የወጣቶች ጥያቄ . . .
ስለ አምላክ መናገር ተገቢ የሚሆነው ለምንድን ነው?
“ሁሉ ሰው የራሱ ሃይማኖት አለው። ሌሎች የአንተን አምላክ እንዲቀበሉ ለማስገደድ መሞከር የለብህም።”— የ14 ዓመቱ ራኪሽ፣ ጉያና
“የሚከተለኝን ዘለፋ ስለምፈራ ስለ አምላክ ለመናገር አመነታለሁ።”— የ17 ዓመቱ ሮሃን፣ ጉያና
“አምላክ ፈጣሪያችን ስለሆነና ከእርሱም ላገኘነው ሕይወት ባለዕዳዎች ስለሆንን ስለ አምላክ መናገር ይኖርብናል።”— የ13 ዓመቱ ማርኮ፣ ጀርመን
በርከት ያሉ ልጆች ሰብሰብ ብለው ሲጫወቱ ብትሰማ በአብዛኛው አምላክ የወጣቶች የመነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ አይደለም ከሚለው መደምደሚያ ላይ መድረስህ አይቀርም። ስለ ስፖርት፣ ስለ ልብስ፣ በቅርቡ ስለ ወጡ ፊልሞች፣ ወይም ስለ ተቃራኒ ጾታ ብታነሳ ሞቅ ያለ ውይይት ይጀመራል። ደፈር ብለህ ስለ አምላክ ብታነሳ ግን አካባቢው የጨፈገገ ደመና በሚመስል ዝምታ ይዋጣል።
አንዳንድ ወጣቶች ፈጽሞ በአምላክ አያምኑም። ሊያዩት ስለማይችሉ አምላክ ፈጽሞ የለም ብለው ያስባሉ። ስለ እርሱ መነጋገር ጊዜ ማባከን ሆኖ ይታያቸዋል። ይሁን እንጂ አምላክ የለም ብለው የሚያምኑ ወጣቶች በጣም አነስተኞች ናቸው። የሕዝብን አስተያየት ለማወቅ በተደረገ አንድ ጥናት መሠረት ከዩናይትድ ስቴትስ ወጣቶች መካከል 95 በመቶ የሚሆኑት በአምላክ ያምናሉ። እንዲያውም ይህ ጥናት እንደሚከተለው በማለት ደምድሟል:- “ለብዙ ወጣቶች የሚያምኑት አምላክ በውል ያልታወቀና ረቂቅ የሆነ አንድ ኃይል ሳይሆን የሚያደርጉትን ሁሉ የሚከታተል፣ በዚህም መሠረት ቅጣት ወይም ሽልማት የሚሰጣቸው የተወሰነ ባሕርይና አካል ያለው ነው።” ታዲያ ይህን የሚያክሉ ብዙ ወጣቶች ስለሚያምኑት ነገር ለመናገር ወደኋላ የሚሉት ለምንድን ነው?
አንዳንዶች ወደኋላ የሚሉበት ምክንያት
አንዳንዶች ስለ እምነት ጉዳዮች ከሰዎች ጋር መነጋገር መልካም ጠባይ እንዳልሆነና የሃይማኖት ጉዳይ በግል ብቻ ቢያዝ ጥሩ እንደሚሆን ይሰማቸዋል። አንዳንድ ወጣቶች ስለ አምላክ መናገር ራሱ ያሳፍራቸዋል። ‘ብቻ ደስ አይልም’ ብለው ያስባሉ።
የዕድሜ እኩዮችህ አመለካከት ምንም ይሁን ምን አንተ በዚህ ጉዳይ ላይ ያለህ አቋም ምንድን ነው? በተለይ ይህ ጥያቄ በይሖዋ ምሥክሮች ቤተሰብ ውስጥ ያደግህ ከሆነ በጣም ሊያሳስብህ ይገባል። ለምን? ምክንያቱም መመሥከር ወይም ስለ አምላክ ለሌሎች መናገር የዚህ ሃይማኖት ዋነኛ ክፍል ነው!— ኢሳይያስ 43:9, 10፤ ማቴዎስ 24:14
አንዳንድ ወጣት ምሥክሮች አልፎ አልፎ በሚያጋጥማቸው ተቃውሞና ጥላቻ ምክንያት በስብከቱ ሥራ ከመካፈል ወደኋላ ይላሉ፣ ወይም ወላጆቻቸው ስለሚገፋፏቸው ብቻ በዚህ ሥራ ይካፈላሉ። ሌሎች ደግሞ በዚህ የስብከት ሥራ ቢካፈሉም በልባቸው ጓደኞቻቸው ሲሰብኩ እንዳያይዋቸው ይመኛሉ። አንዳንዶች እምነታቸው በትምህርት ቤታቸው ሳይታወቅ ምሥጢር ሆኖ እንዲቆይ ለማድረግ ይጥራሉ። አብዛኛውን ጊዜ ይህ የሚሆነው በክፍል ጓደኞቻቸው እንዳይዘለፉ ስለሚፈሩ ነው። ሪያን የተባለው ወጣት “ጓደኞቼ አንድ የቅጽል ስም ስለሚሰጡኝና እነርሱንም ለመቋቋም የሚያስችል ድፍረት ስላልነበረኝ ስለ አምላክ ለመናገር በጣም እፈራ ነበር” ብሏል።
የመጽሐፍ ቅዱስን የሥነ ምግባር ሕግጋት እንደሚገባ ሊጠብቁ እንደማይችሉ ስለሚሰማቸው ስለ አምላክ ከመናገር ወደኋላ የሚሉም አሉ። ‘የወጣትነት ምኞታቸው’ የሚያሳድርባቸው ግፊት ስለሚሰማቸው አንድ የተሳሳተ ነገር እናደርግ ይሆናል ብለው በመፍራት ክርስቲያን መሆናቸውን ባያሳውቁ የሚሻል ሆኖ ይታያቸዋል።— 2 ጢሞቴዎስ 2:22
አንዳንዶች ስለ አምላክ የማይናገሩት ብቃት ያላቸው ሆኖ ስለማይሰማቸው ነው። ዊልተን የተባለው የአሥራ ዘጠኝ ዓመት ወጣት እንደሚከተለው ብሏል:- “ጥያቄ ቢያመጡብኝ መልስ መስጠት እንደማልችል ሆኖ ስለሚሰማኝ ለሥራ ባልደረቦቼ ስለ አምላክ መናገር በጣም ይከብደኛል። እምነቴን የሚቃወም ነገር ቢያመጡ አጥጋቢ መልስ ለመስጠት የምችል ሆኖ አይሰማኝም።”
የሁሉም ክርስቲያን ግዴታ
አንተስ ስለ አምላክ ለመናገር ወደኋላ የምትለው እነዚህን በሚመስሉ ምክንያቶች የተነሳ ነውን? ከሆነ ይህ ዓይነቱ ስሜት የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። ሌሎች ወጣቶችም እንደዚህ የመሰለውን ስሜት ታግለዋል። ይሁን እንጂ ብዙዎቹ ለሰዎች ስለ አምላክ ከመናገር ወደኋላ የሚያሰኙ ብዙ ምክንያቶች ቢኖሩም እንዲናገሩ የሚያስገድዷቸው ብዙ ምክንያቶች እንዳሉ ተገንዝበዋል። ከእነዚህ ምክንያቶች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
በመግቢያችን ላይ የጠቀስነው ወጣቱ ማርኮ አምላክ “ፈጣሪያችን ስለሆነና ከእርሱም ላገኘነው ሕይወት ባለዕዳዎች ስለሆንን” በማለት አንደኛውን ምክንያት በጥሩ ሁኔታ ገልጾታል። (ራእይ 4:11) አዎን፣ ሕይወት በጣም ውድ ስጦታ ነው። መዝሙራዊው ስለ አምላክ ሲናገር “አንተ የሕይወት ሁሉ ምንጭ ነህ” ብሏል። (መዝሙር 36:9 የ1980 ትርጉም ) ለዚህ ለተቀበልነው የሕይወት ስጦታ አመስጋኞች መሆን አይገባንምን?
አመስጋኝ መሆናችንን ከምናሳይባቸው መንገዶች አንዱ ይሖዋ አምላክን በሌሎች ፊት ማወደስ ነው። እርሱ የፀሐይ፣ የጨረቃ፣ የዝናብ፣ የምንተነፍሰው አየርና የምንመገበው ምግብ ፈጣሪ ነው። (ሥራ 14:15–17) ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “በጎ ስጦታ ሁሉ ፍጹምም በረከት ሁሉ ከላይ ናቸው” ብሏል። (ያዕቆብ 1:17) አምላክን ለእነዚህ ስጦታዎቹ ታመሰግነዋለህን? (ቆላስይስ 3:15) ይህን አመስጋኝነትህን ለመግለጽ ስለ እርሱ ለሰዎች ከመናገር የተሻለ ምን ሌላ መንገድ ሊኖር ይችላል?— ሉቃስ 6:45
አምላክም ቢሆን ስለ እርሱ እንድንናገር አዞናል። ልጁ ኢየሱስ ክርስቶስ ክርስቲያኖችን “ሂዱና አሕዛብን ሁሉ . . . እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው” ሲል አዟል። (ማቴዎስ 28:19, 20) ወጣቶች በዚህ ሥራ መካፈል ከሚጠይቀው ኃላፊነት አልተገለሉም። መዝሙራዊው እንደሚከተለው ብሏል:- “እግዚአብሔርን ከምድር አመስግኑት . . . ጎልማሶችና ቆነጃጅቶች፣ ሽማግሌዎችና ልጆች፤ የእግዚአብሔርን ስም ያመስግኑ፤ ስሙ ብቻውን ከፍ ከፍ ብሎአልና፣ ምስጋናውም በሰማይና በምድር ላይ ነው።” (መዝሙር 148:7, 12, 13) ይሁን እንጂ ይህን የሥራ ኃላፊነት እንደሸክም አድርገህ መመልከት አይኖርብህም። እንዲያውም ትልቅ መብት ነው። ‘የአምላክ የሥራ ባልደረባ’ ለመሆን ትችላለህ ማለት ነው።— 1 ቆሮንቶስ 3:9
ስለ አምላክ ለመናገር ፈጽሞ ብቃት እንደሌለህ ሆኖ ከተሰማህስ? በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመናት ይኖር የነበረው ነቢዩ ኤርምያስ እንዲህ ተሰምቶት ነበር። “ወዮ ጌታ እግዚአብሔር፣ እነሆ ብላቴና ነኝና እናገር ዘንድ አላውቅም” ብሎ ነበር። ታዲያ ይሖዋ ምን መልስ ሰጠው? “ወደምሰድህ ሁሉ ዘንድ ትሄዳለህና፣ የማዝዝህንም ሁሉ ትናገራለህና:- ብላቴና ነኝ አትበል” አለው። (ኤርምያስ 1:6, 7) ኤርምያስ በይሖዋ እርዳታ ለ40 ዓመታት ይህን የተሰጠውን ሥራ ሠርቷል!
ለዘመናችን ክርስቲያኖችም ሁኔታው ከዚህ የተለየ አይደለም። “ብቃታችን ከእግዚአብሔር ነው።” (2 ቆሮንቶስ 3:5) በተፈጥሮህ ዓይነ አፋርና ወደ ሰው መቅረብ የሚያስፈራህ ብትሆንም አምላክ ለመናገር የሚያስችልህን ድፍረት እንድታገኝ ሊረዳህ ይችላል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ “ጥሩ ብቃት ያለው” የአምላክ ቃል አስተማሪ እንድትሆን ሊረዱህ የሚችሉ ዝግጅቶች አሉ። አንድ ዓይነት እርዳታ ማግኘት የሚያስፈልግህ ሆኖ ከተሰማህ ለምን ከጉባኤህ የበላይ ተመልካቾች አንዱን አታነጋግርም? የሚያስፈልግህ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የምታደርግበት ፕሮግራም ማውጣት ወይም የተሻለ ተሞክሮ ካለው ሰው ጋር አብሮ ማገልገል ሊሆን ይችላል።
ምን ውጤት ልታገኝ ትችላለህ?
ስለ አምላክ መናገር ውጤት ያለው ሥራ እንዳከናወንህ እንዲሰማህ ያስችልሃል። በመጀመሪያ ደረጃ ከእኩዮችህ ብዙዎቹ መልስ ለማግኘት የሚቃትቱባቸው ብዙ ችግሮችና ጥያቄዎች አሏቸው። ምንም ዓይነት ጥሩ መመሪያ ስለማያገኙ ስለወደፊቱ ጊዜ ያላቸው አመለካከት ግልጽ አይደለም። ‘እዚህች ምድር ላይ የምንኖረው ለምንድን ነው? ወዴት እንሄዳለን? ይህች ዓለም ይህን ያህል በመከራ የተሞላችው ለምንድን ነው?’ እያሉ ራሳቸውን ይጠይቃሉ። አናንተ ግን ክርስቲያን በመሆንህ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ ታውቃለህ። እንዲህ ያለውን እውቀት ለጓደኞችህ ለማስተላለፍ ከአንተ የተሻለ ሰው ሊገኝ አይችልም። ከሌላ ትልቅ ሰው ጋር ከመነጋገር ይልቅ እኩያቸው ከሆንከው ከአንተ ጋር መነጋገርና ሐሳባቸውን መግለጥ ይቀላቸዋል።
እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ ተቃውሞ ያጋጥምሃል። ቢሆንም የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በደስታ የሚቀበሉ አንዳንድ ግለሰቦች ታገኛለህ። አንዲት ወጣት የይሖዋ ምሥክር በአንድ አውቶቡስ ውስጥ ተቀምጣ የግል ቅጂዋ የሆነውን ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎችና ተግባራዊ መልሶቻቸው የተባለ መጽሐፍ ታነብ ነበር።a አንድ አጠገብዋ ተቀምጦ የነበረ ወጣት አብሯት ማንበብ ጀመረ። ልጁ “በጣም ግሩም መጽሐፍ ነው! ስለ አምላክ ብዙ ይናገራል። አብዛኞቹ ሰዎች ስለ ሃይማኖት ደንታ ቢሶች ሆነዋል” አላት። ወጣትዋ ምሥክር በዚህ አጋጣሚ በመጠቀም ስለ አምላክ ስም ከወጣቱ ጋር ጠለቅ ያለ ውይይት አደረገች።
ራስህን ክርስቲያን ነኝ ብለህ ስታስተዋውቅ በክርስቲያናዊ ጠባይ የመመላለስ ግዴታ እንደሚኖርብህ አይካድም። (1 ጴጥሮስ 2:12) ይሁን እንጂ መልካም የሆነው ክርስቲያናዊ ጠባይህ የመልእክትህን ተአማኒነት ከፍ ያደርገዋል። ኤሪክ የሚባለውን ወጣት ተሞክሮ እንውሰድ። ይህ ወጣት በትምህርት ቤቱ ባሉት ወጣት ምሥክሮች መልካም ጠባይ በጣም ተነካ። ይህም ስለ አምላክ ይበልጥ ለማወቅ ያለውን ፍላጎት ቀሰቀሰበት። ወዲያው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተጀመረለት። ይህ ወጣት ዛሬ ኒው ዮርክ በሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት የሚያገለግል የተጠመቀ ክርስቲያን ሆኗል።
ስለ አምላክ መናገር ለአንተ ለራስህም ቢሆን የሚሰጠው ጥቅም አለ! ከተሳሳተ አካሄድ ሊጠብቅህ ይችላል። ባልንጀሮችህ የይሖዋ ምሥክር መሆንህን ሲያውቁ ብዙዎቹ በአክብሮት ይመለከቱሃል። የሥነ ምግባር ደረጃህ ከፍተኛ መሆኑን ሲገነዘቡና በምላሹ እንደምትመሰክርላቸው ስለሚያውቁ መጥፎ ድርጊት እንድትፈጽም ከመገፋፋት ይቆጠባሉ።
እንዲህ ሲባል ግን አፍህን በከፈትህ ቁጥር ከመጽሐፍ ቅዱስ መጥቀስ አለብህ ማለት አይደለም። ስለ ስፓርት፣ ስለ ልብስ ወይም ስለ ሙዚቃ ፍላጎት ያለህ መሆኑ ስለማይቀር አልፎ አልፎ ስለነዚህ ነገሮች መነጋገር ትችላለህ። ይሁን እንጂ ‘ከልብ ሙላት አፍ እንደሚናገር’ መዘንጋት የለብህም። (ማቴዎስ 12:34) ከልብህ አምላክን የምትወድ ከሆነ ስለ አምላክ ለመናገር መፈለግህ አይቀርም። ወደፊት በሚወጣው እትም ላይ ውጤታማ በሆነ መንገድ ስለ አምላክ ለመናገር ስለምትችልበት አንዳንድ መንገዶች እንገልጻለን።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመ።
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በሕዝባዊ አገልግሎት ሥራ እያለህ የትምህርት ቤት ጓደኞችህ እንዳያዩህ ትፈራለህን?