ጥርስህን የማፋጨት ልማድ አለህን?
ከጥንት ዘመን ጀምሮ ሰዎች ውጥረት ሲሰማቸው ጥርሳቸውን የማፋጨት ልማድ አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ንዴትን ወይም ከባድ ስቃይን ለማመልከት ጥርስ ማፋጨት የሚለውን አገላለጽ ደጋግሞ ይጠቀማል። (ኢዮብ 16:9፤ ማቴዎስ 13:42, 50) በብስጭትና በውጥረት በተሞላው በዛሬው ዓለም ውስጥ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ቃል በቃል ጥርሳቸውን ያፋጫሉ። አብዛኞቹ ደግሞ እንዲህ ማድረጋቸውን እንኳ አያውቁትም። ምናልባትም ቀስ በቀስ ጥርሳቸውን እየጨረሱት ሊሆን ይችላል።
አንዳንድ ሰዎች ጥርሳቸውን የሚያፋጩት ለምንድን ነው? መንስኤዎቹ የተወሳሰቡ ከመሆናቸውም በላይ እስካሁን ድረስ ሙሉ በሙሉ ለመረዳት አልተቻለም። ይሁን እንጂ በአንዳንድ ሁኔታዎች የስሜት ውጥረት ዋነኛው መንስኤ ሆኖ ይገኛል። የዩሲ በርክሌይ ዌልነስ ሌተር እንዲህ በማለት ይጠቁማል:- “ጥርሳቸውን የማፋጨት ልማድ ያለባቸው ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ከትዳር ጋር የተያያዘ ወይም ገንዘብ ነክ ችግር እንዳለባቸው፣ የመጨረሻውን ወሳኝ ፈተና እየወሰዱ እንደሆነ፣ ከሥራ የመባረር ስጋት እንዳለባቸው ወይም በሌላ ምክንያት ጭንቀት እንደሚሰማቸው ይገልጻሉ።” መንስኤ ሊሆኑና አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ ከሚባሉት ሌሎች ምክንያቶች መካከል የላይኛውና የታችኛው ጥርስ በትክክል አለመግጠም፣ የእንቅልፍ መረበሽ ወይም የአልኮል መጠጥ መውሰድ ይገኙበታል። ይህም በመሆኑ ዌልነስ ሌተር ይህ ችግር ያለባቸው ሰዎች የሚወስዱትን የአልኮል መጠን እንዲቀንሱ፣ ከመተኛታቸው በፊት በሙቅ ውኃ ገላን እንደመታጠብ የመሳሰሉ ዘና የሚያደርጉ ቀላል ነገሮች እንዲያደርጉ ወይም የሚያስጨንቋቸውን ችግሮች ለጓደኛቸው አሊያም እምነት ለሚጣልበት አማካሪ እንዲነግሩ ሐሳብ ያቀርባል።
ቀን ላይ ጥርሶችህን ስታፋጭ ወይም እርስ በርስ ስታፋትጋቸው አንተው ራስህ ታስተውል ይሆናል። ሆኖም ተኝተህ ሳለ እንደዚያ ማድረግህን እንዴት ማወቅ ትችላለህ? በእንግሊዝኛ ብሩክሲዝም የሚባለው ሥር የሰደደ ጥርስ የማፋጨት ልማድ አንዳንድ ጊዜ እዚያው ክፍል ውስጥ የተኛን ሰው እስከመቀስቀስ የሚያደርስ ከፍተኛ ድምፅ ይፈጥራል። ከእንቅልፍህ በምትነቃበት ጊዜ ራስህን ያምህ ወይም አገጭህ ሲነቃነቅ ድምፅ ያሰማ ይሆናል።a እንዲያውም የጥርስ ሐኪምህ ጥርሶችህ በጣም መበላታቸውን ሊገነዘብ ይችል ይሆናል። ችግሩን በተወሰነ ደረጃ ለማስወገድ ማድረግ ያለብህን ነገር ሊነግርህ ይችላል። ለምሳሌ ያህል ስትተኛ ጥርስ ላይ የሚደረግ ነገር ሊያዝልህ ይችላል። ምንም እንኳ ይህ ዓይነቱ መከላከያ ጥርስ የማፋጨት ልማድህን እንድትተው የሚያስችልህ ባይሆንም ጥርሶችህ የባሰ ጉዳት እንዳይደርስባቸው ሊከላከል ይችላል። ያም ሆነ ይህ ዘና ለማለት ሞክር! ጭንቀትህ በቀነሰ መጠን ጥርሶችህን የማፋጨት ልማድህ ሊቀንስ ይችላል።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት እባክህ የሰኔ 22, 1991 ንቁ! (የእንግሊዝኛ) ከገጽ 20–2 ተመልከት።