የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g96 7/8 ገጽ 14-18
  • የካታኮምብ ዋሻዎች ምን ነበሩ?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የካታኮምብ ዋሻዎች ምን ነበሩ?
  • ንቁ!—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የካታኮምብ ዋሻዎች ታሪክ
  • አንድን የካታኮምብ ዋሻ መጎብኘት
  • የተለያዩ ሐሳቦች
  • የኦዴሳ ዋሻዎች—መግቢያ መውጫው የሚያደናግር የመሬት ውስጥ መተላለፊያ
    ንቁ!—2010
  • ምስሎች
    ንቁ!—2014
ንቁ!—1996
g96 7/8 ገጽ 14-18

የካታኮምብ ዋሻዎች ምን ነበሩ?

በኢጣሊያ የሚገኘው የንቁ! መጽሔት ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

በጥንታዊቷ ሮም በመሬት ውስጥ የሚገኙ ጨለምለም ያሉ መተላለፊያዎች አሉ። እነዚህ መተላለፊያዎች የካታኮምብ ዋሻዎች ናቸው። የካታኮምብ ዋሻዎች ምንድን ናቸው? የተሠሩት ለምን ነበር?

በመሠረቱ የካታኮምብ ዋሻዎች ለመካነ መቃብርነት እንዲያገለግሉ ከድንጋይ ተፈልፍለው የተሠሩ በመሬት ውስጥ የሚገኙ መተላለፊያዎች ናቸው። “ካታኮምብ” የሚባለው ቃል ትርጉም በትክክል የማይታወቅ ቢሆንም (“በጉድጓድ ውስጥ” የሚል ትርጉም ሊኖረው ይችላል) በሮም አቅራቢያ በአፒያን ጎዳና ላይ ይገኝ የነበረ የአንድ መቃብር ቦታ ስም እንደነበረ ይታመናል። ከጊዜ በኋላ ከመሬት በታች ለሚገኙ መቃብሮች ሁሉ ይህ ስም ይሰጥ ጀመር። ምንም እንኳ በሜድትራኒያን ባሕር አካባቢ በሚገኙ አገሮች ውስጥ ብዙ የካታኮምብ ዋሻዎች ቢኖሩም በሮም የሚገኙት በይበልጥ የሚታወቁ ከመሆናቸውም በላይ በስፋት ከሌሎቹ ይበልጣሉ፤ ጠቅላላ ርዝመታቸው ብዙ መቶ ማይል እንደሚሆን ይገመታል። እስካሁን ድረስ 60 የሚያክሉ የካታኮምብ ዋሻዎች የተገኙ ሲሆን ሁሉም የሚገኙት ከታሪካዊቷ ከተማ ማዕከል ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ወጣ ብሎ ሮምን ከቀሩት ግዛቶቿ ከሚያገናኙት አውራ ጎዳናዎች ጎን ለጎን ነው።

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የሮም ክርስቲያኖች የራሳቸው የሆነ የመቃብር ቦታ ያልነበራቸውና ሰው ሲሞትባቸው አረማውያን የሚቀበሩበት ቦታ ወስደው ይቀብሩ የነበረ ይመስላል። የአረማውያን አስተሳሰብ ክርስቲያን ነን በሚሉ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ማድረግ ጀምሮ በነበረበት በሁለተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ላይ ወደ ክርስትና ሃይማኖት የተለወጡ ሀብታሞች “ለክርስቲያኖች” የሚሆኑ የመቃብር ቦታዎችን ገዙ። የቦታ ችግርን ለመፍታት ከከተማዋ ብዙም ሳይርቅ ቁፋሮ ተጀመረ።

የካታኮምብ ዋሻዎች ታሪክ

ምናልባት የመጀመሪያዎቹ ቁፋሮዎች የጀመሩት በኮረብታዎች ግራና ቀኝ ወይም ቀደም ሲል ድንጋይ ይፈለጥባቸው በነበሩ ቦታዎች ሳይሆን አይቀርም። ሉትቪክ ኸርትሊንግና ኢንግልበርት ኪርሽባኡም የካታኮምብ ዋሻዎቸን አስመልክተው በጻፉት መጽሐፋቸው ውስጥ እንዲህ ብለዋል:- “በመጀመሪያ ከሰው ቁመት ጥቂት ከፍ የሚል ክፍል ተቆፈረ። ከዚያም በስተቀኝና በስተግራ ሌሎች ክፍሎች ተቆፈሩ፤ ቆየት ብሎም እነዚህ ክፍሎች ከመጀመሪያው መተላለፊያ ትይዩ በሆነ ሌላ መተላለፊያ አማካኝነት ተያያዙ። በዚህ መንገድ በቀላሉ ተጀምሮ ደረጃ በደረጃ በይበልጥ ሰፋፊ የሆኑና የተወሳሰቡ መተላለፊያ መንገዶች ተቆፈሩ።”

በሦስተኛውና በአራተኛው መቶ ዘመን ትልቅ ለውጥ ተከስቶ ነበር፤ በዚህ ጊዜ ለክርስትና ሃይማኖት ተላልፏል የተባለው ነገር በአረማውያን ትምህርቶችና ልማዶች ሙሉ በሙሉ የተበከለ ነበር። በ313 እዘአ ቆስጠንጢኖስ ወደ ክርስትና ሃይማኖት ተለወጠ ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ በኋላ የካታኮምብ ዋሻዎች የሮም ቤተ ክርስቲያን ንብረት ሆኑ፤ ውሎ አድሮም አንዳንድ የካታኮምብ ዋሻዎች በጣም ትልቅ ቦታ ያዙ። የሮም የካታኮምብ ዋሻዎች በጠቅላላ በትንሹ ቢገመቱ እንኳ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ መቃብሮችን ይዘዋል።

በዚህ ወቅት የመቃብር ቦታዎቹ ማራኪ እንዲሆኑና እንዲሰፉ ከመደረጉም በተጨማሪ በብዛት የሚጎርፉት ጎብኚዎች በቀላሉ ወደ ዋሻዎቹ ውስጥ ገብተው መቃብሮቹን ለማየት እንዲችሉ አዳዲስ ደረጃዎች ተሠርተዋል። የካታኮምብ ዋሻዎች የሊቀ ጳጳሳትና የሰማዕታት መቃብር ናቸው የሚለው ዝና (በተለይ በሰሜን አውሮፓ) በስፋት መናኘቱ በጣም ብዙ ሃይማኖተኞች ወደዚያ እንዲጎርፉ ምክንያት ሆኗል። ሮም ስትወድቅና በአምስተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ላይ ባርባራውያን የመጀመሪያውን ወረራ ሲያካሂዱ አካባቢው በሙሉ እጅግ አደገኛ ሆነ፤ የካታኮምብ ዋሻዎችን ለመካነ መቃብርነት መጠቀም ቀረ።

መቃብሮቹ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰባቸው ሮማውያንን በወረረው ሠራዊት ብቻ አይደለም። ኸርትሊንግና ኪርሽባኡም እንዳሉት ከሆነ በስምንተኛው መቶ ዘመን “ሮማውያን ሸምጋዮዎች” የካቴድራሎቻቸውንና የገዳማቶቻቸውን ክብር ከፍ ለማድረግ ትልቅ ጉጉት ለነበራቸው “የጀርመንና የፍራንካውያን የገዳማት አለቆች” ቅርሶችን መዝብረው በመስጠታቸው ጭምር ነው። ሊቀ ጳጳስ ቀዳማዊ ጳውሎስ የካታኮምብ ዋሻዎችን ወደ ቀድሞ ሁኔታቸው ለመመለስም ሆነ ከዝርፊያ ለመከላከል ስላልቻሉ ቀሪዎቹን አጥንቶች ወደ ከተማዋ ክልል ወሰዷቸው፤ ቆየት ብሎ “የቅዱሳን ሰማዕታት” አፅም አለበት ተብሎ በሚታመነው ቦታ ታላላቅ የቤተ ክርስቲያን ሕንፃዎች ተሠርተውበታል። የካታኮምብ ዋሻዎቹ ግን የተተዉና የተረሱ ሆነው ነበር።

ከአምስተኛው እስከ ዘጠነኛው መቶ ዘመን ጎብኚዎችን ወደ ዝነኛ መቃብሮች ለመምራት ታስበው የተዘጋጁ የጥንት የጉዞ መመሪያዎች በፍርስራሽና በእፅዋት የተሸፈኑትን የመቃብር ቦታዎች ፈልገው አግኝተው መመርመር ለጀመሩት የ17ኛው ከዚያም የ19ኛው መቶ ዘመን ምሁራን ጠቃሚ ፍንጮች ሆነውላቸዋል። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ብዙ ምርምርና እድሳት የተደረገ ሲሆን በዛሬው ጊዜ ከእነዚህ የመታሰቢያ ቦታዎች መካከል በርካታዎቹን መጎብኘት ይቻላል።

አንድን የካታኮምብ ዋሻ መጎብኘት

ሐዋርያው ጳውሎስ እስረኛ ሆኖ ወደ ሮም ሲወሰድ በተጓዘበት በአፒያን ጎዳና ላይ ደረስን። (ሥራ 28:13-16) ምንም እንኳ ከጥንታዊቷ ከተማ ቅጥር ክልል የራቅነው ሦስት ኪሎ ሜትር ብቻ ቢሆንም በአንድ ወቅት እንቅስቃሴ ይበዛበት በነበረው በዚህ ጎዳና መቃብሮችና ፍርስራሾች መካከል በበቀሉ ትላልቅ የጥድ ዛፎች በተከበበ እልም ያለ ገጠር ውስጥ ነበርን።

የመግቢያ ትኬታችንን ከገዛን በኋላ 12 ሜትር የሚያህል ደረጃ ቁልቁል ወረድን። አስጎብኚው ይህ የካታኮምብ ዋሻ በአምስት የተለያዩ ደረጃዎች እንደተከፋፈለ፣ እስከ ሠላሳ ሜትር የሚደርስ ጥልቀት እንዳለውና ከበታቹ ውኃ እንደሚገኝ ገለጸልን። እንዲያውም ሮም ለስላሳና ውኃ በሚያስገባ፣ የዚያኑ ያህል ደግሞ ጠንካራና ጠጣር በሆነ ከፍተኛ ክምችት ባለው የእሳተ ጎመራ አለት የተከበበች ናት።

አንድ ሜትር ስፋትና ሁለት ሜትር ተኩል ከፍታ ባለው አንድ ጠባብ መተላለፊያ ተጓዝን። ጥቁር ቡናማ መልክ ያላቸው ግድግዳዎቹ ሻካራና የወረዙ ሲሆኑ ቆፋሪዎቹ እነዚህን ጠባብ የሆኑ በግድግዳ ውስጥ የሚገኙ ክፍሎች በዶማ በሚቆፍሩበት ወቅት ያወጧቸው ምልክቶች ግድግዳው ላይ በግልጽ ይታያሉ። በሁለቱም ግድግዳዎች በኩል የሚገኙት መቃብሮች ከረጅም ጊዜ በፊት ተከፍተው የተዘረፉ ቢሆንም አንዳንዶቹ አሁንም ቢሆን ጥቂት የአጥንት ስብርባሪዎች ይዘዋል። ጨለማውን እየተላመድን ስንሄድ በዙሪያችን በሺዎች የሚቆጠሩ መቃብሮች እንደሚገኙ ተገነዘብን።

የሞቱ ሰዎችን ለመቅበር በይበልጥ ኢኮኖሚያዊና ተግባራዊ ጠቀሜታ ያለው ዘዴ በግድግዳ ውስጥ አራት ማዕዘን ቅርጽ ያላቸውን ተደራራቢ ጉድጓዶች መቆፈር ነው። ብዙውን ጊዜ እነዚህ ጉድጓዶች አንድ አስከሬን ይዘው የነበረ ሲሆን አንዳንድ ጊዜ ግን ሁለት ወይም ሦስት አስከሬኖች ይደረጉባቸው ነበር። ከሲሚንቶ በተሠሩ ጡቦች፣ በጠፍጣፋ እብነ በረዶች ወይም ከሸክላ አፈር በተሠሩ ጡቦች ይከደኑ ነበር። ብዙዎቹ ምንም ነገር አልተጻፈባቸውም። ከውጭ በተቀመጡ ትናንሽ ዕቃዎች ተለይተው ሊታወቁ ይችሉ ነበር፤ አንድ ሳንቲም ወይም ዛጎል በኖራ እንዲጣበቅ መደረጉ ወይም ልጃቸው ያለ ዕድሜዋ በመቀጨቷ ምክንያት በሐዘን የተደቆሱ ወላጆች ያስቀመጡት ነው ተብሎ የሚገመተው በፕሪሲላ የካታኮምብ ዋሻ ውስጥ የሚገኘው ከአጥንት የተሠራ ትንሽ አሻንጉሊት ለዚህ ምሳሌ ሊሆኑ ይችላሉ። ብዙዎቹ አዲስ ለተወለዱ ሕፃናት ብቻ የሚበቁ ትናንሽ መቃብሮች ናቸው።

“የካታኮምብ ዋሻዎቹን ዕድሜ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው?” በማለት ጠየቅን። አስጎብኚያችን “ስለዚህ ጉዳይ መገመት አያስፈልግም። ይህን ምልክት ታያላችሁ?” በማለት መለሰልን። አንድን ጉድጓድ ለመክደን በተጠቀሙበት ትልቅ ከሸክላ አፈር የተሠራ ጡብ ላይ የታተመውን ምልክት ቀረብ ብለን ለመመልከት ጎንበስ አልን። “ይህ በጡቡ ላይ የሚገኘው ማኅተም የታተመው ጡቡ በተሠራበት ወቅት ነው። በአብዛኛው የንጉሡ ንብረት የነበሩት ፋብሪካዎች በጡቦች ላይ መረጃዎችን በሚጽፉበት ወቅት ሸክላው የተወሰደበት ቦታ፣ የተሠራበት ቦታ ስም፣ የሠራተኞቹ አለቃ ስም፣ በዚያ ዓመት የነበሩትን ቆንስላዎች (ዋነኛ ባለ ሥልጣናት) እና የመሳሰሉትን ይገልጹ ነበር። ይህ የመቃብሮቹን ትክክለኛ ዕድሜ ለማወቅ እጅግ ጠቃሚ የሆነ ነገር ነው። ከሁሉ የበለጠ ዕድሜ ያለው በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ አጋማሽ የተሠራው ሲሆን የቅርቡ ደግሞ በ400 እዘአ ገደማ ነው።”

የተለያዩ ሐሳቦች

በርካታ መቃብሮች መጽሐፍ ቅዱሳዊ በሆኑ ሥዕሎች ስለተጌጡ እነዚህን ቦታዎች ከተጠቀሙባቸው ሰዎች አንዳንዶቹ የተወሰነ የቅዱሳን ጽሑፎች እውቀት እንደነበራቸው በግልጽ ለመረዳት ይቻላል። ሆኖም የማርያም አምልኮ ወይም እንደ መስቀል ያሉ ሌሎች ከጊዜ በኋላ የመጡ “ቅዱስ” ሥነ ጥበብ የሚባሉ ነገሮች የለባቸውም።

በተጨማሪም ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ሥዕሎች ተመልክተናል። አስጎብኚው እንዲህ ብሏል:- “እነዚህና በሌሎች የካታኮምብ ዋሻዎች ውስጥ የሚገኙ ብዙ ሥዕሎች ከአረማውያን ሥነ ጥበብ የተወሰዱ እንደሆነ እሙን ነው። የግሪኮችና የሮማውያን ግማሽ ሰው፣ ግማሽ አምላክ ነው የሚባለው ጣዖትና በአፈ ታሪክ የሚወሳውን ኦሪፈስን ልታገኙ ትችላላችሁ፤ ነፍስ በዚህና በወዲያኛው ሕይወት የሚኖራትን ዕድል የሚያመለክቱት ኩፒድና ሳይክ፤ ከሞት በኋላ ላለው ሐሴት የተሞላበት ሕይወት ምልክት የሆነው የዳይኖሰስ የወይን መከር። አንቶንዮ ፋሩአ የተባሉ አንድ የጀስዊት ምሁር እንደተናገሩት ከሆነ ከጣዖት አምልኮ አንፃር ሲታይ የሚከተሉት ሥዕሎች የረቂቅ ነገሮች መግለጫዎች ናቸው:- በኩፒድ የተመሰሉት አራት ወቅቶች፣ ክረምት በበቆሎ ራስና በአበቦች ተመስሎ የሚታይባቸው የዓመቱን አራት ወቅቶች የሚያመለክቱት ውስብስብ ሥዕሎች፤ እና የመሳሰሉት።”

ብዙውን ጊዜ በሥዕሎቹ ላይ የሚታዩት የሚከተሉት ነገሮች ናቸው:- ሥጋዋ እንደማይበሰብስ ተደርጎ ስለሚታይ የአለመሞት ምልክት እንደሆነች ተደርጋ የምትታሰበው ፒኮክ፣ ለተወሰነ ጊዜ ከኖረች በኋላ በእሳት ተቃጥላ እንደሞተችና ከአመዱ ውስጥ እንደተነሣች የሚነገርላት በአፈ ታሪክ የምትጠቀሰዋ ፊኖክስም አለመሞትን ታመለክታለች ይባላል፤ ሥዕሎቹ ከሞት በኋላ ባለው ሕይወት የሙታን ነፍሳት በአእዋፍ፣ በአበቦችና በፍራፍሬ ተከበው ሲደሰቱ ያሳያሉ። በእርግጥም የአረማዊና የመጽሐፍ ቅዱስ ጽንሰ ሐሳቦች ቅልቅል ነው!

“አኩሊና በሰላም ተኝታለች” እንደሚለው ያሉ አንዳንድ ጽሑፎች ሙታን አንቀላፍተው ትንሣኤን በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ የሚናገሩ ስለሚመስሉ ስሜት የሚነኩ የእምነት መግለጫዎች ናቸው። (ዮሐንስ 11:11, 14) ከቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶች በተቃራኒ እንደሚከተሉት ያሉት ሌሎች ጽሑፎች ሙታን ሕያዋንን ሊረዱ ወይም ከሕያዋን ጋር ሊነጋገሩ ይችላሉ የሚለውን ሐሳብ የሚያንጸባርቁ ናቸው:- “ባልሽንና ልጆችሽን አስታውሺ”፤ “ጸልይልን”፤ “እጸልይልሃለሁ”፤ “ደህና ነኝ።”

ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ የቅዱስ ጽሑፋዊና የአረማዊ ሐሳብ ድብልቅ ሊኖር የቻለው ለምንድን ነው? ታሪክ ጸሐፊው ጄ ስቲቨንሰን “የአንዳንድ ክርስቲያኖች ክርስትና ቀድሞ ከነበሩበት የአረማዊ እምነት የመጡ ሐሳቦች ገብተውበታል” ብለዋል። በሮም ውስጥ ይኖሩ የነበሩ የስም ክርስቲያኖች የኢየሱስ እውነተኛ ደቀ መዛሙርት ካስተላለፉት እውቀት ጋር ተስማምተው እንዳልኖሩ በግልጽ ለመረዳት ይቻላል።— ሮሜ 15:14

ጉብኝታችንን በቀጠልን መጠን ለሙታን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ አክብሮት ማሳየት የሚንጸባረቅበት ሁኔታ በይበልጥ እየጎላ መጣ። ብዙዎች ሰማዕቱ ሰማያዊ ደስታ ከሚያገኝበት ስፍራ ሆኖ አነስተኛ ቦታ የተሰጠው ሰው ተመሳሳይ ሽልማት እንዲያገኝ በመርዳት ሊያማልደው ይችላል በሚል እምነት ሰማዕት ነው ተብሎ ከሚታሰብ ሰው አጠገብ ለመቀበር ይፈልጉ ነበር።

ብዙ ሰዎች የካታኮምብ ዋሻዎች ከከተማዋ ሥር የሚገኙ ቢመስላቸውም ይህ ትክክል አይደለም። የካታኮምብ ዋሻዎች የሚገኙት ከከተማዋ እምብርት ጥቂት ኪሎ ሜትሮች ርቀው ነው። እንዲያውም የሮማውያን ሕግ በከተማ ውስጥ መቅበርን ይከለክል ነበር። በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የወጣው ትዌልቭ ቴብልስ የተባለው ሕግ ሆሚነም ሞርተም ኢን አርቢ ኒ ሴፔሊቶ ኔቬ ዩሪቶ (ሙታን በከተማ ውስጥ ሊቀበሩ ወይም በእሳት ሊቃጠሉ አይችሉም) በማለት ይገልጻል።

አስጎብኚው የሚከተለውን አስተያየት ሰንዝሯል:- “እነዚህ የመቃብር ቦታዎች በባለ ሥልጣናት ዘንድ በስፋት ይታወቁ ስለነበር ክርስቲያኖች ወደ የካታኮምብ ዋሻዎች እንዳይገቡ በተከለከሉበት ንጉሠ ነገሥት ቫለርያን ባስነሣው ስደት ወቅት ሊቀ ጳጳስ ሲክስተስ ዳግማዊ (258 እዘአ) እዚህ በመገኘታቸው ተገድለዋል።”

መውጫውና መግቢያው በማይታወቀው በሌላኛው መተላለፊያ በኩል ስንሄድ በኮሪደሩ መጨረሻ ደብዘዝ ያለ የቀን ብርሃን ተመለከትንና ጉብኝታችን እንደተጠናቀቀ ተገነዘብን። አስጎብኚያችን ይህን አስደሳች እውቀት ስላካፈለን አመስግነነው ከተሰናበትን በኋላ በሌላ ደረጃ ሽቅብ ወጣን፤ ስለ ተመለከትነው ነገር በጥሞና ለማሰላሰል ተገፋፋን።

እነዚህ ነገሮች የእውነተኛ ክርስቲያኖች አጽሞች ናቸውን? ፈጽሞ አይደሉም። ቅዱሳን ጽሑፎች ሐዋርያት ከሞቱ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ያስተማሯቸው መሠረተ ትምህርቶች እንደሚበከሉ አስቀድመው ተናግረው ነበር። (2 ተሰሎንቄ 2:3, 7) በእርግጥም የሙታንና የሰማዕታትን አምልኮ እንዲሁም ነፍስ ለዘላለም ሕያው ሆና ትቀጥላለች የሚለውን ሐሳብ አስመልክቶ ያየነው መረጃ በኢየሱስ ትምህርቶች ላይ የተመሠረተ እምነትን ሳይሆን ከሁለተኛው እስከ አራተኛው መቶ ዘመን እንደ ዘመናችን አቆጣጠር የነበሩት እምነታቸውን የካዱ የሮም ክርስቲያኖች በአረማውያን ተጽዕኖ ሥር ወድቀው እንደነበር የሚያሳይ ጠንካራ ማስረጃ ነው።

[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የሊቀ ጳጳሳት መቃብር ናቸው ተብለው የሚታሰቡት ቦታዎች ብዙ ሃይማኖተኞች ወደዚያ እንዲጎርፉ ምክንያት ሆነዋል

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

አንድ የካታኮምብ ዋሻ ሠላሳ ሜትር ጥልቀት ያላቸው አምስት የተለያዩ ክፍሎች አሉት

[በገጽ 18 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]

የካታኮምብ ዋሻዎች በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ ይነሣል ተብሎ የተተነበየው ክህደት ያሳደረውን መጥፎ ተጽዕኖ ያሳያሉ

[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕሎች]

በስተቀኝ:- አንዳንድ አእዋፍ የአለመሞት ምልክት ሆነው ያገለግሉ ነበር

[ምንጭ]

Archivio PCAS

በስተቀኝ ራቅ ብሎ:- የአንዳንድ የሮማውያን የካታኮምብ ዋሻዎች ውስብስብ ፕላን

በስተቀኝ ታች:- የመቃብሮቹን ዕድሜ ለማወቅ የሚያገለግለው የሸክላ ማኅተም

[ምንጭ]

Soprintendenza Archeologica di Roma

ታች:- ከመሬት በታች የሚገኝ የሊቀ ጳጳሳት መቃብር

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ