በስልክ ስትነጋገር ምን ዓይነት ጠባይ ታሳያለህ?
“ከቤተሰብ ፍቅር፣ ከጤናና ከሥራ ፍቅር ቀጥሎ የደግነት ቃላት የመለዋወጥን ያህል ለሕይወት አስደሳችነት አስተዋጽኦ የሚያደርግ፣ ለራሳችን ያለንን ግምት ከፍ የሚያደርግና የሚያድስ ነገር ሊኖር ይችላልን?”
ሟቿ አሜሪካዊት ደራሲና የትምህርት ባለሞያ ሉሲ ኤልየት ኪለር ይህን ጥያቄ ሲጠይቁ የሰው ልጅ በተፈጠረበት ጊዜ ከፈጣሪ ከተሰጠው በአንደበት የመነጋገር ችሎታ ምን ያህል ደስታና እርካታ እንደሚገኝ መግለጻቸው ነበር።— ዘጸአት 4:11, 12
ባለፉት 120 ዓመታት የሰው ልጆች እንደልብ የንግግር ልውውጥ እንዲያደርጉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገው በአሌክሳንደር ግራሃም ቤል የተፈለሰፈው ስልክ ነው። በዛሬው ጊዜ በመላው ዓለም ለሚኖሩ በቢልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለሥራ ጉዳይም ሆነ እንዲሁ ለመደሰት ትልቅ የመገናኛ መስመር የሆነው ስልክ ነው።
ስልክና አንተ
የስልክ አገልግሎት ኑሮህን ምን ያህል አበልጽጎታል? ለዚህ ጥያቄ የምትሰጠው መልስ የሚመካው ከግዑዙ መሣሪያ ይልቅ በመሣሪያው ተጠቃሚዎች ላይ እንደሆነ አትስማማም? በእርግጥም በስልክ ስትነጋገር የጨዋነት ጠባይ ታሳያለህን? ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።
በስልክ አጠቃቀም ረገድ ጨዋነት ማሳየት የአእምሮ ዝንባሌን፣ የንግግር ችሎታንና የማዳመጥ ችሎታን የሚመለከት ጉዳይ ነው። በተጨማሪም የስልክ አጠቃቀምንና ለመረበሽ ታስበው የሚደወሉ ጥሪዎችን በተገቢ ሁኔታ ማስተናገድን ይመለከታል።
ለሌሎች አሳቢነት ማሳየት
በስልክ አጠቃቀም ጨዋነት ማሳየት እንደማንኛውም ሰብዓዊ መስተጋብር ለሌሎች ሰዎች አሳቢ ከመሆን የሚመነጭ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “እያንዳንዱ የራሱን ጥቅም ብቻ ሳይሆን የሌላውንም ሰው ጥቅም ያስብ” ሲል ጽፏል።— ፊልጵስዩስ 2:4 ዘ ኒው ኢንግሊሽ ባይብል
ሰፊ ተሞክሮ ያላት አንዲት የስልክ ኦፕሬተር “በጣም ከተለመዱት መጥፎ የስልክ አጠቃቀም ልማዶች አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?” ተብላ ስትጠየቅ በአንደኛነት የጠቀሰችው “አበበ ነኝ ብሎ ጥሪውን የሚጀምርን ሰው ነው። (ስንት አበበዎች አሉ?) ከዚህ የሚብሰው ደግሞ ‘እኔ ነኝ’ ወይም ‘ማን እንደሆንኩ እወቂ’ የሚለው ሰው ነው።” በቅን ልቦና የተደረገ ቢሆንም እንዲህ ያለው አሳቢነት የጎደለው አቀራረብ ግራ የሚያጋባና ትዕግሥትን የሚፈትን ሊሆን ይችላል። ይህችው ኦፕሬተር በመቀጠል “ማንነታችሁን በግልጽ በማሳወቅና ለደወላችሁለት ሰው አሳቢነት ለማሳየት ልታነጋግሩት ትችሉ እንደሆነ ጠይቃችሁ ጥሪያችሁን አስደሳች በሆነ አቀራረብ ብትጀምሩ አይሻልም?” ብላለች።
የፊትህ ገጽታ ሊታይ ባይችልም ዝንባሌህ ከአነጋገርህ ግልጽ ሊሆን እንደሚችል አስታውስ። እንዴት? በድምፅህ ቅላጼ ነው። ትዕግሥት ማጣት፣ መሰልቸት፣ ቁጣ፣ ቸልተኝነት፣ ቅንነት፣ ደስተኝነት፣ ለመርዳት ፈቃደኛ መሆንና የፍቅር ስሜት ከአነጋገር ይታወቃል። እርግጥ ማንም ሰው የሚሠራው ሥራ በስልክ ጥሪ ሲቋረጥበት በስጨት ይል ይሆናል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥምህ ለጨዋነት ስትል ስልኩን ከመመለስህ በፊት ቆም ብለህ “ፈገግ” ለማለት ሞክር። የሚያስከፋ አነጋገር ሳይጠቀሙ አለመስማማትን መግለጽ ይቻላል።
በአሳቢነት ላይ ደስ የሚል የአነጋገር ቅላጼ ሲጨመር “ለሚሰሙት ጸጋን ይሰጥ ዘንድ፣ እንደሚያስፈልግ ለማነጽ የሚጠቅም ማናቸውም በጎ ቃል” መናገር ይቻላል።— ኤፌሶን 4:29
የጨዋ አነጋገር
አዎን፣ የአነጋገር ስልታችን ትልቅ ቦታ አለው። ከሚከተሉት ሕጎች ጋር ትስማማለህ? ሕጎቹንስ ታከብራለህ? በተፈጥሮ የአነጋገር ስልትህ በሚገባ ሁኔታ ተናገር። የስልክ ጥሪው ሩቅ ቦታ ቢሆንም አትጩህ። አጥርተህ ተናገር። ስትናገር አንዳንድ ፊደላትን አትዋጥ። የተናገሩትን መልሶ መድገም ወይም እ––እ ማለት ግራ ስለሚያጋባና ስለሚያናድድ መወገድ ይኖርበታል። በአንድ ዓይነት ቅላጼ አትናገር። የድምፅን ቃና፣ መጠንና ቅላጼ መለዋወጥና አስፈላጊ ቃላትን በተገቢ ሁኔታ ማጥበቅ አንድን ንግግር ትርጉም ያለው፣ ውብና አስደሳች ያደርጋል። በተጨማሪም ምግብ እየበሉ በስልክ መነጋገር የንግግርህን ጥራት የሚያበላሽ ከመሆኑም በላይ ጨዋነት እንዳልሆነ አትዘንጋ።
የቃላት ምርጫም ሊታሰብበት የሚገባ ነገር ነው። በዚህ ረገድ አስተዋይ መሆን አስፈላጊ ነው። ለመረዳት በማያስቸግሩ ግልጽና ቀላል ቃላት ተጠቀም። ቃላት የየራሳቸው አንድምታ አላቸው። ጭካኔን ወይም ደግነትን የሚገልጹ፣ ለስላሳ ወይም ሻካራ፣ የሚያበረታቱ ወይም ተስፋ የሚያስቆርጡ ሊሆኑ ይችላሉ። ከዚህም በላይ ሌሎችን ሳያስቆጡ መቀለድ፣ አጠራጣሪ ነገር ሳይናገሩ ዘዴኛ መሆንና ጨዋነት የጎደለው ቃል ሳይናገሩ ግልጽ መሆን ይቻላል። “እባክዎ” እና “አመሰግናለሁ” እንደሚሉት ያሉት የጨዋነት ቃላት ምን ጊዜም ተፈላጊዎች ናቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ “ለእያንዳንዱ እንዴት እንድትመልሱ እንደሚገባችሁ ታውቁ ዘንድ ንግግራችሁ ሁልጊዜ በጨው እንደተቀመመ በጸጋ ይሁን” ሲል የጻፈው ደግነትና አሳቢነት በሚንጸባረቅባቸውና ጣዕምና ለዛ ባላቸው ቃላት እንድንጠቀም ሊያሳስብ ፈልጎ ነው።— ቆላስይስ 4:6
ጥሩ አዳማጭ ሁን
አንድ ወጣት አባቱን ከሰዎች ጋር የመነጋገር ችሎታ እንዲኖረኝ የሚያስችለኝ ምስጢር ምንድን ነው? ብሎ ጠየቀው ይባላል። አባትዬውም “ልጄ ሆይ፣ አዳምጥ” አለው። ወጣቱም “አዳምጣለሁ፣ ሌላስ?” አለው። አባትም መልሶ “ምንም ሌላ የምነግርህ ነገር የለም፣ ምስጢሩ ይኸው ነው” አለው ይባላል። በእርግጥም ስልክ ስታነጋግር የጨዋነት ጠባይ ለማሳየት አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች አንዱ በፍላጎትና በስሜት ማዳመጥ ነው።
አንድ ቀላል ደንብ አለማክበር አሰልቺ ከሆኑ የስልክ ተናጋሪዎች ሊያስመድብህ ይችላል። ይህ ደንብ ምንድን ነው? አንተ ብቻ ተናጋሪ አትሁን። ለምሳሌ ያህል ስላጋጠመህ ነገር የማያልቅ ተራ ወሬ በማውራት ወይም ስላሉብህ የጤና ችግሮች ሰፊ ገለጻ በመስጠት አትመሰጥ። በዚህም ላይ ተገቢ መመሪያ የሚሰጠን የመጽሐፍ ቅዱስ ሕግ አለ። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ለማዳመጥ ፈጣን ለመናገር ግን የዘገየህ ሁን” ብሏል።— ያዕቆብ 1:19 ጀሩሳሌም ባይብል
በመጨረሻ ሊታሰብባቸው የሚገቡ ነገሮች
አሁን በስልክ አጠቃቀም ረገድ ጨዋነት በማሳየት ዘርፍ ውስጥ የሚካተቱ ሁለት የመጨረሻ ጥያቄዎችን እንመልከት። ስለ ስልክ አጠቃቀም ምን ሊባል ይችላል? ለመረበሽ ታስበው የሚደወሉ የስልክ ጥሪዎችን በተመለከተ አንዳንድ ጠቃሚ የሆኑ ሐሳቦች ይኖራሉ?
በስልክ ሰው ስታነጋግር የሚያነጋግርህ ሰው ድምፅ ሄድ፣ መጣ እያለ አስቸግሮህ ያውቃልን? ይህ ዓይነቱ ሁኔታ የስልኩን መነጋገሪያ ከከንፈሮችህ 2 ሳንቲ ሜትር ያህል ብቻ አርቀህ እንድትናገር ሊያሳስብህ ይገባል። በተጨማሪም ሊረብሹ የሚችሉ ድምፆችን ማጥፋት ጨዋነት ነው። ስልክ በምትደውልበት ጊዜ ጥሪው ወደ ተሳሳተ ቦታ እንዳይሄድ ቁጥሮቹን በጥንቃቄ ተጫን ወይም አዙር። ንግግርህን ከጨረስክ በኋላ ደግሞ መነጋገሪያውን በቦታው ላይ በቀስታ አስቀምጥ።
አንተን ለመረበሽ ሲሉ ብቻ ስልክ ደውለውልህ የሚያውቁ ሰዎች አሉን? እንደነዚህ ያሉ ጥሪዎች እየጨመሩ መሄዳቸው በጣም የሚያሳዝን ነው። ጨዋነት የጎደለው፣ አንተነትህን የሚዳፈር ወይም የብልግና ንግግር ስትሰማ ማድረግ የሚገባህ አንድ ነገር ብቻ ነው። ስልኩን ዝጋ። (ከኤፌሶን 5:3, 4 ጋር አወዳድር።) ደዋዩ ማንነቱን ካላሳወቀህም ስልኩን ከመዝጋት የተሻለ አማራጭ አይኖርህም። አንድን ጥሪ የምትጠራጠሩበት ምክንያት ካላችሁ ሃው ቱ ራይት ኤንድ ስፒክ ቤተር የተባለው መጽሐፍ “አንድ የማታውቁት ሰው ድምፅ ‘ማን ልበል?’ ብሎ ቢጠይቃችሁ መልስ አትስጡ፣ ልታደርጉ ያሰባችሁትንም ነገር እንግዳ ለሆነ ሰው አትግለጹ” ሲል ይመክራል።
በመጨረሻም በስልክ አጠቃቀም ረገድ ጨዋነት ለማሳየት በርካታ ሕጎችና ደንቦች አስፈላጊ አለመሆናቸውን ማወቅ በጣም ጥሩ ነው። እንደ ማንኛውም የሰው ከሰው ግንኙነት አስደሳችና ዋጋ ያለው ዝምድና ሊመሠረት የሚችለው በተለምዶ ወርቃማው ሕግ ተብሎ የሚጠራውን ትእዛዝ ሥራ ላይ በማዋል ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ “እንግዲህ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተ ደግሞ እንዲሁ አድርጉላቸው” ብሏል። (ማቴዎስ 7:12) ክርስቲያን የሆነ ሰው ደግሞ ለሰው ልጅ የመናገር ስጦታ የሰጠውን አምላክ ለማስደሰት ይፈልጋል። መዝሙራዊው “አቤቱ፣ ረድኤቴ መድኃኒቴም፣ የአፌ ቃልና የልቤ አሳብ በፊትህ ያማረ ይሁን” ሲል ጸልዮአል።— መዝሙር 19:14