የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g95 10/8 ገጽ 18-20
  • ዕዳ መግባት ያዋጣልን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ዕዳ መግባት ያዋጣልን?
  • ንቁ!—1995
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ብዙ ዕዳ እንዳይኖርብህ ተጠንቀቅ
  • መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳህ ይችላልን?
  • ዕዳ በሚኖርባችሁ ጊዜ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2012
  • የገንዘብ ችግርና ዕዳ​—መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳህ ይችላል?
    የመጽሐፍ ቅዱስ ጥያቄዎችና መልሶቻቸው
  • የገንዘብ አያያዝ
    ንቁ!—2019
  • ለሰዎች ያለብን ዕዳ
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2005
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1995
g95 10/8 ገጽ 18-20

ዕዳ መግባት ያዋጣልን?

“እጅህ ውስጥ ከመግባቱ በፊት ገንዘብህን አታጥፋው።” በዛሬው ጊዜ ዕዳ መግባት ለብዙ ሰዎች የተለመደ የሕይወታቸው ክፍል ስለሆነ ቶማስ ጀፈርሰን የተባሉት የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ ፕሬዚደንት የሰጡት ይህ ምክር ዘመኑ ያለፈበት ምክር ነውን?

በብዙ አገሮች የሠራተኞች ደመወዝ ከዕቃዎች ዋጋ ጋር ሲወዳደር አነስተኛ ሲሆን የተጠራቀመ ገንዘብ ቢኖር እንኳን በዋጋ ንረት የተነሣ ተሟጥጦ ያልቃል። በተጨማሪም የሰዎች አመለካከት በኢኮኖሚ ሁኔታዎች ይለወጣል። ይሁን እንጂ ሐቀኝነት በጣም አስፈላጊ ነው። በግብር አከፋፈል ማጭበርበርና ዕዳ አለመክፈል በጣም የተስፋፋ በመሆኑ ንጹሕ ሕሊና ይዞ መኖር በጣም አዳጋች ሆኗል። የኢኮኖሚ ጉዳይ የሰዎች የዕለት ተዕለት መወያያ የሆነውና በጋዜጦች፣ በመጽሔቶችና በቴ ሌቪዥን ገንዘብ ስለማጠራቀም ወይም ስለማግኘት የሚገልጹ ጽሑፎች በብዛት የሚወጡት በዚህ ምክንያት ነው። ሰዎች የኢኮኖሚ ችግሮቻቸውን እንዴት እንደሚወጡ አጥብቀው ያስባሉ። አንተም ብትሆን ለራስህና ለቤተሰብህ የሚያስፈልገውን እንዴት ለማቅረብ እንደምትችል ማሰብህ ተገቢ ነው።— 1 ጢሞቴዎስ 5:8

የተደላደለ ኢኮኖሚ ያላቸው ሰዎች በጣም ጥቂቶች በመሆናቸው ቤተሰብህ በችግር እንዳይጠቃ እንዴት መከላከል ትችላለህ? በመጀመሪያ ደረጃ በአእምሮአችን ልንይዘው የሚገባ አንድ አስፈላጊ ቁም ነገር አለ።

ብዙ ዕዳ እንዳይኖርብህ ተጠንቀቅ

አንዳንዶች ዕዳ ውስጥ የሚገቡት ለምንድን ነው? ሰዎች ገንዘብ የሚበደሩት እንደ ሕመም ያለ አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ብቻ አይደለም። አንዳንድ ቁሳዊ ነገሮችን የማግኘት ፍላጎታቸው በጣም ከፍተኛ ሊሆን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ መበደር በራሱ ስህተት ላይሆን ይችላል። የቤት ኪራይ ከመክፈል ተበድሮ ቤት መሥራት ወይም መግዛትና ዕዳውን መክፈል የተሻለ ሊሆን ይችላል። መኪና መግዛትም አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። አንድ አባወራ ቤተሰቦቹ ደስተኛ እንዲሆኑ ይፈልጋል። የተዋጣለት ባልና አባት ለመሆን ይፈልጋል። በዚህም ምክንያት ቤተሰቦቹ ሌሎች ያሏቸውን ቁሳዊ ነገሮች ማግኘት እንደሚያስፈልጋቸው ሊሰማው ይችላል።

ገንዘብ ተበድረን የግድ አስፈላጊ ያልሆነ፣ ግን እንዲኖረን የምንፈልገውን ነገር ለመግዛት እንጓጓ ይሆናል። የአንዳንድ ነገሮች ባለቤት መሆን ያስደስታል። አይደለም እንዴ? ቆንጆ ልብስ፣ አዲስ ጫማ ወይም አዲስ መኪና ቢኖረው የማይደሰት ማን ነው? ይበልጥ የሚያምር ቤት ቢያገኝ የሚጠላ ማን ነው? ቢሆንም መጠንቀቅ ያስፈልጋል! የንግድ ሰዎች የማያስፈልገንን ነገር እንደሚያስፈልገን አድርገው ሊያሳምኑን ይችላሉ። ብዙ ትርፍ የሚያጋብሱት የማያስፈልጉ ሸቀጦችን የሚገዙበት በቂ ገንዘብ ለሌላቸው ሰዎች በመሸጥ ነው።

በተጨማሪም ያለማቋረጥ ዕዳ ለመክፈል የሚደረገው ጥረት በቤተሰብ ግንኙነት ላይ ከፍተኛ ውጥረት ሊያስከትል እንደሚችል አስታውስ። አለመግባባትና ምሬት ሊያመጣ ይችላል። የቲያትር ደራሲ የሆኑት ሄንሪክ ኢብሰን “የቤተሰብ ኑሮ በብድርና በዕዳ ላይ መመሥረት ሲጀምር ወዲያው ነጻና የሚያስደስት መሆኑ ያቆማል” ማለታቸው ትክክል ነው። ዕዳህን በጊዜው ባትከፍል ስምህ ሊጠፋ ይችላል። የተበደሩትን ገንዘብ ከነወለዱ መክፈል የተበደሩትን ገንዘብ የማጥፋትን ያህል ቀላል ስለማይሆን በዱቤ የገዙት ነገር እናገኛለን ብለው ያሰቡትን ደስታ እንዳላመጣላቸው የተገነዘቡ ሰዎች በርካታ ናቸው።

መንግሥታት በዕዳ ላይ ዕዳ እየጨመሩ የሚከፍሉትን ወለድ መከመራቸው የተለመደ ነገር ነው። ይህ የተለመደ ነገር ይሁን እንጂ እኛ ዕዳ ውስጥ የተዘፈቁትን መንግሥታት የምንመስልበት ምን ምክንያት አለ? የመንግሥታት ዕዳ ውስጥ መዘፈቅ ብልጽግና ከማስገኘት ይልቅ ድህነትና አለመረጋጋት እንዲጨምር አድርጓል። አንድ የዴንማርክ ተረት እንደሚለው “ለተበላ ዳቦ ዋጋ መክፈል ይከብዳል።”

ገንዘብህን እንዴት በጥበብ እንደምታወጣ ካወቅህ ግን ዕዳ በመጫንህ ምክንያት የሚደርስብህ ጭንቀት በእጅጉ ይቀንሳል። ስለዚህ ዕዳ ውስጥ እንድትገባ የሚያስገድድህ ሁኔታ እንዳይፈጠር ገበያ ስትሄድ ለምትገዛቸው ነገሮች በጥንቃቄ እቅድ አውጣ። እጅግ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ባለባቸው አገሮች እንኳን ቅናሽ ከሚገኝባቸው ቦታዎች በመሸመትና የግድ አስፈላጊ የሆኑ ሸቀጦችን ብቻ በመግዛት ገንዘብ ለመቆጠብ የሚቻልባቸው መንገዶች አሉ። በአቅም መኖር ለመግዛት የፈለጉትን ነገር ቆየት ብሎ ለመግዛት ወይም ለመተው ፈቃደኛ መሆንን ይጠይቃል።

ራስህን ‘ዕዳ መግባቴ በቤተሰቤ ላይ ችግር ያስከትላልን? ለመክፈል ባልችል መልካም ስሜን አያበላሽብኝምን?’ ብለህ ጠይቅ። የሰዎችን አመኔታ መልሰህ ለማግኘት በርካታ ጊዜ ሊወስድብህ ይችላል። በዚህ ረገድ የተሰጠ ተግባራዊ የሆነና ጥሩ ምክር አለ። መጽሐፍ ቅዱስ አንተና ቤተሰብህ በዕዳ ረገድ የሚያጋጥማችሁን ችግር ለመቋቋም እንድትችሉ ይረዳችሁ እንደሆነና እንዳልሆነ ለማወቅ ለምን አትመረምርም?

መጽሐፍ ቅዱስ ሊረዳህ ይችላልን?

መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉ በላይ በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ እንድንታመን ሊረዳን ይችላል። በዚህ ‘አስጨናቂ ዘመን’ እርዳታ እንደሚያስፈልገን የተረጋገጠ ነው። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) “አካሄዳችሁ ገንዘብን ያለ መውደድ ይሁን፣ ያላችሁም ይብቃችሁ፤ እርሱ ራሱ:- አልለቅህም ከቶም አልተውህም ብሎአልና፤ ስለዚህ በድፍረት:- ጌታ ይረዳኛልና አልፈራም፤ ሰው ምን ያደርገኛል? እንላለን” የሚል ምክር ተሰጥቶናል። (ዕብራውያን 13:5, 6) አምላክ የሚያስፈልገንን ሁሉ እንደሚሰጠን ማመን ምንኛ አስፈላጊ ነው!

መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዱ ሰው እንዴት ኑሮውን ማሸነፍ እንዳለበት ባይናገርም በጣም ጠቃሚ የሆኑ መመሪያዎችን ይሰጣል። ኢየሱስ ክርስቶስ አድማጮቹ ከሁሉ አስቀድመው ስለመንፈሳዊነታቸው እንዲያስቡ ሲመክር “በመንፈሳዊ የጎደላቸው ነገር እንዳለ የሚታወቃቸው ደስተኞች ናቸው” ብሏል። (ማቴዎስ 5:3 አዓት) በተጨማሪም ግብ እንድናወጣ ተመክረናል:- “በጸጥታ ለመኖር እንድትጣጣሩ፣ የራሳችሁን ጉዳይ እንድታስቡ፣ ከዚህ በፊት እንዳዘዝናችሁም በገዛ እጃችሁ እንድትሠሩ ነው። በዚህ ዓይነት በማያምኑት ሰዎች ዘንድ የተከበራችሁ ትሆናላችሁ፤ የማንም ጥገኛ ሳትሆኑ ራሳችሁን ችላችሁ ትኖራላችሁ።” (1 ተሰሎንቄ 4:11, 12 የ1980 ትርጉም) በተቻለ መጠን በጸጥታና በእርጋታ ለመኖር በአቅም መኖር አስፈላጊ አይደለምን?

የአምላክ ቃል አስተሳሰባችንን እንድናስተካክል ሊረዳን ይችላል። የምሳሌ መጽሐፍ ጸሐፊ አምላክን እንደሚከተለው ብሎ በመጠየቅ ሊኖረን የሚገባውን ሚዛናዊ አመለካከት አመልክቷል:- “ድህነትንና ባለጠግነትን አትስጠኝ፣ ነገር ግን የሚያስፈልገኝን እንጀራ ስጠኝ፣ እንዳልጠግብ እንዳልክድህም:- እግዚአብሔርስ ማን ነው? እንዳልል፤ ድሀም እንዳልሆን እንዳልሰርቅም፣ በአምላኬም ስም በሐሰት እንዳልምል።” (ምሳሌ 30:8, 9) ስለዚህ ለጊዜውም ቢሆን ኑሮህ ከሌሎች በጥቂት ቢያንስ እፍረት ሊሰማህ አይገባም። ራሳቸውን ከሌሎች ጋር እንደሚያወዳድሩት ወይም ቁሳዊ ንብረት ስለማካበት ከመጠን በላይ እንደሚጨነቁት ብዙ ሰዎች ደስታህ በቁሳዊ ነገሮች ላይ እንዲያተኩር አትፍቀድ።— ማቴዎስ 6:31–33

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ጥሩ ልማዶችን እንድትኮተኩት ሊረዳህ ይችላል። ንፉግ ሳትሆን ብኩን አለመሆንን ተለማመድ። ባሉህ ነገሮች ለመርካት ሞክር። ወጣት ከሆንክ ትላልቅ ሰዎች ለበርካታ ዓመታት ደክመው ያፈሩትን ነገር አንተ በአንድ ጊዜ ለማግኘት አትሞክር። የፍቅረ ነዋይ ባሪያ አትሁን። መጽሐፍ ቅዱስ “ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፣ አንዳንዶችም ይህን ሲመኙ፣ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ” በማለት ከገንዘብ ሳይሆን ‘ገንዘብን ከመውደድ’ እንድንጠበቅ ያስጠነቅቀናል። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) በእርግጥ የግድ በሚያስፈልጉህና እንዲሁ ብቻ እንዲኖሩህ በምትፈልጋቸው ነገሮች መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅህ በጣም አስፈላጊ ነው!

ይሁን እንጂ ገቢህ በጣም አነስተኛ እንደሆነ ይሰማሃልን? ማጣት ቀላል ነገር እንዳልሆነ የተረጋገጠ ነው። ቢሆንም ከባድ ሸክም የሚሆንብህ ወይም የገንዘብ ኪሣራ የሚያስከትልብህ ዕዳ ውስጥ ገብተህ የግድ አስፈላጊ ያልሆኑ ነገሮችን ከመግዛት አለ እነርሱ ብትኖር ይሻልሃል። ጥንቃቄ የተሞላበት ዕቅድ አውጣ። ቆጣቢ ሁን። ጥሩ ተሞክሮ ካለው ወዳጅ ተግባራዊ የሆነ ምክር ለማግኘት ትችል ይሆናል። አዲስ ሞያ ብትማር ይረዳህ ይሆን? ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥምህ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች መከተል፣ መንፈሳዊ ነገሮችን ማስቀደምና ሙሉ በሙሉ በይሖዋ መታመን እጅግ አስፈላጊ መሆናቸውን አስታውስ።— ፊልጵስዩስ 4:11–13

አዎን፣ ዕዳ መግባት የሚያዋጣ ነገር ላይሆን ይችላል። “ዕዳ የገባ ሰው በመረብ የተያዘ ሰው ነው” የሚል አባባል አለ። ዕዳ የሚያስከትለው ጭነት በቤተሰብ ሕይወት፣ በጤናና በመንፈሳዊነት ላይ ትልቅ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል። ዕዳ ተበዳሪውን ይበልጥ ሊያደኸየው ይችላል። ምሳሌ 22:7 እንዲህ ይላል:- “ባለጠጋ ድሆችን ይገዛል፣ ተበዳሪም የአበዳሪ ባሪያ ነው።” ስለዚህ አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ ከመግባት ተጠበቅ። ሐዋርያው ጳውሎስ ለክርስቲያኖች ያሳሰበው መሠረታዊ ሥርዓት ዛሬም በጣም ሊጠቅመን ይችላል:- “እርስ በርሳችሁ ከመዋደድ በቀር ለማንም ዕዳ አይኑርባችሁ፣ ሌላውን የሚወድ ሕግን ፈጽሞታልና።”— ሮሜ 13:8

በአገርህ ያለው የኢኮኖሚ ሁኔታ ምንም ዓይነት ቢሆን የአምላክን አዲስ ዓለም በእርግጠኝነትና በትምክህት ተጠባበቅ። በቅርቡ የሰው ልጅ አበዳሪና ተበዳሪ ተብሎ በሁለት ጎራ መከፈሉ ያቆማል። በአምላክ መንግሥት ውስጥ ድሀ አይኖርም። “ችግረኛውን ከቀማኛው እጅ፣ ረዳት የሌለውንም ምስኪን ያድነዋልና። ለችግረኛና ለምስኪን ይራራል፣ የችግረኞችንም ነፍስ ያድናል” የሚለው የይሖዋ ተስፋ ይፈጸማል። (መዝሙር 72:12, 13) የምድር ነዋሪዎች ነፍሳቸውን ለማቆየት ከመታገል ይልቅ ‘በብዙ ሰላም ይደሰታሉ።’— መዝሙር 37:11

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ቶማስ ጀፈርሰን

[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል18]

Painting by Gilbert Stuart. Courtesy Bowdoin College Museum of Art/Dictionary of American Portraits/Dover

[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ዕዳ ውስጥ መዘፈቅ በትዳርህ ላይ ውጥረት ሊያስከትል ይችላል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ