የኪየቭ ሪፖርተር የይሖዋ ምሥክሮችን አደነቀ
የይሖዋ ምሥክሮች በዩክሬን በኪየቭ ከተማ ውስጥ ከነሐሴ 5 እስከ 8, 1993 ያደረጉትን ትልቅ ስብሰባ ኦሌክሳ ኩርፓስ በጣም አድንቆ ነበር። ነሐሴ 10 በወጣው ዲሞክራቲክ ዩክሬን በተባለ የኪየቭ ጋዜጣ ላይ እንዲህ በማለት ጻፈ:-
“በሪፑብሊካን ስታዲየም ይህን ያህል ቁጥር ያለው ተሰብሳቢ ከታየ ረዘም ያለ ጊዜ ሆኖታል . . . 64,000 ሰዎች (ከእነዚህ መካከል በሺህ የሚቆጠሩት ከውጪ የመጡ ናቸው) ሆቴሎች ውስጥ ሲያድሩ፣ የሸቀጣ ሸቀጥ መደብሮችን ሲጎበኙ፣ በሕዝብ መጓጓዣ ወዲያ ወዲህ ሲንቀሳቀሱ ያለውን ሁኔታ እስኪ በዓይነ ሕሊናችሁ ተመልከቱት። . . . የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ በጣም ልዩ ነበር። ንግግሩን ለሚያቀርቡ ተናጋሪዎች ሞቅ ያለ ጭብጨባ ይደረግላቸው ነበር (እንደ ጥንቱ ጥሩ ዘመን)፤ እንባ በጉንጮቼ ላይ ወረደ።
“ስለዚህ ሃይማኖት የሚያውቁት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። የይሖዋ ምሥክሮች ከኦርቶዶክስ ሃይማኖት በተለየ ሁኔታ ኢየሱስ ክርስቶስ የአምላክ ልጅ ብቻ እንደሆነና መንፈስ ቅዱስ የአምላክ ኃይል እንደሆነ ያምናሉ፤ (ሦስቱ አንድ ናቸው የሚለውን የሥላሴ እምነት አይቀበሉም)። መቃጠያ ሲኦል እንደሌለና ከባድ የሆነ ፍርድ ተከናውኖ ኃጥአን ከጠፉ በኋላ ይህ ዓለም ተለውጦ ጻድቃን የሚኖሩበት ገነት እንደሚሆን ያስተምራሉ። የዚህ እምነት ተከታዮች ለቤተሰብ ዋነኛ ትኩረት ይሰጣሉ። ይህም ቅዱስ የሆነ፣ የብዙ ነገሮች እውነተኛ መሠረት፣ በዓለም ውስጥ ካሉት ነገሮች ይበልጥ ማራኪና አስደሳች የሆነ ነገር ነው። ለወንድሞቻቸውና ለእህቶቻቸው ወዳጃዊ አመለካከት አላቸው (ሌላ እምነት ላላቸው ሰዎችም ያላቸው አመለካከት ይበልጥ የሚያስደንቅ ነው)። እንደዚህ ያለ ነገር አይቼ አላውቅም። . . .
“ቅዳሜ ነሐሴ 7 ስሜት የሚስብ ነገር ተከናወነ። በዚህ ቀን በተደረገው የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ከዚያ በፊት ሆኖ በማያውቅ መጠን 7,402 ሰዎች ተጠምቀው ነበር። ለዚህ ልዩና ታላቅ ሥነ ሥርዓት የሚገጣጠሙ ስድስት ትላልቅ ገንዳዎች በስታዲየሙ የሩጫ ሜዳ ላይ ተዘጋጁ። ስልሳ በመንፈሳዊ የጎለመሱ ወንዶች እነዚህን አዲስ የምሥራቹ ሰባኪዎች ውኃ ውስጥ ሙሉ በሙሉ በማጥለቅ ጥምቀቱን አከናወኑ። ሙሉው የጥምቀት ሥነ ሥርዓት የፈጀው 2 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ነበር። . . .
“አዲሶቹ ደቀ መዛሙርት በስታዲየሙ ውስጥ በአምስት ረድፍ ሲጓዙ በስብሰባው ላይ የተገኙት የይሖዋ ምሥክሮች ያጨበጭቡላቸው ነበር። በኪየቭ የተጠመቁት ብዛት ከዚህ ቀደም በ1958 ኒው ዮርክ ውስጥ በተደረገው ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ ከተመዘገበው ቁጥር [7,136] የሚበልጥ ነበር። ባጭሩ የይሖዋ ምሥክሮች ባላቸው እንዲህ ባለው ግሩም ድርጅታዊ አሠራር ይህ ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ብዙም ሳይቆይ የኦርቶዶክስን እምነት ለረዥም ጊዜያት ሲከታተሉ የቆዩ ብዙ ነፍሳትን መማረኩ የማይቀር ነው።
“የልዩ ልዩ ሃይማኖት መሪዎች ይቅርታ ያድርጉልኝና በመካከላቸው ያለውን እርባና የሌለው ንትርክ እስካላቆሙ ድረስ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሃይማኖታዊ ሰዎችን ያጣሉ። ይህ ስብሰባ ከተለያየ ብሔርና አገር በተውጣጡ ሰዎች መካከል ሰላምና ስምምነት ሊገኝ እንደሚችል አሳይቷል።”
[በገጽ 14 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በዩክሬን በኪየቭ ከተማ ውስጥ በተደረገው ትልቅ ስብሰባ ላይ ከተጠመቁት 7,402 ሰዎች መካከል ጥቂቶቹ