ጤንነትህን መጠበቅ የምትችልባቸው ስድስት መንገዶች
ናይጄርያ የሚገኘው የንቁ! መጽሔት ዘጋቢ እንዳጠናቀረው
የዓለም ጤና ድርጅት እንደሚለው በታዳጊ አገሮች ውስጥ ከሚኖሩ ሰዎች 25 በመቶ የሚያክሉት ንጹሕ ውኃ አያገኙም። ከ66 በመቶ በላይ ወይም 2.5 ቢልዮን የሚሆኑት ደግሞ የአካባቢ ንጽሕና አገልግሎት አያገኙም። በዚህ ምክንያት የሚታመሙና የሚሞቱ በርካታ ናቸው።
እንደዚህ ባለው ሁኔታ ንጽሕናን በሚገባ ጠብቆ መኖር በጣም አስቸጋሪ ነው። ቢሆንም የግል ንጽሕና አጠባበቅን የሕይወትህ ክፍል ካደረግህ ራስህን ከብዙ በሽታዎች መከላከል ትችላለህ። ወደ ሰውነት ገብተው በሽታ ከሚያስከትሉ ጀርሞች ራስህንና ቤተሰብህን ልትጠብቅ የምትችልባቸው ስድስት መንገዶች ቀጥሎ ተዘርዝረዋል።
1. ከዐይነ ምድር ጋር ማንኛውንም ንኪኪ ካደረግህ በኋላና ምግብ ከመንካትህ በፊት እጅህን በሳሙናና በውኃ ታጠብ።
በሽታን ለመከላከል ከሚያስችሉ አስፈላጊ ዘዴዎች አንዱ የቤተሰብህ አባላት በሙሉ እጃቸውን ለመታጠብ እንዲችሉ ሁልጊዜ ሳሙናና ውኃ ተዘጋጅቶ እንዲጠብቃቸው ማድረግ ነው። ሳሙናና ውኃ ወደ ምግባችን ወይም ወደ አፋችን ሊገቡ የሚችሉ ጀርሞችን ከእጃችን ላይ ያስወግዱልናል። ትናንሽ ልጆች ብዙ ጊዜ ጣቶቻቸውን ወደ አፋቸው ማድረግ ስለሚቀናቸው ቶሎ ቶሎ፣ በተለይም ምግብ ከመስጠታችን በፊት እጃቸውን እንዲታጠቡ ማድረግ አስፈላጊ ነው።
በተለይ ከተጸዳዳህ በኋላ፣ ምግብ ከመንካትህ በፊትና ሕፃን ልጅ ዐይነ ምድር ወጥቶ መቀመጫውን ካጸዳህለት በኋላ እጅህን በሳሙና መታጠብ አስፈላጊ ነው።
2. በመጸዳጃ ቤት ተጠቀም።
ጀርሞች እንዳይሠራጩ ለመከላከል በተገቢው መንገድ መጸዳዳት በጣም አስፈላጊ ነው። ብዙ በሽታዎች፣ በተለይም ተቅማጥ የሚመጣው በሰው ዐይነ ምድር ውስጥ ከሚገኙ ጀርሞች ነው። እነዚህ ጀርሞች ወደ ውኃ ወይም ወደ ምግብ፣ ወደ እጃችን ወይም ምግብ ለማዘጋጀትና ለማቅረብ ወደ ሚያገለግሉ ዕቃዎች ሊሻገሩ ይችላሉ። ከዚያ በኋላ ሰዎች ጀርሞቹን ሊውጡና ሊታመሙ ይችላሉ።
እንዲህ ያለው ሁኔታ እንዳይደርስ በመጸዳጃ ቤት ተጠቀሙ። የእንስሳት እዳሪ ከመኖሪያ ቤትና ከውኃ ምንጮች መራቅ አለበት። የሕፃናትና የትናንሽ ልጆች ዐይነ ምድር ከአዋቂዎች ዐይነ ምድር ይበልጥ አደገኛ መሆኑ ያስገርማችሁ ይሆናል። ስለዚህ ትናንሽ ልጆች እንኳን በመጸዳጃ ቤት እንዲጠቀሙ መሰልጠን አለባቸው። ልጆች ከመጸዳጃ ቤት ውጭ ዓይነ ምድር ከወጡ ወዲያውኑ ማጽዳትና ወደ መጸዳጃ ቤት መጨመር ወይም መቅበር ያስፈልጋል።
መጸዳጃ ቤቶች መከደንና በንጽሕና መያዝ ይኖርባቸዋል።
3. በንጹሕ ውኃ ተጠቀም።
ንጹሕ የቧንቧ ውኃ ያላቸው ቤተሰቦች የሌሏቸውን ያህል አይታመሙም። የቧንቧ ውኃ የሌሏቸው የውኃ ጉድጓዶቻቸውን በመክደንና የቆሸሸውን ውኃ ለመጠጥ፣ ለመታጠቢያና ዕቃ ለማጠቢያ ከሚያገለግል ውኃ በመለየት ጤንነታቸውን ሊጠብቁ ይችላሉ። በተጨማሪም እንስሳትን ከቤትና ከመጠጥ ውኃ ማራቅ አስፈላጊ ነው።
ራስህን ከበሽታ ለመጠበቅ የምትችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ ውኃ ለመቅጂያና ለማጠራቀሚያ የሚያገለግሉ ባልዲዎችን፣ ገመዶችንና ጋኖችን በተቻለ መጠን በንጽሕና መያዝ ነው። ለምሳሌ ያህል ባልዲ መሬት ላይ ከማስቀመጥ ይልቅ መስቀል የተሻለ ይሆናል።
በቤት ውስጥ ያለ የመጠጥ ውኃ ንጹሕ በሆነና በተከደነ ዕቃ ውስጥ መቀመጥ ይኖርበታል። ሲቀዳም ንጹሕ በሆነ ኩባያ ወይም ጭልፋ መሳይ ዕቃ መቀዳት አለበት። ሰዎች እጃቸውን ውኃው ውስጥ እንዲያስገቡ ወይም በቀጥታ ከዕቃው እንዲጠጡ አትፍቀድ።
4. ንጹሕ የቧንቧ ውኃ የማይገኝ ከሆነ ለመጠጥ የምትጠቀምበትን ውኃ አፍላው።
አብዛኛውን ጊዜ ንጹሕ ውኃ የሚገኘው ከቧንቧ ነው። ከሌላ ቦታ የተገኘ ውኃ ንጹሕ መስሎ ቢታይም ጀርሞች ይኖሩታል።
ውኃ ሲፈላ ጀርሞቹ ይሞታሉ። ስለዚህ ከምንጭ፣ ከወንዝ ወይም ከማጠራቀሚያ ገንዳ የተቀዳ ውኃ ከሆነ ከመጠጣትህ በፊት አፍልተህ ብታቀዘቅዘው ጥሩ ይሆናል። በተለይ ትናንሽ ልጆች ጀርሞችን የመከላከል አቅማቸው ከአዋቂዎች ያነሰ ስለሆነ ከጀርም የጸዳ የመጠጥ ውኃ ማግኘት በጣም ያስፈልጋቸዋል።
የመጠጥ ውኃ ማፍላት የማይቻል ከሆነ ብርሃን ሊያስተላልፍ በሚችል የፕላስቲክ ወይም የመስታወት ዕቃ ውስጥ ጨምረህ ክደነው። ከመጠጣትህ በፊት ዕቃውን ለሁለት ቀናት ፀሐይ አስመታው።
5. ምግብህን በንጽሕና ያዝ።
ሳይበስል የሚበላ ምግብ ሁሉ በደንብ መጽዳት አለበት። ሌሎች ምግቦች፣ በተለይ የከብትና የዶሮ ሥጋ በደንብ መቀቀል ይኖርባቸዋል።
ማንኛውንም ምግብ እንደበሰለ ወዲያው መብላት ጥሩ ነው። ወዲያው ከተበላ ለመበላሸት ጊዜ አያገኝም። የበሰለ ምግብ ከአምስት ሰዓት በላይ ማቆየት አስፈላጊ ከሆነ በትኩስነቱ ወይም በማቀዝቀዣ ውስጥ እንዲቆይ ማድረግ ያስፈልጋል። ከመብላትህ በፊት በደንብ አሙቀው።
ጥሬ ሥጋ አብዛኛውን ጊዜ ጀርሞች ስለሚኖሩት የበሰለ ምግብ እንዲነካ መፍቀድ የለብህም። ከጥሬ ሥጋ ምግብ ካዘጋጀህ በኋላ ጥሬ ሥጋው የነካቸውን ዕቃዎችና መክተፊያዎች በሙሉ በደንብ አጽዳቸው።
የምግብ ማዘጋጃ ጠረጴዛዎችና መክተፊያዎች ሁልጊዜ ንጹሕ መሆን አለባቸው። ምግብ መከደንና ዝንቦች፣ አይጦችና ሌሎች እንስሶች ሊደርሱ በማይችሉበት ቦታ መቀመጥ ይኖርበታል።
6. የቤት ውስጥ ጥራጊዎችን ቅበር ወይም አቃጥል።
ጀርሞችን የሚያስተላልፉ ዝንቦች በምግብ ነክ ቆሻሻ ውስጥ ይራባሉ። ስለዚህ የቤት ውስጥ ጥራጊዎችና ቆሻሻዎች መሬት ላይ መጣል የለባቸውም። በየቀኑ መቀበር፣ መቃጠል ወይም በአንድ ዓይነት መንገድ መወገድ ይኖርባቸዋል።
እነዚህን መመሪያዎች ሥራ ላይ ብታውል ራስህንና ቤተሰብህን ከተቅማጥ፣ ከኮሌራ፣ ከአንጀት ተስቦ፣ ከጥገኛ ትላትል፣ ከምግብ መመረዝና ከሌሎች በርካታ በሽታዎች መጠበቅ ትችላለህ።
ምንጭ:- ፋክትስ ፎር ላይፍ፣ የተባበሩት መንግሥታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት፣ የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ ሳይንስና ባሕል ድርጅትና የዓለም ጤና ድርጅት በቅንጅት ያሳተሙት።