ሰውነትህ እንቅልፍ የሚያስፈልገው ለምንድን ነው?
“ጥሩ እንቅልፍ ባገኘሁና የተፈለገውን ገንዘብ በከፈልኩ!” በዛሬው ጊዜ ይህን የመሰለውን እሮሮ የሚያሰሙ ሰዎች በርካታ ናቸው። ብዙ ሰዎች ራሳቸውን አስገድደው ያሠራሉ። ዘመናዊው ኑሮ የሚያስከትለው ውጥረትና ጭንቀትም ቢሆን የበኩሉን ጉዳት ማድረሱ አልቀረም።
ሐኪሞች፣ ፖሊሶች፣ የእሳት አደጋ መከላከያ ሠራተኞች፣ የከባድ መኪና ሾፌሮች፣ የፈረቃ ሠራተኞች፣ ሕፃናት ልጆች ያሏቸው እናቶችና ሌሎች በርካታ ሰዎች ለሰውነታቸው አስፈላጊ የሆነውን እንቅልፍ በበቂ መጠን አያገኙም። እንቅልፍ ማጣት የሚያስከትለውን ብስጭት የቀመሱ ሁሉ ጥሩና ሰውነት የሚያድስ እንቅልፍ እንዴት ሊያገኙ እንደሚችሉ ለማወቅ ይፈልጋሉ።
እንቅልፍ የሚጫወተው ሚና
እንቅልፍ መተኛት ወይም ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ ማረፍ ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ በጋራ የሚጋሩት ባሕርይ ነው። እንደ ድመት፣ ውሻ ወይም ወፍ የመሰለ ለማዳ እንስሳ ኖሮህ የሚያውቅ ከሆነ ውሾችና ድመቶች ጥቅልል ብለው እንደሚተኙና ወፎችም ሲጨልም ፀጥ ብለው እንደሚያንቀላፉ ሳትመለከት አትቀርም። ሁሉም እንስሳት፣ አእዋፍና አነስተኛ ነፍሳት ለማለት ይቻላል፣ መተኛት ወይም ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜ እንቅስቃሴያቸውን መቀነስ ያስፈልጋቸዋል። ለሰው ልጆችም እንቅልፍ የግድ አስፈላጊ ነው።
አንዳንድ ሰዎች እንቅልፍ የዕረፍት ጊዜ ብቻ ይመስላቸዋል። ይሁን እንጂ እንቅልፍ የዕረፍት ጊዜ ብቻ አይደለም። “እንቅልፍ ጡንቻዎች የሚወጠሩበትና የሚረግቡበት፣ የደም ግፊትና የልብ ምት ከፍ የሚልበትና የሚወርድበት፣ አእምሮ ራሱ የሠራውን ፊልም የሚያጠነጥንበትና ውስብስብ ሂደቶች የሚከናወኑበት ወቅት ነው ” በማለት ዘ ቶሮንቶ ስታር ዘግቧል። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ “አንድ ሰው ሲተኛ ማንኛውም እንቅስቃሴ ይቀንስና ጡንቻዎቹ ይረግባሉ። የልቡ ምትና የአተነፋፈሱ ፍጥነት ይቀንሳል” ይላል።
የሳይንስ ሊቃውንት፣ ዶክተሮችና ተመራማሪዎች ስለ እንቅልፍ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ሰፊ ጥናት ቢያደርጉም እንቅልፍ ስለሚጫወተው ወሳኝ ሚና ገና ያልተረዷቸው በርካታ ነገሮች አሉ። እንዲያውም እነዚህ ተመራማሪዎች እንቅልፍ ምን እንደሆነ ወይም ለምን እንደምንተኛ ገና አላወቁም። በቶሮንቶ ንግሥት ኤልሳቤጥ ሆስፒታል የእንቅልፍ ምርምር ላቦራቶሪ ዲሬክተር የሆኑት ዶክተር ኤልየት ፊልፕሰን “ሰውነታችንን በሚያድሰው እንቅልፍ ወቅት የሚከናወኑትን ወሳኝ የሆኑ ባዮሎጂያዊ ሂደቶች ገና አናውቅም” ብለዋል።
በእንቅልፍ ጊዜ በሰውነታችን ውስጥ በበሽታ ተከላካይ ሕዋሶቻችን ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ለውጦች ይካሄዳሉ። የሰውነታችን የተለያዩ ክፍሎች ዕረፍት አግኝተው የዕለቱ ሥራ ካስከተለባቸው ጉዳትና ድቀት ያገግማሉ። በደም አማካኝነት የሚከናወነው አጠቃላይ የሆነ የማጽዳት ሥራ በተቀላጠፈ ሁኔታ ይከናወንና የሰውነታችን ኬሚካላዊ ሚዛን ይጠበቃል። ስለዚህ እንቅልፍ አንድን የሥራ አካባቢ አጽድቶ በማግስቱ ለሚከናወነው ሥራ ዝግጁ አድርጎ እንደሚሄድ የማታ ሠራተኞች ቡድን ነው ለማለት ይቻላል።
እንቅልፍ ከሚያከናውናቸው በጣም አስፈላጊ የሆኑ ተግባራት አንዱ የሰውነታችን ሥርዓት ነርቭ ሙሉ ቀን ባከናወነው ሥራ ምክንያት ከደረሰበት ድካም እንዲያገግም ማስቻል ነው። ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ እንደሚለው “እንቅልፍ ሰውነት፣ በተለይ ደግሞ አእምሮና ሥርዓተ ነርቭ ያጡትን ኃይልና ጉልበት መልሶ እንዲያገኙ ያስችላል።”
ምን ያህል መተኛት ያስፈልጋል?
አብዛኞቹ በጉልምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች በየምሽቱ ሰባት ወይም ስምንት ሰዓት መተኛት ያስፈልጋቸዋል። አንዳንዶች ከዚህ የበለጠ መተኛት ሲያስፈልጋቸው ከዚያ ያነሰ ሰዓት የሚበቃቸውም አሉ። አንዳንዶች አራት ወይም አምስት ሰዓት ብቻ መተኛት እንደሚበቃቸው ይናገራሉ። እርግጥ ከእነዚህ መሃል እንዳንዶቹ በቀኑ ውስጥ ለጥቂት ጊዜ ጋደም ሊሉና ሊያንቀላፉ ይችላሉ። ሕፃናት ከአዋቂዎች የበለጠ መተኛት ያስፈልጋቸዋል።
በተለይ ሰዎች እያረጁ ሲሄዱ ሌሊት በተደጋጋሚ ከእንቅልፍ እንደሚነቁ ሊገነዘቡ ይችላሉ። አንዳንዶች ከበድ ያለ የእንቅልፍ ችግር እየጀማመራቸው እንዳለ የሚያሳይ ምልክት ሊመስላቸው ይችላል። ይሁን እንጂ ሸምገል ያሉ ሰዎች ወጣት በነበሩበት ጊዜ የነበራቸው ዓይነት ድብን አድርጎ የሚወስድ እንቅልፍ ባይኖራቸውም በአንድ ምሽት ውስጥ ለጥቂት ጊዜያት መንቃት የሚያሳስብ ነገር እንዳልሆነ ጥናቶች ያመለክታሉ። እነዚህ ሰዎች ነቅተው የሚቆዩባቸው ጊዜያት አብዛኛውን ጊዜ አጭር፣ ምናልባትም ከጥቂት ደቂቃዎች የማያልፍ ሲሆን ወዲያው ተመልሶ እንቅልፍ ይወስዳቸዋል።
በማንኛውም ዕድሜ ላይ የሚገኝ ሰው ሙሉውን ሌሊት አንድ ዓይነት የሆነ ድብን አድርጎ የሚወስድ እንቅልፍ እንዲወስደው መጠበቅ የለበትም። በአንድ ሌሊት የእንቅልፍ ወቅት ውስጥ ከባድና ቀላል የእንቅልፍ ዓይነቶች ይፈራረቃሉ። አንድ ሰው በአንድ ሌሊት ውስጥ ይህን የመሰሉ በርካታ የእንቅልፍ ዑደቶች ሊፈራረቁበት ይችላሉ።
እንቅልፍ ማጣት የሚያስከትላቸው አደጋዎች
“በጣም ጥቂት እንቅልፍ የሚያገኙ ሰዎች ቁጥር መጨመር ተመራማሪዎችን በእጅጉ ማሳሰብ ጀምሯል። ለረዥም ጊዜ እንቅልፍ ማጣት በራሳችንም ሆነ በአጠገባችን በሚኖሩ ሰዎች ላይ መጥፎ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል ያስጠነቅቃሉ” በማለት ዘ ቶሮንቶ ስታር ዘግቧል።
“እንቅልፍ ያጡ ሰዎች አቅመቢስና ነጭናጮች ይሆናሉ። አንድ ሰው ለሁለት ቀናት እንቅልፍ ካጣ ረዘም ላለ ጊዜ በአንድ ነገር ላይ ማተኮር ያስቸግረዋል። . . . በተለይ በተለምዶ በሚሠራቸው ሥራዎች ላይ በርካታ ስህተት ይፈጽማል። አልፎ አልፎም ትኩረቱ ይዋዥቅበታል። . . . ከሦስት ቀን በላይ እንቅልፍ ያልተኙ ሰዎች ማሰብ፣ አጥርቶ ማየትና መስማት ያስቸግራቸዋል። አንዳንዶች በቁማቸው ይቃዣሉ ማለትም ፈጽሞ የሌለ ነገር ይታያቸዋል ወይም ይሰማቸዋል” በማለት ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳይክሎፔድያ ይገልጻል።
አንድ ሰው ለአራት ቀናት እንቅልፍ ሳይተኛ ከቆየ በተለምዶ ያከናውን ከነበራቸው ሥራዎች መካከል ጥቂቶቹን ብቻ ለማከናወን እንደሚችል በሙከራ ተረጋግጧል። ትኩረት ወይም መጠነኛ የሆነ የማሰብ ችሎታ የሚጠይቁ ሥራዎችን ፈጽሞ ሊሠራ አይችልም። እንቅልፍ ማጣት የሚያስከትለው ችግር ትኩረትና የማሰብ ችሎታ በማጣት ብቻ አያቆምም። ለአራት ተኩል ቀናት እንቅልፍ ያጣ ሰው የመቅበጥበጥ፣ የመቃዠት ወይም ግራ የመጋባት ምልክቶች ይታዩበታል፤ የሚያያቸውም ነገሮች ይጭበረበሩበታል።
እንቅልፍ ማጣት ከባድ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል። መኪና እየነዱ መሪያቸውን ጨብጠው እንዳሉ እንቅልፍ ወስዷቸው ከባድ አደጋ ያደረሱ ሰዎች በርካታ ናቸው። በተጨማሪም እንቅልፍ ማጣት ለቤተሰብና ለትዳር ችግር መንስዔ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱም አንድ ሰው ዘወትር በቂ እንቅልፍ የማያገኝ ከሆነ ነጭናጫና ከሌሎች ጋር የማይግባባ ይሆናል። ጥሩ እንቅልፍ መተኛት አንዳንዶች ከሚገነዘቡት በላይ በጣም አስፈላጊ ነው።
ጥሩ እንቅልፍ መተኛት
በቶሮንቶ ከተማ በሚገኘው የእንቅልፍ ችግር ጥናት በሚካሄድበት ማዕከል የሚሠሩትና እንቅልፍን አስመልክቶ ስፔሽያሊስት የሆኑት ዶክተር ጀፍሪ ጄ ሊፕሲትስ ጥሩ እንቅልፍ ለመተኛት የሚከተሉትን ምክሮች ይሰጣሉ። እርጋታና ጸጥታ ባለበት ጨለም ያለ አካባቢ ምቹ በሆነ አልጋ ላይ ተኛ። ወደ ቀኑ መገባደጃ ላይ አጠር ላለ ጊዜ አትተኛ። ባለፈው ሌሊት በቂ እንቅልፍ ባታገኝ እንኳን ሳትተኛ ለመቆየትና በተለመደው የመኝታ ጊዜህ ለመተኛት ሞክር። ከመተኛትህ በፊት ካፊን ያለበት ነገር አትጠጣ። አልጋህ ውስጥ ሆነህ አታንብብ ወይም ቴሌቪዥን አትመልከት። ከመተኛትህ ቀደም ብለህ ከበድ ያለ አካላዊ እንቅስቃሴ አታድርግ ወይም ከበድ ያለ ነገር አትብላ። ሰውነትህ የሚያንቀላፋበትና የሚነቃበት የተወሰነ ሰዓት ይኖረው ዘንድ ቋሚ የሆነ የመኝታ ጊዜ ይኑርህ።
አልጋ ውስጥ ከመግባትህ በፊት ሰውነትህን የሚያዝናና ነገር አድርግ። የሚያነቃህ ወይም ስሜትህን የሚያነሳሳ ነገር አታድርግ። ለምሳሌ ያህል ስሜት ቀስቃሽ የሆኑ ፊልሞችን ወይም የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ወይም መጻሕፍት አትመልከት ወይም አታንብብ። በተጨማሪም ከመኝታ በፊት ሞቅ ያለ ውይይት ማድረግ እንቅልፍ ሊያሳጣ ይችላል።
አንዳንዶች ሞቅ ባለ ውኃ (በጣም የሞቀ መሆን የለበትም) ገላቸውን መታጠብ ወይም ስሜት ቀስቃሽ ያልሆነ የሚያዝናና ጽሑፍ ማንበብ ጥሩ እንቅልፍ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። ትኩስ ወተት፣ አሬራ፣ ትንሽ የወይን ጠጅ ወይም እንደ ናና እና ካሞሚላ የመሰሉትን ቅጠሎች በሻይ መልክ መጠጣት እንቅልፍ የሚያስወስዳቸው ሰዎችም አሉ። ካፊን ያለበት ሻይ መጠጣት ግን ጥሩ አይደለም።
ይሁን እንጂ ከእንቅልፍ በፊት ሰውነትን ማዝናናት ብቻውን እንደማይበቃ ብዙዎች ይስማማሉ። ጤናማና ሚዛናዊ የሆነ ኑሮ መኖር፣ አዘውትሮ አካላዊ እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ስግብግነት፣ ምቀኝነት፣ ጥላቻና አንድ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የመድረስ ምኞት የሚያስከትሏቸውን ጭንቀቶችና ብስጭቶች ማስወገድ ጥሩ እንቅልፍ ለመተኛት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። በተጨማሪም ምግብና መጠጥ ከመጠን በላይ አለመውሰድና ከሥነ ምግባር ውጭ የሆነ ድርጊት መፈጸም ከሚያስከትላቸው ብስጭቶች የጸዳ ኑሮ መኖር ጥሩ እንቅልፍ ለማግኘት ይረዳል።
የሚያስፈልጉንን መንፈሳዊ ነገሮች ማሟላትም ጥሩና ሰውነት የሚያድስ እንቅልፍ ለመተኛት አስፈላጊ ነው። ይህን የምንኖርበትን የተወሳሰበ ዓለም እንድንረዳና የሚያረካና ሚዛኑን የጠበቀ አኗኗር እንድንከተል ያስችለናል። አንድ ጥበበኛ የአምላክ አገልጋይ ማስተዋልን እንድንኮተኩትና የይሖዋን ጥበብ አጥብቀን እንድንይዝ ይመክረናል። “እነርሱ በተድላና በደስታ የተሞላ ሕይወት ይሰጡሃል።” በመቀጠልም “በምትተኛበት ጊዜ አትፈራም፤ ሌሊቱንም ሙሉ በሰላም ታንቀላፋለህ” ብሏል።— ምሳሌ 3:21–24 የ1980 ትርጉም
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ለረዥም ጊዜ እንቅልፍ ማጣት ከፍ ያለ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አብዛኞቹ በጉልምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች በየዕለቱ ሰባት ወይም ስምንት ሰዓት መተኛት ያስፈልጋቸዋል
[በገጽ 22 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ብዙ ሰዎች የእንቅልፍ ማጣት ችግር አለባቸው