የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • g98 10/8 ገጽ 11-13
  • ጥፍሮችህን ትንከባከባቸዋለህን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጥፍሮችህን ትንከባከባቸዋለህን?
  • ንቁ!—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ውስብስብ መዋቅር
  • ጠቀሜታቸው
  • ተገቢውን እንክብካቤ ካገኙ ጠንካራ ይሆናሉ
  • ዕድገቱንና ውበቱን መጠበቅ
  • ከዓለም አካባቢ
    ንቁ!—2001
  • በሳምንቱ መካከል በምናደርገው ስብሰባ ላይ የሚካተት አዲስ ገጽታ
    ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን​—የስብሰባው አስተዋጽኦ—2017
  • ይህን ያውቁ ኖሯል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2014
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2004
ለተጨማሪ መረጃ
ንቁ!—1998
g98 10/8 ገጽ 11-13

ጥፍሮችህን ትንከባከባቸዋለህን?

በስዊድን የሚገኘው የንቁ! ዘጋቢ እንዳጠናቀረው

አንድ ሰው “እስቲ ጥፍሮችህን አሳየኝ?” ብሎ ቢጠይቅህ ምን ምላሽ ትሰጣለህ? በደንብ የተያዙ ጥፍሮችህን በደስታ ታሳየዋለህ ወይስ ወዲያውኑ እጆችህን ትደብቃለህ? ጥፍሮችህን የምትደብቅበት በቂ ምክንያት ይኖርህ ይሆናል። ጥፍሮችህ አያምሩ ይሆናል ወይም ደግሞ ጥፍርህን ትበላ ይሆናል። ስለ ጥፍሮቻችን አስደናቂ አሠራር ይበልጥ ማወቃችን የተሻለ ግንዛቤ እንድናገኝ ሊረዳንና በሚገባ እንድንንከባከባቸው ሊያነሳሳን ይችላል።

ጥፍሮችህ በአብዛኛው የተሠሩት እንደ ቃጫ ያለ ነገር ያለውን ጸጉረ ፕሮቲን (keratin) በያዙ ጠጣር የሆኑ በድን ሕዋሳት ነው። ጥፍሮች የሚያድጉበት ፍጥነት ከጣት ወደ ጣት እንዲሁም ከሰው ወደ ሰው ይለያያል። ጥፍሮች በወር ውስጥ በአማካይ 3 ሚሊ ሜትር ያህል ያድጋሉ። ሳይቆረጡ እንዲሁ የተተዉ ጥፍሮች በጣም ሊረዝሙ ይችላሉ። ዘ ጊነስ ቡክ ኦቭ ወርልድ ሪከርድስ 1998 ባወጣው ዘገባ መሠረት አንድ ሕንዳዊ ሰው የግራ እጁን አምስት ጥፍሮች በድምሩ 5 ሜትር ከ74 ሴንቲ ሜትር ያህል አሳድጓቸዋል። የአውራ ጣቱ ጥፍር ብቻ 1 ሜትር ከ32 ሴንቲ ሜትር ርዝማኔ አለው።

ውስብስብ መዋቅር

በመጀመሪያ ከላይ የሚታየውን ጠፍጣፋ ነገር በመመልከት ጥፍር አንድ ክፍል ብቻ ያለው ነገር እንደሆነ አድርገህ ታስብ ይሆናል። ስለዚህ ጥፍር የሚታዩም ሆኑ የማይታዩ የተለያዩ ዋና ዋና ክፍሎች እንዳሉት ስታውቅ ትገረም ይሆናል። እስቲ የጥፍርን መዋቅር ይበልጥ ጠለቅ ብለን እንመልከት።

1. ኔል ፕሌት። ይህ ክፍል በተለምዶ ጥፍር እያልን የምንጠራው ጠጣር አካል ነው። ኔል ፕሌቱ ከላይና ከታች ሁለት ንብብር አለው። በእነዚህ ሁለት ክፍሎች ላይ ያሉት ሕዋሳት በተለያየ መንገድ የተደራጁና በተለያየ ፍጥነት የሚያድጉ ናቸው። የላይኛው ክፍል ልሙጥ ሲሆን የታችኛው ግን ጥፍሩ በሚያርፍበት የጣታችን ክፍል ላይ ካሉት መስመሮች ጋር የሚገናኙ ትይዩ መስመሮች አሉት። እነዚህ መስመሮች ከሰው ወደ ሰው የሚለያዩ በመሆናቸው እንደ መለያ ሆነው ሊያገለግሉ ይችላሉ።

2. ሉንዩል። ይህ ከኔል ፕሌቱ በታች በኩል የሚገኝ የግማሽ ጨረቃ ቅርጽ ያለው ነጭ የሆነ ክፍል ነው። የአንዳንዶቹ ጣቶች ሉንዩል አይታይም። ጥፍር የሚያድገው ሜትሪክስ ተብሎ የሚጠራው ከኔል ፕሌቱ በታች የሚገኘው ሕያው ኅብረሕዋስ ካለበት አነስተኛ ቦታ ነው። ይህ እጅግ አስፈላጊ የሆነ የጥፍር አካል ነው። ሉንዩል የሜትሪክሱ የላይኛ ጫፍ በመሆኑ ሕያው የሆነው ጥፍር የሚታይ ክፍል ነው ለማለት ይቻላል። የተቀረው የኔል ፕሌት ክፍል በድን በሆኑ ሕዋሳት የተዋቀረ ነው።

3. ኔል ፎልድስ፣ ፕሮክሲማል እና ላተረል። እነዚህ በኔል ፕሌቱ ዙሪያ ያሉት ቆዳዎች ናቸው። ይህ ቆዳ ጠርዙ በኔል ፕሌቱ ላይ የሚቀር ሳይሆን ወደ ሥር ታጥፎ ከሥር እየወጣ ያለውን ኔል ፕሌት የሚሸፍን በመሆኑ ኔል ፎልድ በመባል ይታወቃል። ይህ የቆዳ ዕጥፋት በጥፍሩ ዙርያ ያለውን ቦታ ከጉዳት የሚጠብቅና ደግፎ የሚይዝ ነው።

4. ኤፐኒኪየም። ይህ ክፍል በኔል ፕሌቱ መነሻ ላይ የሚያበቃ መስሎ የሚታይ የቆዳ ዕጥፋቱ አነስተኛ አካል ነው። አንዳንድ ጊዜ ይህ ክፍል ኪውቲክል እየተባለ ይጠራል።

5. ኪዩቲክል። እውነተኛው ኪዩቲክል ከኤፐኒኪየም ሥር የሚገኝ አነስተኛ ቅጥያ ነው። ወደ ውጪ ወጣ ያለው ቆዳ ደርብ ሲሆን ከኔል ፕሌቱ የታችኛው ክፍል ጋር የተጣበቀ ምንም ቀለም የሌለው ቆዳ ነው።

6. ፍሪ ኤጅ። ከጣታችን በላይ የሚያድገው የኔል ፕሌት ክፍል።

7. ሃይፖኒኪየም። ወደ ላይ ከሚያድገው ጥፍራችን ሥር የሚገኝ ኅብረሕዋስ ሲሆን ጥፍራችን የሚያርፍበትን የጣታችን ክፍል ከኢንፌክሽን የሚከላከል ውኃ የማይዘልቀው ማሸጊያ ይሠራል።

ጠቀሜታቸው

ጥፍሮቻችን በብዙ መንገዶች ይጠቅሙናል፤ ለምሳሌ ያህል ለመቧጠጥ ወይም ለማከክ ያገለግሉናል። ብርቱካን ለመላጥ፣ ቋጠሮ ለመፍታት ወይም ደግሞ ጥቃቅን ነገሮችን እንደፈለግነው ለማድረግ ያገለግሉናል። በተጨማሪም ጥፍር በቀላሉ ሊጎዱ የሚችሉትንና ስስ የሆኑትን የጣቶቻችን ጫፎች ለመደገፍና ከአደጋ ለመጠበቅ ይረዳል።

ጥፍር በውበት በኩል የሚያበረክተው ድርሻም በቀላሉ የሚታይ አይደለም። ጥፍሮቻችን ጥሩ የንጽሕና አጠባበቅ ልማድ እንዳለንና እንደሌለን ሊጠቁሙ ይችላሉ። በየዕለቱ በምናደርጋቸው አካላዊ መግለጫዎች ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወቱ ከመሆናቸውም በላይ በደንብ ከተያዙ ለእጆቻችን ውበት ሊጨምሩለት ይችላሉ። ጥፍሮቻችን ባይኖሩ ኖሮ የዕለት ተዕለት ሕይወታችን ሳንካ ይገጥመው ነበር፤ በተጨማሪም እጃችን የጎደለው ነገር እንዳለ ሆኖ ይሰማን ነበር።

ተገቢውን እንክብካቤ ካገኙ ጠንካራ ይሆናሉ

ጥፍሮቻችን ግሩምና ድንቅ የሆነው አካላችን ክፍል እንደ መሆናቸው መጠን ተገቢውን እንክብካቤ ማግኘት አለባቸው። ከባድ የሆነ የጥፍር ችግር ካለብህ ሐኪም ቤት መሄድ ይኖርብሃል። እንዲያውም አንዳንድ አካላዊ ችግሮችን የሚጠቁሙ ምልክቶች በጣቶችህ ጫፍ ላይ ሊታዩ ይችላሉ። አዎን፣ ጥፍሮችህን በመመልከት አንዳንድ አካላዊ ሕመሞችን ለይቶ ማወቅ እንደሚቻል ይነገራል።

ተጨማሪ ካልሲየም ወይም ቫይታሚኖች መውሰድ ጥፍሮችን ሊያጠነክር ይችላልን? በስዊድን ስቶክሆልም ውስጥ በሚገኘው በካሮሊንስክ ኢንስቲትዩት የጥፍር ጥናት ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ቦው ፎርስሊንድ ይህን ጥያቄ በሚመለከት ለንቁ! መጽሔት የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥተዋል:- “ይህን አመለካከት የሚደግፍ ምንም ማስረጃ የለም። በተደረገው ምርመራ እንደታየው በጤናማ ጥፍሮች ውስጥ ያለው የካልስየም መጠን በጣም አነስተኛ ነው።”

ይሁንና ውኃ ጥፍሮችህ ጠንካራና በቀላሉ የሚታጠፉ እንዲሆኑ ሊያደርጋቸው ይችላል። ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ጥፍሮች ፀጉረ ፕሮቲን አላቸው። እነዚህ ፀጉረ ፕሮቲኖች በቀላሉ የሚታጠፉ ዓይነት እንዲሆኑ ውኃ ያስፈልጋቸዋል። ፕሮፌሰር ፎርስሊንድ አንድ ምሳሌ ሰጥተዋል:- “ጥፍርህ መጀመሪያ ላይ ስትቆርጠው በቀላሉ የሚታጠፍ ዓይነት የነበረ ቢሆን እንኳ ያው የተቆረጠው ጥፍር በአንድ ሌሊት ደርቆ በቀላሉ የሚሰበር ሊሆን ይችላል።” ርጥበት ጥፍሮችህ በቀላሉ የሚታጠፉና ጠንካራ እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል። ይሁን እንጂ ይህ ርጥበት የሚመጣው ከየት ነው? ኔል ፕሌቱ ጠጣር ቢመስልም እንኳ ፈሳሽ የሚመጥ ነው። ጥፍሩ ከሚያርፍበት የጣታችን ክፍል ላይ የሚወጣው ርጥበት ወደ ኔል ፕሌቱ የላይኛው ገጽ በመውጣት ይተናል። ጥፍሮች እንዳይደርቁ ለመከላከልና ጠንካራ እንዲሆኑ ምን ማድረግ ይቻላል? ፕሮፌሰር ፎርስሊንድ “በየዕለቱ ቅባት መቀባት ጠቃሚ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

ዕድገቱንና ውበቱን መጠበቅ

ጥፍር የሚያድገው ከሜትሪክስ በመሆኑ ይህን የጥፍር ክፍል በደንብ መንከባከብ በጣም አስፈላጊ ነው። ሜትሪክሱን ዘወትር በክሬም ወይም በቅባት በማሸት ማነቃቃት ኔል ፕሌቱን ሊጠቅመው ይችላል። በተጨማሪም ከጣታችን በላይ ከሚያድገው ጥፍር ሥር ቅባት ጠብ ማድረግ ጥፍሩ እንዳይደርቅ ስለሚረዳ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል።

ጥፍሮችህን የምትሞርድበት ወይም የምትቆርጥበት መንገድ ጥፍሮችህን ጠንካራ አለዚያም ደካማ ሊያደርጋቸው ይችላል። ጥፍሮችህን ከጎን ወደ መሃል ብትሞርድ የተሻለ ይሆናል። ጥፍርህን ከዳርና ከዳር በጣም የምትሞርደው ከሆነ ጥንካሬው ይዳከማል። ጥፍርህ ሹል ይሆንና ከጎንና ከጎን ምንም ዓይነት ድጋፍ ስለማይኖረው በቀላሉ የሚሰበር ይሆናል። ጥፍሮችህ አጠር ያሉ ሆነው ጠንካራ እንዲሆኑ ከፈለግህ ከጎንና ከጎን እስከ 1.5 ሚሊ ሜትር ድረስ እንዲያድጉ በማድረግ የጣትህን ጫፍ ቅርጽ በተከተለ መንገድ ሞለል ያለ ቅርጽ እንዲይዙ ብታደርግ የተሻለ ይሆናል።

አንዳንድ ሴቶች ጥፍሮቻቸው ትንሽ ረዘም እንዲሉ ይፈልጉ ይሆናል። ሆኖም እዚህ ላይ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ረጅም የሆኑ ጥፍሮች አላስፈላጊ የሆነ ትኩረት የሚስቡ ከመሆናቸውም በላይ በየዕለቱ በምናከናውናቸው ነገሮች ላይ እንቅፋት ሊፈጥሩ ይችላሉ። ስለዚህ የጥፍሮችህን ርዝማኔ በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት ይኑርህ። እንዲህ የምታደርግ ከሆነ ጥፍሮችህ ጠቃሚና ውበት ያላቸው ይሆናሉ።

ጥፍሮቻችሁን ሹል በሆኑ ነገሮች አትጎርጉሩ ሲሉ ጠበብት ይመክራሉ። እንዲህ ማድረጉ ሃይፖኒኪየም ተብሎ የሚጠራውን ከጣታችን በላይ ከሚያድገው ጥፍር ሥር ያለውን ኅብረሕዋስ ሊጎዳው ይችላል። ይህ ኅብረሕዋስ የጥፍሩን የሥረኛ ክፍል የሚጠብቅ ጥብቅ የሆነ ማሸጊያ ይሠራል። ይህ ክፍል ከተጎዳ ጥፍሩ ከጣታችን ሥጋ ሊለያይና በበሽታ ሊለከፍ ይችላል። ጥፍርህን ከሥር ለማጽዳት በጣም ለስላሳ የሆነ ብሩሽ ተጠቀም።

በዘር የሚወረሱ ነገሮችም በጥፍሮች ጥንካሬና ጤንነት ላይ በተወሰነ ደረጃ ተጽዕኖ ያደርጋሉ። አንዳንድ ሰዎች ጠንካራና በቀላሉ የሚታጠፍ ኔል ፕሌት ሲኖራቸው የሌሎቹ ጥፍር ደግሞ ደረቅ ወይም በቀላሉ የሚሰበር የሚሆነው በዚህ ምክንያት ነው። የጥፍሮችህ ሁኔታ ምንም ይሁን ምን ዘወትር ልከኛ በሆነ መንገድ ጥሩ እንክብካቤ የምታደርግላቸው ከሆነ ሁኔታቸው ሊሻሻል ይችላል። በእርግጥም የጥፍሮችን መዋቅር፣ ተግባርና ትክክለኛ አያያዝ መገንዘብህ መሠረታዊ የሆነ እውቀት እንዲኖርህ ይረዳሃል። ይህን መረጃ በጥበብ በመጠቀም ጥሩ ውጤት ታገኛለህ።

በእርግጥም ጥፍር ዕጹብ ድንቅ የሆነ የሰው አካል ክፍል ነው። መዋቅሩና ተግባሩ ከበስተጀርባ ስላለው ጠቢብ አእምሮ ጥሩ ምሥክርነት ይሰጣል። በመዝሙር 139:14 ላይ ተመዝግቦ እንደሚገኘው በጥንት ዘመን ይኖር የነበረው ንጉሥ ዳዊት ለፈጣሪው ያለውን አድናቆት እንዲህ ሲል በትሕትና ገልጿል:- “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ፤ ሥራህ ድንቅ ነው፣ ነፍሴም እጅግ ታውቀዋለች።”

[በገጽ 13 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

1. ኔል ፕሌት፤

2. ሉንየል፤

3. ኔል ፎልድስ፣ ፕሮክሰማል እና ላተረል፤

4. ኤፐኒኪየም፤

5. ኪውቲክል፤

6. ፍሪ ኤጅ፤

7. ሃይፖኒኪየም፤

8. ሜትሪክስ፤

9. ኔል ቤድ

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ