“ሳይንስ ከፍጥረት ይማራል”
ከላይ የተጠቀሰው ነሐሴ 31, 1993 ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ መጽሔት ላይ የወጣ ርዕስ ነው። ይህ ጽሑፍ ቁጥራቸው እየጨመረ የሄደ አዳዲስ ነገሮችን የሚፈለስፉ ሳይንቲስቶች በባዮሚሜቲክስ መስክ ጥናት ማድረግ እንደጀመሩ ይገልጻል። ባዮሚሜቲክስ ማለት “ሰው ሠራሽ የሆኑ ነገሮችን ለመሥራት በሞዴልነት ለመጠቀም እንዲቻል በተፈጥሮ የሚገኙ ነገሮችን አሠራርና አዘገጃጀት ማጥናት” ማለት እንደሆነ ታይምስ ገልጿል።
ጽሑፉ ዝቅተኛ የሆኑ የባሕር ፍጥረታትና ሸረሪቶች የዘመናችን ሳይንቲስቶች ሊሠሩ ከሚችሏቸው ተመሳሳይ ነገሮች በእጅጉ የሚልቅ ጥንካሬ ያላቸው ነገሮች ለመሥራት እንደሚችሉ አምኗል። ለምሳሌ ያህል አባሎን የተባለው ፍጥረት ዱቄታማ የሆነውንና ካልስየም ካርቦኔት የተባለውን ኖራ መሰል ንጥረ ነገር ከውኃ ውስጥ ለይቶ አውጥቶ እጅግ በጣም ስስ የሆኑ ጠፍጣፋ ሳህን መሰል ነገሮችን ይሠራል። ከዚያም እነዚህን እጅግ ስስ የሆኑ ሳህን መሰል ነገሮች እንደ ሲሚንቶ በሚያጣብቅ የፕሮቲንና የስኳር ውሁድ እርስ በርስ ያያይዛቸዋል። ዶክተር ሜህሜት ሳሪካያ እንደሚሉት በዚህ ዓይነት የተዘጋጀው ቅርፊት መሰል ነገር በቤተ ሙከራ ውስጥ ከሚሠራው ተራ ካልስየም ካርቦኔት በጥንካሬው 30 ጊዜ ይበልጣል። “የባሕር ፍጥረታት የሚሠሩትን ያህል ስስ የሆነ ጠፍጣፋ ነገር ለመሥራት የሚያስችል ቴክኖሎጂ የለንም” ብለዋል።
የሸረሪት ድርም በተመሳሳይ ከብረት ሽቦ የበለጠ ጥንካሬ ሲኖረው ከናይለን የበለጠ ዕድሜ አለው። ሳይንቲስቶች ጥይት የማይበሳው ልብስ ለመሥራት ከሚጠቀሙበት ኬቭላር ከተባለው ንጥረ ነገር የበለጠ ጥንካሬ ያለው ነገር ለመሥራት በማሰብ የሸረሪት ድርን አሠራር በማጥናት ላይ ናቸው። ይሁን እንጂ የሰው ልጆች እስከ ዛሬ ድረስ ሸረሪት የምትጠቀምበትን የተወሳሰበ አሠራር ለመቅዳት አልቻሉም።
በሲያትል የሚገኘው የዋሽንግተን ዩኒቨርሲቲ ባልደረባ የሆኑት ዶክተር ክሪስቶፈር ቫይኒ “ሸረሪቶች ድራቸውን የሚሠሩት ከከባቢ አየር ሙቀትና ግፊት ባልተለየ አካባቢና ውኃን በአሟሚነት በመጠቀም ነው። ብዙ የአሠራር ሂደቶችን ካለፈ በኋላ ከፍተኛ ጥንካሬ ያለውና በውኃ የማይርስ ክር ይሆናል” ብለዋል። “ሰዎች ግን እንደ ኬቭላር ያሉትን ጠንካራ ክሮች ለመሥራት በጣም ከፍተኛ ግፊትና ያልተበረዘ ሰልፊዩሪክ አሲድ ያስፈልጋቸዋል።” እኚህ ሳይንቲስት “ገና የምንማራቸው ብዙ ነገሮች አሉ” ብለዋል።
ለአንድ አፍታ ቆም ብላችሁ አስቡ። እጅግ የተራቀቀው የሰው ልጅ ቴክኖሎጂ በጣም ዝቅተኛ የሆኑት የባሕር ፍጥረታትና ሸረሪቶች ሊሠሩ የሚችሉትን መሥራት ካቃተው እነዚህ ፍጥረታት ራሳቸው በጣም ከፍተኛ የሆነ ጥበብ ያለው ፈጣሪ ውጤት መሆን አለባቸው ብሎ ማመን ምክንያታዊ አይሆንምን? የዘመናችን ሳይንቲስቶች ሥራዎቹን ለመኮረጅ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉትን ይህን ታላቅ ፈጣሪ ምድርን ወደር የለሽ በሆኑት የፍጥረት ሥራዎቹ በመሙላቱ ብናመሰግነው ትልቅ ጥበብ ይሆናል።— መዝሙር 104:24