የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 3/8 ገጽ 16-18
  • ቢልሃርዚያን በቅርቡ ማጥፋት ይቻል ይሆን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ቢልሃርዚያን በቅርቡ ማጥፋት ይቻል ይሆን?
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የጥገኛ ተውሳኩ ዑደተ ሕይወት
  • መፍትሔዎችና ችግሮች
  • ለወደፊቱ ምን ተስፋ አለ?
  • የስኬሊ ፉት ቀንድ አውጣ ዛጎል
    ንቁ!—2011
  • የክላስተርዊንክ ቀንድ አውጣ ዛጎል
    ንቁ!—2012
  • ልጃችሁ ትኩሳት ሲይዘው
    ንቁ!—2004
  • ከጥገኛ ተውሳኮች ራሳችሁን ጠብቁ!
    ንቁ!—1999
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 3/8 ገጽ 16-18

ቢልሃርዚያን በቅርቡ ማጥፋት ይቻል ይሆን?

በናይጄርያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

በሳይንስና በሕክምና መስኮች እጅግ አስደናቂ ዕድገቶች የታዩ ቢሆንም የሰው ልጅ ብዙ ዘመናት ያስቆጠሩ ችግሮቹን ሊፈታ አልቻለም። ቢልሃርዚያን ለማጥፋት የተደረጉ ጥረቶችም ከዚህ የተለየ ውጤት አላስገኙም።

ቢልሃርዚያን ለማጥፋት የሚያስችል አቅም ያለ ይመስላል። ዶክተሮች በሽታውን የሚያመጣውን ጥገኛ ተውሳክ ዑደተ ሕይወት ለመረዳት ችለዋል። በሽታው በቀላሉ በምርመራ ይታወቃል። ፈዋሽ መድኃኒቶችም አሉ። የመንግሥታት መሪዎች በሽታውን ለመከላከል ጥረቶች እንዲደረጉ በጣም ይፈልጋሉ። ሆኖም በአፍሪካ፣ በእስያ፣ በካረቢያን ደሴቶችና በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች እንዲሁም በደቡብ አሜሪካ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን የሚያጠቃው ይህ በሽታ በቅርቡ መጥፋት የሚችል አይመስልም።

ቢልሃርዚያ (ሽስቶሶሚያሲስ ተብሎም ይጠራል) ለብዙ ሺህ ዓመታት የሰውን ዘር ሲያሠቃይ ኖሯል። በመድኃኒት እንዳይበሰብሱ በተደረጉ የግብፃውያን አስከሬኖች ላይ ደርቀው የተገኙ የቢልሃርዚያ እንቁላሎች በፈርዖኖች ዘመን ግብፃውያን በዚህ በሽታ ይጠቁ እንደነበር ማረጋገጫ ይሆናሉ። ከሠላሳ ምዕተ ዓመት በኋላ ይኸው በሽታ ግብፅን መውረሩን የቀጠለ ሲሆን በሚልዮን የሚቆጠሩ የአገሪቱን ዜጎች ጤና አቃውሷል። በናይል ዴልታ በሚገኙ አንዳንድ መንደሮች ውስጥ ከ10 ሰዎች መካከል ዘጠኙ በበሽታው ተለክፈዋል።

ግብፅ ቢልሃርዚያ ከሚገኝባቸው 74 ወይም ከዚያ የሚበልጡ አገሮች መካከል አንዷ ብቻ ናት። የዓለም የጤና ድርጅት እንዳሰላው ከሆነ በመላው ዓለም 200 ሚልዮን ሰዎች በዚህ በሽታ ተለክፈዋል። በሽታው ከሚጠናባቸው 20 ሚልዮን ሰዎች መካከል በየዓመቱ 200,000 የሚያህሉት ይሞታሉ። በሽታው ከሚያጠቃቸው ሰዎች ብዛትና ከሚያስከትላቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች አንፃር ሲታይ በሐሩር ክልል ከሚገኙ በጥገኛ ተውሳኮች ከሚመጡ በሽታዎች መካከል ቢልሃርዚያ ከወባ በሽታ ቀጥሎ በሁለተኛነት ደረጃ ይገኛል ተብሏል።

የጥገኛ ተውሳኩ ዑደተ ሕይወት

የቢልሃርዚያን ሁኔታ ተረድቶ ቢልሃርዚያን እንዴት መከላከልና ማዳን እንደሚቻል ለማወቅ ይህን በሽታ የሚያመጣውን ጥገኛ ተውሳክ መረዳት ያስፈልጋል። ቁልፉ ነጥብ የሚከተለው ነው:- ይህ ጥገኛ ተውሳክ በሕይወት ቆይቶ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተባዛ እንዲሄድ ሁለት ባዕድ አስጠጊዎች ማለትም በውስጣቸው ሆኖ ራሱን መመገብና ማሳደግ የሚችልባቸው ሁለት ሕያዋን ፍጥረታት የግድ ያስፈልጉታል። አንዱ ባዕድ አስጠጊ እንደ ሰው ያለ አጥቢ እንስሳ ሲሆን ሌላው ደግሞ ጨው አልባ ውኃ ውስጥ የሚገኝ ቀንድ አውጣ ነው።

ዑደቱ ይህን ይመስላል:- ጥገኛ ተውሳኩ ያለበት አንድ ግለሰብ በኩሬ፣ በሐይቅ፣ በጅረት ወይም በወንዝ አጠገብ በሚጸዳዳበት ወቅት በቀን ወደ አንድ ሚልዮን የሚጠጉ የጥገኛ ተውሳኩ እንቁላሎች ከሰውነቱ ሊወጡ ይችላሉ። እነዚህ እንቁላሎች በጣም ረቂቅ ከመሆናቸው የተነሣ ያለ አጉሊ መነፅር ሊታዩ አይችሉም። እንቁላሎቹ ከውኃ ጋር ሲገናኙ ይፈለፈሉና ጥገኛ ተውሳኮቹ እንደልባቸው መዘዋወር ይጀምራሉ። ጥገኛ ተውሳኮቹ በአካሎቻቸው ላይ ያሉትን ፀጉር የሚመስሉ ጥቃቅን ነገሮች ተጠቅመው በውኃ ውስጥ ወደሚገኙት ቀንድ አውጣዎች ከሄዱ በኋላ የቀንድ አውጣውን አካል ሰርስረው ይገባሉ። ለሚቀጥሉት ከአራት እስከ ሰባት የሚያህሉ ሳምንታት በቀንድ አውጣው አካል ውስጥ ሆነው ይራባሉ።

ከቀንድ አውጣው ከወጡ በኋላ ወደ ሰው ወይም ወደ ሌላ አጥቢ እንስሳ ሳይተላለፉ ከ48 ሰዓታት በላይ ከቆዩ ይሞታሉ። ጥገኛ ተውሳኩ ውኃው ውስጥ ገብቶ እንዲህ ዓይነት ባዕድ አስጠጊ ሲያገኝ ቆዳውን በስቶ ይገባና ከደሙ ጋር ይቀላቀላል። ብዙውን ጊዜ ሰውየው በሰውነቱ ላይ የተካሄደውን ወረራ ባይገነዘበውም በመጠኑ ሊያሳክከው ይችላል። ጥገኛ ተውሳኩ ከሰውየው ደም ጋር ከተቀላቀለ በኋላ እንደ ተውሳኩ ዝርያ ወደ ፊኛ የደም ስሮች አሊያም አንጀት ውስጥ ይገባል። ጥገኛ ተውሳኮቹ በአንድ ሳምንት ውስጥ አድገው 25 ሚሊ ሜትር ርዝመት ያላቸው ወንድና ሴት ትላትሎች ይሆናሉ። ግንኙነት ከፈጠሩ በኋላ ሴቷ በባዕድ አስጠጊያቸው ደም ውስጥ እንቁላሎችን ትጥላለች። በዚህ መንገድ ዑደቱ ያበቃል።

ግማሽ የሚያህሉት እንቁላሎች ከእዳሪ (የአንጀት ቢልሃርዚያ ከሆነ) ወይም ከሽንት ጋር (የፊኛ ቢልሃርዚያ ከሆነ) ከባዕድ አስጠጊያቸው ሰውነት ይወጣሉ። ቀሪዎቹ እንቁላሎች በሰውነቱ ውስጥ ቀርተው በጣም አስፈላጊ የሆኑ የሰውነት ክፍሎችን ያጠቃሉ። በሽታው እየተባባሰ ሲሄድ በሽተኛው ሊያተኩሰው፣ ሆዱ ሊነፋና ውስጣዊ መድማት ሊያጋጥመው ይችላል። ከጊዜ በኋላ ይህ በሽታ የፊኛ ካንሰር ሊያስከትል ወይም የሰውየው ጉበት ወይም ኩላሊት በትክክል እንዳይሠራ ሊያደርግ ይችላል። አንዳንድ የበሽታው ተጠቂዎች መሃን ወይም ሽባ ይሆናሉ። ሌሎች ደግሞ ይሞታሉ።

መፍትሔዎችና ችግሮች

ይህ በሽታ እንዳይስፋፋ ለመግታት ቢያንስ አራት ነገሮችን ማድረግ ይቻላል። ሁሉም ሰው ከእነዚህ እርምጃዎች ውስጥ አንዱን እንኳ በተግባር ላይ ቢያውል በሽታው ይጠፋ ነበር።

የመጀመሪያው እርምጃ በውኃ ውስጥ የሚገኙ ቀንድ አውጣዎችን ማጥፋት ነው። ቀንድ አውጣዎች ለጥገኛ ተውሳኩ እድገት እጅግ አስፈላጊ ናቸው። ቀንድ አውጣዎች ጠፉ ማለት ቢልሃርዚያ ጠፋ ማለት ነው።

አካባቢውን ሳይበክል ቀንድ አውጣዎችን የመግደል ኃይል ያለው መርዝ ለማምረት ከፍተኛ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል። በ1960ዎቹና በ1970ዎቹ ቀንድ አውጣዎችን ለማጥፋት በተደረጉ ሙከራዎች ሳቢያ በውኃ ውስጥ ያሉ ነፍሳት በሙሉ አልቀዋል። ግብፅ ውስጥ የሚገኘው ቲኦዶር የቢልሃርዚያ ምርምር ተቋም ሌሎች ፍጥረታትን የማይጎዳ ሞሉሲሳይድ የተባለ (የቀንድ አውጣ ማጥፊያ) ለማግኘት ብዙ ደክሟል። የተቋሙ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶክተር አሊ ዜን ኢል አብደን ይህን ማጥፊያ በተመለከተ እንዲህ ሲሉ አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል:- “በውኃ ውስጥ ይረጫል፣ በሰብሎች ላይ እንጠቀምበታለን፣ ሰዎችና እንስሳት ከውኃ ጋር ይጠጡታል ደግሞም ዓሦች የሚኖሩት ውኃ ውስጥ ነው። ስለዚህ እነዚህን ሁሉ የማይጎዳ ማጥፊያ መሥራት አለብን።”

ሁለተኛው እርምጃ ደግሞ በሰው ውስጥ የሚገኙትን ጥገኛ ተውሳኮች መግደል ነው። እስከ 1970ዎቹ ድረስ በመድኃኒት የሚሰጠው ሕክምና ብዙ ጉዳቶችንና የጤና ችግሮችን ያስከትል ነበር። ብዙውን ጊዜ ሕክምናው በጣም የሚያም መርፌ ለተከታታይ ቀናት መወጋትን የሚጠይቅ ነበር። አንዳንዶች ሕክምናው ከበሽታው የከፋ ነው ሲሉ አማረዋል! ከዚያ ጊዜ ወዲህ እንደ ፕራዚኳንተል ያሉ ውጤታማ የሆኑ አዳዲስ መድኃኒቶች ተፈልስፈዋል። በተጨማሪም እነዚህ መድኃኒቶች በአፍ ጭምር ሊወሰዱ ይችላሉ።

እነዚህ መድኃኒቶች በአፍሪካና በደቡብ አሜሪካ የመስክ ጥናቶች የተሳካ ውጤት ያስገኙ ቢሆንም ለአብዛኞቹ አገሮች ትልቅ ችግር የሆነባቸው መድኃኒቱ በጣም ውድ መሆኑ ነው። የዓለም የጤና ድርጅት በ1991 እንዲህ ሲል አማሯል:- “በሽታው ያለባቸው አገሮች ሕክምናው በሚያስከትለው ከባድ ወጪ ምክንያት ከፍተኛ [የቢልሃርዚያ] መቆጣጠሪያ መርሃ ግብሮችን ማካሄድ ተስኗቸዋል፤ ብዙውን ጊዜ መድኃኒቱን ለመግዛት የሚያስፈልገው የውጭ ምንዛሪ ራሱ አብዛኞቹ የአፍሪካ የጤና ጥበቃ ሚኒስትር መሥሪያ ቤቶች ካላቸው አጠቃላይ ባጀት ይበልጣል።”

መድኃኒቶቹ ለበሽተኛው በነፃ በሚሰጡባቸው አገሮች እንኳ ብዙ ሰዎች ወደ ሕክምና ተቋማት አይሄዱም። ለምን? አንዱ ምክንያት በበሽታው ሳቢያ የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በጣም አነስተኛ በመሆኑ አንዳንዶች በሽታው ከባድ ስለማይመስላቸው ነው። ሌላው ምክንያት ደግሞ ብዙውን ጊዜ ሰዎች የበሽታውን ምልክቶች ስለማያውቋቸው ነው። በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች በሽንት ውስጥ ደም መታየቱ (የበሽታው ዋነኛ ምልክት ነው) በጣም የተለመደ ስለሆነ አንድ ሰው ወደ ጉልምስና ዕድሜ ሲደርስ የሚታይ ነገር ነው ተብሎ ይታሰባል።

ሦስተኛው እርምጃ እንቁላሎቹን ከውኃ ውስጥ ማጥፋት ነው። በየአካባቢው የሚገኙ ምንጮችንና ኩሬዎችን ከብከላ ለመከላከል መጸዳጃ ቤቶች ቢሠሩና ሁሉም ሰው በእነሱ ቢጠቀም በቢልሃርዚያ የመያዝ አደጋ ሊቀንስ ይችል ነበር።

የቧንቧ ውኃ አቅርቦት መጨመርና የመጸዳጃ ቤቶች በብዛት መሠራት በሽታው በከፍተኛ ደረጃ እንዲቀንስ እንዳደረገ ዓለም አቀፍ ጥናቶች የሚያሳዩ ቢሆንም እነዚህ ነገሮች አስተማማኝ መከላከያ አይደሉም። ከ20 ዓመታት በላይ ስለ ቢልሃርዚያ ያጠኑት ሳይንቲስት አለን ፌንዊክ “ዑደቱ እንዲቀጥል አንድ ግለሰብ በውኃ ምንጮች አጠገብ መጸዳዳቱ ብቻ ይበቃል” ብለዋል። በተጨማሪም ከተሰበሩ የፍሳሽ ማስወገጃ ቧንቧዎች የሚወጣው ሽንትና ዓይነ ምድር የውኃ ምንጮችን የሚበክልበት ሁኔታም አለ።

አራተኛው እርምጃ ደግሞ ሰዎች በጥገኛ ተውሳኩ ወደ ተበከለ ውኃ ውስጥ እንዳይገቡ መከላከል ነው። ይህም ቢሆን እንደሚታሰበው ቀላል አይደለም። በብዙ አገሮች ለመጠጥነት የሚያገለግል የውኃ ምንጭ የሆኑት ሐይቆች፣ ምንጮችና ወንዞች ለገላ መታጠቢያነት፣ ለመስኖና ለልብስ ማጠቢያነት ጭምር ያገለግላሉ። ዓሣ አጥማጆች በየቀኑ ውኃ ውስጥ ይገባሉ። በተጨማሪም በሐሩር ክልሎች ባለው ኃይለኛ ሙቀት ምክንያት ልጆች ባገኙት ውኃ ውስጥ ገብተው ከመዋኘት ወደኋላ አይሉም።

ለወደፊቱ ምን ተስፋ አለ?

በቅን ልቦና የተነሣሡ ሰዎችና ድርጅቶች ቢልሃርዚያን ለመዋጋት ተግተው በመሥራት ላይ መሆናቸውና በዚህ ረገድም አስደናቂ እድገት በመገኘት ላይ መሆኑ አይካድም። እንዲያውም ተመራማሪዎች ክትባት ለመሥራት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው።

ሆኖም በሽታውን ፈጽሞ ማስወገድ የሚቻል አይመስልም። ላ ሪቨ ደ ፕራቲሲየ በተባለው የፈረንሳይ የሕክምና መጽሔት ላይ ዶክተር ኤም ላሪቪዬር “የተሳካ ውጤት ቢገኝም . . . በሽታው ከቶ ሊጠፋ አይችልም” ብለዋል። ምንም እንኳ ግለሰቦች በሽታውን ለመከላከልና ከበሽታው ለመዳን ቢችሉም የአምላክ አዲስ ዓለም እስኪመጣ ድረስ ለቢልሃርዚያ ዓለም አቀፍ መፍትሔ አይገኝ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስ በዚያ ዓለም ውስጥ ‘ማንም ታምሜለሁ አይልም’ የሚል ተስፋ ይሰጣል።—ኢሳይያስ 33:24

[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሰዎች የተበከለ ውኃ ውስጥ በሚገቡበት ወቅት ቢልሃርዚያን በሚያመጡ ጥገኛ ተውሳኮች ሊለከፉ ይችላሉ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ