ድህነት ‘ድምፅ አልባው አደጋ’
ዶክተር ማህቡብ ኡልሃቅ የተባሉት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አማካሪ “የዓለማችን ሙቀት ስለ መጨመሩ፣ የኦዞን ሽፋን ስለ መሳሳቱና ስለ ውቅያኖሶች ብክለት በብዛት ሲለፈፍ እንሰማለን። ይሁን እንጂ የምድር ሙቀት መጨመርም ሆነ በስፋት የሚለፈፍላቸው ሌሎች አደጋዎች ገና አንድም ሰው ያልገደሉ ሲሆን ድምፃቸውን ያላሰሙት አደጋዎች ግን በየቀኑ ባላደጉ አገሮች የሚኖሩ በርካታ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፉ ነው” ብለዋል። ዶክተር ኡልሃቅ ከእነዚህ ድምፅ አልባ አደጋዎች መካከል ስለ አንዱ አስተያየታቸውን ሲሰጡ “ተወዳዳሪ የሌለው ነፍሰ ገዳይ ድህነት ነው” ብለዋል። እንዴት ሊሆን ይችላል?
ከአንድ ዶላር ባነሰ የቀን ገቢ ኑሯቸውን ከሚገፉት 1.3 ቢልዮን የሚያክሉ የዓለም ሕዝቦች መካከል ብዙዎቹ ሕይወታቸው የሚቀጠፈው በድህነት ምክንያት ነው። ዩ ኤን ክሮኒክል የተባለው መጽሔት እንደዘገበው በየዓመቱ 18 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች “ከድህነት ጋር ተዛምዶ ባላቸው ምክንያቶች” ይሞታሉ። ይህ በጣም ከፍተኛ የሆነ ቁጥር ነው! 18 ሚልዮን የሚያክለው የአውስትራሊያ ሕዝብ በአንድ ዓመት ውስጥ በችጋር አለቀ ቢባል ምን ያህል የዜና ማሰራጫዎች ትኩረት እንደሚሰጠው ገምቱ! የእነዚህ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ግን አንድ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የራዲዮ ስርጭት እንዳለው “ብዙ አይወራለትም።” በእርግጥም ‘ድምፅ አልባ እልቂት’ ነው።
ዝምታው እንዲያበቃ ለማድረግ ከ117 አገሮች የተውጣጡ ልዑካን የመጀመሪያውን የዓለም ማኅበራዊ እድገት ጉባኤ አድርገው የዓለምን የድህነት ችግር ማሸነፍ ስለሚቻልበት መንገድ ተወያይተዋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም አስተዳዳሪ የሆኑት ጄምስ ጉስታቭ ስፔት “ከአንድ መቶ ሃምሳ ዓመታት በፊት መላው ዓለም በባርነት ላይ ጦርነት አውጆ ነበር” ካሉ በኋላ “ዛሬ ደግሞ በዓለም አቀፍ ድህነት ላይ ዓለም አቀፍ ጦርነት ማወጅ ይኖርብናል” ብለዋል። ይህን ያህል አሳሳቢ የሆነው ለምንድን ነው? እኚሁ ሰው ድህነት “ተስፋ መቁረጥና አለመረጋጋት በማምጣት ላይ ስለሆነ መላውን ዓለም አደጋ ላይ ይጥላል” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ይሁን እንጂ ልዑካኑ ድህነትን ስለሚያጠፉበት መንገድ እየተወያዩ እንዳሉ እንኳን በየቀኑ ድሃ በሆኑ ቤተሰቦች የሚወለዱትን ሕፃናት ብዛት የሚቆጥረው ‘የድህነት ሰዓት’ ዓለም አቀፉ የድህነት ሁኔታ እየከፋ መሆኑን ያመለክት ነበር። በስብሰባው አዳራሽ ውስጥ የተሰቀለው ሰዓት ጉባኤው በተካሄደበት አንድ ሳምንት ውስጥ ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ በሄደው የድሆች ቁጥር ላይ 600,000 አዳዲስ ሕፃናት እንደተጨመሩ አመልክቷል። የጉባኤው የመጨረሻ ቀን ስብሰባ እንዳበቃ ሰዓቱ እንዲቆም ቢደረግም ስፔት እንደተናገሩት “ሰዓቱ መቁጠሩን ቀጥሏል።” አሁን የሚነሳው ጥያቄ ችግሩ ሰሚ ጆሮ ያገኝ ይሆን? የሚለው ነው።