ምግብ ለሁሉ እንዲያው ሕልም ብቻ ነውን?
በኢጣሊያ የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
የተባበሩት መንግሥታት የምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) ያዘጋጀው የዓለም ምግብ ጉባኤ በ1974 “እያንዳንዱ ወንድ፣ ሴትና ሕፃን ከረሐብና ከተመጣጠነ ምግብ እጦት ነጻ የመሆን መብት አለው” የሚል መግለጫ አውጥቶ ነበር። በዚሁ ዓመት “በአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ” ረሐብን ከምድር ገጽ ለማጥፋት ጥሪ ተደርጎ ነበር።
ይሁን እንጂ ባለፈው ዓመት የዓለም አቀፍ ምግብን በተመለከተ ሮም በሚገኘው የምግብና የእርሻ ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ የተገኙት የ173 አገሮች ተወካዮች ዋነኛ ዓላማ “የተሳሳትነው ምን ላይ ነው?” ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ነበር። ይህ መግለጫ ከወጣ ከሃያ ዓመታት በላይ ያለፉ ሲሆን ምግብ ለሁሉ ማዳረስ ይቅርና ሁኔታው ከነበረበት እንዳይባባስ ማድረግ አልተቻለም።
ስለ ምግብ፣ ስለ ሥነ ሕዝብና ስለ ድህነት የሚነሱት ዋነኛ ጥያቄዎች በጣም አጣዳፊ ሆነዋል። በዚህ ስብሰባ ላይ የወጣ አንድ ሰነድ እንዳስገነዘበው ለእነዚህ ችግሮች መፍትሔ ካልተገኘ “የብዙ አገሮችና አካባቢዎች ማኅበራዊ ሕይወት ትልቅ አደጋ ላይ ሊወድቅ ምናልባትም የመላውን ዓለም ሰላም እስከማናጋት ሊደርስ ይችላል።” አንድ ታዛቢ ይበልጥ ግልጽ በመሆን “ሥልጣኔና ብሔራዊ ባሕሎች ሲወድሙ መመልከታችን የማይቀር ነው” ብለዋል።
የምግብና የእርሻ ድርጅት ዋና ዲሬክተር የሆኑት ዣክ ዲዩፍ እንደተናገሩት ከሆነ “በአሁኑ ጊዜ ከ800 ሚልዮን የሚበልጡ ሰዎች በቂ ምግብ አያገኙም። ከእነዚህ መካከል 200 ሚልዮን የሚሆኑት ሕፃናት ናቸው።” አሁን 5.8 ቢልዮን የደረሰው የዓለም ሕዝብ ብዛት በ2025 ወደ 8.3 ቢልዮን እንደሚደርስና አብዛኛው የሕዝብ ቁጥር ጭማሪ የሚኖረው በታዳጊ አገሮች እንደሚሆን ተገምቷል። ዲዩፍ እንደሚከተለው በማለት ምሬታቸውን ይገልጻሉ:- “ሊገሰስ የማይቻለውን በሕይወት የመኖርና ሰብዓዊ ክብር የማግኘት መብታቸውን የተነፈጉ ወንዶች፣ ሴቶችና ሕፃናት ቁጥር ልንቀበል ከምንችለው በላይ በጣም ከፍተኛ ነው። ረሐብተኞች በሚያሰሙት የረሐብ ጩኸት ላይ ለምነታቸውን ያጡ ማሳዎች፣ የተራቆቱ ደኖችና ዓሦቻቸው ተበዝብዘው ያለቁባቸው ባሕሮች ድምፅ አልባ ሰቆቃ ታክሏል።”
ታዲያ ምን ዓይነት መፍትሔ ታስቧል? ዲዩፍ እንደሚሉት መፍትሔው የምግብ እጥረት ያለባቸው አገሮች ራሳቸውን እንዲመግቡ የሚያስችሏቸውን ችሎታዎች፣ ኢንቨስትመንትና ቴክኖሎጂ እንዲሁም “የምግብ ዋስትና” የሚያገኙበትን “ቆራጥ እርምጃ” መውሰድ ነው።
“የምግብ ዋስትና”—የማይጨበጥ ሕልም የሆነው ለምንድን ነው?
የጉባኤው የውሳኔ ሰነድ እንደሚያመለክተው “የምግብ ዋስትና አለ ሊባል የሚችለው ሁሉም ሰው ቀልጣፋና ጤናማ ሕይወት ለመምራት የሚያስፈልገውንና አማርጦ ለመብላት የሚያስችለውን በቂ፣ ንጹሕና የተመጣጠነ ምግብ ለማግኘት የሚያስችል የምግብ አቅርቦትና ኢኮኖሚያዊ አቅም ሲኖረው ነው።”
የምግብ ዋስትና እንዴት ባሉ ምክንያቶች አደጋ ላይ ሊወድቅ እንደሚችል የዛይር ስደተኞች ችግር ጥሩ ምሳሌ ይሆናል። አንድ ሚልዮን የሚያክሉ የሩዋንዳ ስደተኞች በረሐብ ባለቁበት ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አካላት እነዚህን ረሐብተኞች ሊመግብ የሚችል በቂ የምግብ ክምችት ነበራቸው። የወጡትን የመጓጓዣና የማከፋፈያ ዝግጅቶች ሥራ ላይ ለማዋል የፖለቲካ ባለሥልጣናትን ፈቃድና የአካባቢ ሹሞችን ወይም የስደተኞች ካምፖችን በቁጥጥራቸው ሥር ያዋሉ የጦር አበጋዞችን ትብብር ማግኘት ያስፈልግ ነበር። በዛይር የታየው አደገኛ ሁኔታ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በቂ ምግብ በእጁ እያለ እንኳን ረሐብተኞችን መመገብ ምን ያህል አስቸጋሪ ሊሆንበት እንደሚችል ያሳያል። አንድ ታዛቢ እንደተናገሩት “አንድ ትንሽ ነገር ለመሥራት በጣም ብዙ ድርጅቶችንና አካላትን ማማከርና መለማመጥ ያስፈልጋል።”
አንድ የዩናይትድ ስቴትስ የእርሻ መሥሪያ ቤት ሰነድ እንዳመለከተው የምግብ ዋስትና አደጋ ላይ ሊወድቅ የሚችልባቸው ምክንያቶች በጣም በርካታ ናቸው። ከተፈጥሮ አደጋዎች በተጨማሪ፣ ጦርነት፣ የእርስ በርስ ግጭት፣ ተገቢ ያልሆኑ ብሔራዊ ፖሊሲዎች፣ ብቃት የሌለው ጥናትና ቴክኖሎጂ፣ የአፈር መሸርሸር፣ የደን መራቆት፣ ድህነት፣ የሕዝብ ቁጥር መጨመር፣ የጾታ እኩልነት አለመኖርና የጤንነት መጓደል ከእነዚህ ጥቂቶቹ ናቸው።
አንዳንድ የተገኙ ውጤቶች አሉ። ከ1970ዎቹ ዓመታት ወዲህ የምግብ ፍጆታ መጠን ጠቋሚ የሆነው አማካይ የጉልበት ሰጭ ምግቦች አቅርቦት በመልማት ላይ በሚገኙ አገሮች ለአንድ ሰው በአንድ ቀን ከ2,140 ካሎሪ ወደ 2,520 ካሎሪ ከፍ ብሏል። ይሁን እንጂ የምግብና እርሻ ድርጅት እንዳለው በ2030 የዓለም ሕዝብ ብዛት በብዙ ቢልዮን ስለሚጨምር “የምግባችንን አቅርቦት አሁን ባለበት ደረጃ ለማቆየት ብቻ እንኳን ለሁላችንም ሕልውና የግድ አስፈላጊ በሆኑት የተፈጥሮ ሀብቶቻችን ላይ ጉዳት ሳናደርስ የምርታችንን መጠን ከ75 በመቶ በላይ ማሳደግ ይኖርብናል።” ስለዚህ በረሐብ ላይ ለሚገኙ ሕዝቦች ምግብ የማቅረብ ግዴታ የሚሳካ አይመስልም።
‘የሚያስፈልገን እርምጃ መውሰድ እንጂ ተጨማሪ ስብሰባዎች ማድረግ አይደለም’
በዓለም ምግብ ጉባኤ የስብሰባ ሂደትና ጉባኤው በወሰዳቸው አቋሞች ላይ በርካታ ትችቶች ተሰንዝረዋል። አንድ የላቲን አሜሪካ ተወካይ በቂ ምግብ የማያገኙ ሕዝቦችን ቁጥር አሁን ካለበት አሐዝ በግማሽ ለመቀነስ የተሰጠውን “የተለሳለሰ” ተስፋ “አሳፋሪ” ሲሉ አውግዘውታል። አሥራ አምስት ብሔራት ጉባኤው ባጸደቃቸው ሐሳቦች ላይ የአተረጓጎም ልዩነት እንዳላቸው ተናግረዋል። ላ ረፑብሊካ የተባለው የኢጣልያ ጋዜጣ እንዳለው የተለሳለሰ ተስፋ ለመስጠትና የድርጊት መርሐ ግብር ለመንደፍ እንኳን “ለሁለት ዓመት መወዛገብና መደራደር ግድ ሆኗል። የቆየው ቁስል እንደገና እንዳያመረቅዝ . . . እያንዳንዱ ቃል፣ እያንዳንዱ ነጥብ በጥንቃቄ ሲመዘን ቆይቷል።”
የጉባኤውን የውሳኔ ሰነዶች በማዘጋጀት ሥራ የተካፈሉ በርካታ ሰዎች በተገኘው ውጤት አልተደሰቱም። አንደኛው “በመግለጫው ላይ የሠፈሩት ግሩም ሐሳቦች ሥራ ላይ የሚውሉ መሆናቸው በጣም ያጠራጥረናል” ብለዋል። ከፍተኛ ጭቅጭቅ ከተደረገባቸው ነጥቦች አንዱ የምግብ አቅርቦት ማግኘት “ዓለም አቀፍ እውቅና የተሰጠው መብት ነው” ይባል አይባል የሚለው ነበር። ምክንያቱም “መብት” ነው ከተባለ ይህንን መብት በፍርድ ቤቶች ከሶ ማስከበር ሊቻል ነው። አንድ ካናዳዊ እንደሚከተለው በማለት አስረድተዋል:- “ባለጠጎቹ አገሮች እርዳታ ለመስጠት እንገደድ ይሆናል የሚል ፍርሐት አላቸው። የመግለጫው ቃል ለዘብ እንዲል ሽንጣቸውን ገትረው የተከራከሩት በዚህ ምክንያት ነው።”
አንድ የአውሮፓ መንግሥት ሚኒስትር የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚያዘጋጃቸው ስብሰባዎች ወሬ ብቻ ሆነው በመቅረታቸው እንዲህ ብለዋል:- “በካይሮ ጉባኤ ላይ [በ1994 ስለ እድገትና ስለ ሥነ ሕዝብ የተደረገ ጉባኤ ነው] ያን የመሰለ ውሳኔ ካስተላለፍን በኋላ ከዚያ ወዲህ ባደረግናቸው ስብሰባዎች በሙሉ ወደነዚሁ ውሳኔዎች ስንመለስ ቆይተናል።” እኚሁ ሴት “በአጀንዳችን ላይ የመጀመሪያውን ቦታ ሊይዝ የሚገባው ወገኖቻችን ለሆኑት የሰው ዘሮች የሚጠቅሙ የድርጊት መርሐ ግብሮችን ሥራ ላይ ማዋል እንጂ ሌሎች ተጨማሪ ስብሰባዎች ማድረግ አይደለም” ሲሉ ሐሳብ አቅርበዋል።
በተጨማሪም ትላልቅ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ራሱ አቅም ለሌላቸው በርካታ አገሮች ትልቅ ኪሣራ እንደሆነባቸው ታዛቢዎች ይናገራሉ። አንዲት ትንሽ የአፍሪካ አገር 14 ተወካዮችና 2 ሚኒስትሮች ልካ ሁሉም በሮማ ከተማ ለሁለት ሳምንት ቆይተዋል። ኮሪየር ዴላ ሴራ የተባለው የኢጣልያ ጋዜጣ የዜጎችዋ አማካይ ዓመታዊ ገቢ በነፍስ ወከፍ ከ3,300 ዶላር የማይበልጥ የአንዲት አፍሪካዊት አገር ፕሬዚዳንት ባለቤት እጅግ ውድ የሆኑ ሱቆች በሚገኙበት የሮማ ከተማ የገበያ ማዕከል 23,000 ዶላር የፈጀ ሸመታ አካሂደዋል።
ጉባኤው ያጸደቀው የድርጊት ዕቅድ ሥራ ላይ ይውላል ብለን እንድናምን የሚያስችል ምክንያት አለ? አንድ ጋዜጠኛ እንዲህ በማለት ይመልስልናል:- “በአሁኑ ጊዜ ተስፋ የምናደርገው መንግሥታት ጉዳዩን በጥሞና ተመልክተው የጉባኤው ውሳኔዎች ሥራ ላይ እንዲውሉ የሚያስችል እርምጃ እንዲወስዱ ነው። ታዲያ በቂ እርምጃ ይወስዱ ይሆን? . . . ታሪክ በዚህ ረገድ ብሩሕ ተስፋ እንዲኖረን አያስችልም።” ይኸው ጋዜጠኛ በ1992 በሪዮ ዲ ጀኔይሮ በተደረገው ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ ከአገር ውስጥ ጠቅላላ ምርቶች 0.7 በመቶ የሚሆነውን ለእድገት እርዳታ ለማዋል ውሳኔ የተላለፈ ቢሆንም “ይህን ለማድረግ የቻሉ አገሮች በጣት የሚቆጠሩ ብቻ” መሆናቸው በእጅጉ እንደሚያሳዝን ገልጿል።
ታዲያ ድሆችን ማን ይመግብ?
የሰው ልጅ ምንም ያህል በጎ ፈቃድ ቢኖረው “የሰው መንገድ ከራሱ እንዳይደለ . . . አካሄዱንም ለማቅናት ከሚራመድ ሰው” እንዳልሆነ ታሪክ በበቂ ሁኔታ አረጋግጧል። (ኤርምያስ 10:23) ስለዚህ የሰው ልጆች በራሳቸው ጥረት ብቻ ምግብ ለሁሉ ማዳረስ የሚችሉ አይመስልም። ስግብግብነት፣ የአስተዳደር ጉድለትና ራስ ወዳድነት የሰውን ልጅ አሁን ለሚገኝበት አደገኛ ሁኔታ ዳርገውታል። የምግብና የእርሻ ድርጅት ዋና ዲሬክተር የሆኑት ዲዩፍ “የሚያስፈልገው የልብ፣ የአእምሮና የዝንባሌ ለውጥ ነው” ብለዋል።
ይህን ለውጥ ሊያስገኝ የሚችለው የአምላክ መንግሥት ብቻ ነው። እንዲያውም ይሖዋ ከበርካታ መቶ ዓመታት በፊት ስለ ሕዝቦቹ ሲናገር “ሕጌን በልቡናቸው አኖራለሁ፣ በልባቸውም እጽፈዋለሁ። እኔም አምላክ እሆናቸዋለሁ፣ እነርሱም ሕዝብ ይሆኑኛል” ብሏል።—ኤርምያስ 31:33
ይሖዋ አምላክ የሰው ልጆች የመጀመሪያ መኖሪያ ቦታ የሆነውን የአትክልት ቦታ ባዘጋጀ ጊዜ “በምድር ፊት ሁሉ ላይ ዘሩ በእርሱ ያለውን ሐመልማል ሁሉ የዛፍን ፍሬ የሚያፈራውንና ዘር ያለውንም ዛፍ ሁሉ” ምግብ እንዲሆናቸው ሰጥቶ ነበር። (ዘፍጥረት 1:29) ይህ ዝግጅት የተትረፈረፈ፣ በቀላሉ የሚገኝና አካል የሚገነባ ነበር። የሰውን ልጅ የምግብ ፍላጎቶች በሙሉ የሚያሟላ ነበር።
የአምላክ ዓላማ አልተለወጠም። (ኢሳይያስ 55:10, 11) ከረዥም ዘመናት በፊት በክርስቶስ በሚተዳደረው መንግሥት አማካኝነት ለሰው ሁሉ የሚበቃ ምግብ በማቅረብ፣ ድህነትን በማስወገድ፣ የተፈጥሮ አደጋዎችን በመቆጣጠርና ግጭቶችን በማስወገድ የሰው ልጆችን ፍላጎቶች በሙሉ እንደሚያረካ ዋስትና ሰጥቷል። (መዝሙር 46:8, 9፤ ኢሳይያስ 11:9፤ ከማርቆስ 4:37-41፤ 6:37-44 ጋር አወዳድር።) በዚያ ጊዜ ‘ምድር ፍሬዋን ትሰጣለች፣ እግዚአብሔርም ይባርከናል።’ ‘በምድር ላይ በቂ እህል ይኖራል፣ ተራራዎች በሰብል ይሸፈናሉ።’—መዝሙር 67:6፤ 72:16 የ1980 ትርጉም
[ምንጭ]
Dorothea Lange, FSA Collection, Library of Congress