕክምና ለመስጠት የሚያስችላቸው መረጃ ማግኘት ይችሉ እንደሆነ በአካባቢው ለሚገኘው የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ አስቸኳይ ጥያቄ አቀረቡ። እርዳታ የሚያስፈልግ መሆኑ በአውስትራሊያ ለሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ቅርንጫፍ ቢሮ ተነገረ። እነርሱም በብሩክሊን ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ ያለው የሆስፒታል መረጃ አገልግሎት መረጃ እንዲሰጣቸው ጠየቁ። የመረጃ አገልግሎቱም ስለ ሕክምና በወጡ ጽሑፎች ላይ ምርምር አደረገ። ያለ ደም ሕክምና ለመስጠት የሚረዱ ጽሑፎች ወደ አውስትራሊያ በፋክስ ተላኩ። የአውስትራሊያው የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ አባል የሆነው ወንድም ከሐኪሙ ቢሮ በወጣ በ11 ሰዓት ውስጥ አስፈላጊዎቹን ጽሑፎች ይዞ ወደ ሐኪሙ ቢሮ ተመለሰ። የተሰጡት መረጃዎች ፍቱን ነበሩ፤ በሽተኛውም አገገመ። የሕክምና መረጃዎችን የያዙ ጽሑፎች ከኒው ዮርክ እስከ ኔፓል ድረስ በፋክስ ተልከዋል።
ጥራት ያለው ምርምርና እርዳታ
የይሖዋ ምሥክሮች በሕክምና ጽሑፎች ላይ የሚያደረጉት ምርምር አስተማማኝና በቅርቡ የተደረጉትን ግኝቶች ሁሉ አሰባስቦ የያዘ ነው። በዩናይትድ ስቴትስ በኦሪገን ክፍለ ሃገር በሚገኝ አንድ ሆስፒታል ውስጥ የቀዶ ሕክምና አገልግሎት ተባባሪ ዲሬክተር የሆኑ አንዲት ነርስ በቀዶ ሕክምናው ክፍል ለሚሠሩ ሠራተኞች በሚታተም መጽሔት ውስጥ በአንድ ርዕስ ላይ እንደሚከተለው ብለዋል:- “የይሖዋ ምሥክሮች . . . ከእኛ ቀድመው ሄደዋል። ደምንና የደም ተዋጽኦዎችን ስለሚተኩ አማራጭ መድኃኒቶች ከማንም የበለጠ ያውቃሉ። ብዙውን ጊዜም ሰምተነው እንኳ ስለማናውቀው ዘዴ የሚናገር ጽሑፍ ይሰጡናል።”—ኦ አር ማኔጀር የተባለ የእንግሊዝኛ መጽሔት፣ ጥር 1993፣ ገጽ 12
በሽተኞቻቸውን ያለ ደም የሚያክሙ አንዳንድ ስመ ጥር ሐኪሞችና የሕክምና ማዕከላት ስለ ደረሱባቸው ግኝቶችና ስለ ተጠቀሙባቸው አሠራሮች ምክር ለመስጠት ፈቃደኞች ሆነው ተገኝተዋል። በዚህ ረገድ በልግስና የሰጡት ምላሽ ሉኪሚያ የተባለውን በሽታ በተሳካ ሁኔታ ለማከምና ልዩ ልዩ ቀዶ ሕክምናዎችን በማከናወን የብዙዎችን ሕይወት ለማትረፍ አስችሏል። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ምክሮች የተገኙት ዓለም አቀፍ የቴሌፎን መሥመሮችን በመጠቀም ነው።
በተጨማሪም የይሖዋ ምሥክሮች እምነት ፈታኝ የሆነ የጤና ችግር ያጋጠማቸውን ለመርዳት ሕመምተኛውን ከአንዱ ሆስፒታል ወደ ሌላ ሆስፒታል፣ ከአንዱ ክፍለ ሀገር ወደ ሌላው ክፍለ ሀገር ሌላው ቀርቶ ከአንዱ አገር ወደ ሌላው አገር ለማዛወር የሚያስችል ዝግጅት እስከ ማድረግ ድረስ ጥረት አድርገዋል። አንዳንድ ምሳሌዎችን ለመጥቀስ ያህል አንዲት ሕመምተኛ ከሱሪናም ወደ ፖርቶ ሪኮ፤ ሌላውን ደግሞ ከሳሞአ ወደ ሃዋይ፤ አንዷን ሕፃን ከአውስትራሊያ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ፍሎሪዳ በአውሮፕላን ማጓጓዝ አስፈልጎ ነበር።
የሚተባበሩን ሐኪሞች ቁጥር እየጨመረ ሄዷል
በተጨማሪም ሁኔታው እየተሻሻለ መምጣቱን ደም አልባ የሆነ ሕክምና ለመስጠት ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር የሚተባበሩ ሐኪሞች ቁጥር እየጨመረ ከመሄዱ መረዳት ይቻላል። ከአምስት ዓመት በፊት አለ ደም ለማከም ፈቃደኛ የነበሩት ሐኪሞች ቁጥር 5, 000 ብቻ ነበር። ዛሬ ግን በ65 አገሮች ከ30, 000 በላይ የሚሆኑ ሐኪሞች አለ ደም ለማከም ፈቃደኛ ሆነዋል። በዚህ ረገድ ብቃት ያላቸው ሐኪሞች ቁጥር በመጨመሩ በተለያዩ አገሮች አለ ደም የውስጥ ሕክምናና የቀዶ ሕክምና አገልግሎቶች የሚሰጥባቸው ከ30 በላይ የሚሆኑ ማዕከላትን ለማቋቋም ተችሏል።
ስለዚህ በአሁኑ ጊዜ ሌላው ቢቀር በሰሜን አሜሪካ አዋቂ ሕመምተኞችን አስገድዶ ደም ለመስጠት ስለ ተደረጉ ሙከራዎች እምብዛም አይሰማም፤ ሌሎች ብዙ አገሮችም ይህን ዓይነት አመለካከት እየያዙ መጥተዋል። አሁን በአብዛኛው ችግሮች የሚከሰቱት አዲስ በተለይም እድገታቸውን ሳይጨርሱ ያለ ቀናቸው በሚወለዱ ሕፃናት ላይ ነው። እነዚህ ያለ ቀናቸው የሚወለዱ ሕፃናት እንደ ኩላሊትና ሳንባ የመሰሉት ብልቶቻቸው ገና ያልዳበሩና እንደሚገባቸው የማይሠሩ በመሆናቸው ብዙ የጤና ችግር ይደርስባቸዋል። ቢሆንም ሐኪሞች እነዚህን ችግሮች ደም ሳይሰጡ ለማከም የሚችሉባቸውን መንገዶች በመፈለግ ላይ ናቸው። ለምሳሌ የሳንባ ህብረሕዋስ አንድ ላይ እንዳይጣበቅ የሚከላከል ሰው ሠራሽ መድኃኒት በመጠቀም በእንግሊዝኛ ሪስፓይራቶሪ ዲስትረስ ሲንድሮም የሚባለውን የመተንፈስ ችግር ማስታገስ ይቻላል። ያለ ቀናቸው በተወለዱ ሕፃናት ላይ የሚከሰተውን ደም ማነስ ለማከምም ኢፒኦ የተባለውን ሰው ሠራሽ ቅመም መጠቀም በሰፊው ተቀባይነት ያገኘ ሕክምና ሆኗል።
ለሕክምና ባለሙያዎችና ለባለ ሥልጣኖች የቀረበ እርዳታ
የሕፃናት ሐኪሞች ደም ሳይሰጡ የይሖዋ ምሥክሮችን ልጆች ማከም እንዲችሉ ለመርዳት የሆስፒታል መረጃ አገልግሎት ከሕክምና ጽሑፎች ያሰባሰበውን መረጃ 55 ርዕሶችን በያዘና ሦስት ዓይነት የማመሣከሪያ ማውጫ ባለው ትልቅ መጽሐፍ አዘጋጅቶ በአራስ ልጆች ላይ የሚከሰቱትን ችግሮች አለ ደም ለማከም የሚቻልባቸውን ዘዴዎች አቅርቧል።
የይሖዋ ምሥክሮች በተለይ ለሕክምና ባለሙያዎችና ለባለ ሥልጣኖች ማለትም ለዳኞች፣ ለማኅበራዊ ጉዳይ ሠራተኞች፣ ለሕፃናት ሆስፒታሎችና ለሕፃናት ሐኪሞች ሥራ ላይ ስለዋሉ ደም አልባ የሕክምና አማራጮች መረጃዎችን ለመስጠት ሲሉ ፋሚሊ ኬር ኤንድ ሜዲካል ማኔጅመንት ፎር ጀሆቫስ ዊትነስስ የተባለ ባለ 260 ገጽ መጽሐፍ አዘጋጅተዋል።a የመመሪያ መጽሐፉ ባልተጠረዙ ወረቀቶች የተዘጋጀ ስለሆነ በቅርብ የተገኙት መረጃዎችን መጨመር ይቻላል። የይሖዋ ምሥክሮችን የቤተሰብ ኑሮ በተመለከተ አንዳንድ የተሳሳቱ አመለካከቶች በመኖራቸው መጽሐፉ ወላጆች መቶ በመቶ ጠቃሚ በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ የአኗኗር ሥርዓት መሠረት ልጆቻቸውን በፍቅር የሚያሳድጉ መሆናቸውን በተጨማሪ ይገልጻል።
ይህ ጽሑፍ ምን ያህል ተቀባይነት አግኝቷል? በዩናይትድ ስቴትስ በፔንሲልቫንያ ክፍለ ሀገር በሚገኝ አንድ የሕፃናት ሆስፒታል ምክትል ፕሬዘዳንት የሆኑ ሰው መጽሐፉን ካነበቡ በኋላ፣ ሠራተኞቻቸውም በደንብ እንዲያነቡትና እንዲጠቀሙበት የሚጠብቁባቸው መሆናቸውን ተናግረዋል። አክለውም “መጽሐፉ ተሻሽቶና አርጅቶ ካልተመለሰልኝ ምክንያቱን ማወቅ እፈልጋለሁ!” ብለዋል። አንዳንድ ዳኞች ሐኪሞች ለሕሙማን ደም ከመስጠታቸው በፊት ደም አልባ የሕክምና አማራጮችን ሁሉ ሞክረው የማየት ግዴታ እንዳለባቸው በመግለጽ የፍርድ ቤት ትእዛዛቸውን አሻሽለዋል። አለ ደም ሕክምና የተደረገላቸው ሕፃናትም ተሽሏቸው ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል።
በዩናይትድ ስቴትስ ኦሃዩ ሕጋዊ ዕድሜ ላይ ያልደረሱ ልጆችን ጉዳይ የሚመለከቱ አንድ ዳኛ ይህን ጽሑፍ ካነበቡ በኋላ የወሰዱት እርምጃ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው። ፋሚሊ ኬር በተባለው መጽሐፍ በጣም ከመነካታቸው የተነሣ ለሥራ ጓደኞቻቸውም ሰባት ተጨማሪ ቅጂዎች አዘዙ። በአሁኑ ጊዜ የሐኪሞችን ችግርና የወላጆችን መብት ግምት ውስጥ የሚያስገባ ሚዛናዊ ውሳኔ መስጠት ጀምረዋል። ይህንንም የሚያደርጉት በሁለት መንገዶች ነው። (1) ሐኪሞች ለሕሙማን ደም ከመስጠታቸው በፊት ደም አልባ የሕክምና አማራጮችን ሁሉ ሞክረው ማየት እንደሚገባቸው። (2) ሐኪሞች ለሕመምተኛው የሚሰጡት ደም ከኤድስና ከሄፓታይተስ ነፃ መሆኑ ተመርምሮ እንደተረጋገጠ የሚያሳምን ማስረጃ ማቅረብ እንዳለባቸው ይጠቅሳሉ። እኚሁ ዳኛ የፍርድ ቤት ትእዛዛቸውን ማሻሻል ከጀመሩ በኋላ ባስተላለፏቸው ሦስት ትእዛዞች ላይ ሦስቱም ልጆች ደም ሳይሰጣቸው የተሳካ ሕክምና ተደርጎላቸዋል።
በቦስተን ኮሌጅ በሕግ ትምህርት የሕግ ፕሮፌሰር የሆኑት ዶክተር ቻርልስ ኤች ባሮን ባለፈው ዓመት በፓሪስ ዩኒቨርሲቲ በተደረገው የምሁራን ስብሰባ ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርበው ነበር። በእንግሊዝኛ የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ርዕስ “ደም፣ ኃጢአትና ሞት፤ የይሖዋ ምሥክሮችና የአሜሪካ ሕሙማን መብት ንቅናቄ” የሚል ነበር። በጥናታዊ ጽሑፉ ላይ የምሥክሮቹ የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች የሚያከናውኗቸው ተግባራት እንደሚከተለው ተገልጿል:-
“ኮሚቴዎቹ የአሜሪካ የሕክምና ተቋሞች የነበሯቸውን እምነቶች አዲስ ከተገኙ ተጨማሪ መረጃዎች ጋር እንዲያስማሙና እንዲለውጡ አድርገዋቸዋል። በዚህ ምክንያት መላው የአሜሪካ ኅብረተሰብ ተጠቅሟል። በአሁኑ ጊዜ የምሥክሮቹ የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴዎች ባበረከቷቸው ሥራዎች ምክንያት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ሳይሆኑ ሕሙማን በአጠቃላይ አስፈላጊ ሳይሆን ደም የሚስዱበት አጋጣሚ በጣም ቀንሷል። የአጠቃላይ ሕሙማን መብት ንቅናቄ ክፍል የሆነው የይሖዋ ምሥክሮች እንቅስቃሴ ባስገኘው ውጤት ምክንያት ሕሙማን በብዙ የሕክምና ጉዳዮች ላይ የራሳቸውን ነፃ ውሳኔ የማድረግ መብት አግኝተዋል። በተጨማሪም ምሥክሮቹ ከእምነታቸው ጋር የማይስማሙ እርምጃዎችን እንዲወስዱ በኃይል በመጠቀም ለማስገደድ የተደረጉ ሙከራዎችን አጥብቀው በመቃወም ቆራጥ አቋም በመውሰዳቸው ነፃነት በአጠቃላይ በተለይ ደግሞ ሃይማኖታዊ ነፃነት ሊስፋፋ ችሏል።”
በሆስፒታል አገናኝ ከሚቴዎች የሚከናወነው ይህ ሥራ የአምላክን መንግሥት ምሥራች ከመስበክ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ላይኖረው ይችላል። ሆኖም እምነታችንን በቀጥታ ለሚፈታተኑ ጥያቄዎች መልስ እያስገኘ ነው። ይህም ለቅዱስ አገልግሎታችን አስተዋጽኦ የሚያደርግና በመጀመሪያው መቶ ዘመን የአስተዳደር አካል ‘የሚያስፈልጉ ነገሮች’ ተብለው ከተጠቀሱት ነገሮች መካከል አንዱ ነው። (ሥራ 15:28, 29) ከሕክምና ባለሙያዎች ጋር ድፍረትና አክብሮት በተሞላበት መንገድ የሐሳብ ልውውጥ ማድረግ መቻላችን አንዳንዶቹ የመንግሥቱን መልእክት እንዲቀበሉ መንገድ ከፍቷል። ይህም በጣም ያስደስታል። የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ አባል ከሆኑት ብዙዎቹ በኮሚቴው ሥራ ምክንያት ከተገናኟቸው ዶክተሮች ጋር የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀምረዋል። ከእነዚህ ዶክተሮች መካከል ሁለቱ በቅርቡ ተጠምቀዋል።
የሆስፒታል አገናኝ ኮሚቴ በሚሰጠው እርዳታ አማካኝነት የይሖዋ ምሥክሮች ከደም ራቁ የሚለውን ፍጹሙን የይሖዋን ሕግ ሳይጥሱና ፍጹም አቋማቸውን ሳያላሉ የሚያስፈልጋቸውን ሕክምና እያገኙ ነው። (መዝሙር 19:7) ከዚህ በፊት የነበረውን የአመለካከት ልዩነት በማስወገድ ረገድ የሚገኘው ውጤት አሁንም አላቋረጠም። ሐኪሞችና ሆስፒታሎች አሁን ከበፊቱ ጊዜ በተሻለ ሁኔታ ደም አልባ የሆነ ሕክምና ለመስጠት የሚያስችሏቸውን መረጃዎች ማግኘት ችለዋል። ይህም ሁሉም ክፍሎች ማለትም ሕሙማን፣ ዘመዶች፣ የሃይማኖት ባልደረቦችና የሆስፒታል ሠራተኞች የሚፈልጉትን የሕመምተኛውን ጤንነት መሻሻል ያስገኛል። — በመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት በሚገኘው የሆስፒታል መረጃ አገልግሎት የተጻፈ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a መጽሐፉ የሚገኘው በእንግሊዝኛ ቋንቋ ብቻ ነው።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአገናኝ ኮሚቴ አባሎች ከአንድ ሐኪም ጋር ሲወያዩ
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“ቤተሰብ የሚሰጠው እንክብካቤ”