የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 4/8 ገጽ 15-17
  • የዘር ኩራትን በተመለከተ ምን ለማለት ይቻላል?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • የዘር ኩራትን በተመለከተ ምን ለማለት ይቻላል?
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ተገቢ የሆነና ተገቢ ያልሆነ ኩራት
  • የዘር ኩራት መነሾ
  • ስለ ዘር የበላይነት የሚነገር አፈ ታሪክ
  • ሁሉም የሰው ዘሮች በሰላም አንድ ላይ የሚኖሩበት ጊዜ
    ንቁ!—1995
  • አምላክ አንድን ዘር ከሌላው አስበልጦ ይመለከታል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2011
  • ዘረኝነት
    ንቁ!—2014
  • ኩራት
    ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 4/8 ገጽ 15-17

ወጣቶች የሚጠይቋቸው ጥያቄዎች . . .

የዘር ኩራትን በተመለከተ ምን ለማለት ይቻላል?

“አብረውኝ ከሚማሩት ተማሪዎች አንዱ ስለ ሌሎች ሰዎች ዘርና ቀለም ሁልጊዜ ያወራል” ትላለች የ17 ዓመቷ ታንያ። “አብዛኛውን ጊዜ ከእነሱ ይልቅ የእሱ ዘር ምርጥ እንደሆነ ይናገራል።”

አንድ ሰው በቤተሰቡ፣ በባህሉ፣ በቋንቋው ወይም በትውልድ ቦታው መኩራቱ ያለ ነገር ነው። ፎን የተባለች አንዲት የ15 ዓመት ወጣት “እኔ ቬትናማዊት ነኝ። በባህሌም እኮራለሁ” ስትል ተናግራለች።

አብዛኛውን ጊዜ ግን በዘር መኩራትና ዘረኝነት እጅ ለእጅ ተያይዘው የሚሄዱ ነገሮች ናቸው። እንዲህ የመሰለው ኩራት በትሕትና ጭንብል ቢሸፈን እንኳ ከሌሎች ጋር ያለንን ዝምድና ሊያበላሽብን ይችላል። ኢየሱስ ክርስቶስ “በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና” ብሏል። (ማቴዎስ 12:34) ሥር የሰደደ የበላይነት ወይም የንቀት ስሜት ብዙውን ጊዜ ገንፍሎ ሊወጣና ጉዳትና ሕመም ሊያስከትል ይችላል።

አንዳንድ ጊዜ የዘር ኩራት ወደ ጠብም ሊመራ ይችላል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለተደረጉ ጦርነቶች፣ ዓመፆች እንዲሁም ደም አፋሳሽ ለሆኑ “የጎሣ ምንጠራዎች” ምክንያት ሆኗል። ይሁን እንጂ የዘር ኩራትን አስቀያሚ ገጽታ ለማወቅ በዘር ኩራት ምክንያት የተከሰተን ደም አፋሳሽ ግጭት የግድ ማየት አያስፈልግህም። ለምሳሌ ያህል በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ ወይም በጎረቤቶች ላይ የዘር ኩራት ያስከተለውን ነገር ተመልክተህ ታውቃለህ? “አዎን፣ በትክክል ተመልክቻለሁ” ስትል አንዲት መሊሳ የተባለች ወጣት ተናግራለች። “አብረውኝ ከሚማሩት ውስጥ አንዳንዶቹ የቋንቋውን ድምፀ ቅላፄ በደንብ በማይችሉ ልጆች ያሾፉባቸዋል፤ እንዲሁም ከእነሱ እንደሚሻሉ ይናገራሉ።” በተመሳሳይ ታንያ “በትምህርት ቤት ውስጥ ልጆች ‘እኔ ከአንተ እሻላለሁ’ ብለው በግልጽ ሲናገሩ ሰምቻለሁ” ብላለች። በዩናይትድ ስቴትስ በተደረገ አንድ ጥናት ላይ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ ከሰጡት ሰዎች መካከል ግማሽ የሚሆኑት ባለፈው ዓመት ውስጥ በዘራቸው ምክንያት የጥላቻ ድርጊት እንደተፈጸመባቸው ተናግረዋል። ናታሻ የተባለች ወጣት “እኔ በምማርበት ትምህርት ቤት ውስጥ ዘረኝነት ከፍተኛ ውጥረት ፈጥሯል” ስትል ተናግራለች።

የምትኖርበት አገር ወይም አካባቢ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች በመጉረፋቸው ምክንያት የትምህርት ቤትህን፣ የጎረቤቶችህን ወይም የክርስቲያን ጉባኤህን አጠቃላይ ሁኔታ ግልጽ በሆነ መንገድ ቀየረው እንበል። እንዲህ በመሆኑ ቅር ይልሃልን? እንዲህ የሚሰማህ ከሆነ ምናልባት የዘር ኩራት አንተ ከምታስበው በላይ አስተሳሰብህን ተቆጣጥሮታል ማለት ነው።

ተገቢ የሆነና ተገቢ ያልሆነ ኩራት

ታዲያ እንዲህ ሲባል የኩራት ስሜት መጥፎ ነው ማለት ነው? በደፈናው እንዲህ ለማለት አይቻልም። ተገቢ የሆነውን የኩራት ዓይነት ማሳየት ተገቢ የሚሆንበት ጊዜ እንዳለ መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ ለሚገኙ ክርስቲያኖች ሲጽፍ “በእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት ስለ እናንተ ራሳችን እንመካለን [“እንኮራለን፣” NW]” ብሏል። (2 ተሰሎንቄ 1:4) በተመሳሳይም ቢያንስ በተወሰነ መጠን ስለ ራስ ጥሩ ግምት ማሳደር ጤናማና ተቀባይነት ያለው ነው። (ሮሜ 12:3) ስለዚህ አንድ ሰው በዘሩ፣ በቤተሰቡ፣ በቋንቋው፣ በቀለሙ ወይም በትውልድ ስፍራው በተወሰነ መጠን የኩራት ስሜት ቢያድርበት ምንም ስህተት የለበትም። በእርግጥ አምላክ እንደዚህ በመሳሰሉ ነገሮች እፍረት እንዲሰማን አይፈልግም። ሐዋርያው ጳውሎስ በስህተት እንደ አንድ ግብጻዊ ወንጀለኛ ተደርጎ በተቆጠረ ጊዜ “እኔስ አይሁዳዊ በኪልቅያ ያለው የጠርሴስ ሰው ሆኜ ስመ ጥር በሆነ ከተማ የምኖር ነኝ” ብሎ ለመናገር አላመነታም።—ሥራ 21:39

ይሁን እንጂ አንድ ሰው ስለ ራሱ ከልክ በላይ ማሰብና ሌሎችን በንቀት መመልከት ሲጀምር የዘር ኩራት አስቀያሚ ገጽታ ይይዛል። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔርን መፍራት ክፋትን ይጠላል፤ ትዕቢትንና እብሪትን ክፉንም መንገድ ጠማማውንም አፍ እጠላለሁ” በማለት ይናገራል። (ምሳሌ 8:13) እንዲሁም ምሳሌ 16:18 “ትዕቢት ጥፋትን፣ ኩሩ መንፈስም ውድቀትን ይቀድማል” ይላል። ስለዚህ ከምርጥ ዘር ነው የመጣሁት ብሎ ጉራ መንዛት በአምላክ ፊት የተጠላ ነው።—ከያዕቆብ 4:16 ጋር አወዳድር።

የዘር ኩራት መነሾ

ሰዎች በዘራቸው ከልክ በላይ የሚኮሩት ለምንድን ነው? ሊዝ ፉንደርቡርግ ብላክ፣ ዋይት፣ አዘርስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ብለዋል:- “ለብዙ ሰዎች የመጀመሪያው (እንዲሁም ለረጅም ጊዜ አብሯቸው የሚቆየው) የዘር አመለካከት የሚመጣው ከወላጆችና ከቤተሰብ ነው።” የሚያሳዝነው ነገር አንዳንድ ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያስተላልፉት አመለካከት ብዙውን ጊዜ ሚዛናዊነት የጎደለው ወይም የተዛባ ነው። አንዳንድ ወጣቶች የእነሱ ዘር ሰዎች ምርጥ እንደሆኑና የሌሎች ዘር ሰዎች ግን የተለዩ ወይም ከእነሱ እንደሚያንሱ በቀጥታ ይነገራቸዋል። እንዲሁም ብዙውን ጊዜ ወጣቶች ወላጆቻቸው የተለየ ዘር ካላቸው ሰዎች ጋር ያላቸው ግንኙነት ያን ያህል መሆኑን በቀላሉ ሊመለከቱ ይችላሉ። ይህም በአስተሳሰባቸው ላይ ኃይለኛ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል። በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ልጆችና ወላጆቻቸው ልብስን ወይም ሙዚቃን በተመለከተ አንድ ዓይነት ምርጫ ላይኖራቸው ቢችልም ዘርን በተመለከተ ግን አብዛኞቹ ወጣቶች የወላጆቻቸውን አመለካከት እንደሚጋሩ ጥናቶች ያመለክታሉ።

በጭቆናና በበደል ምክንያትም ስለ ዘር ሚዛናዊነቱን ያልጠበቀ አስተሳሰብ ሊዳብር ይችላል። (መክብብ 7:7) ለምሳሌ ያህል ምሁራን አናሳ ከሚባሉ ቡድኖች የሚመጡ ልጆች ስለ ራሳቸው ጥሩ ግምት እንደሌላቸው ይናገራሉ። ይህን ለማስተካከል ሲባል አንዳንድ ምሁራን ልጆችን ስለ ዘራቸው ታሪክ ለማስተማር የሚያስችል የትምህርት መርሐ ግብር አውጥተዋል። ተቺዎች የዘር ኩራትን ማጉላት ዘረኝነትን ያስፋፋል በማለት መከራከራቸው ትኩረትን የሚስብ ነው።

ስለ ዘር ጤናማ ያልሆነ አመለካከት በማዳበር ረገድ በግል ያጋጠመ ተሞክሮም ትልቅ ሚና ይጫወታል። አንድ ሰው የተለየ ዘር ካለው ሰው ጋር ቢጋጭ የዚያ ሰው ዘር አባላት በሙሉ የሚያስጠሉ ወይም ግትሮች እንደሆኑ አድርጎ ሊደመድም ይችላል። በተመሳሳይም መገናኛ ብዙሃን የትኩረት አቅጣጫቸውን በጎሣ ግጭቶች፣ ፖሊስ በሚፈጽመው የጭካኔ ድርጊትና በተቃውሞ ሰልፎች ዙሪያ ማድረጋቸው ወይም የጎሣ ቡድኖችን አሉታዊ በሆነ መንገድ ማቅረባቸው በብዙዎች ላይ አፍራሽ ስሜቶችን ሊያሳድር ይችላል።

ስለ ዘር የበላይነት የሚነገር አፈ ታሪክ

ዘራቸው ከሌሎች እንደሚበልጥ አፋቸውን ሞልተው ስለሚናገሩ አንዳንድ ሰዎችስ ምን ለማለት ይቻላል? በመጀመሪያ ደረጃ ሰዎችን እንደየዘራቸው መፈረጅ ይቻላል የሚለው አስተሳሰብ አጠያያቂ ነው። በኒውስዊክ ላይ የወጣ አንድ ርዕስ እንዲህ ይላል:- “በዘር ላይ ጥናት ያካሄዱ ሳይንቲስቶች፣ ለዘር ትክክለኛ ማብራሪያ ለመስጠት አስቸጋሪ የሆነ የማይጨበጥ ርዕስ ሆኖባቸዋል።” “በቆዳ ቀለም፣ በፀጉር ዓይነት እንዲሁም በዓይን ወይም በአፍንጫ ቅርጽ ላይ ግልጽ ልዩነቶች” ሊኖሩ እንደሚችሉ የተረጋገጠ ነው። ይሁን እንጂ ኒውስዊክ እንዳለው “እነዚህ ልዩነቶች እንዲያው ከላይ የሚታዩ ነገሮች ናቸው። ሳይንቲስቶች የቱንም ያህል ቢጥሩ አንድን ዘር ከሌላው ለመለየት የሚያስችል ይህ ነው የሚባል የጎላ ልዩነት ሊያገኙ አልቻሉም። . . . በዚህ መስክ የተሠማሩ ሳይንቲስቶች የደረሱበት መደምደሚያ ቢኖር ዘር [ብልሹ] የወገናዊነት ጥላቻ የተቀላቀለበት፣ አጉል እምነትና አፈ ታሪክ የሆነ ‘ማኅበራዊ ሐሳብ’ መሆኑን ነው።”

ሌላው ቀርቶ በዘሮች መካከል ሳይንሳዊ መለያዎች ማድረግ ቢቻል እንኳ “ምርጥ” ዘር የሚባለው ሐሳብ ልብ ወለድ ነው። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ “ምርጥ የሚባሉ ዘሮች የሉም፤ በአሁኑ ጊዜ ያሉት ሁሉም የዘር ቡድኖች እርስ በርሳቸው ተቀላቅለዋል” ብሏል። ጉዳዩ ምንም ይሁን ምን አምላክ “የሰውን ወገኖች ሁሉ ከአንድ ፈጠረ” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምራል። (ሥራ 17:26) ምንም እንኳ የቆዳ ቀለም፣ የፀጉር ዓይነት ወይም የፊት ገጽታ ቢለያይም በምድር ላይ ያለው ዘር አንድ ነው፤ እሱም የሰው ዘር ነው። በቀድሞ አባታችን በአዳም አማካኝነት ሁሉም ሰው ተዛምዷል።

የጥንቶቹ አይሁዶች የሁሉም ዘሮች መገኛ ማን መሆኑን በደንብ ያውቁ ነበረ። ቢሆንም አንዳንዶች ክርስቲያኖች ከሆኑ በኋላ አይሁዳውያን ያልሆኑትን የእምነት አጋሮቻቸውን ጨምሮ አይሁድ ካልሆኑ ሰዎች እንበልጣለን የሚል እምነት ተጠናውቷቸው ነበር! ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ 3:9 ላይ እንደተመዘገበው የዘር የበላይነት የሚለውን ሐሳብ ውድቅ አድርጓል:- “አይሁድም የግሪክ ሰዎችም ሁሉ ከኃጢአት በታች [ናቸው]።” ስለዚህ የትኛውም የዘር ቡድን ከአምላክ ጋር የተለየ ዝምድና አለኝ ብሎ በጉራ ሊናገር አይችልም። እንደ እውነቱ ከሆነ ግለሰቦች ከአምላክ ጋር ዝምድና ሊኖራቸው የሚችለው በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ባላቸው እምነት ብቻ ነው። (ዮሐንስ 17:3) እንዲሁም አምላክ ‘ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ እንዲደርሱ’ ፈቃዱ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 2:4 NW

ሁሉም ዘሮች በአምላክ ፊት እኩል መሆናቸውን መገንዘብህ ለራስህና ለሌሎች ያለህን አመለካከት በሚያስደንቅ መንገድ ሊለውጠው ይችላል። የሌሎችን ክብርና ቦታ እንድትጠብቅ፣ ልዩነቶቻቸውን እንድትገነዘብና እንድታደንቅ ሊገፋፋህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል ቀደም ሲል የተጠቀሰችው መሊሳ አብረዋት ከሚማሩ ጋር በመሆን የቋንቋውን ድምፀ ቅላፄ በደንብ በማይችሉት ልጆች ላይ አልሳቀችም። “እነዚያ ሁለት ቋንቋ መናገር የሚችሉ ልጆች ጎበዞች ናቸው። ሌላ ቋንቋ የመናገር ፍላጎቱ ቢኖረኝም መናገር የምችለው ቋንቋ ግን አንድ ብቻ ነው” ስትል ተናግራለች።

በዘርህና በባህልህ ውስጥ የሚገኙ ሰዎች ብዙ የሚኮሩበት ነገር እንዳለ ሁሉ የሌላ ዘር ሰዎችም እንዲሁ የሚኮሩበት ብዙ ነገር እንዳላቸው አስታውስ። በባህላችሁና የቀድሞ አባቶቻችሁ ባከናወኑት የሥራ ውጤት በተወሰነ ደረጃ መኩራታችሁ ምክንያታዊ ቢሆንም በግላችሁ ጥራችሁና ግራችሁ ባገኛችሁት የሥራ ውጤት መኩራት የበለጠ የሚያረካ ነው! (መክብብ 2:24) እርግጥ ነው መጽሐፍ ቅዱስ ልትኮሩበት የሚገባ አንድ ነገር እንዳለ ይናገራል። በኤርምያስ 9:24 ላይ አምላክ ራሱ እንዲህ ብሏል:- “ነገር ግን የሚመካው:- ምሕረትንና ፍርድን ጽድቅንም በምድር ላይ የማደርግ እኔ እግዚአብሔር መሆኔን በማወቁና በማስተዋሉ በዚህ ይመካ።” እንዲህ ብለህ በኩራት ለመናገር ትችላለህን?

[በገጽ 1 ላይ የሚገኝ ሥዕል16]

አምላክ ስለ ዘር ያለውን አመለካከት ማወቃችን ከሌላ ዘር ሰዎች ጋር ባለን ግንኙነት ደስተኞች እንድንሆን ይረዳናል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ