ወረርሽኝ የዓለም ፍጻሜ ምልክት ነውን?
በዘመናችን ወረርሽኝ መብዛቱ የዓለም ፍጻሜ መቅረቡን ያመለክታልን? ይህን ጥያቄ ከመመለሳችን በፊት “የዓለም መጨረሻ” ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እንመልከት።
ብዙ ሰዎች የዓለም ፍጻሜ ሲባል አምላክ ምድርንም ሆነ በምድር ላይ የሚኖረውን ሕይወት በሙሉ የሚያጠፋበት ጊዜ እንደሆነ ያምናሉ። የአምላክ ቃል ግን ‘ምድርን መኖሪያ እንድትሆን እንደፈጠራት’ ይናገራል። (ኢሳይያስ 45:18) የአምላክ ዓላማ ምድር ጤነኛና ደስተኛ በሆኑ እንዲሁም ከጽድቅ ደንቦቹ ጋር ተስማምተው ለመኖር ልባዊ ፍላጎት ባላቸው ሰዎች እንድትሞላ ነው። ስለዚህ የዓለም ፍጻሜ ሲባል የምድርና የነዋሪዎችዋ ፍጻሜ ይሆናል ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ የዚህ የአሁኑ ሥርዓትና የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ አሻፈረን የሚሉ በሥርዓቱ ውስጥ የሚኖሩ ሰዎች ፍጻሜ ይሆናል ማለት ነው።
ይህንንም ሐዋርያው ጴጥሮስ “[በኖኅ ዘመን] የነበረ ዓለም በውኃ ሰጥሞ ጠፋ” ብሎ በመጻፍ አመልክቷል። በኖኅ ዘመን የነበረው ዓለም በጠፋ ጊዜ የጠፉት ክፉ ሰዎች ነበሩ። ምድርም ሆነ ጻድቁ ኖህና ቤተሰቦቹ አልጠፉም። ጴጥሮስ ቀጥሎ እንደተናገረው ወደፊትም ቢሆን አምላክ “እግዚአብሔርን የማያመልኩትን ሰዎች” ለማጥፋት እንደገና እርምጃ ይወስዳል።—2 ጴጥሮስ 3:6, 7
ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችም ይህንን አመለካከት ይደግፋሉ። ለምሳሌ ያህል ምሳሌ 2:21, 22 “ቅኖች በምድር ላይ ይቀመጣሉና፣ ፍጹማንም በእርስዋ ይኖራሉና፣ ኃጥአን ግን ከምድር ይጠፋሉ፣ ዓመፀኞችም ከእርስዋ ይነጠቃሉ” ይላል።—በተጨማሪም መዝሙር 37:9-11ን ተመልከት።
ወረርሽኝ በሽታና የዓለም ፍጻሜ
ይሁን እንጂ ይህ የሚሆነው መቼ ነው? አራት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ይህን ጥያቄ አቅርበው ነበር። “ይህ መቼ ይሆናል? የመምጣትህና የዓለም መጨረሻ ምልክቱስ ምንድር ነው?” ሲሉ ጠየቁት። ኢየሱስም “ሕዝብ በሕዝብ ላይ መንግሥትም በመንግሥት ላይ በጦርነት ይነሣል፣ በልዩ ልዩ ስፍራ ረሀብና የምድር መናወጥ ይሆናል” ሲል መለሰላቸው። (ማቴዎስ 24:3, 7 የ1980 ትርጉም) ስለዚሁ ጉዳይ በሚተርከው በሉቃስ 21:10, 11 (የ1980 ትርጉም) ላይ ደግሞ ኢየሱስ በማከል “በየቦታውም . . . በሽታ ይሆናል። የሚያስፈሩ ነገሮችና ታላላቅ ምልክቶች በሰማይ ላይ ይታያሉ” ብሏል።—በሠያፍ የጻፍነው እኛ ነን።
ኢየሱስ ወረርሽኝ በሽታ ብቻውን መጨረሻው መቅረቡን ያመለክታል እንዳላለ ልብ በል። ከዚህ ይልቅ ታላላቅ ጦርነቶችን፣ የምድር መናወጦችንና ረሀብን አብሮ ጠቅሷል። ኢየሱስ በማቴዎስ 24 እና 25፣ በማርቆስ 13 እና በሉቃስ 21 ላይ በሚገኘው ሰፋ ያለ ትንቢቱ ሌሎች በርካታ ነገሮች እንደሚከሰቱ አስቀድሞ ተናግሯል። አምላክ ክፋትን ከምድር ላይ ለማጥፋት እርምጃ ከመውሰዱ በፊት እነዚህ ነገሮች በሙሉ አንድ ላይ መፈጸም ይኖርባቸዋል። ዛሬ በዚህ ዘመን እንደምንኖር የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎች አሉ።
የሚመጣው ገነት
የወደፊቱ ጊዜ መላው የሰው ዘር በበሽታ ወይም በአምላክ እጅ ተጠራርጎ የሚጠፋበት አይሆንም። ይሖዋ አምላክ ይህችን ምድር ወደ ገነትነት እንደሚለውጥ ቃል ገብቷል። (ሉቃስ 23:43) ከሌሎች ነገሮች በተጨማሪ በአሁኑ ጊዜ የሰውን ልጅ እንደ ቅጠል በማርገፍ ላይ የሚገኙትን በሽታዎች ያስወግዳል።
የአባቱን ባሕርያት በፍጽምና ደረጃ ያንጸባረቀውን የኢየሱስ ክርስቶስን አገልግሎት ስንመረምር ይህ ተስፋ እንደሚፈጸም እርግጠኞች እንሆናለን። ኢየሱስ ከሰማያዊ አባቱ ባገኘው ሥልጣን አንካሳዎችን፣ አካለ ስንኩላንን፣ ዓይነ ስውራንን፣ ድዳዎችን ፈውሷል። (ማቴዎስ 15:30, 31) በተጨማሪም በሥጋ ደዌ የተመቱትን ፈውሷል። (ሉቃስ 17:12-14) ደም የሚፈሳትን ሴት፣ የሰለለ እጅ የነበረውን ሰው፣ እንዲሁም ሰውነቱ ውኃ የቋጠረበትን ሰው አድኗል። (ማርቆስ 3:3-5፤ 5:25-29፤ ሉቃስ 14:2-4) የሚጥል በሽታ ይዟቸው የነበሩትንና ሽባዎችን ፈውሷል። (ማቴዎስ 4:24) እንዲያውም በሦስት የተለያዩ ጊዜያት ሙታንን አስነስቷል!—ሉቃስ 7:11-15፤ 8:49-56፤ ዮሐንስ 11:38-44
እነዚህ ተአምራዊ ፈውሶች አምላክ በሚፈጥረው የወደፊት ዓለም ‘የሚኖር ታምሜአለሁ አይልም’ የሚለውን ተስፋ ተጨባጭነት ያጠናክርልናል። (ኢሳይያስ 33:24) ከዚያ በኋላ በተላላፊ በሽታ ምክንያት ጤናውን ወይም ሕይወቱን የሚያጣ ሰው አይኖርም። አፍቃሪ የሆነው ፈጣሪያችን በሽታንና ሕመምን ሙሉ በሙሉ፣ ለዘላለም ለማጥፋት ችሎታም ሆነ በጎ ፈቃድ ያለው በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች መሆን ይገባናል!—ራእይ 21:3, 4
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ በሽተኞችን ለመፈወስ የሚያስችለው ሥልጣን ከአምላክ ተቀብሏል
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ በሚመጣው ምድራዊ ገነት በሽታንና ሕመምን ጠራርጎ ያጠፋል