የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g96 4/8 ገጽ 4-7
  • ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ የሚችለው ማን ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ የሚችለው ማን ነው?
  • ንቁ!—1996
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ወታደራዊ ወጪ መቀነስ
  • ዓለም አቀፉ የጦር መሣሪያዎች ንግድ
  • የኑክሌር ስጋት አሁንም እንዳለ ነው
  • የጦር መሣሪያ ቅነሳና ሰላም
  • የጎሣ ሽኩቻ ጨምሯል
  • ከፊታችን የተደቀኑ ችግሮች
  • መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኑክሌር ጦርነት ምን ይላል?
    ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች
  • የኑክሌር ስጋት ለዘለቄታው ይወገዳል!
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1994
ንቁ!—1996
g96 4/8 ገጽ 4-7

ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ የሚችለው ማን ነው?

“ሰይፋቸውንም ማረሻ፣ ጦራቸውንም ማጭድ ለማድረግ ይቀጠቅጣሉ፤ ሕዝብም በሕዝብ ላይ ሰይፍ አያነሣም፣ ሰልፍም ከእንግዲህ ወዲህ አይማሩም።”

ይህ ትንቢት ከኢሳይያስ ምዕራፍ 2 ቁጥር 4 ላይ የተወሰደ ነው። ሂውማን ዴቨሎፕመንት ሪፖርት 1994 የተባለው የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም (ዩ ኤን ዲ ፒ) ያወጣው ዘገባ ይህን ከጠቀሰ በኋላ አክሎ ሲናገር “ቀዝቃዛው ጦርነት [በ1990] ሲያከትም ይህ ትንቢት የሚፈጸምበት ጊዜ የደረሰ መስሎ ነበር። ሆኖም እስካሁን ድረስ እንደታየው ይህ የማይጨበጥ ተስፋ ሆኗል” ብሏል።

ወታደራዊ ወጪ መቀነስ

የሰላም ተስፋ የጨለመበት አንዱ ምክንያት ከመላው ዓለም ፖለቲካዊ ሁኔታ ለውጥ ጎን ለጎን ከፍተኛ ወታደራዊ ወጪ ቅነሳዎች አለመደረጋቸው ነው። እርግጥ አንዳንድ ቅነሳዎች ተደርገዋል። የተባበሩት መንግሥታት ያወጣቸው አሃዞች እንደሚያሳዩት የዓለም ወታደራዊ ወጪ በ1987 ከምን ጊዜውም በበለጠ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶ 995 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የተደረገ ሲሆን በ1992 ወደ 815 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ዝቅ ብሏል። ሆኖም 815 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ከፍተኛ ወጪ ነው። በግምት ግማሹ የዓለም ሕዝብ ከሚያገኘው ጠቅላላ ገቢ ጋር ይመጣጠናል!

ሌላው የጦር መሣሪያ ቅነሳ እንዳይደረግ እንቅፋት የሆነው ወታደራዊ ኃይል ደኅንነት ሊያስገኝ ይችላል የሚለው አመለካከት ነው። ስለዚህ ቀዝቃዛው ጦርነት ቢያከትምም ብዙ የሠለጠኑ አገሮች ለብሔራዊ ደኅንነት የሚመደበው ወጪ አሁንም ከፍተኛ መሆን እንዳለበት ይከራከራሉ። ጄምስ ውልሲ የአሜሪካ የስለላ ድርጅት ዲሬክተር በነበሩበት ወቅት በየካቲት 1993 ለኮንግሬሱ ባደረጉት ንግግር “ምንም እንኳ ትልቁን ዘንዶ [ሶቭየት ኅብረትን] የገደልነው ቢሆንም አሁን የምንኖረው የተለያዩ መርዛማ እባቦች በሞሉበት ጫካ ውስጥ ነው” ብለው ነበር።

ታዳጊ አገሮችም ወደፊት ኃያላን ሊሆኑ ይችላሉ ብለው የሚያስቧቸውን አገሮችና እንደ መርዛማ እባቦች አድርገው የሚመለከቷቸውን ሌሎች አገሮች ለመከላከል ከፍተኛ ወታደራዊ ወጪዎች ማድረጋቸው ተገቢ እንደሆነ ይናገራሉ። ሆኖም የተባበሩት መንግሥታት የልማት ፕሮግራም “ታዳጊ አገሮች በአገር ደረጃ ያካሄዷቸው ጦርነቶች እምብዛም ሲሆኑ ብዙዎቹ የጦር ኃይላቸውን የሚጠቀሙበት ሕዝባቸውን ረግጠው ለመግዛት ነው” በማለት እውነታውን ገልጾታል። እንዲያውም እንዲህ ሲል ሪፖርት አድርጓል:- “በታዳጊ አገሮች ውስጥ ማኅበራዊ ጉዳዮች ችላ በመባላቸው የተነሣ (በተመጣጠነ ምግብ እጥረትና ሊከላከሏቸው በሚችሏቸው በሽታዎች ሳቢያ) ሊሞቱ የሚችሉት ሰዎች ቁጥር ከውጪ ከሚመጣ ወራሪ ኃይል ጋር በሚደረግ ጦርነት ሊሞቱ ከሚችሉት ሰዎች በ33 እጥፍ ይበልጣል። ሆኖም የወታደሮች ብዛት ከሐኪሞች ብዛት ጋር ሲወዳደር በአማካይ ለእያንዳንዱ ሐኪም 20 ወታደሮች ይደርሱታል። የወታደሮች መብዛት ደግሞ የግለሰቦችን ደኅንነት አስተማማኝ ከማድረግ ይልቅ ይበልጥ አደጋ ላይ እንደሚጥለው የታወቀ ነው።”

ዓለም አቀፉ የጦር መሣሪያዎች ንግድ

በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ሁለቱ ልዕለ ኃያላን አገሮች ከአጋሮቻቸው ጋር ያላቸውን አንድነት ለማጠናከር፣ ወታደራዊ የጦር ሰፈር ለማግኘትና የኃይል ሚዛንን ለመጠበቅ ሲሉ ለጦር አጋሮቻቸው የጦር መሣሪያዎችን ይሸጡ ነበር። የብዙ ብሔራት ሠራዊት በከፍተኛ ደረጃ አድጎ ነበር። ለምሳሌ ያህል በአሁኑ ጊዜ 33 አገሮች እያንዳንዳቸው ከ1,000 በላይ የጦር ታንኮች አሏቸው።

ቀዝቃዛው ጦርነት በማክተሙ የጦር መሣሪያዎች ሽያጭ እንዲጧጧፍ ያደረጉት ፖለቲካዊና ስትራቴጂካዊ ምክንያቶች አሁን ቀንሰዋል። ሆኖም አሁንም ቢሆን ኃይለኛ ኢኮኖሚያዊ ግፊቶች አሉ። የጦር መሣሪያዎች ከፍተኛ ትርፍ ያስገኛሉ! ስለዚህ የአገር ውስጥ የጦር መሣሪያዎች ፍላጎት እየቀነሰ ሲሄድ የጦር መሣሪያ አምራቾች ሥራው ሳይቋረጥ እንዲቀጥልና ኢኮኖሚው እንዳይቆረቁዝ ማድረግ የሚቻለው የጦር መሣሪያዎችን ወደ ውጭ ልኮ በመሸጥ እንደሆነ በመግለጽ መንግሥታቶቻቸውን ያሳምናሉ።

ወርልድ ዎች የተባለው መጽሔት “ልዕለ ኃያላኑ አገሮች ትላልቅ የኑክሌር ሚሳኤሎቻቸውን እንዳስወገዱ ሁሉ ወዲያውኑ ተራ ቦምቦቻቸውንና የጦር መሣሪያዎቻቸውን ለሚገዛቸው ሁሉ መሸጥ የሚችሉባቸውን መንገዶች ለማግኘት መሯሯጣቸው ግራ የሚያጋባ ሆኗል” የሚል አስተያየት ሰጥቷል። ምን ያህል ዋጋ የሚያወጣ መሣሪያ ሸጠዋል? የስቶክሆልሙ ዓለም አቀፍ የሰላም ምርምር ተቋም እንዳለው ከሆነ ከ1988 እስከ 1992 ድረስ ባሉት ዓመታት በዓለም ገበያ የተሸጡት ተራ የጦር መሣሪያዎች ዋጋ 151 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር ነው። ከሁሉ ይበልጥ በብዛት የጦር መሣሪያዎችን በመሸጥ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘችው ዩናይትድ ስቴትስ ስትሆን ከእርሷ ቀጥሎ ያለውን ደረጃ የያዙት የቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት አገሮች ነበሩ።

የኑክሌር ስጋት አሁንም እንዳለ ነው

ስለ ኑክሌር ስጋትስ ምን ለማለት ይቻላል? ዩናይትድ ስቴትስና ሶቭየት ኅብረት (ወይም በእርሷ የተተኩት መንግሥታት) በ1987 የመካከለኛ ርቀት የኑክሌር የጦር መሣሪያዎችን ለማስወገድ የተፈራረሙ ሲሆን በ1991 እና በ1993 ደግሞ ስትራቴጂካዊ የጦር መሣሪያዎችን ለመቀነስ (ስታርት) የተባሉ ሁለት ስምምነቶች አድርገው ነበር።

ስታርት የተባሉት ስምምነቶች ከአንድ በላይ አረር ያላቸውን መሬት ለመሬት የሚምዘገዘጉ ሚሳኤሎች ከማገዳቸውም በላይ እስከ 2003 ባሉት ዓመታት ውስጥ ሦስት አራተኛ የሚሆኑት የኑክሌር አረር ተሸካሚዎች እንዲወገዱ ይጠይቃሉ። ምንም እንኳ ሦስተኛው የዓለም የኑክሌር ጦርነት ስጋት የተወገደ ቢሆንም አሁንም ቢሆን በምድር ላይ ያለውን ሕይወት ብዙ ጊዜ ማጥፋት የሚችሉ የኑክሌር የጦር መሣሪዎችን የያዙ ሰፋፊ ግምጃ ቤቶች አሉ።

የእነዚህ መሣሪያዎች የተለያዩ ክፍሎች ተፈታተው መቀመጣቸው የኑክሌር ሌብነት እንዲስፋፋ አድርጓል። ለምሳሌ ያህል ሩስያ በየዓመቱ 2,000 አረሮችን እየፈታታች ታስቀምጣለች፤ በዚህ ጊዜ ከእነርሱ ውስጥ ፒት የሚባሉ የእጅ ጭብጥ የሚያክሉ የፕሉቶኒየም ኳሶች ይወጣሉ። ከፍተኛ ወጪና ቴክኖሎጂ የሚጠይቀው አንድ የአረር ፒት የኑክሌር ቦምብ ለመሥራት የሚያስፈልግ መሠረታዊ ነገር ነው። አብዛኛውን ጊዜ ፒቶቹ የራዲዮ አክቲቭ ጨረሮች እንዳይወጡ ለማድረግ ሲባል በጠንካራ ብረት ስለሚታሸጉ ሌባ በኪሱ ይዟቸው ሊሄድ ይችላል። ተዘጋጅቶ የተቀመጠ ፒት ያገኘ አንድ ሽብር ፈጣሪ ፒቱን የሚያፈነዳ መሣሪያ በመግጠም እጅግ ኃይለኛ የሆነ ቦምብ መሥራት ይችላል።

ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ የኑክሌር መሣሪያ ያላቸው አገሮች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ሊሄድ የሚችል መሆኑ ነው። የኑክሌር መሣሪያ እንዳላቸው በይፋ የሚታወቁ አምስት አገሮች አሉ፤ እነርሱም:- ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ሩስያ፣ እንግሊዝና ዩናይትድ ስቴትስ ናቸው። ሌሎች በርካታ አገሮችም በአጭር ጊዜ ውስጥ የኑክሌር መሣሪያ የመሥራት አቅም እንዳላቸው ይገመታል።

የኑክሌር መሣሪያ ባለቤት የሆኑ አገሮች ቁጥር እየጨመረ በሄደ መጠን አንድ ሰው በእነዚህ መሣሪያዎች መጠቀም የሚችልበት አጋጣሚ ይጨምራል። ሰዎች እነዚህን በጣም ኃይለኛ የሆኑ የጦር መሣሪያዎች የሚፈሩበት በቂ ምክንያት አላቸው። ዘ ትራንስፎርሜሽን ኦቭ ዎር የተባለው መጽሐፍ እንደገለጸው “የኑክሌር መሣሪያዎች ያላቸው ኃይል እጅግ ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሣ ሌሎቹ የጦር መሣሪያዎች ከኑክሌር መሣሪያዎች አንፃር ሲታዩ ከቁብ አይቆጠሩም።”

የጦር መሣሪያ ቅነሳና ሰላም

ሆኖም ብሔራት እጅግ የተራቀቁ የጥፋት መሣሪያዎቻቸውን ቢያስወግዱስ? ይህ ሰላማዊ ዓለም ለማምጣት ዋስትና ይሆናልን? ፈጽሞ አይሆንም። የጦርነት ታሪክ ጸሐፊ የሆኑት ጆን ኪገን የሚከተለውን አስተያየት ሰንዝረዋል:- “ከነሐሴ 9, 1945 ወዲህ አንድም ሰው በኑክሌር መሣሪያዎች አልተገደለም። ከዚህ ቀን አንሥቶ በነበሩት ዓመታት በጦርነት የሞቱት 50,000,000 ሰዎች በአብዛኛው የተገደሉት ርካሽ በሆኑና በብዛት በሚመረቱ አነስተኛ የጦር መሣሪያዎች ሲሆን እነዚህ የጦር መሣሪያዎች የሚያወጡት ዋጋ በወቅቱ የዓለምን ገበያ ካጥለቀለቁት የትራንዚስተር ሬዲዮዎችና ባትሪዎች ዋጋ እምብዛም አይበልጥም።”

የተራቀቀ ቴክኖሎጂ በማይጠይቁ የጦር መሣሪያዎች በመጠቀም ረገድ በቅርቡ በሩዋንዳ የተካሄደው ጭፍጨፋ ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል፤ ይህችን አገር በተመለከተ ዘ ወርልድ ቡክ ኢንሳክሎፔድያ (1994) እንዲህ ይላል:- “አብዛኞቹ ሰዎች የሮማ ካቶሊኮች ናቸው። . . . የአብዛኞቹን አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ሥራ የሚያካሂዱት የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንና ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።” ሆኖም በሩዋንዳ ውስጥ ግማሽ ሚልዮን የሚያህሉ ሰዎች በቆንጨራ ተገድለዋል። በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ለዓለም ሰላም ለማምጣት የኑክሌር ጦር መሣሪያዎችንና ሌሎች የጦር መሣሪያዎችን ከመቀነስ የበለጠ ነገር ማድረግ ይጠይቃል። በተጨማሪም የዓለም ሃይማኖቶች ከሚያስተምሯቸው ትምህርቶች ሌላ አንድ የሚያስፈልግ ነገር አለ።

የጎሣ ሽኩቻ ጨምሯል

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር የሆኑት ሳዳኮ ኦጋታ በቅርቡ እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ከቀዝቃዛው ጦርነት በኋላ ችግሮቹ በሙሉ ይወገዳሉ ብለን አስበን ነበር። በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት ልዕለ ኃያላኑ በእነርሱ ቁጥጥር በነበሩ አገሮች ውስጥ በየበኩላቸው ኃይል ተጠቅመውም ቢሆን ሥርዓት የሚያስከብሩበት ሁኔታ እንደነበረ አልተገነዘብንም ነበር። . . . ስለዚህ አሁን ቀዝቃዛው ጦርነት ካለፈ በኋላ በአብዛኛው ኋላ ቀር የሆነ፣ ታምቆ የቆየና ምናልባትም ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በፊት እንደ ነበሩት ያለ የጎሣ ግጭት ሲፈነዳ በመመልከት ላይ ነን።”

ታሪክ ጸሐፊና ደራሲ የሆኑት የፑልትዘር ሽልማት አሸናፊ አርተር ሽሌዚንገር እንዲህ በማለት ተመሳሳይ ነጥብ ገልጸዋል:- “አንዱ ዓይነት ጥላቻ በሌላው ዓይነት ጥላቻ ይተካል። በምሥራቅ አውሮፓና በሶቭየት ኅብረት ሕዝቡን አፍኖ ይዞት የነበረው የፖለቲካ አመለካከት መወገዱ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ሥር ሰደውና በሰው አእምሮ ውስጥ ሰርጸው የኖሩትን የጎሣ፣ የብሔረተኝነት፣ የሃይማኖትና የቋንቋ ቅራኔዎች እንዲገነፍሉ አድርጓል። . . . 20ኛው መቶ ዘመን የፖለቲካ አመለካከት ጦርነት የተደረገበት ዘመን ከነበረ 21ኛው መቶ ዘመን ደግሞ የጎሣ ጦርነቶች የሚካሄድበት ዘመን ይሆናል።”

የተባበሩት መንግሥታት ባደረገው ቆጠራ መሠረት ከ1989 እስከ 1992 ድረስ 82 የትጥቅ ውጊያዎች የነበሩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ አብዛኞቹ የተደረጉት በታዳጊ አገሮች ውስጥ ነው። በ1993 በ42 አገሮች ውስጥ ከባድ ፍልሚያዎች የተካሄዱ ሲሆን በሌሎች 37 አገሮች ውስጥ ፖለቲካዊ ዓመፅ ተካሂዷል። ይህ በእንዲህ እያለ የተባበሩት መንግሥታት የሚቻለውን ያህል ከፍተኛ በጀት መድቦ ሰላምን ለማምጣት 17 ወታደራዊ ዘመቻዎችን በማድረግ ቢታገልም ብዙም አልተሳካለትም። በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው የሰው ልጅ ሰላማዊ ዓለም ለማግኘት ወደ ሌላ አቅጣጫ መመልከት ይኖርበታል።

ከፊታችን የተደቀኑ ችግሮች

ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ብዙ ሰዎች የወደፊቱን ጊዜ በብሩህ ሁኔታ ከመመልከት ይልቅ ስጋታቸውን በመግለጽ ላይ ናቸው። ዘ አትላንቲክ መንዝሊ የተባለው መጽሔት የካቲት 1994 ባወጣው እትም ሽፋኑ ላይ ከፊታችን ያሉትን አሥርተ ዓመታት በተመለከተ የሚከተለውን አጠር ያለ ትንበያ አቅርቦ ነበር:- “በተፈጥሮና በማኅበራዊ አደጋ ምክንያት ከቀዬአቸው የሚፈናቀሉ ስደተኞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ብሔራት ይንኮታኮታሉ። . . . በተፈጥሮ ሀብቶች መመናመን በተለይም በውኃ እጥረት ሳቢያ ጦርነቶች ይደረጋሉ። የታጠቁ መንግሥት የለሽ ዘራፊዎች ከታላላቅ ሰዎች የጥበቃ ጓዶች ጋር በሚያደርጉት ግጭት ጦርነትና ወንጀል መፈጸማቸውን ይቀጥላሉ።”

ታዲያ ይህ ማለት ዘላቂ ሰላም ሊገኝ አይችልም ማለት ነውን? ፈጽሞ አይደለም! የሚቀጥለው ርዕስ የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ የምንችልባቸውን ምክንያቶች ይገልጻል።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ሃይማኖት ሰላም እንዲሰፍን አስተዋጽኦ አድርጓልን?

መንግሥታት ወደ ጦር ሜዳ ሲሄዱ የዓለም ሃይማኖቶች ስለ ሰላምና ወንድማማችነት መስበካቸውን ያቆማሉ። በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት የነበረውን ሁኔታ በተመለከተ የብሪታንያው ብርጋዴል ጄኔራል ፍራንክ ፒ ክሮዜር “አብያተ ክርስቲያናት ደም ለማፋሰስ እንደፈለግን የምንጠቀምባቸው ከሁሉ የተሻሉ መሣሪያዎቻችን ናቸው” ብለው ነበር።

በየትኛውም ዘመን ሃይማኖት በጦርነት ውስጥ የተጫወተው ሚና ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ነው። የካቶሊክ እምነት ተከታይ የሆኑት ታሪክ ጸሐፊው ኢ አይ ዋትኪን እውነታውን አምነው በመቀበል እንዲህ ሲሉ ገልጸዋል:- “ጳጳሳት በሀገራቸው መንግሥት የተደረጉትን ጦርነቶች ያለማቋረጥ እንደደገፉ መናገር ደስ የማይል ቢሆንም ሞራልን ይጎዳል ወይም ታማኝነት የጎደለው ድርጊት ነው በሚል የተሳሳተ ምክንያት ታሪካዊውን ሐቅ መካድ ወይም ችላ ማለት አንችልም።” በተጨማሪም በቫንኩቨር ካናዳ እየታተመ የሚወጣው ሳን የተባለው ጋዜጣ ርዕሰ አንቀጽ “ቤተ ክርስቲያን የባንዲራ ተከታይ መሆኗ የሁሉም የተደራጁ ሃይማኖቶች ደካማ ጎን ሳይሆን አይቀርም። . . . አምላክ በሁሉም ጎራ ከጎናቸው እንደ ተሰለፈ ያልተነገረለት ጦርነት ተደርጎ ያውቃልን?” ብሏል።

በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው የዓለም ሃይማኖቶች ሰላም እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ከማድረግ ይልቅ በሩዋንዳ ውስጥ ጎልቶ እንደታየው ጦርነትንና እልቂትን አስፋፍተዋል።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

የጦርነት ከንቱነት

በ1936 በታተመው አይ ፋውንድ ኖ ፒስ በተባለው መጽሐፍ ላይ በውጭ አገር ቃል አቀባይ ሆነው ይሠሩ የነበሩት ዌብ ሚለር “በጣም የሚገርመው [የአንደኛው የዓለም ጦርነት] ሰቆቃ፣ ዘግናኝነትና ከንቱነት የተሰማኝ ጦርነቱ ካበቃ ከስምንት ዓመት በኋላ ነበር” ሲሉ ጽፈዋል። የ1,050,000 ሰዎች ሕይወት የረገፈበት ሥፍራ ነው ብለው የገለጹትን የቬርደን የጦር አውድማ በዚያ ወቅት እንደገና ጎብኝተው ነበር።

ሚለር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት ተታልለው እንደነበሩት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እኔም ተታልዬ ነበር። የመጀመሪያው የዓለም ጦርነት አዳዲስ ጦርነቶች እንዲነሡ ከማድረግ ሌላ ያስገኘው ፋይዳ የለም። ስምንት ሚልዮን ተኩል ሰዎች በከንቱ ሞተዋል፣ በአሥር ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ይህ ነው የማይባል ሰቆቃ ደርሶባቸዋል፤ በብዙ መቶ ሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከባድ ሐዘን፣ ድህነትና ሥቃይ ደርሶባቸዋል። ይህ ሁሉ የተፈጸመው በጣም ስለ ተታለልን ነው።”

ይህ መጽሐፍ ታትሞ ከወጣ ከሦስት ዓመት በኋላ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ፈነዳ። ዘ ዋሽንግተን ፖስት የተባለው ጋዜጣ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “በ20ኛው መቶ ዘመናችን የተካሄዱት ጦርነቶች በወታደሮችም ሆነ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥፋት ለማድረስ የታለሙ ‘የጅምላ ጦርነቶች’ ነበሩ። . . . በቀደሙት መቶ ዘመናት ያልሠለጠኑ ናቸው በሚባሉ ሕዝቦች የተፈጸሙት ጦርነቶች ከእነዚህ ጦርነቶች ጋር ሲወዳደሩ በጣም አነስተኛና ከቁጥር የማይገቡ ናቸው።” አንድ ምሁር እንደገመቱት ከሆነ ከ1914 ወዲህ በጦርነቶችና በሕዝብ ረብሻዎች ሳቢያ 197 ሚልዮን ሰዎች ሞተዋል።

ሆኖም ሰዎች ያካሄዷቸው ጦርነቶችና ዓመፆች በሙሉ ሰላምና ደስታ አላስገኙም። ዘ ዋሽንግተን ፖስት “በዚህ መቶ ዘመን በሚልዮን የሚቆጠሩ ረብሸኞችን ሊያረጋጋና ሊያሳርፍ የቻለ አንድም ፖለቲካዊ ወይም ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት እስካሁን ድረስ አልተገኘም” ብሏል።

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ይህች እናት በሩዋንዳ ውስጥ በግፍ ከተጨፈጨፉት በሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች አንዷ ናት፤ ብዙዎቹ የተገደሉት በራሳቸው የሃይማኖት አባላት ነው

[ምንጭ]

Albert Facelly/ Sipa Press

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ