ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .
ሌሎች በጾታ ስሜት እንዳይዳፈሩኝ ራሴን መጠበቅ የምችለው እንዴት ነው?
አኒታ ፍልቅልቅና ሳቅ የሚቀናት የ16 ዓመት ልጅ ነች። ሆኖም በቅርቡ ትምህርት ቤት ውስጥ ስላጋጠሟት ሁኔታዎች ስትናገር ፊቷ ላይ የሐዘን ስሜት ይነበብ ነበር። እንዲህ ብላለች:- “በብዙዎች ዘንድ ተወዳጅ የሆነ አንድ ልጅ በመተላለፊያው ላይ ወደ ጥግ አስቆመኝና ይደባብሰኝ ጀመር። ከብዙ ልጃገረዶች ጋር እንደዚህ ያደርግ ነበር። እነርሱ የልጁ ዓይን ስላረፈባቸው ይደሰቱ የነበረ ሲሆን እኔ ግን እንደነርሱ አልነበርኩም! እጁን ከላዬ እንዲያነሳ በትሕትና ብጠይቀውም ከድርጊቱ አልታቀበም። እየተግደረደርኩ እንዳለሁ አድርጎ አስቦ ነበር።”
አኒታ ያጋጠማት አስቸጋሪ ሁኔታ አዲስ ነገር አይደለም። በጾታ ስሜት የመዳፈር ጠባይ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የተለመደ ነበር። (ከሩት 2:8, 9, 15 ጋር አወዳድር።) በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በጣም አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ ተስፋፍቷል። አንዲት በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ የምትገኝ ወጣት “አብረውኝ የሚሠሩ ወንዶች ሰውነቴን በተመለከተ ጸያፍ የብልግና ቃላት ይሰነዝራሉ” ብላለች። ሆኖም በጾታ ስሜት የመዳፈር ጠባይ ብዙውን ጊዜ በቃላት ብቻ አይወሰንም። “አንዳንዶቹ ሊነኩኝ ወይም ሊይዙኝ ይሞክራሉ” በማለት አክላ ተናግራለች። ረኔ የምትባል በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ የምትገኝ ወጣት “መሥሪያ ቤት ውስጥ የሚዳፈሩኝ ወንዶች ሁኔታ እየከፋ ስለመጣ ሥራዬን ለማቆም ተገድጃለሁ” በማለት ለንቁ! መጽሔት ተናግራለች።
በቅርቡ የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያሳየው ከ8ኛ እስከ 11ኛ ባሉት ክፍሎች ውስጥ ከሚማሩት ተማሪዎች መካከል 81 በመቶው ቢያንስ አንድ ጊዜ ሌሎች በጾታ ስሜት እንደተዳፈሯቸው ተናግረዋል። ዩ ኤስ ኒውስ ኤንድ ዎርልድ ሪፖርት “ከእነዚህ መካከል 65 በመቶዎቹ ሴቶችና 42 በመቶዎቹ ወንዶች ሌሎች በወሲባዊ ስሜት እንደነካኳቸው፣ እንደያዟቸው ወይም እንደቆነጠጧቸው ተናግረዋል” በማለት ሪፖርት አድርጓል። አዎን፣ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በዚህ ጉዳይ ተነክተዋል። በአፍላ ጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኝ ልጅ ያላቸው አንድ አባት እንዲህ ብለዋል:- “ከልጄ ጋር የሚማሩት ልጃገረዶች ዓይናውጣነታቸው በጣም አስገርሞኛል። ከ12 ዓመቱ ገደማ ጀምሮ ሳያቋርጡ ስልክ ይደውሉለታል፣ ከእነርሱ ጋር እንዲጫወት ይጋብዙታል፣ የብልግና ቃላት ይሰነዝሩበታል እንዲሁም ሌሎች ብዙ ነገሮች ያደርጉ ነበር።”
ይህንን የሚያበሳጭ ሁኔታ ቸል ብሎ ማለፉ ቀላል ነው። አንዲት ወጣት “አንዳንድ ጊዜ ሰዎች በጾታ ስሜት የሚዳፈሩት በቀልድ መልክ ነው” በማለት ተናግራለች። ክርስቲያኖች ግን እንደ ቀልድ አይቆጥሩትም! በጾታ ስሜት የመዳፈር ጠባይ አብዛኛውን ጊዜ አንድን ሰው አባብሎ ይሖዋ አምላክ የሚያወግዘውን የጾታ ብልግና እንዲፈጽም ለማግባባት የሚደረግ ሙከራ እንደሆነ ያውቃሉ። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) በተጨማሪም የአምላክ ቃል ወጣት ሴቶች “በፍጹም ንጽሕና” እንዲያዙ ያዝዛል። (1 ጢሞቴዎስ 5:2) እንዲሁም ‘ጸያፍ ቀልድን’ ያወግዛል። (ኤፌሶን 5:3, 4 አዓት) ስለዚህ ክርስቲያን ወጣቶች ሌሎች በጾታ ስሜት እንዲዳፈሯቸው መፍቀድ የለባቸውም! ጥያቄው የዚህ ጥቃት ዒላማ እንዳትሆኑ ራሳችሁን መጠበቅ የምትችሉት እንዴት ነው? የሚል ነው። ይህን መከላከል የሚቻለው እንዴት እንደሆነ እንመልከት።
ሌሎች በጾታ ስሜት እንዳይዳፈሯችሁ መከላከል የምትችሉባቸው መንገዶች
ከክርስቲያናዊ ጠባይ ጋር የሚስማማ ስም ይኑራችሁ። ኢየሱስ “ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” በማለት አጥብቆ መክሯል። (ማቴዎስ 5:16) የምታምኑበትን ነገር ለትምህርት ቤት ጓደኞቻችሁ ወይም ለሥራ ባልደረቦቻችሁ ማካፈል ይህን ማድረግ የምትችሉበት አንዱ መንገድ ነው። ጠንካራ እምነትና ከፍተኛ የሥነ ምግባር አቋም እንዳላችሁ በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ከሆነ ብዙም የጥቃቱ ዒላማ አትሆኑም።
በአለባበሳችሁና በፀጉር አያያዛችሁ ረገድ ጠንቃቃ ሁኑ። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ብልሹ ሥነ ምግባር ያላትን ሴት ለይተው የሚያሳውቁ አንዳንድ የአለባበስ ዓይነቶች ነበሩ። (ከምሳሌ 7:10 ጋር አወዳድር።) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ የጾታ ፍላጎት የሚቀሰቅሱ አለባበሶች በእኩዮቻችሁ ዘንድ ተወዳጅ ሊያደርጓችሁ ቢችሉም በሌሎች ዘንድ የተሳሳተ ግምት ሊያሳድሩ ይችላሉ። ሳትፈልጉት የተቃራኒ ጾታ ትኩረት እየሳባችሁ ሊሆን ይችላል። አንዲት ልጃገረድ በመኳኳል ትልቅ መስላ ለመታየት የምትጥር ከሆነ ይህንን የመሰለ ችግር ሊፈጠር ይችላል። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ጭምቶች እንደሆናችሁና ጤናማ አስተሳሰብ እንዳላችሁ በሚያሳይ ሥርዓታማ አለባበስ ራሳችሁን እንድታስጌጡ’ ይመክራል።— 1 ጢሞቴዎስ 2:9
ጓደኞቻችሁን በጥንቃቄ ምረጡ። (ምሳሌ 13:20) ሰዎች የሚያዩአችሁ በጓደኞቻችሁ ዓይን ነው። በመሆኑም ጓደኞቻችሁ ስለ ተቃራኒ ጾታ በማውራት ብዙ ጊዜ የሚያሳልፉ ከሆነ ሰዎች ስለ እናንተ የተሳሳተ አመለካከት ሊያድርባቸው ይችላል።— ከዘፍጥረት 34:1, 2 ጋር አወዳድር።
ከሌሎች ጋር አትዳሩ። ሰዎችን ወዳጃዊ በሆነ ስሜት መመልከቱ ስሕተት ባይሆንም አትኩሮ መመልከትና መነካካት ግን ተቃራኒው ወገን በቀላሉ የተሳሳተ ትርጉም ሊሰጠው ይችላል። ከሌላ ሰው ጋር ለመጨዋወት የግዴታ ያንን ሰው መነካካት አያስፈልግም። ተቃራኒ ጾታ ያላቸው ሰዎች በንጽሕና እና በአክብሮት እንዲይዟችሁ እንደምትፈልጉ ሁሉ እናንተም ወርቃማውን ሕግ በሥራ ላይ በማዋል እንዲሁ አድርጉላቸው። (ማቴዎስ 7:12) እንዲሁ ለመደሰት ብቻ ብላችሁ የተቃራኒ ጾታ ትኩረት አትሳቡ። እንዲህ ማድረጉ ጭካኔና ሌሎች የተሳሳተ አመለካከት እንዲያድርባቸው የሚያደርግ ብቻ ሳይሆን አደገኛም ነው። መጽሐፍ ቅዱስ በምሳሌ 6:27 ላይ “በጉያው እሳትን የሚታቀፍ፣ ልብሶቹስ የማይቃጠሉ ማን ነው?” በማለት ይጠይቃል።
የጥቃቱ ሰለባ ከሆናችሁ
ምንም እንኳ የአለባበስ፣ የፀጉር አያያዝ ወይም የጠባይ ለውጦች ማድረግ ተገቢ ቢሆንም ሌሎች እናንተን የመደባበስ ወይም በእናንተ ላይ የብልግና ቃላት የመሰንዘር መብት የላቸውም። ሆኖም ለሌሎች አርዓያ የሚሆን አቋምና ጠባይ ያላቸው አንዳንድ ወጣቶች እንኳ ሳይቀሩ የዚህ ጥቃት ሰለባ ሆነዋል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ቢያጋጥማችሁ ምን ማድረግ አለባችሁ? ቀጥሎ አንዳንድ ሐሳቦች ቀርበዋል።
የማትፈልጉ መሆናችሁን ቁርጥ ባለ አነጋገር ግለጹ። አንዳንድ ሰዎች ሲያሽኮረምሟቸው በልባቸው ደስ እያላቸው በአፋቸው ግን አልፈልግም እንደሚሉ የታወቀ ነው። በመሆኑም ጥቃቱን የሚሰነዝሩባችሁ ሰዎች እስካላሳመናችኋቸው ድረስ በግማሽ ልብ አልፈልግም ማለት እፈልጋለሁ ማለት እንደሆነ አድርገው፣ ወይም ደግሞ እሺ ሊሉን ይችላሉ ብለው እንዲያስቡ ሊያደርጋቸው ይችላል። ኢየሱስ ቃላችሁ አይደለም ከሆነ አይደለም ይሁን ብሎ የሰጠው ምክር እዚህ ላይም ይሠራል። (ማቴዎስ 5:37) አትሳቁላቸው ወይም አትሽኮርመሙ። የሰውነት እንቅስቃሴያችሁ፣ ድምፃችሁ ወይም ፊታችሁ ላይ የሚነበበው ነገር ከምትናገሩት ጋር መጋጨት የለበትም።
ቁጣችሁን ግለጹ። በጾታ ስሜት የሚዳፈሩ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ያሰቡት ነገር የሚሟላላቸው ዒላማቸው የሆነው ሰው አሜን ብሎ ሲቀበላቸው ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንዲት እስራኤላዊት ሴት የሚደርስባትን የጾታ ጥቃት የመከላከል መብትና ግዴታ ነበረባት። (ዘዳግም 22:23, 24) በዛሬው ጊዜም ክርስቲያኖች አንድ ሰው ተገቢ ባልሆነ መንገድ ቢነካካቸው ወይም ቢደባብሳቸው ነገሩን አቅልለው መመልከት የለባቸውም። ይህ አግባብነት የጎደለው ድርጊት ነው። በሰብዓዊና በክርስቲያናዊ ክብራችሁ ላይ የሚሰነዘር ጥቃት ነው። አሜን ብላችሁ መቀበል የለባችሁም! መጽሐፍ ቅዱስ “ክፉውን ነገር ተጸየፉት” በማለት አጥብቆ ይመክራል!— ሮሜ 12:9
ተገቢ ያልሆነውን ድርጊት ለማቆም የሚያስችል አንዱ ጥሩ ዘዴ የሚዳፈራችሁን ሰው ተቆጥታችሁ ማሳፈር ነው፤ እንዲህ ካደረጋችሁ ምናልባት ከድርጊቱ ሊገታ ይችላል። በመግቢያው ላይ የተጠቀሰውን የአኒታን ተሞክሮ መለስ ብለን እንመልከት። ልጁን አትነካካኝ ብላ በትሕትና ብትጠይቀውም ከድርጊቱ አልታቀበም። አኒታ “አትነካካኝ! ብዬ በመጮህ በጓደኞቹ ፊት አሳፈርኩት” በማለት ገልጻለች። ውጤቱ ምን ሆነ? “ጓደኞቹ በጠቅላላ ሳቁበት። ለጊዜው ቅር ቢለውም ከጥቂት ቀናት በኋላ ላደረገው ነገር ይቅርታ ከመጠየቁም በላይ ሌላ ልጅ ሲያስቸግረኝ ተከላክሎልኛል።”
በምትናገሩት ነገር አልመለስ ካላችሁ የሚዳፈራችሁን ሰው ትታችሁ ልትሄዱ ወይም ልትሮጡ ትችላላችሁ። ማምለጥ የማይቻል ከሆነ እንዳይዳፈራችሁ ለመከላከል የሚያስችል ማንኛውንም ዘዴ መጠቀም ትችላላችሁ። አንዲት ክርስቲያን ልጃገረድ “አንድ ልጅ ሊይዘኝ ሲሞክር ባለ በሌለ ኃይሌ ተጠቅሜ በቡጢ መታሁትና ሮጥኩ!” በማለት በአጭሩ ገልጻለች። እርግጥ ነው እንዲህ ካደረጋችሁ በጾታ የሚዳፈራችሁ ሰው እንደገና አይሞክርም ማለት አይደለም። ስለዚህ የሌላ ሰው እርዳታ ሊያስፈልጋችሁ ይችላል።
ለሌላ ሰው ተናገሩ። የአሥራ ስድስት ዓመቷ አድሪያን “እኔም በመጨረሻ ያደረግሁት ይህንኑ ነው” ብላለች። “ጥሩ ጓደኛ አድርጌ እመለከተው የነበረ ልጅ ያለማቋረጥ በጾታ ስሜት ሲዳፈረኝ ስለዚህ ጉዳይ ወላጆቼን አማከርኳቸው። እንደማልፈልግ በገለጽኩለት መጠን ጨዋታ ይመስል ጭራሽ እየባሰበት መጣ።” የአድሪያን ወላጆች ችግሩን ለመወጣት የሚያስችል ተግባራዊ ምክር ሰጧት።
የእናንተም ወላጆች ቢሆኑ ሌሎች ሲዳፈሯችሁ የሚሰማችሁ ሐፍረት፣ ፍርሃት ወይም ውርደት የሚያስከትሏቸውን ስሜታዊ ተጽዕኖዎች ለመቋቋም እንድትችሉ ሊረዷችሁ ይችላሉ። ጥቃቱ የተሰነዘረባችሁ በእናንተ ጥፋት እንዳልሆነ ሊያረጋግጡላችሁ ይችላሉ። በተጨማሪም ወደፊት እንዲህ ያለ ነገር እንዳይደርስባችሁ ለማድረግ እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ።
ለምሳሌ ችግሩን ለአስተማሪያችሁ ወይም ለትምህርት ቤታችሁ ባለ ሥልጣኖች ማስታወቁ የተሻለ ሆኖ ሊያገኙት ይችላሉ። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ያሉ አብዛኞቹ ትምህርት ቤቶች የሚቀርቡላቸውን አቤቱታዎች አክብደው የሚመለከቱ ከመሆናቸውም በተጨማሪ በተማሪዎች መካከል በሚፈጸም በጾታ ስሜት የመዳፈር ድርጊት ላይ ምን እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ የሚያሳዩ በግልጽ የተቀመጡ መመሪያዎች አሏቸው።
እርግጥ ሁሉም የትምህርት ቤት ኃላፊዎች ችግራችሁን ተረድተው ይረዷችኋል ማለት አይቻልም። የሰው ችግር የሚገባቸው ሁሉም የትምህርት ቤት ሠራተኞች አይደሉም። የ14 ዓመቷ ኧርሊሻ እንዲህ ብላለች:- “አንዳንድ ጊዜ በምማርበት ትምህርት ቤት ውስጥ ያሉ አስተማሪዎች ከመሳደባቸውም በላይ ከተማሪዎቹ የከፋ ነገር ይፈጽማሉ። ማንን እርዳታ እንደምትጠይቁ ግራ ይገባችኋል።” ኧርሊሻ አንድ ልጅ በጾታ ስሜት እንደሚዳፈራት ስታመለክት አትንኩኝ ባይ ነሽ መባሏ አያስደንቅም። ሆኖም ኧርሊሻ ተስፋ አልቆረጠችም። ይኸው ልጅ እየቆነጠጠና እየደባበሰ ካስቸገራቸው ከሌሎች ስድስት ልጃገረዶች ጋር ሆና አመለከተች። “ርዕሰ መምህሩ ችግር መኖሩን ያመነው ስድስታችን አንድ ላይ ሆነን ካመለከትን በኋላ ነው” ብላለች። በመጨረሻ ከችግሩ ለመላቀቅ ችላለች።
አምላክ እንዲረዳችሁ ለምኑት። አንዳንድ ጊዜ ትምህርት ቤት ውስጥ ስትሆኑ የአንበሳ ጉድጓድ ውስጥ እንደገባችሁ ያህል ሆኖ የሚሰማችሁ ከሆነ ዳንኤል ቃል በቃል በአንበሳ ጉድጓድ ውስጥ በተጣለ ጊዜ ይሖዋ አምላክ እንዳዳነው አስታውሱ። (ዳንኤል 6:16-22) ይሖዋ እናንተንም ሊረዳችሁ ይችላል። ትምህርት ቤት ውስጥ የሚደርሱባችሁን ተጽዕኖዎች ያውቃል። ያጋጠማችሁ ሁኔታ እየከፋ ከሄደ እንደ አስፈላጊነቱ ጮክ ብላችሁ እርዳታ ልትጠይቁት ትችላላችሁ! የእውነተኛው አምላክ አገልጋዮች እንደሆናችሁ መታወቁ ሊያስፈራችሁ ወይም ሊያሳፍራችሁ አይገባም። መጽሐፍ ቅዱስ ለይሖዋ የታመኑ አገልጋዮች የሚከተለውን ተስፋ ይሰጣል:- “እግዚአብሔር የቅዱሳኑን ነፍሶች ይጠብቃል፣ ከኀጥኣንም እጅ ያድናቸዋል።”— መዝሙር 97:10
ይህ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከአስቸጋሪ ሁኔታዎች እንድናለን ማለት አይደለም። ራሳችሁን ከአደጋ ለመጠበቅ የምትችሉትን ሁሉ ማድረግ አለባችሁ። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተከተሉ። በንግግራችሁም ሆነ በአቋማችሁ ልከኛ ሁኑ። ከተቃራኒ ጾታ ጋር ባላችሁ ግንኙነት ጠንቃቆች ሁኑ። እንዲህ በማድረግ ሰዎች በጾታ ስሜት እንዳይዳፈሯችሁ መከላከል ትችላላችሁ።
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የሚሰነዘሩባችሁን ተገቢ ያልሆኑ የጾታ ፍላጎት የሚያነሳሱ ሁኔታዎች ስትቃወሙ አታመንቱ፤ ሁኔታችሁም አቋማችሁን በሚገባ የሚያንጸባርቅ መሆን አለበት!