የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት
ብሕትውና ከክርስቲያን አገልጋዮች የሚፈለግ ብቃት ነውን?
በአጭር አነጋገር ብሕትውና ሳያገቡ መኖር ማለት ነው። ይሁን እንጂ ዘ ኒው ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ እንደሚለው ቃሉ “አብዛኛውን ጊዜ የሚሠራበት ባሕታዊ የሆነው ሰው የሃይማኖት ባለሥልጣን፣ ሊቅ ወይም አጥባቂ አማኝ በመሆን ከሚጫወተው ሚና ጋር በተያያዘ ነው።” “ባሕታዊ” የሚለው ቃል የሚያመለክተው “ቅዱስ ቃል ኪዳን በመግባታቸው ወይም ራሳቸውን በመካዳቸው ምክንያት ወይም አንድ ሰው በሃይማኖቱ ውስጥ ካለው ኃላፊነት አሊያም ለሃይማኖቱ ካለው ቅንዓት አኳያ ሳያገባ መኖሩ ይመረጣል በሚል እምነት ሳያገቡ የሚኖሩ ሰዎችን ነው።”
አንዳንድ ታላላቅ ሃይማኖቶች ባለፉት ጊዜያት በሆነ ወቅት ላይ ባወጡት ድንጋጌ መሠረት አገልጋዮቻቸው የግድ ባሕታዊ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ይሁን እንጂ ብሕትውና ከየትኛውም የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖት ይበልጥ የካቶሊክ እምነት መለያ ሆኗል። በዛሬው ጊዜ የካቶሊክ እምነት የምትከተለውን ብሕትውና በተመለከተ ከፍተኛ ውዝግብ አለ። ዘ ዊልሰን ኳርተርሊ የተባለው መጽሔት “በቅርብ አሥርተ ዓመታት ውስጥ የተካሄዱ በርካታ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከ12ኛው መቶ ዘመን ጀምሮ የካቶሊክ ቄሶች እንዲያሟሉ የሚጠበቅባቸው የግዴታ ብሕትውና ቤተ ክርስቲያኗ አዳዲስ ቄሶች በማሰልጠንም ሆነ ያሉትን በቅስና እንዲቀጥሉ በማድረግ ረገድ ለገጠማት ችግር ዋነኛ መንስኤ ነው” ሲል ዘግቧል። የማኅበራዊ ኑሮ ጉዳይ ተመራማሪ የሆኑት ሪቻርድ ኤ ሾንኸር እንዳሉት “ተጨባጩ የታሪክ ሐቅም ሆነ ማኅበራዊ ለውጦች የካቶሊክ ቅስናን የሚያገኘው ባሕታዊ የሆነ ወንድ ብቻ መሆኑን ይጻረራሉ።” መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ብሕትውና ያለው አመለካከት ምንድን ነው?
ጋብቻ ወይስ ነጠላነት?
በታሪክ ዘመናት በሙሉ የተለያየ ሃይማኖት ተከታዮች የሆኑ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ለእምነታቸው ያደሩ ወንዶችና ሴቶች ባሕታዊ ለመሆን መርጠዋል። ለምን? በአብዛኛዎቹ ሁኔታዎች ሥጋዊና ቁሳዊ ነገሮች “የክፋት ምንጭ” ናቸው ብለው ያምኑ ስለነበር ነው። ይህ እምነት መንፈሳዊ ንጽሕና ሊገኝ የሚችለው ከጾታ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ በመራቅ ብቻ ነው የሚለውን ፍልስፍና አስገኝቷል። ይሁን እንጂ ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ጋብቻ ከአምላክ የተገኘ ንጹሕና ቅዱስ ስጦታ እንደሆነ ይገልጻል። የዘፍጥረት መጽሐፍ የፍጥረት ታሪክ ጋብቻ በአምላክ ዓይን “መልካም” እንደሆነ በግልጽ ይናገራል እንጂ ከአምላክ ጋር ንጹሕ የሆነ መንፈሳዊ ዝምድና ለመመሥረት እንቅፋት እንደሆነ በፍጹም አይገልጽም።—ዘፍጥረት 1:26–28, 31፤ 2:18, 22–24፤ በተጨማሪም ምሳሌ 5:15–19ን ተመልከት።
በጥንቱ የክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የኃላፊነት ቦታ የነበራቸው ሐዋርያው ጴጥሮስና ሌሎች በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ አገልጋዮች ያገቡ ወንዶች ነበሩ። (ማቴዎስ 8:14፤ ሥራ 18:2፤ 21:8, 9፤ 1 ቆሮንቶስ 9:5) ሐዋርያው ጳውሎስ የጉባኤ የበላይ ተመልካቾችን ወይም ‘የኤጲስ ቆጶሳትን’ ሹመት በተመለከተ ለጢሞቴዎስ የሰጠው መመሪያ ይህን ጉዳይ ግልጽ ያደርገዋል። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ የማይነቀፍ፣ የአንዲት ሚስት ባል።” (1 ጢሞቴዎስ 3:2፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።) በማንኛውም ሁኔታ ቢሆን “ኤጲስ ቆጶስ” ማግባቱ ተገቢ አይደለም የሚል ሐሳብ በጭራሽ አለመኖሩን ልብ በል። ጳውሎስ በአጭሩ የገለጸው “ኤጲስ ቆጶስ” ከአንድ በላይ ሚስት ማግባት እንደሌለበት ነው። ያገባ ከሆነ አንዲት ሚስት ብቻ ልትኖረው ይገባል። እንዲያውም በማክ ክሊንቶክና ስትሮንግ የተዘጋጀው ሳይክሎፒዲያ ኦቭ ቢብሊካል፣ ቲኦሎጂካል ኤንድ ኤክለስያስቲካል ሊትሬቸር እንዲህ የሚል ድምዳሜ ሰጥቷል:- “ወንጌሉ በያዘው መመሪያ ላይ ቄሶች እንዳያገቡ ይከለክላል ተብሎ ሊተረጎም የሚችል አንድም ምንባብ አዲስ ኪዳን ውስጥ የለም።”
መጽሐፍ ቅዱስ ጋብቻን ከፍ አድርጎ ቢመለከትም በውዴታ እስከተደረገ ድረስ ነጠላነትን በፍጹም አያወግዝም። መጽሐፍ ቅዱስ ነጠላነት ለአንዳንዶች ተስማሚ የሕይወት ጎዳና መሆኑን ይገልጻል። (1 ቆሮንቶስ 7:7, 8) ኢየሱስ ክርስቶስ አንዳንድ ወንዶችና ሴቶች የነጠላነትን ሕይወት በፍላጎታቸው እንደሚመርጡ ተናግሯል። (ማቴዎስ 19:12) ለምን? ጋብቻ በራሱ መንፈሳዊ እድገታቸውን የሚያስተጓጉል አንድ ዓይነት ጉድለት ስላለው አይደለም። ይህን የሕይወት ጎዳና የመረጡት አጣዳፊ መሆኑን ባስተዋሉት ጊዜ ውስጥ ጥረታቸው በሙሉ የአምላክን ፈቃድ በማድረግ ላይ እንዲያተኩር ስለፈለጉ ብቻ ነው።
ብሕትውና ግዴታ እንዲሆን ያደረገው ነገር
ክርስቶስ ከኖረበት ጊዜ በኋላ በነበሩት መቶ ዘመናት ግን ሁኔታዎች ተለወጡ። ከክርስቶስ ልደት አንስቶ ባሉት በመጀመሪያዎቹ ሦስት መቶ ዘመናት ውስጥ “ያገቡም ሆነ ያላገቡ አገልጋዮች ነበሩ” በማለት ለማግባት ሲሉ የክህነት አገልግሎታቸውን የተዉት የደሚኒካን እምነት ተከታይ ዴቪድ ራይስ ገልጸዋል። ከጊዜ በኋላ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች አንድ ሃይማኖታዊ ጸሐፊ “የግሪካውያንና የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ውኅደት” ብለው በገለጹት ነገር መመራት ጀመሩ፤ ይህም የጾታ ግንኙነትንና ጋብቻን በተመለከተ የተዛባ አመለካከት እንዲኖራቸው አድርጓል።
ይህም ሆኖ አንዳንዶች ነጠላነትን የመረጡት “ሙሉ በሙሉ [ራሳቸውን] በአምላክ መንግሥት ሥራ ላይ ለማዋል እንዲችሉ የተሟላ ነፃነት ለማግኘት” ፈልገው እንደሆነ የተረጋገጠ ነው። ይሁን እንጂ ሌሎቹ ይህን ለማድረግ ያነሳሳቸው የቀሰሙት አረማዊ ፍልስፍና ነበር። ዘ ኒው ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “የጾታ ግንኙነት ያረክሳል እንዲሁም ከቅድስና ጋር አይጣጣምም የሚለው እምነት ለብሕትውና ልማድ ዋነኛው ግፊት ሆኖ [ክርስቲያን ነኝ በምትለዋ ቤተ ክርስቲያን] ብቅ አለ።”
በአራተኛው መቶ ዘመን ቤተ ክርስቲያኗ “አንድ ባለ ትዳር ቄስ የቁርባን ሥነ ሥርዓት ከማካሄዱ በፊት ባለው ምሽት የጾታ ግንኙነት እንዳያደርግ ከለከለች” በማለት ራይስ ተናግረዋል። ቤተ ክርስቲያን የቁርባን ሥነ ሥርዓት በየዕለቱ እንዲደረግ ስትደነግግ ቄሶች ሙሉ በሙሉ ከጾታ ግንኙነት መራቃቸው ግዴታ ሆነ። በመጨረሻም ቄሶች ፈጽሞ እንዳያገቡ ተከለከለ። በመሆኑም የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ለመሆን የሚፈልግ ማንኛውም ሰው ባሕታዊ መሆን እንዳለበት ተደነገገ።
ሐዋርያው ጳውሎስ ይህ ዓይነቱ አዝማሚያ እያቆጠቆጠ መሆኑን አስታውቆ ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “መንፈስ ግን በግልጥ:- በኋለኞች ዘመናት አንዳንዶች የሚያስቱ መናፍስትንና በውሸተኞች ግብዝነት የተሰጠውን የአጋንንትን ትምህርት እያደመጡ፣ ሃይማኖትን ይክዳሉ ይላል፤ . . . እነዚህ ውሸተኞች መጋባትን ይከለክላሉ [“መጋባት ክልክል ነው ይላሉ፣” ጀሩሳሌም ባይብል]።”—1 ጢሞቴዎስ 4:1, 3
ኢየሱስ ክርስቶስ “የጥበብ ትክክለኛነት በሥራዋ ይገለጣል” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 11:19፣ የ1980 ትርጉም) ከአምላክ የአቋም ደረጃዎች ፈቀቅ ማለት ሞኝነት መሆኑ በሥራዎቹ ወይም በውጤቶቹ ታይቷል። ደራሲው ዴቪድ ራይስ የግዳጅ ብሕትውናን በተመለከተ በዓለም ዙሪያ ላሉ በርካታ ቄሶች ቃለ መጠይቅ አቅርበው ነበር። ቃለ መጠይቅ ከቀረበላቸው መካከል አንዳንዶቹ እንዲህ ብለዋል:- “በክህነት ሥራህ ቀጥል፣ አቅምህ በሚፈቅድልህ መጠን ለሰዎች ጥሩ አድርግ። አንተን ለሚያደንቁና ካንተ ጋር የጾታ ግንኙነት ለመፈጸም ፈቃደኛ ለሆኑ ሃይማኖተኛ ሴቶች ደግሞ ራስህን በስውር አቅርብ።”
ራይስ ማቴዎስ 7:20ን በመጥቀስ “ኢየሱስ ‘ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ’ ብሏል” ሲሉ ተናግረዋል። በመቀጠልም የግዳጅ ብሕትውና ያስከተለውን አሳዛኝ ውጤት እንዲህ በማለት ገልጸዋል:- “ሁለት ዓይነት ኑሮ የሚመሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ወንዶች፣ የተመሰቃቀለ ሕይወት የሚመሩ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሴቶች፣ ቀሳውስት የሆኑት አባቶቻቸው የካዱዋቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ ልጆች አልፎ ተርፎም በዚህ ሁኔታ የተነሳ የስሜት ስቃይ የሚደርስባቸው ቄሶች ራሳቸው የግዳጅ ብሕትውና ፍሬዎች ናቸው።”
የተከበረ ጋብቻ ከአምላክ የሚገኝ በረከት ነው። የግዳጅ ብሕትውና በመንፈሳዊ ጎጂ ውጤት አስከትሏል። ከዚህ በተቃራኒ በውዴታ ነጠላ መሆን ምንም እንኳ ለቅድስና ወይም ለመዳን አስፈላጊ ባይሆንም ለአንዳንዶች የሚክስና በመንፈሳዊ አርኪ የሆነ የሕይወት ጎዳና ሆኖላቸዋል።—ማቴዎስ 19:12
[በገጽ 20 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
Life