የጭቅጭቅ መንስኤና ባሕርይ
እሷ የፈለገችው ስሜቷን ለመግለጽ ነው። እርሱ ግን መፍትሔ ለመስጠት ይፈልጋል። በዘመናት በሙሉ በትዳር ውስጥ የተነሱት በሚልዮን የሚቆጠሩ ጭቅጭቆች የተለያየ ይዘት ቢኖራቸውም በአብዛኛው በጥቂት መሠረታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሚሽከረከሩ ናቸው። የትዳር ጓደኛችሁ ከእናንተ የተለየ አመለካከት ወይም የሐሳብ አገላለጽ እንዳለው/ላት ከተረዳችሁ እንደ ቋያ እሳት የሚንቀለቀለውን ወላፈን አብርዳችሁ ደስታ የሰፈነበትን ቤት የሚያሞቅ የከሰል ፍም ለማድረግ ትችላላችሁ።
“ሕይወቴን እንድትቆጣጠሪ አልፈልግም!”
አንድ ባል ጨቅጫቃና በባልዋ ላይ ለመሠልጠን የምትፈልግ ሚስት ካለችው ከሚስቱ በሚሰነዘሩት ምክሮች፣ ጥያቄዎችና ትችቶች ምክንያት መፈናፈኛ እንዳጣ ሆኖ ሊሰማው ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ “ጠበኛ ሚስት እንደማያቋርጥ ነጠብጣብ ናት” በማለት ይህ ዓይነቱ ስሜት ሊያጋጥም የሚችል መሆኑን ያመለክታል። (ምሳሌ 19:13) ሚስት ባልዋን አንድ ነገር ስትጠይቅ እርስዋ ባላወቀችው ምክንያት ጥያቄዋን በዝምታ ያልፋል። ያልሰማ ይመስላትና ደግማ እንዲህ አድርግ ትለዋለች። በዚህ ጊዜ ባል የባሰውን ይናደድና ዝም ይላል። ሴቲቱ ነዝናዛ ሚስት፣ ወንዱ ደግሞ በሚስቱ ቁጥጥር ሥር እንደሆነ የሚሰማው ባል ናቸው? ወይስ እንዲያው ሐሳብ ለሐሳብ ያልተግባቡ ሁለት ግለሰቦች?
በሚስት አመለካከት ለባልዋ ጠቃሚ ምክር ስትሰጥ ለእርሱ ያላትን ፍቅር ከሁሉ በተሻለ መንገድ መግለጿ እንደሆነ ይሰማታል። በባልዬው አመለካከት ግን አለቃው ለመሆን መፈለግዋና ብቃት የሌለው መሆኑን ማመልከትዋ ነው። ለእርስዋ “ቦርሳህን እንዳትረሳ” ስትል አሳቢነትዋን መግለጽዋና የሚያስፈልገውን ሁሉ መያዙን ማረጋገጥዋ ነው። ለእርሱ ግን ልጅ ሳለ እናቱ “ሹራብህን ለብሰሃል?” ትለው የነበረውን ያስታውሰዋል።
ሚስት ድካም ተሰምቷት ባሏን “ዛሬ ውጭ መብላት ትፈልጋለህ?” ብላ ትጠይቃለች። እንደ እውነቱ ግን “ዛሬ ስለደከመኝ ምግብ ማብሰል አልችልምና ውጭ ወጥተን እንብላ” ማለቷ ነው። ለሚስቱ ከፍተኛ አክብሮት ያለው ባል ግን ይህን አጋጣሚ በመጠቀም እርስዋ የምትሠራውን ያህል የሚጥመው ምግብ እንደሌለ ያረጋግጥላታል። አለበለዚያም ‘እንደፈለገች ልትጠመዝዘኝ ነው’ ብሎ ሊያስብ ይችላል። በዚህ ጊዜ ሚስቲቱ ቅር በመሰኘት ‘ቀድሞውንስ ምን አስጠየቀኝ?’ ትላለች።
“አትወደኝም!”
የተበሳጨውና ግራ የተጋባው ባል “እንዴት እንዲህ ይሰማታል?” “እሠራለሁ፣ የቤቱን ወጪ በሙሉ እሸፍናለሁ፣ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ አበባ አመጣላታለሁ” ይላል።
መወደድ የሁሉ ሰው የጋራ ፍላጎት ቢሆንም ሴት የምትወደድ መሆኗ በተደጋጋሚ እንዲረጋገጥላት ትፈልጋለች። አውጥታ በአፍዋ ባትናገርም በውስጧ በተለይ፣ በወርሐዊ ልማድዋ ምክንያት ስሜትዋ በሚነካበት ጊዜ ያልተፈለገች ሸክም እንደሆነች ሊሰማት ይችላል። በእነዚህ ጊዜያት ባልዋ ለብቻዋ መሆን ያስፈልጋታል ብሎ በማሰብ ሊርቃት ይችላል። እርስዋ ግን ይህን የእርሱን መራቅ በጣም የፈራችውን ነገር ማለትም የማይወዳት መሆኑን እንደሚያረጋግጥ ማስረጃ አድርጋ ትተረጉመዋለች። እንዲወዳትና ድጋፍ እንዲሰጣት ለማስገደድ ፈልጋ በቁጣ ልትናገረው ትችላለች።
“ምን ሆነሃል ውዴ?”
ወንድ አሳሳቢ ችግር ሲያጋጥመው ጸጥ ያለ ቦታ ይፈልግና ችግሩን ያሰላስላል። በዚህ ጊዜ ሚስቱ አንድ ውጥረት እንዳለበት በደመ ነፍስ ትገነዘብና ራሱን ከቀበረበት የሐሳብ ጉድጓድ ልታወጣው ትሞክራለች። ይህን ያደረገችው በቅን ልቦና ቢሆንም ባልዬው በግል ጉዳዩ እንደገባችበትና እንዳዋረደችው አድርጎ ይቆጥረዋል። ከሐሳቡ ነቅቶ ወደኋላው ዞር ሲል ታማኝ ሚስቱ በቁርጠኝነት ስትከታተለው ይመለከታል። “እባክህ ምን ሆነሃል? ደህና አይደለህም እንዴ? እስቲ እንነጋገርበት?” የሚለውን የሚስቱን ድምፅ ይሰማል።
ሚስት ምላሽ ካላገኘች በጣም ይከፋታል። እርሷ ችግር ሲያጋጥማት ከባልዋ ጋር መነጋገር ትፈልጋለች። ይህ የምትወደው ሰው ግን ስሜቱን ሊያካፍላት አይፈልግም። “ባይወደኝ ነው” ከሚል መደምደሚያ ላይ ትደርሳለች። ስለዚህ በሚስቱ አእምሮ ውስጥ የሚጉላላውን ሐሳብ ያላወቀው ባል ባገኘው መፍትሔ ረክቶ ከራሱ ውስጣዊ ዓለም ሲወጣ የሚያገኘው አፍቃሪና አሳቢ የነበረችውን የትዳር ጓደኛ ሳይሆን ቸል ያልከኝ ለምንድን ነው ብላ የምታፋጥጠውን የተቆጣች ሴት ይሆናል።
“ፈጽሞ አትሰማኝም!”
መሠረተ ቢስ ክስ ሆኖ ይሰማዋል። ከዚህ የበለጠ እንዴት ሊያዳምጣት እንደሚችል ግራ ይገባዋል። ይሁን እንጂ ሚስቱ በምትናገርበት ጊዜ ቃሎችዋ የሂሣብ ስሌት በሚያደርግ ኮምፒዩተር በመመዘን ላይ ያለ ሆኖ ይሰማታል። ባልዋ በንግግርዋ መካከል ጣልቃ ገብቶ “ታዲያ ለምን . . .” ብሎ የመፍትሔ ሐሳብ ሲያቀርብላት ጥርጣሬዋ እውነት መሆኑን ታረጋግጣለች።
ሚስት ያጋጠማትን ችግር ይዛ ወደ ባልዋ ስትመጣ አብዛኛውን ጊዜ የችግሯ ምክንያት ባልዋ መሆኑን ለመናገር ወይም ለችግርዋ መፍትሔ ለማግኘት አይደለም። ከሁሉ በላይ የምትፈልገው ደረቁን ሐቅ ብቻ ሳይሆን ስሜትዋን ጭምር በአዘኔታ የሚያዳምጣት ሰው ነው። ስለዚህ የምትፈልገው ምክር ሳይሆን ስሜትዋን የሚረዳላት ሰው ነው። አንድ ባል በቀና መንፈስ “ውዴ፣ እንዲህ ሊሰማሽ አይገባም። ነገሩኮ ይህን ያህል ከባድ አይደለም” በማለቱ ብቻ ሚስቱ በቁጣ ትገነፍላለች።
ብዙ ሰዎች የትዳር ጓደኞቻቸው በአእምሮአቸው ውስጥ ያለውን የማንበብ ችሎታ እንዲኖራቸው ይጠብቃሉ። አንድ ሰው “ከተጋባን 25 ዓመት አልፎናል” ይላል። “ይህን በሚያህል ጊዜ ውስጥ ምን እንደምፈልግ ለማወቅ ካልቻለች ለማወቅ አትፈልግም ወይም በቂ ትኩረት አላደረገችም ማለት ነው።” አንድ ደራሲ ስለ ጋብቻ ግንኙነት በጻፉት መጽሐፍ እንዲህ ብለዋል:- “የጋብቻ ተጓዳኞች ምን እንደሚፈልጉ ከመናገር ይልቅ እርስ በርስ ከተተቻቹና እንዲህ አላደረግህም፣ እንዲህ አላደረግሽም እየተባባሉ ከተካሰሱ የፍቅርና የትብብር መንፈስ እየጠፋ ይሄዳል። በቦታው . . . እያንዳንዱ ተጓዳኝ ሌላው ፍላጎቱን እንዲፈጽምለት የሚያስገድድበት የትግል መድረክ ይከፈታል።”
“ፈጽሞ ኃላፊነት አይሰማህም!”
ሚስት አፍዋን አውጥታ ባልዋን በቀጥታ እንዲህ ባትልም በአነጋገርዋና በድምፅዋ እንዲህ የሚል መልእክት ልታስተላልፍ ትችላለች። “ለምን እስካሁን አመሸህ?” የሚለው ጥያቄ መረጃ ለማግኘት ብቻ የቀረበ ሆኖ ሊታይ ይችል ይሆናል። ፈርጠም ባለ አመለካከት ሽንጧን ይዛ ከተናገረች ግን “ፈጽሞ ኃላፊነት የማይሰማህ ሰው ነህ። በጣም አስጨነቅኸኝ። አትደውልም ነበር? ለሰው አታስብም! ይኸው የሠራሁት ራት ተበላሸ” የሚል መልእክት ያስተላልፋል።
ስለ ራት መበላሸት የተናገረችው እውነት መሆኑ አይካድም። በዚህ ጉዳይ ላይ ጭቅጭቅ ከተነሣ ግን በመካከላቸው ያለውም ዝምድና መበላሸቱ ይቀር ይሆን? ዶክተር ጆን ግሬይ እንደሚሉት “አብዛኞቹ ጭቅጭቆች የሚፈጠሩት ሁለት ሰዎች ስላልተስማሙ ሳይሆን ወንድዬው ሚስቱ አስተሳሰቡን እንደማትቀበል ሲሰማው ወይም ሴቲቱ የባልዋን አነጋገር ስላልወደደች ነው።”
አንድ ሰው በራሱ ቤት ውስጥ ለአፉ ልጓም ሳያደርግ እንደልቡ መናገር አለበት ብለው የሚያስቡ ሰዎች አሉ። ይሁን እንጂ ሐሳቡን በጥሩ ሁኔታ የሚገልጽ ሰው የአድማጩን ስሜት ግምት ውስጥ በማስገባት ስምምነትና ሰላም ማስፈን ይኖርበታል። እንዲህ ያለውን አነጋገር ለትዳር ጓደኛ ቀዝቃዛ ውኃ በማቀበል ወይም ፊት ላይ በመርጨት መመሰል ይቻላል። ልዩነት ያመጣው አቀራረቡ ብቻ ነው።
የቆላስይስ 3:12-14ን ቃላት ሥራ ላይ ማዋል ጭቅጭቅ አስወግዶ ደስታ የሰፈነበት ቤት እንዲኖር ያስችላል። “እንግዲህ እንደ እግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳን ሆናችሁ የተወደዳችሁም ሆናችሁ፣ ምሕረትን፣ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ የዋህነትን፣ ትዕግሥትን ልበሱ፤ እርስ በርሳችሁ ትዕግሥትን አድርጉ፣ ማንም በባልንጀራው ላይ የሚነቅፈው ነገር ካለው፣ ይቅር ተባባሉ፤ ክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉ፤ በእነዚህም ሁሉ ላይ የፍጻሜ ማሰሪያ የሆነውን ፍቅርን ልበሱት።”
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
እሱ የሚሟገተው ስለ ሐቅ ነው፣ እሷ የምትሟገተው ስለ ስሜት ነው