ጥሩ ትምህርት ለማግኘት የሚያስችሉ ቁልፎች
በቅርቡ ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ላቶያ ስለ ተባለች የ16 ዓመት የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ የሚገልጽ ጽሑፍ በመጀመሪያው ገጹ ላይ አውጥቶ ነበር። አባትዋ እሷን መደብደብና በጾታ ማስነወር የጀመረው ገና የ11 ዓመት ልጅ ሳለች እንደነበረ ትናገራለች። የዕፅ ሱሰኛ የሆነችው እናትዋ ቤተሰቧን ጥላ ኮብልላለች። “ለእሷ ቤትዋ መጸዳጃ ቤት የሌለው አንድ የተረሳ አፓርታማ ወይም በፍርሃት እየተሸማቀቀች የምታድርባት አንዲት ክፍል ናት” በማለት ጋዜጣው ይዘግባል። ላቶያ ግን የተለየች ልጅ ነበረች። ይህ ሁሉ ችግር ቢደርስባትም በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ናሽናል ኦነር ሶሳይቲ የተባለ ማኅበር ፕሬዚደንት ለመሆን ከመቻሏም በላይ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርትዋ የተመረጡ ጎበዝ ተማሪዎች ካሉበት ክፍል የቢ አማካይ ነጥብ አግኝታለች።
አንድ ልጅ በመጥፎ አካባቢ ያደገ ቢሆን እንኳ ጥሩ የትምህርት ውጤት ለማግኘት ምን ሊረዳው ይችላል? ብዙውን ጊዜ ጥሩ ትምህርት ለማግኘት ቁልፉ የአንድን አሳቢ የሆነ ትልቅ ሰው፣ ቢቻል የአንዱን ወይም የሁለቱንም ወላጆች ልባዊ ድጋፍና ማበረታቻ ማግኘት ነው። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ልትጨርስ የተቃረበች አንዲት ወጣት ይህ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ስለተገነዘበች “ልጆች በትምህርት ቤት ሕይወታቸው ሊዘልቁ የሚችሉት የወላጆቻቸውን ድጋፍ ካገኙ ብቻ ነው” ብላ ለመናገር ተገፋፍታለች።
አብዛኞቹ መምህራን በዚህ ይስማማሉ። አንድ የኒው ዮርክ ከተማ መምህር “በመማር ማስተማሩ ሂደት የሚዘልቅና ጥሩ ውጤት የሚያገኝ ተማሪ ሁሉ የተሟላ ድጋፍ የሚሰጥ ወላጅ ያለው መሆኑን ለማወቅ ተችሏል” ብለዋል።
የወላጆች ድጋፍ ቁልፍ ሚና አለው
ባለፈው ዓመት ሪደርስ ዳይጀስት “አንዳንድ ተማሪዎች ከሌሎች የተሻለ ውጤት የሚያገኙት ለምንድን ነው?” በሚለው ጥያቄ ላይ ጥናት አድርጎ ነበር። ከደረሰባቸው ድምዳሜዎች አንዱ “ጠንካራ ቤተሰቦች ያሏቸው ልጆች ከትምህርት ጓደኞቻቸው የመብለጥ ዕድል ይኖራቸዋል” የሚል ነበር። ጠንካራ ቤተሰቦች ለልጆቻቸው ፍቅራዊ እንክብካቤ ከመስጠታቸው በተጨማሪ ትክክለኛ የሆኑ ግቦችና ዓላማዎች እንዲኖሯቸው ያስችላሉ። ይሁን እንጂ “በትምህርት ቤት የሚካሄደውን ሁኔታ ማወቅ ካልተቻለ ትክክለኛውን አመራር መስጠት አይቻልም” ሲሉ አንድ ወላጅ ተናግረዋል።
በትምህርት ቤት ያለውን ሁኔታ ለማወቅ የሚቻልበት ጥሩ መንገድ ሄዶ ማየት ነው። ልጅዋ የምትማርበትን ትምህርት ቤት ሄዳ የምትመለከት አንዲት እናት እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “ልጄ በምትማርበት ትምህርት ቤት በኮሪደር ሳልፍ በጣም ጸያፍ የሆኑ ቆሻሻ ቃላት እሰማለሁ። በየቦታው ልጆች ብልግና ሲፈጽሙ እመለከታለሁ። ፊልም ቢሆን ኖሮ የኤክስ ደረጃ ይሰጠው ነበር።” እናንተም ይህን የመሰለ ጉብኝት ብታደርጉ ልጆች ጥሩ ትምህርት ለማግኘትና የሥነ ምግባር ንጽሕናቸውን ለመጠበቅ ምን ያህል እንደሚቸገሩ ለመገንዘብ ትችሉ ይሆናል።
ዘ አሜሪካን ቲቸር 1994 የተባለው ጽሑፍ ትልቅ ግምት ሊሰጠው የሚገባ አስተያየት ሰጥቷል። “የጉልበት ጥቃት ከደረሰባቸው ተማሪዎች መካከል አብዛኞቹ ወላጆቻቸው ከትምህርት ቤታቸው ጋር በቂ ግንኙነት ያላደረጉ፣ በወላጆች ስብሰባ ላይ የማይገኙ፣ ወይም ጨርሶ ወደ ልጆቻቸው ትምህርት ቤት ሄደው የማያውቁ ናቸው።”
ነገሩ በጣም ያሳሰባት አንዲት እናት ወላጆች ማድረግ የሚኖርባቸውን ነገር ገልጻለች። “ከትምህርት ቤት አትጥፉ! የትምህርት ቤቱ አስተዳደር ልጃችሁ ስለሚማረው ነገር የምታስቡ መሆናችሁን ይወቅ። ብዙ ጊዜ ወደ ትምህርት ቤት እሄዳለሁ፣ ክፍል ገብቼም አዳምጣለሁ።” ሌላይቱ እናት ደግሞ የልጃችሁ ጠበቃ መሆን አስፈላጊ እንደሆነ ተናግራለች። እንዲህ በማለት ታስረዳለች:- “ልጆቼ የትምህርት ቤቱን ምክር ሰጪ ለማነጋገር ፈልገው ፈጽሞ ሳይሳካላቸው ቀርቶ ነበር። ልጄ እኔን ይዞ በሄደ ጊዜ ግን እኔንም ሆነ ልጄን ለመርዳት የተቻላቸውን ሁሉ አድርገዋል።”
ይህች የአራት ልጆች እናት ልጃችሁ ከሚያገኘው ትምህርት ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ያላቸውን የትምህርት ቤት እንቅስቃሴዎች በንቃት መከታተል አስፈላጊ መሆኑን አበክራ ገልጻለች። “በወላጆች ቀን፣ የሳይንስ ትርዒት በሚቀርብባቸው ቀናት፣ በጠቅላላው ወላጆች እንዲገኙ በሚጋበዙባቸው ፕሮግራሞች በሙሉ ተገኙ። በእነዚህ አጋጣሚዎች ከልጃችሁ መምህራን ጋር የመገናኘት አጋጣሚ ታገኛላችሁ። ልጃችሁ ለሚያገኘው ትምህርት ከፍተኛ ግምት የምትሰጡ መሆናችሁን ማወቅ ያስፈልጋቸዋል። አስተማሪዎች ይህን ሲያውቁ ለልጃችሁ ተጨማሪ ጊዜና ጥረት ለመስጠት ይገፋፋሉ” ብላለች።
ከአስተማሪዎች ጋር መተባበር
ትምህርት ቤቶች ወላጆችና አስተማሪዎች እንዲገናኙ የሚያስችሉ ልዩ ፕሮግራሞች ሲያዘጋጁ አንዳንድ ወላጆች በዚያ ቀን ሌላ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ጉዳይ እንዳላቸው ይሰማቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ ልጆቻቸው ጥሩ ትምህርት እንዲያገኙ ጥረት ከሚያደርጉ መምህራን ጋር ከመገናኘት የበለጠ አስፈላጊ ነገር ሊኖር ይችላልን? በአስተማሪዎችና በወላጆች መካከል ጥሩ ትብብር መኖሩ በጣም አስፈላጊ ነው።
በሩስያ በወላጆችና በአስተማሪዎች መካከል ያለው ትብብር እንዲጠናከር የሚያስችል ጥሩ ዝግጅት አለ። በየቀኑ በትምህርት ቤት የሚሰጡ የክፍል ሥራዎችና የቤት ሥራዎች የሚመዘገብበት ድንዬቭኒክ የሚባል የቀን መቁጠሪያ ያለው መዝገብ አለ። እያንዳንዱ ተማሪ ድንዬቭኒኩን ወደ እያንዳንዱ ክፍል ማምጣትና አስተማሪው ሲጠይቀው ማሳየት ይኖርበታል። በተጨማሪም ተማሪዎች ድንዬቭኒካቸውን ለወላጆቻቸው ማሳየትና በየሳምንቱ ማስፈረም አለባቸው። በትምህርት ላይ የሚገኙ ልጆች ያሉት ቪክትር ለቦቪች የተባለ መስኮባዊ እንደተናገረው “ከዚህ የሚገኘው መረጃ ወላጆች ለልጆቻቸው ከሚሰጡ የቤት ሥራዎችና ማርኮች ጋር እንዲተዋወቁ ይረዳል።”
ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ ብዙ መምህራን ወላጆች ስለ ልጆቻቸው ትምህርት ደንታ ቢሶች እንደሆኑና በንቃት እንደማይከታተሏቸው በምሬት ይናገራሉ። በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር አንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተማሪ አንድ ጊዜ የልጆቻቸውን የትምህርት ደካማነት የሚገልጽ ደብዳቤ ለ63 ወላጆች ልኮ ነበር። ይህን መምህር መጥተው በማነጋገር ለደብዳቤው ምላሽ የሰጡት ሦስት ወላጆች ብቻ ናቸው!
በእርግጥም የሚያሳዝን ነው! ወላጆች ለልጆቻቸው የሚሰጠውን ትምህርት በሚገባ መከታተል ይኖርባቸዋል። ምክንያቱም ልጆችን የማስተማር ኃላፊነት በዋነኛነት የሚያርፈው በወላጆች ላይ ነው። አንድ የትምህርት ባለሞያ እንዲህ በማለት በትክክል ገልጸውታል:- “የመሠረታዊ ትምህርት ዋነኛ ዓላማ ኃላፊነት የሚሰማቸው ጎልማሳ ልጆች ለማፍራት ለሚያደርጉት ጥረት ለወላጆች ድጋፍ መስጠት ነው።”
ስለዚህ ወላጆች በራሳቸው ተነሳስተው ከልጆቻቸው አስተማሪዎች ጋር መተዋወቅ ይኖርባቸዋል። አንድ ወላጅ እንዳለው “አስተማሪዎቹ በማንኛውም ጊዜ ሊጠሯችሁ እንደሚችሉ ሊሰማቸው ይገባል።” ወላጆችም አስተማሪዎች ስለ ልጆቻቸው በግልጽ እንዲነግሯቸው ማበረታታትና የሚናገሩትን መቀበል ይገባቸዋል። ልጄ ያስቸግራችኋል? ያከብራችኋል? በሁሉም የትምህርት ክፍለ ጊዜዎች ይገኛል? በጊዜ ይደርሳልን? እንደሚሉ ያሉ ቀጥተኛ ጥያቄዎች ወላጆች መጠየቅ አለባቸው።
አስተማሪው ስለ ልጃችሁ መጥፎ ነገር ቢናገርስ? ውሸቱን ነው ብላችሁ አታስቡ። እቤታቸው ወይም በአምልኮ ቦታዎች በጣም ጨዋ መስለው የሚታዩ ብዙ ወጣቶች ሁለት ዓይነት ኑሮ የሚኖሩ ናቸው። ስለዚህ አስተማሪውን በአክብሮት አዳምጡና የተናገረው እውነት መሆንና አለመሆኑን አጣሩ።
ልጃችሁ ቤት ሲመጣ
ወላጆች ሥራ ውላችሁ ቤታችሁ ስትመጡ እንዴት ይሰማችኋል? ድካምና ውጥረት ይሰማችሁ የለምን? ልጃችሁም ከትምህርት ቤቱ ሲመጣ ከእናንተ የባሰ ሊሰማው ይችላል። በዚህም ምክንያት አንድ አባት “ቤት መምጣት አስደሳች ነገር እንደሆነ እንዲሰማቸው አድርጉ። በጣም መጥፎ የሆነ ጊዜ አሳልፈው ይሆናል” የሚል ምክር ሰጥቷል።
የሚቻል ከሆነ ልጆች እቤት ሲመጡ አባታቸው ወይም እናታቸው ጠብቀው ቢቀበሏቸው በጣም ጥሩ ይሆናል። አንዲት እናት “እቤት ተገኝታችሁ ካላነጋገራችኋቸው ልጆች ያጋጠማቸውን ሊነግሯችሁ አይችሉም። ስለዚህ ልጆቼ ከትምህርት ቤት ሲመጡ እቤት ሆኜ ለመቀበል ጥረት አደርጋለሁ” ብላለች። እያንዳንዱ ወላጅ ልጁ ምን እንደሚያደርግ ብቻ ሳይሆን ምን እንደሚያስብና ምን እንደሚሰማው ጭምር ማወቅ ያስፈልገዋል። ይህንንም ለማወቅ በርካታ ጊዜ፣ ጥረትና ምርመራ ማድረግ ይጠይቃል። (ምሳሌ 20:5) በየቀኑ ሐሳብ ለሐሳብ መለዋወጥ አስፈላጊ ነው።
አንድ በኒው ዮርክ የሚኖር የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተማሪ “በማንኛውም ቀን ልጃችሁ በከባድ ችግር ላይ የወደቀው የትምህርት ሥርዓት ነጸብራቅ በሆነ አንድ ዓይነት ብልግና ሊለከፍ ይችላል” ብሏል። በዚህም ምክንያት “በልጃችሁ ልብ ውስጥ ምን ነገር በማቆጥቆጥ ላይ እንደሚገኝ በንቃት ተከታተሉ። የቱንም ያህል ድካም ቢሰማችሁ ጊዜ ወስዳችሁ ሐሳቡን አወጣጡና ወደ ልቡ የገባውን መጥፎ ጠባይ በጥሩ ጠባይ ተኩ” ሲል መክሯል።— ምሳሌ 1:5
ለረዥም ዘመናት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተማሪ ሆኖ የሠራ አንድ ሰውም እንዲህ ሲል መክሯል:- “ትምህርት ቤት እንዴት ነበር የሚል አጠቃላይ ጥያቄ ከመጠየቅ ይልቅ ዕለቱንና የዕለቱን እንቅስቃሴዎች የሚመለከት ቀጥተኛ ጥያቄዎች መጠየቅ ጠቃሚ ይሆናል። ይህ ዓይነቱ ጥያቄ ግትርና ለወንጀለኛ እንደሚቀርብ የምርመራ ጥያቄ ሆኖ መቅረብ የለበትም። ከዚህ ይልቅ በተዝናና ሁኔታ ከልጁ ጋር በሚደረግ ጭውውት ሊቀርብ ይችላል።”
የዩናይትድ ስቴትስ የትምህርት ሚኒስትር የሆኑት ሪቻርድ ራይሌ እንደሚከተለው በማለት ጥብቅ ማሳሰቢያ ሰጥተዋል:- “ከልጃችሁ ጋር፣ በተለይም በአፍላ የጉርምስና ዕድሜ ላይ ከሚገኝ ልጃችሁ ጋር ስለ አደንዛዥ ዕፅና ስለ አልኮል አደገኛነት እንዲሁም እንዲያዳብር ስለምትፈልጉት ጥሩ ጠባይ በቀጥታና በግልጽ ተነጋገሩ። ይህን የመሰለው ውይይት ምንም ያህል አስቸጋሪ መስሎ ቢታይ የልጆቻችሁን ሕይወት ሊያድንላችሁ ይችላል።”
ማንኛውም ወላጅ፣ በተለይ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ ያለው ከሆነ፣ ልጁ የሚናገረውን ለማዳመጥ ጊዜ እንደሌለው ሆኖ ሊታየው አይገባም። የሚናገሩትን መስማት የሚያስቆጣ ቢሆንም በአነጋገራችሁና በፊታችሁ ገጽታ በነጻነት ሐሳባቸውን መግለጻቸው ያስደሰታችሁ መሆኑን አሳዩ። አንዲት ተማሪ “ልጃችሁ ስለ አደንዛዥ ዕፅ ወይም ስለ ወሲብ ሲናገር ስትሰሙ የመደንገጥ ፊት አታሳዩት” ስትል መክራለች።
የቤተሰብ ሕይወት በመፈራረስ ላይ የሚገኝ በመሆኑ በአሁኑ ጊዜ “ድሃ አደጎች” ወይም ወላጅ የሌላቸው ልጆች ሊባሉ የሚችሉ በርካታ ልጆች አሉ። (ኢዮብ 24:3፤ 29:12፤ መዝሙር 146:9) በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ወጣቶች የሚረዳ ሰው አይታጣም። አንተስ ለመርዳት ትችላለህን?
የማጥናት ፍላጎትና የኃላፊነት ስሜት እንዲያድርባቸው አድርጉ
አብዛኞቹ ወጣቶች በመግቢያችን ላይ እንደተጠቀሰችው ላቶያ ትምህርታቸውን በትጋትና በቆራጥነት የሚከታተሉ አይደሉም። አብዛኞቹ ወጣቶች እንዲያጠኑ መበረታታት ያስፈልጋቸዋል። የኒው ዮርክ ከተማ ትምህርት ቤት ቻንስለር የነበሩት ጆሴፍ ፈርናንዴዝ ስለ ራሳቸው ልጆች ሲናገሩ “እቤታችን ውስጥ ልጆች በግዴታ የሚያጠኑባቸው ሰዓቶች ወስነን ነበር። መጻሕፍት እናቀርብላቸዋለን፣ ወደ ቤተ መጻሕፍት እንዲሄዱ እናበረታታቸዋለን በተጨማሪም ለትምህርታቸው ቅድሚያ እንዲሰጡ እናደርጋቸዋለን” ብለዋል።
ሌላው የትምህርት ቤት አስተዳዳሪ “ልጆቻችን በዛሬው ጊዜ በቴሌቪዥን፣ በፊልሞች፣ በቪዲዮዎችና በተለያዩ ሸቀጦች እንዲከበቡ እንደምናደርግ ሁሉ በመጻሕፍትና በተለያዩ ታሪኮች እንዲከበቡ ማድረግ ያስፈልገናል” ብለዋል። ልጆች የቤት ሥራቸውን በሚሠሩበት ጊዜ ወላጆች አጠገባቸው ሆነው የግል ጥናታቸውን ሊያደርጉ ወይም ሊያነቡ ይችላሉ። ልጆቻችሁ እናንተም ስታነቡ ወይም ስታጠኑ ሲመለከቱ ለትምህርት ከፍተኛ ዋጋ እንደምትሰጡ ሊመለከቱ ይችላሉ።
በብዙ ቤቶች ለጥናት ትልቅ እንቅፋት የሚሆነው ቴሌቪዥን ነው። አንድ የትምህርት ባለሞያ “አንድ ልጅ 18 ዓመት ሲሞላው በትምህርት ላይ ሆኖ ያሳለፈው ጊዜ 11,000 ሰዓት ሲሆን ቴሌቪዥን በመመልከት ያሳለፈው ግን 22,000 ሰዓት ይሆናል” ብለዋል። ወላጆች ልጆቻቸው ቴሌቪዥን በማየት የሚያሳልፉትን ጊዜ ሊገድቡ ይችላሉ። ራሳቸውም ቢሆኑ አልፎ አልፎ ብቻ መመልከት ይኖርባቸው ይሆናል። በተጨማሪም ከልጆቻችሁ ጋር ሆናችሁ አንድ ነገር ለማጥናት ቁርጥ ውሳኔ አድርጉ። አብራችሁ አንብቡ። የቤት ሥራቸውን የምትቆጣጠሩበት ጊዜ መድቡ።
ልጆቻችሁ በትምህርት ቤታቸው ብዙ ሥራ እንዲያከናውኑ ይጠየቃሉ። እነዚህን የክፍል ወይም የቤት ሥራዎች አሟልተው ይሠራሉን? በቤት ውስጥ የሚሰጧቸውን ኃላፊነቶች እንዲወጡ ካስተማራችኋቸው በትምህርት ቤት የሚሰጧቸውንም ሥራዎች አጠናቅቀው ለመሥራት ይችላሉ። ይህን ለማድረግ በየቀኑ ማከናወን የሚኖርባቸው ሥራ መመደብ በጣም አስፈላጊ ነው። ሥራ ከመደባችሁላቸው በኋላ በየቀኑ ማከናወናቸውን ተቆጣጠሩ። እርግጥ ነው፣ እንዲህ ያለው ሥልጠና ብዙ ጥረት የሚጠይቅባችሁ ይሆናል። ቢሆንም ልጆቻችሁ በትምህርት ቤትና በኋላም በሕይወታቸው የተሳካላቸው እንዲሆኑ የሚያስፈልጋቸውን የኃላፊነት ስሜት ያስተምራቸዋል።
የተማሪዎች ቆራጥነት፣ ዋነኛ ቁልፍ ነው
የተማሪዎች አማካሪ የሆኑት አርተር ከርሰን ቀደም ስንል ስለጠቀስናት ስለ ላቶያ በተናገሩት ቃል ሌላውን ጥሩ ትምህርት ለማግኘት የሚያስችል ቁልፍ አመልክተዋል። እንዲህ አሉ:- “ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘኋት በቤትዋ ውስጥ ካጋጠማት ጥቃት በኋላ ነበር። [አባቷ ደብድቧት] ፊትዋ በሙሉ ተቦጫጭሮ ተቀምጣለች። እርስዋን ግን ያሳሰባት የትምህርትዋ ጉዳይ ብቻ ነበር።”
አዎን፣ ጥሩ ትምህርት ለማግኘት ዋነኛው ቁልፍ ልጁ ለመማር ያለው ቆራጥ አቋም ነው። በኒው ዮርክ የሚኖር አንድ ወጣት እንዲህ ብሏል:- “በዛሬው ጊዜ ማንኛውም ተማሪ ከትምህርት ቤት ጥቅም ማግኘት ከፈለገ ዲስፕሊንና ልባዊ ፍላጎት ሊኖረው ይገባል።”
ለምሳሌ ያህል አንድ መምህር የልጅዋ የትምህርት ሁኔታ ላሳሰባት አንዲት እናት “እሜቴ፣ ፈጽሞ አይጨነቁ። ልጅዎ በጣም ጎበዝ በመሆኑ አስተካክሎ መጻፍ ባይችል ምንም አይደለም። ጸሐፊው ትጽፍለታለች” ብሏል። አንድ ልጅ ምንም ያህል ጎበዝ ቢሆን ጥሩ የድርሰትና የአጻጻፍ ችሎታን ጨምሮ የማንበብንና የመጻፍን ክህሎት አሟልቶ መገኘቱ በጣም አስፈላጊ ነው።
ካርል ሮጀርስ የተባሉ እውቅ የሥነ ልቦና ምሁር “ማንም ሰው ወደፊት ይጠቅመኛል ብሎ የማያስበውን ነገር ለመማር መሞከር የለበትም” ሲሉ የተናገሩትን ቃል አንዳንድ የትምህርት ባለሞያዎች አለመቃወማቸው በእጅጉ የሚያሳዝን ነው። ይህ አባባላቸው ስህተት የሆነው ለምንድን ነው? በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ማንኛውም ልጅ በአሁኑ ጊዜ እንዲማር የሚጠየቀው ነገር ወደፊት በምን መንገድ እንደሚጠቅመው በቅድሚያ ማወቅ አይችልም። አብዛኛውን ጊዜ ያገኘው ትምህርት የሚሰጠውን ጥቅም የሚገነዘበው ዕድሜው ከገፋ በኋላ ነው። ማንኛውም ልጅ ጥሩ ትምህርት ለማግኘት ቆራጥ መሆን እንደሚያስፈልገው ግልጽ ነው!
የዘጠነኛ ክፍል ተማሪ የሆነችው የ14 ዓመትዋ ሲንዲ ይህን የመሰለ ቆራጥ አቋም ላላቸው ወጣቶች ጥሩ ምሳሌ ትሆናለች። “ትምህርት ካለቀ በኋላ ወደ ኋላ ቀረት እልና አስተማሪዎቹን በማነጋገር እተዋወቃቸዋለሁ። ከተማሪዎቻቸው ምን እንደሚፈልጉ ለመረዳት እሞክራለሁ” ብላለች። በተጨማሪም በክፍል ውስጥ በጥሞና ታዳምጣለች፤ ለሚሰጣትም የቤት ሥራ ከማንኛውም ነገር ይበልጥ ቅድሚያ ትሰጣለች። ጥሩ ውጤት የሚያገኙ ተማሪዎች በክፍል ሆነው በሚያዳምጡበትም ሆነ በግላቸው በሚያነቡበት ጊዜ ማስታወሻ ለመያዝ እንዲችሉ ወረቀትና እርሳሳቸውን አዘጋጅተው በቅርብ የማስቀመጥ ልማድ አላቸው።
በተጨማሪም ከመጥፎ ባልንጀሮች ለመራቅ ቆራጥ መሆን ጥሩ ትምህርት ለማግኘት በጣም አስፈላጊ ነው። ሲንዲ እንደሚከተለው በማለት ታብራራለች:- “ሁልጊዜ ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸውን ልጆች እፈልጋለሁ። ለምሳሌ ያህል የትምህርት ቤት ጓደኞቼን እገሌ የሚባለው ልጅ ዕፅ ስለመውሰዱ ወይም ከማንም ጋር ስለመተኛቱ ምን እንደሚሰማቸው እጠይቃቸዋለሁ። ‘ታዲያ ምናለበት?’ ካሉኝ ጥሩ ባልንጀሮች እንደማይሆኑኝ አውቃለሁ። እንዲህ ያለውን ጠባይ በማጥላላትና በመጸየፍ የምትናገር ልጅ ከሆነች ግን በምሳ ሰዓት አብራኝ እንድትቀመጥ እፈልጋለሁ።”
ጥሩ ትምህርት ለማግኘት ብዙ ችግሮችን መቋቋም እንደሚያስፈልግ ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ ወላጆችም ሆኑ ተማሪዎች በተጠቀሱት ቁልፎች ከተጠቀሙ ጥሩ ትምህርት ማግኘት ይቻላል። ቀጥለን ጥሩ ትምህርት በማግኘት ረገድ በእጅጉ ሊረዳችሁ የሚችል ሌላ ዝግጅት እንመለከታለን።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ማቀማጠል ወይስ በፍቅር መቅጣት?
መጽሐፍ ቅዱስ ልጆችን ማቀማጠል ከፍተኛ ውድቀት እንደሚያስከትል ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 29:21) የአሜሪካ መምህራን ፌዴሬሽን ፕሬዚደንት የሆኑት አልበርት ሻንከር “ልጆቻቸው የሚፈልጉትን ሁሉ ካደረጉላቸው የሚገባቸውን ሁሉ እንዳደረጉ የሚሰማቸው ወላጆች አሉ። ግን ይህ ስህተት እንደሆነ እናውቃለን” በማለት ከዚህ ጋር የሚስማሙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
እንዲህ ያለው ማቀማጠል ትክክል አለመሆኑን ወጣት ልጆች ሳይቀሩ ያውቃሉ። ባለፈው ዓመት እንድ የማሳቹሴትስ ጋዜጣ የሚከተለውን ሪፖርት አውጥቶ ነበር:- “በምዕራብ ስፕሪንግፊልድ ከስድስተኛ እስከ አሥራ ሁለተኛ ክፍል በሚማሩ 1572 ተማሪዎች ላይ በተደረገ ጥናት በዚህ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆች ዕፅ ወሳጆችና አልኮል ጠጪዎች እንዲሆኑ ያደረጋቸው ከእኩዮቻቸው ተጽእኖ ይልቅ በወላጆቻቸው ስድ መለቀቃቸው እንደሆነ ለመገንዘብ ተችሏል።”
በተጨማሪም ልጆች ተቀማጥለው ማደጋቸው ለወሲባዊ ብልግና መስፋፋት ምክንያት ሆኗል። በእርግጥም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ልጆችን ተቆጣጥሮ አለማሳደግ በቤተሰብ ላይ እፍረት ያስከትላል።— ምሳሌ 29:15
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ወላጆች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
✔ ልጃችሁ የሚማርበትን ትምህርት ቤት ደህና አድርጋችሁ እወቁ። ዓላማው ምን እንደሆነና ስለ እምነታችሁና ለጥሩ ጠባይ ስላላችሁ አመለካከት ምን ዓይነት ዝንባሌ እንዳለው ተገንዘቡ።
✔ ከልጃችሁ መምህራን ጋር ተዋወቁና በመካከላችሁ ጥሩ መግባባት እንዲኖር አድርጉ።
✔ ልጃችሁ የሚሰጠውን የቤት ሥራ ተከታተሉ። በየጊዜው አብራችሁት አንብቡ።
✔ ልጃችሁ በቴሌቪዥን ላይ የሚመለከተውን ነገርና ቴሌቪዥን በመመልከት የሚያሳልፈውን ጊዜ ተቆጣጠሩ።
✔ የልጃችሁን የአመጋገብ ልማድ ተከታተሉ። ሰውነት የማይገነቡ ጣፋጭ ምግቦች በትምህርቱ ላይ የማተኮር ችሎታውን ሊቀንሱበት ይችላሉ።
✔ ልጃችሁ በቂ እንቅልፍ ማግኘቱን አረጋግጡ። የደከሙ ልጆች ትምህርታቸውን ለመከታተል አይችሉም።
✔ ልጃችሁ ጥሩ ጓደኞች እንዲመርጥ ለመርዳት ሞክሩ።
✔ የልጃችሁ የቅርብ ጓደኛ ሁኑ። በሳል ወዳጆች ያስፈልጉታልና።
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ልጆች ምን ሊያደርጉ ይችላሉ?
✔ ወላጆቻችሁ እየረዷችሁ ለትምህርታችሁ ግብ አውጡ። እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ የሚያስችላችሁንም መንገድ ቀይሱ። ስለግባችሁ ከአስተማሪዎቻችሁ ጋር ተነጋገሩ።
✔ አስተማሪዎቻችሁና ወላጆቻችሁ እየረዷችሁ የምትማሯቸውን ትምህርቶች በጥንቃቄ ምረጡ። ቀላል ትምህርቶች አብዛኛውን ጊዜ ጥሩዎች አይደሉም።
✔ ከአስተማሪዎቻችሁ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖር ለማድረግ ሞክሩ። ከእናንተ ምን እንደሚጠብቁ እወቁ። ምን እድገት እንዳደረጋችሁና ምን ችግሮች እንዳጋጠሟችሁ አዋዩአቸው።
✔ በክፍል ውስጥ በትኩረት አዳምጡ። ፈጽሞ በረብሻ አትካፈሉ።
✔ ጓደኞቻችሁን በጥበብ ምረጡ። በትምህርት ቤት የምታገኙትን እድገት ሊያፋጥኑላችሁ ወይም እንቅፋት ሊሆኑባችሁ ይችላሉ።
✔ በክፍል ውስጥና እቤታችሁ እንድትሠሩ የሚሰጧችሁን ሥራዎች በተቻላችሁ መጠን ጥሩ አድርጋችሁ ሥሩ። ከሁሉ የሚሻለውን ጊዜ መድቡላቸው። ካስፈለጋችሁ ወላጆቻችሁ ወይም ሌላ የጎለመሰ ሰው እንዲረዳችሁ ጠይቁ።
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አስተማሪው ስለ ልጃችሁ ጥፋት የሚናገረው ነገር ካለው በጥሞና አዳምጡት
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በየቀኑ ልጃችሁ በትምህርት ቤት ስላጋጠመው ሁኔታ ጠይቁት