የወጣቶች ጥያቄ . . .
ራስን መግደል መፍትሔ ይሆናልን?
“በየጠዋቱ መነሳት ሰልችቶኛል። የማደርገው ይጠፋኛል። በጣም ተናድጃለሁ። ልቤ ቆስሏል። . . . ስለዚህ ሁሉንም ጥዬ ለማለፍ አስቤአለሁ። . . . ለማለፍ አልፈልግም፣ ግን የግድ ራሴን ማጥፋት እንዳለብኝ ይሰማኛል። . . . የወደፊቱን ጊዜ ስመለከት የሚታየኝ ጨለማና ሥቃይ ብቻ ነው።”— 21 ዓመት የሆነው ፒተርa ራሱን ሲገድል ጽፎ የተወው ማስታወሻ
በዩናይትድ ስቴትስ ሁለት ሚልዮን የሚያክሉ ወጣቶች ራሳቸውን የመግደል ሙከራ እንዳደረጉ ሊቃውንት ይናገራሉ። ከእነዚህ መካከል በአንድ ዓመት ውስጥ 5,000 የሚያክሉት ራሳቸውን ይገድላሉ። ይሁን እንጂ ወጣቶች ራሳቸውን የሚገድሉት በዩናይትድ ስቴትስ ብቻ አይደለም። በ1990 በሕንድ አገር 30,000 የሚያክሉ ወጣቶች ራሳቸውን ገድለዋል። እንደ ካናዳ፣ ፊንላንድ፣ ፈረንሣይ፣ እስራኤል፣ ኔዘርላንድ፣ ስፔይን፣ ስዊዘርላንድ እና ታይላንድ ባሉት አገሮች ራሳቸውን የሚገድሉ ወጣቶች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ጨምሯል።
አንድ ሰው በከፍተኛ ሐዘን ቢዋጥና ምንም ዓይነት መውጫ በሌለው ችግር ውስጥ ተተብትቦ እንደተያዘ ቢሰማውስ? ራሱን መግደል አማራጭ የሌለው መፍትሔ ሆኖ ሊታየው ይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ ራስን መግደል አሳዛኝ የሆነ ብክነት ከመሆን አያልፍም። ከግድያው በኋላ ለወዳጆችና ቤተሰቦች ሐዘንና ምሬት ትቶ ከማለፍ ሌላ ምንም የሚፈይደው ነገር የለም። የወደፊቱ ጊዜ ምንም ያህል ጨለማ ሆኖ ቢታይ፣ ችግሮች ምንም ያህል ግዙፍ ሆነው ቢታዩ ራስን መግደል ለምንም ነገር መፍትሔ አይሆንም።
አንዳንዶች እንዲህ የሚሰማቸው ለምንድን ነው?
ጻድቁ ኢዮብ ተስፋ መቁረጥ ምን ማለት እንደሆነ ያውቅ ነበር። ኢዮብ ቤተሰቡን፣ ንብረቱንና ጤንነቱን ካጣ በኋላ “ነፍሴም ከአጥንቴ ይልቅ መታነቅንና ሞትን መረጠች” ብሎ ነበር። (ኢዮብ 7:15) ዛሬም አንዳንድ ወጣቶች እንዲህ ተሰምቷቸዋል። አንድ ጸሐፊ “ጭንቀት . . . ሥቃይ (የስሜት መጎዳትና ፍርሃት) ያስከትላል። ይህ ደግሞ ከሥቃዩ ለማምለጥ የሚያስችል እርምጃ ወደ መውሰድ ይመራል” ብሏል። ስለዚህ ራስን መግደል ለመሸከም የማይቻል ከሚመስል ሥቃይ ለማምለጥ የሚደረግ የተሳሳተ እርምጃ ነው።
እንደዚህ ያለውን ሥቃይ የሚያስከትሉ ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ከወላጆች፣ ከወንድ ወይም ከሴት ጓደኛ ጋር በሚፈጠር የከረረ ጠብ ምክንያት የሚመጣ ሊሆን ይችላል። 16 ዓመት የሆነው ብራድ ከሴት ጓደኛው ጋር ተጣልቶ ከተለያየ በኋላ በጣም ተጨነቀ። ቢሆንም ስለ ተሰማው ስሜት ከማንም ጋር አልተነጋገረም። ራሱን ሰቅሎ በመግደል ሁኔታው ፍጻሜ እንዲያገኝ አደረገ።
የአሥራ ዘጠኝ ዓመትዋ ሱኒታ ወላጆችዋ ከወንድ ጓደኛዋ ጋር ዝሙት እንደምትፈጽም ሲያውቁባት ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ወደቀች። “በዚህ ዓይነት ሁኔታ ለመኖር እንደማልፈልግ አውቅ ነበር። ስለዚህም አንድ ቀን ማታ ቤት ገባሁና የአስፕሪን ኪኒኖች አከታትዬ ዋጥኩ። በማግስቱ ደም ማስታወክ ጀመርኩ። ላጠፋ የፈለግኩት ሕይወቴን ሳይሆን አኗኗሬን ነበር” በማለት የደረሰባትን ሁኔታ ታስታውሳለች።
ትምህርት ቤትም ለከፍተኛ ተጽእኖ ምክንያት ሊሆን ይችላል። ወጣቱ አሺሽ (ዶክተሮች የሆኑት) ወላጆቹ እርሱም ዶክተር እንዲሆን ከፍተኛ ግፊት ያደርጉበት ስለነበረ እንቅልፍ ማጣትና ራሱን ከሰዎች ማግለል ጀመረ። ወላጆቹ ከሚፈልጉት የትምህርት ደረጃ ለመድረስ ስላልቻለ እንቅልፍ የሚያስወስድ መድኃኒት ከመጠን በላይ ዋጠ። ይህም በምሳሌ 15:13 ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌ ያስታውሰናል። “በልብ ኀዘን ግን ነፍስ ትሰበራለች።”
የቤተሰብ ችግር
ለአንዳንድ ወጣቶች ራሳቸውን እንዲገድሉ ምክንያት የሚሆናቸው የወላጆች መፋታት ወይም መለያየት፣ ወደ አዲስ ቦታ መዛወር ወይም የአንድ የቤተሰብ አባል ሞት የመሰለ የቤተሰብ ችግር ነው። ለምሳሌ ያህል ቀደም ብሎ የተጠቀሰው ብራድ ሁለት የቅርብ ወዳጆቹና አንድ ዘመዱ በመኪና አደጋ ሞቱበት። ከዚያም ቤተሰቦቹ የገንዘብ ችግር ደረሰባቸው። ብራድ ፈጽሞ መቋቋም የማይችለው ሁኔታ ሆነበት። “ነፍሴ መከራን ጠግባለችና . . . በአንድነትም ያዙኝ” ሲል እንደጮኸው መዝሙራዊ ሳይሰማው አልቀረም።— መዝሙር 88:3, 17
በአስደንጋጭ ሁኔታ ቁጥራቸው እየጨመረ የሄደ ወጣቶች ደግሞ ሌላ ዓይነት አስጨናቂ ሁኔታ እያጋጠማቸው ነው። በአካላቸው፣ በስሜታቸውና በሩካቤ ሥጋ የሚፈጸምባቸው በደል ነው። በሕንድ አገር ራሳቸውን የሚገድሉ ወጣቶች ቁጥር በጣም ከፍተኛ ከሆነባቸው ክፍላተ ሐገራት አንዷ ኬረላ ናት። በዚህች ክፍለ ሐገር ብዙ ወጣት ሴቶቸ በአባቶቻቸው በሚፈጸምባቸው ግፍ ምክንያት ራሳቸውን ለመግደል ሞክረዋል። በመላው ዓለም በልጆች ላይ የሚፈጸሙ የተለያዩ ግፎች በጣም ተስፋፍተዋል፤ ይህ ደግሞ ግፍ በተፈጸመባቸው ልጆች ላይ ከፍተኛ ጭንቀት ያስከትላል።
ሌሎች የጭንቀት መንስዔዎች
ይሁን እንጂ ራስን ለመግደል የሚያነሳሱ ስሜቶች የሚመነጩት ሁሉም ውጫዊ በሆኑ ምክንያቶች ብቻ አይደሉም። ባላገቡ ወጣቶች ላይ የተደረገ የአንድ ጥናት ሪፖርት እንዲህ ይላል:- “ሩካቤ ሥጋ የሚፈጽሙና አብዝተው አልኮል የሚጠጡ ወንዶችና ሴቶች ወጣቶች ራሳቸውን ለመግደል ያላቸው ዕድል ከእነዚህ ድርጊቶች ከታቀቡት ወጣቶች የበለጠ ነው።” ሱኒታ በፈጸመችው ዝሙት ምክንያት አረገዘችና አስወረደች። (ከ1 ቆሮንቶስ 6:18 ጋር አወዳድር።) ከፍተኛ የሆነ የበደለኛነት ስሜት ስለ ተሰማት ራስዋን ለመግደል ፈለገች። ብራድም በተመሳሳይ ከ14 ዓመት ዕድሜው ጀምሮ አልኮል ይጠጣና ብዙ ጊዜም ይሰክር ነበር። አዎን፣ አልኮል ከአግባብ ውጭ ሲወሰድ “እንደ እባብ ይነድፋል።”— ምሳሌ 23:32
አንድ ሰው በውስጡ የሚመላለሰው እረፍት የሚነሳ “አሳብና ጭንቀት” ራስን የመግደል ስሜት ሊያመጣበት ይችላል። (መዝሙር 94:19 የ1980 ትርጉም ) ዶክተሮች አንዳንድ ጊዜ በባዮሎጂያዊ ምክንያቶች የሚያስጨንቅ ሐሳብ ሊመጣ እንደሚችል ይናገራሉ። ለምሳሌ በመግቢያው ላይ የተጠቀሰው ፒተር ራሱን ከመግደሉ በፊት ተመርምሮ በአንጎሉ ውስጥ የኬሚካል አለመመጣጠን ችግር እንዳለበት ታውቆ ነበር። የጭንቀት ስሜት በጊዜው እልባት ካልተደረገበት በጣም ሊባባስና ራስን መግደል እንደ ጥሩ አማራጭ ሆኖ ሊታይ ይችላል።
እርዳታ ማግኘት
ይሁን እንጂ ራስን መግደል እንደ አንድ አማራጭ ሆኖ መታየት አይኖርበትም። ሁላችንም ተገነዘብነውም አልተገነዘብነው የአእምሮ ጤና ባለሞያ የሆኑት አለን ኤል በርማንና ዴቪድ ኤ ጆብስ እንዳሉት ‘ጭንቀቶችንና ግጭቶችን በተሳካ ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስችሉ ውጪያዊና ውስጣዊ እርዳታዎችና ችሎታዎች’ አሉን። አንደኛው የእርዳታ ምንጭ ቤተሰቦቻችንና ወዳጆቻችን ሊሆኑ ይችላሉ። ምሳሌ 12:25 (የ1980 ትርጉም ) “በአሳብ መጨነቅ ሐዘንን ያመጣብሃል፤ በጎ ንግግር ግን ያስደስትሃል” ይላል። አዎን፣ የሰው ችግር ከሚገባው ሰው የተነገረ ጥሩ ቃል ከፍተኛ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል!
ስለዚህ አንድ ሰው ትካዜ ወይም ጭንቀት ከተሰማው ጭንቀቱን አምቆ ይዞ ብቻውን ባይሠቃይ ጥሩ ነው። (ምሳሌ 18:1) ችግር የደረሰበት ሰው ለሚያምነው ሰው የልቡን ገልጾ መናገር ይችላል። ከሌላ ሰው ጋር መነጋገር የስሜታችንን ክብደት ከመቀነሱም በላይ ችግራችንን አዲስ ከሆነ ሌላ አቅጣጭ እንድንመለከት ያስችለናል። ወዳጁ ወይም የሚወደው ሰው በሞት ተለይቶት ቅስሙ የተሰበረ ሰው ምሥጢረኛው ከሆነ ሰው ጋር ስለ ሐዘኑ መነጋገር ይኖርበታል። አንድ ሰው የተሰማውን ሐዘን ሲገልጥና ሲያወጣ ይጽናናል። (መክብብ 7:1–3) ራሱን እንዲገድል የሚያነሳሳው ስሜት ከተመለሰበት ይህን ምሥጢረኛ ወዳጁን ተመልሶ እንደሚያነጋግር ቃል ቢገባለት ጥሩ ይሆናል።
እርግጥ፣ የሚታመን ሰው ማግኘት ሊያስቸግር ይችላል። ይሁን እንጂ የሕይወት ጉዳይ ስለሆነ የተገኘውን ሰው መሞከር ተገቢ አይሆንምን? በራስ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚገፋፋው ስሜት በጉዳዩ ላይ የሐሳብ ልውውጥ ከተደረገበት በኋላ መጥፋቱ አይቀርም። አንዳንዶች ‘ከማን ጋር ልንነጋገር እንችላለን?’ ይሉ ይሆናል። ወላጆቻችሁ ፈሪሃ አምላክ ያላቸው ከሆኑ ‘የልባችሁን ገልጣችሁ ለምን ልትነግሯቸው’ አትሞክሩም? (ምሳሌ 23:26) ብዙዎች ከሚያስቡት የበለጠ ችግራችሁ ሊገባቸውና ሊረዷችሁ ይችሉ ይሆናል። እንደ ሐኪም ምርመራ ያለ ተጨማሪ እርዳታ የሚያስፈልግ ሆኖ ከታያቸው በዚህ ረገድ ዝግጅት ሊያደርጉላችሁ ይችላሉ።
የክርስቲያን ጉባኤ አባሎችም ሌሎቹ የእርዳታ ምንጮች ናቸው። በጉባኤ ውስጥ ያሉት በመንፈሳዊ የሸመገሉ ሰዎች ጭንቀት ያደረባቸውን ሊደግፉና ሊረዱ ይችላሉ። (ኢሳይያስ 32:1, 2፤ ያዕቆብ 5:14, 15) ሱኒታ ራስዋን ለመግደል ሙከራ ካደረገች በኋላ ከአንዲት የሙሉ ጊዜ ወንጌላዊ (አቅኚ) እርዳታ አገኘች። ሱኒታ “በችግሬ ሁሉ አልተለየችኝም። እርስዋን ባላገኝ ኖሮ ቃል በቃል አብድ ነበር” ብላለች።
ችግሩን መቋቋም
በተጨማሪም ሊያግዙን የሚችሉ ውስጣዊ እርዳታዎች አሉ። ለምሳሌ ያህል ሥቃዩ አንድ ዓይነት በደል በመፈጸም ምክንያት የመጣ የበደለኛነት ስሜት ነውን? (ከመዝሙር 31:10 ጋር አወዳድር።) እንዲህ ያለው ስሜት ሥር እንዲሰድ ከመፍቀድ ይልቅ ነገሩን ለማስተካከል ጥረት ማድረግ ይገባል። (ኢሳይያስ 1:18፤ ከ2 ቆሮንቶስ 7:11 ጋር አወዳድር።) ለወላጆች መናዘዝ አንደኛው አዎንታዊ እርምጃ ነው። በመጀመሪያ ላይ ሊቆጡ እንደሚችሉ አይካድም። ይሁን እንጂ እናንተን ለመርዳት በሚያስችላቸው ጉዳይ ላይ የበለጠ ትኩረት ማድረጋቸው አይቀርም። በተጨማሪም ይሖዋ ከልባቸው የተጸጸቱትን ሰዎች ‘አብዝቶ እንደሚምር’ ማረጋገጫ ተሰጥቶናል። (ኢሳይያስ 55:7) የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ንሥሐ የገቡ ሰዎችን ኃጢአት ይሸፍናል።— ሮሜ 3:23, 24
በተጨማሪም ክርስቲያኖችን እምነታቸው፣ ከቅዱሳን ጽሑፎች ያገኙት እውቀትና ከይሖዋ አምላክ ጋር ያላቸው ዝምድና ሊረዳቸው ይችላል። መዝሙራዊው ዳዊት በብዙ አጋጣሚዎች በጣም በመጨነቁ ምክንያት “ጠላት . . . ሕይወቴንም በምድር ውስጥ አጎስቁሎአታል” እስከ ማለት ደርሶ ነበር። በደረሰበት አስጨናቂ ሁኔታ አልተሸነፈም። እንደሚከተለው በማለት ጽፏል:- “በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፣ በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ለመንሁ።” “የቀድሞውን ዘመን አሰብሁ፣ ሥራህንም ሁሉ አሰላሰልሁ፤ የእጅህንም ሥራ ተመለከትሁ።”— መዝሙር 142:1፤ 143:3–5
አንድ ሰው በራሱ ላይ ጉዳት ለማድረስ የሚገፋፋው ስሜት እያየለበት ከሄደ በጸሎት ወደ ይሖዋ መጮህ ይኖርበታል። ይሖዋ የደረሰበትን ጭንቀትና ችግር ይረዳለታል፣ በሕይወት እንዲኖርም ይፈልጋል! (መዝሙር 56:8) ሥቃዩን ለመቋቋም የሚያስችለውን ‘ከፍተኛ ኃይል’ ይሰጠዋል። (2 ቆሮንቶስ 4:7) በተጨማሪም ራስን በራስ መግደል በቤተሰብ፣ በወዳጆችና በይሖዋ ላይ የሚያመጣውን ሐዘን ማሰብ ይገባል። እንደነዚህ ያሉትን ነገሮች ማሰላሰል አንድ ሰው በሕይወት እንዲቀጥል ሊረዳው ይችላል።
አንዳንዶች የደረሰባቸውን ጉዳት ፈጽሞ ሊረሱ የማይችሉ ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ እነርሱ የደረሰባቸውን ዓይነት ችግር ያሳለፉ ሌሎች ሰዎች እንዳሉ አረጋግጡላቸው። እነዚህ ሰዎች ከራሳቸው ተሞክሮ ነገሮች ሊለወጡ እንደሚችሉና እንደሚለወጡም ሊነግሯቸው ይችላሉ። እንዲህ ያለውን የመከራ ጊዜ በአሸናፊነት እንዲወጡ የሚያስችል እርዳታ ሊሰጡ የሚችሉ ሰዎች አሉ። የተጨነቁና የተከዙ ሰዎች ማግኘት የሚገባቸውን እርዳታ ሁሉ ማግኘትና በሕይወት መቀጠል ይኖርባቸዋል!
[የግርጌ ማስታወሻ]
a አንዳንዶቹ ስሞች ተለውጠዋል።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጭንቀታችሁን ለሌላ ሰው ብታዋዩ የሻለ ይሆናል